Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Wednesday, 21 November 2012

ድብልቅልቅ ስሜቶችን የፈጠረው የኢትዮጵያ የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባልነት

በዮሐንስ አንበርብር
ሰሞኑን ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች 18 አገሮችን በሥሩ ለሚገኘው የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል አድርጐ መርጧል፡፡
ኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል ሆና መመረጧ በርካታ ኢትዮጵያውያንን አስደንቋል፤ አንዳንድ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የኢትዮጵያን አባል መሆን በአገሪቱ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ያላገናዘበ ሲሉ ተችተውታል፡፡ በሌላ በኩል የውጭ ሰብዓዊ መብት ድርጅቶች አጋጣሚውን የወደዱት ቢመስልም የሰብዓዊ መብት ወቀሳቸው ግን ቀጥሏል፡፡

የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ባለፈው ሳምንት ባካሄደው ምርጫ 47 መቀመጫዎች ላሉት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤቱ 18 አባል አገሮችን በተተኪ አባልነት ለቀጣይ ሦስት ዓመታት እንዲያገለግሉ መምረጡን ይፋ አድርጓል፡፡ የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ የ193 አባል አገሮችን ድምፅ የያዘ ሲሆን፣ በሰብዓዊ መብቶች ካውንስል ውስጥ አባል ለመሆን ከ96 በላይ የሚሆኑ አባል አገሮችን ይሁንታ ማግኘት ይጠይቃል፡፡ ባለፈው ሳምንት በተካሄደው ምርጫ ከኢትዮጵያ ጋር ሌሎች ስድስት የአፍሪካ አገሮችም ተመርጠዋል፡፡ እነዚህ የአፍሪካ አገሮች ያገኙት ድምፅ የተሻለ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ከ193 የጠቅላላ ጉባዔው አባላት ድምፅ የ178 አገሮችን ይሁንታ በማግኘት ምክር ቤቱን በአባልነት ተቀላቅላለች፡፡

ለሰብዓዊ መብቶች  መከበር የፀና እምነት መኖርና ለተግባራዊነታቸው መንቀሳቀስ፣ የተሻለ የሰብዓዊ መብቶች አያያዝና ለዚህ የሚሠሩ ጠንካራ ተቋማት መኖር የምክር ቤቱ አባል ሆኖ ለመመረጥ ከሚያበቁ ዋነኛ መስፈርቶች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ምክር ቤቱ ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲፈጠር በመላው የዓለም አገሮች ውስጥ የሚሠራ ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በአገሮች እንዲሰፍን የመተባበር፣ የማጐልበትና የመከታተል መሠረታዊ ኃላፊነቶቹ ሲሆኑ፣ በተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በሚፈጽሙ አገሮች ላይ እስከ ማዕቀብ መጣል የደረሰ ዕርምጃ ሊወሰድ ይችላል፡፡


የምክር ቤቱ አባል አገሮችም ለዚህ ዓለም አቀፋዊ ኃላፊነት አስተዋጽኦ ከማበርከት ጐን ለጐን በአባልነት ዘመናቸው ልዩ ተሞክሮን በመውሰድ በአገራቸው ያለውን የመብት አከባበር ማጠናከር እንዲችሉ ዕድልን ይፈጥራል፡፡ ይሁን እንጂ አንድ አባል አገር በአባልነት ዘመኑ ወቅት በአገሩ ያለውን የሰብዓዊ መብት ሁኔታ ማስተካከልና ማሻሻል ከተሳነው ካውንስሉ የመተባበር አስተዋጽኦውን ወደ ጐን በመተው፣ በአባል አገሩ የካውንስል ወንበር ላይ በመወያየት በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ከአባልነት የማስወገድ ሥልጣን አለው፡፡

በጉዳዩ ዙሪያ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡ አንዳንድ ግለሰቦች የኢትዮጵያ በአባልነት መመረጥ በእጅጉ አስገርሟቸዋል፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ መብቶቻቸው መጣሱ በየጊዜው ይነገራል፡፡ ይህ ጥሰት ለማንም የተደበቀ እንዳልሆነም በግልጽ የሚናገሩ አሉ፡፡ በሥራ ቦታዎች፣ በአገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የጤና ተቋማትን ጨምሮ የዜጐች መብቶች ይረገጣሉ የዕለት ተዕለት የኑሯችን አካልን ነው የሚሉት እነዚሁ አስተያየት ሰጪዎች የኢትዮጵያን የተመድ ሰብዓዊ መብት ምክር ቤት አባልነት የሰሙት በመደነቅ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ራሱ ተመድን ጨምሮ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አገሮች ይህንኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተገንዝበው ወቀሳቸውን በኢትዮጵያ ላይ በተደጋጋሚ ሲዘነዝሩ እስከዛሬ ቆይተው፣ በአሁኑ ወቅት ምን ታይቷቸው እንደሆነ ለማወቅ እንቆቅልሽ እንደሆነባቸውም ይናገራሉ፡፡ እነዚሁ ዓለም አቀፍ ተቋማት ወቀሳቸውን በተለያዩ ጊዜያት ሲሰነዝሩ በተለያዩ መገናኛ ብዙኅን ቢሰሙም በኢትዮጵያ የተለወጠ ነገር የለም ብለው፣ ሰሞኑን የኢትዮጵያን መመረጥ አስመልክቶ የሰሙትን በተለየ ሁኔታ ባያዩትም በምን መስፈርት እንደተመረጠች መጠየቃቸው ግን አልቀረም፡፡

በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ የሆኑት አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ግን ኢትዮጵያ የተመረጠችበትን መስፈርቶች እንዲሁም አግባብነቱን ይናገራሉ፡፡ ኢትዮጵያ ያለማንም ተፅዕኖ የራሷን የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፣ እንዲሁም የእንባ ጠባቂ ተቋምን በመመሥረት የዜጐቿን ሰብዓዊ መብቶች ለማስከበር የምትሠራ አገር መሆኗን፣ እንዲሁም ለተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት መመሥረትና መጠናከር ያደረገችው አስተዋጽኦና እገዛ ለመረጧ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

የአገሪቱ በምክር ቤቱ የአባልነት ወንበር ማግኘትም የተለያዩ የውጭ ሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘሩትን ወቀሳ ያጋለጠና መሠረት የሌለው መሆኑን የጠቆመ ነው ሲሉ አክለው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያውያን ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ሊቀመንበር አቶ ሙሼ ሰሙ የኢትዮጵያን የተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል መሆን መልካም ጐኖች ይኖሩት ይሆናል የሚል እምነት ቢኖራቸውም፣ መመረጧ ብቻውን ግን በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ሊቀረፍ አይችልም በማለት ያስረዳሉ፡፡ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የአገሪቱን መመረጥ አስመልክተው በሰጡት አስተያየት ላይም አይስማሙም፡፡ ‹‹ሲጀመር በማንኛውም መስፈርት ብትመረጥ በአገሪቱ የሰብዓዊ መብት ጉድለቶች እንዳልነበሩ ሊያደርግ አይችልም፤›› ሲሉ ሊቀመንበሩ አቶ ሙሼ ያስረዳሉ፡፡

ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ባደረገችው አስተዋጽኦ ልትመረጥ ትችላለች ብሎ ለመቀበል ይቅርና ለማሰብ እንደሚከብድ የሚናገሩት አቶ ሙሼ፣ ከዚህ ይልቅ በዲፕሎማሲ የፈጠረችው ጫና ለመገለጫነቱ ሚዛን ይደፋል ብለዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአፍሪካ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያላት ሚና እየገዘፈ መጥቷል፡፡ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ፣ በአፍሪካም ሆነ በራሷ ጉዳዮች ላይ ተሰሚነትን አግኝታለች፡፡ ይህም የምክር ቤቱ አባል ለመሆን ረድቷታል፤›› የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ የምክር ቤቱ አባል መሆን ተገቢ አይደለም የሚል እምነት እንደሌላቸው የሚገልጹት ሊቀመንበሩ፣ የአገሪቱ ባለሥልጣናት በዚህ ከመኩራራትና ለሚሰነዘርባቸው ወቀሳ ጋሻ ከሚያደርጉት በቅንነት ቢጠቀሙበት ለሕዝብ ይጠቅማል ብለዋል፡፡

‹‹የዓለም አገሮች ለኢትዮጵያ ዕድል ሰጥተዋል፡፡ በመሆኑም በአባልነት ቆይታዋ ወስጥ ሯሳን ከሌሎች ተሞክሮዎች አርማ ማውጣት ብልህነት ነው፡፡ ይህንን ተቀብሎ መተግበርና ኃላፊነትን መውሰድ ካልተቻለ ግን ከካውንስሉ አባልነት በውርደት መሰናበትን ሊያመጣ ይችላል፤›› የሚል ምክር አዘል አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ ሥልጣን መያዙን ተከትሎ የፀደቀው የአገሪቱ ሕገ መንግሥት በርካታ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎችን የያዘ፣ እንዲሁም በዚሁ ዙርያ ተመድ ያፀደቃቸውን ስምምነቶች የካተተ ከመሆኑም ባሻገር ባለው አጠቃላይ ይዘት ከሞላ ጐደል ደረጃውን የጠበቀ እንደሆነ ይነገርለታል፡፡

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ከፀደቀ በኋላ የመጀመርያው የኢትዮጵያ ርእሰ ብሔር በመሆን የተመረጡት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳም በዚሁ ጉዳይ ላይ ይስማማሉ፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ከሕገ መንግሥቱ መፅደቅ በኋላም የአገሪቱ ሕግ አውጪ አካል ያወጣቸውን የሕዝቦች መብትን የተመለከቱ ማስፈጸሚያ አዋጆችን ፕሬዚዳንት በነበሩባቸው ወቅቶች በፊርማቸው አፅድቀዋል፡፡

‹‹በሕገ መንግሥቱ የተካተቱ ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ ሰብዓዊ መብቶችን የተመለከቱ ድንጋጌዎች አሉ፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥታችን ሚዛኑን የጠበቀ ነው፡፡ ነገር ግን አገሪቱ በተመድ ምክር ቤት ውስጥ የተመረጠችው በዚህ ከሆነ አስገራሚ ነው፤›› በማለት በአሁኑ ወቅት የአንድነት ለፍትሕና ዲሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ነጋሶ ይገልጻሉ፡፡

ድንጋጌዎቹ በወረቀት ላይ የሰፈሩ ከመሆን ያለፈ ትርጓሜ ለመስጠት አስቸጋሪ እንደሆነ በአገሪቱ በየዕለቱ የሚስተዋሉት የመብት ጥሰቶች ምስክር ናቸው ብለዋል፡፡ በርካታ አገሮች እንዲሁም ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ረገጣ ዙሪያ ወቀሳቸውን እየሰነዘሩ ባለበት በአሁኑ ወቅት፣ አገሪቱን የምክር ቤቱ አባል አድርጐ መምረጥ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹ እንዳይጋለጡና እንዳይመረመሩ ከለላ ለመስጠት መተባበር የመጨረሻው ውጤት እንዳይሆን ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

መቀመጫቸውን በተለያዩ የውጭ አገሮች ያደረጉ በሰብዓዊ መብቶች መከበር ዙርያ የሚሰሩ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ በተደጋጋሚ በኢትዮጵያ ላይ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ወቀሳዎችን በመሰንዘር ከመንግሥት ጋር ንትርክ ውስጥ እስከ መግባት ደረጃ የደረሰው ሒዩማን ራይትስ ዎች የተባለውን ድርጅት ጨምሮ የኢትዮጵያ በተመድ ሰብዓዊ መብት ካውንስል ውስጥ አባል መሆን የተለየ አጋጣሚን ይፈጥራል የሚል ግምት የያዙ ይመስላሉ፡፡

ሒዩማን ራይትስ ዎችና ስድስት የሚሆኑ ሌሎች ተመሳሳይ ተግባር ላይ የተሰማሩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ኢትዮጵያ አባል ለመሆን እያደረገች የነበረውን ፉክክር ቀደም ብለው የተገነዘቡ ሲሆን፣ ተመድና አባል አገሮቹ ኢትዮጵያን እንዳይመርጡ መወትወት ውስጥ ከመግባት በመቆጠብ ለየት ያለ ባህሪ አሳይተዋል፡፡ በተጨማሪም ተመድ ኢትዮጵያን ከመምረጡ በፊት ድርጅቶቹ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በጋራ በመሆን ደብዳቤ ልከዋል፡፡

በደብዳቤያቸውም ኢትዮጵያ የተመድ ሰብዓዊ መብት ምክር ቤት አባል ለመሆን እየተወዳደረች እንደመሆኗ መጠን አሁን ባለው የሰብዓዊ መብት አያያዟ ላይ ማስተካከያ እንድታደርግ ጠይቀዋል፡፡

የመናገር፣ የመሰብሰብና የመደራጀት መብቶች ላይ በአገሪቱ ሕገ መንግሥትና በዓለም አቀፍ ሕጎች መሠረት ማሻሻያ እንዲደረግ በደብዳቤያቸው አቶ ኃይለ ማርያምን አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ለተመድ ሰብዓዊ መብት ካውንስል ዕጩ ሆኖ ስትቀርብ አልያም ከተመረጠች በኋላ ጫናን ለመፍጠር በሚመስል ሁኔታ አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት አያያዝ ላይ ወቀሳቸውን መሰንዘር ቀጥለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምክር ቤቱ ውስጥ አባል ለመሆን በዕጩነት እየተወዳደረች ባለችበት ሳምንት ውስጥ ኮሚሽን ኦን ኢንተርናሽናል ረሊጂየስ ፍሪደም የተባለ በእምነት ነፃነት ላይ የሚሠራ የአሜሪካ መንግሥት ተቋም ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግሥትን የእስልምና ሃይማኖት ነፃነትን በማፈን ወቅሷል፡፡

የዚህ ኮሚሽን አባላት በቀጥታ በፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የሚመረጡ ሲሆን፣ በመግለጫቸውም መንግሥት በሃይማኖቱ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ በመግባትና በማፈን እንዲሁም እስካሁን 29 የሚሆኑ ጣልቃ ገብነቱን የተቃወሙ አማኞችን ማሰሩን ገልጾ ከድርጊቱ እንዲታቀብ ጠይቀዋል፡፡  

በኮሚሽኑም ሆነ በተለያዩ ወገኖች በዚሁ ጉዳይ ለሚቀርቡ ወቀሳዎች መንግሥት ምላሹን ሲሰጥ፣ በእምነት ጉዳይ ላይ ጨርሶ ጣልቃ እንዳልገባ የታሰሩት ግለሰቦች ከእምነት ጋር በተገናኘ ሳይሆንሕ እምነትን ሽፋን በማድረግ አገሪቱን የማወክና እስላማዊ መንግሥት የማቋቋም ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚጋጭ እንቅስቃሴ ውስጥ በመሆናቸው ነው ሲል ገልጿል፡፡

ባለፈው ሳምንት ውስጥም የጀርመኑ ዓለም አቀፍ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ሄኒሪክ ቦል ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ መብት ረገጣ ቀጥሏል፣ ሰብዓዊ መብትንና የዲሞክራሲ ሥርዓት በአገሪቱ እንዲሰፍን እየተወጣሁ ያለሁትን ሚናም ገድቦብኛል የሚል ወቀሳ በማቅረብ በአገሪቱ ያከናውናቸው የነበሩ ሥራዎችን አቋርጦ መውጣቱን አሳውቋል፡፡

አሁንም ባለፈው ሳምንት ውስጥ በተመሳሳይ ነገር ግን ባልተለመደ ሁኔታ ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ድርጅት (ILO) ኢትዮጵያ የሠራተኞችን የመደራጀት መብት በማፈን መብታቸውን እየረገጠች ነው ሲል ኮንኗል፡፡

በተለይ የመምህራን ማኅበርን ለመመሥረትና ሕጋዊ ምዝገባና ፈቃድ እንዲኖረው በመምህራን በተደጋጋሚ የተደረገውን ጥረት መንግሥት የመከልከልና ዕውቅና የመንፈግ ተግባሩን ቀጥሎበታል ያለው ድርጅቱ፣ በመሆኑም ከድርጊቱ በመታቀብ የመደራጀትና መብታቸውን የማስከበር ጥረታቸውን እንዲደግፉ ጠይቋል፡፡

መንግሥት ግን ይህንን ተግባር እንዳልፈጸመ በመግለጽ ወቀሳውን አጣጥሏል፡፡ በአገሪቱ ውስጥ መላ መምህራንን የሚወክል ማኅበር መኖሩን በመጠቆም ወቀሳው በመረጃ ላይ ያልተመሠረተ ነው ብሏል፡፡

ይሁን እንጂ ከዓመት በፊት በአዲስ አበባ የሚገኙ መምህራን የደመወዝ ጭማሪ ሊደረግልን ይገባል በማለት ተቃውሟቸውን ያቀረቡ ሲሆን፣ ከዚህ አልፎም በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች የሥራ ማቆም አድማ እስከማድረግ መድረሳቸው ይታወቃል፡፡ በወቅቱ ካነሷቸው ተቃውሞዎች መካከል የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር አይወክለንም፣ መንግሥት የመምህራንን የመብት ጥያቄ ለማፈን ያቋቋመው ነው ማለታቸው ይታወሳል፡፡

ሰሞኑን የተመረጡት አገሮች በአባልነት ሥራቸውን የሚጀምሩት እ.ኤ.አ በጃንዋሪ 2013 ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም ባላት የሰብዓዊ መብት አያያዝ ጉድለት እንዲሁም ከተመረጠች በኋላ እየቀረበባት ባለው ወቀሳ ውስጥ የሦስት ዓመታት የአባልነት ዘመኗን እንዴት ታገባድድ ይሆን? የሚል ጥያቄን ጭሯል፡፡

አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ግን፣ ‹‹ይህ የመንግሥት ሥጋት አይደለም፡፡ የካውንስሉ አባል ባይኮንም በአገሪቱ ሰብዓዊ መብቶችን ሥር ለማስያዝ የተጀመሩ ጥረቶች ይቀጥላሉ፤›› በማለት ለዚህም የመንግሥት ቁርጠኝነት እንዳለ ገልጸዋል፡

No comments:

Post a Comment