Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Thursday, 22 November 2012

የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመኘውና ማየት የሚፈልገው! ተቃዋሚው መመለስ ያለበት! ከፈቃዱ በቀለ

መግቢያ

ባለፉት ዐመታት በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች ምርጫዎች ተካሂደዋል። ከአምስት ዐመት በፊት በኬንያ የተካሄደውንና፣ በሚያዚያ ወር 2011 ዓ.ም ደግሞ በናይጄሪያ የተደረገውን የፕሬዚደንትና የፓርላሜንት ምርጫ ትዝ ሳይለን አይቀርም። ከአንድ ዐመት በፊት ደግሞ በቱኒዚያ የተለኮሰው የሰሜን አፍሪካው የጥቢው አብዮት እየተባለ የሚጠራው ወደ ግብጽና ወደ ሊቢያ፣ ከዚያም ወደ የመን በመሸጋገር የስርዓት ለውጥ ሳይሆን የፕሬዚደንቶችን ለውጥ አስከትሏል። ከአንድ ዐመት በላይ በሰሜን አትላንቲክ የጦር ድርጅትና፣ በሳውዲ አረብያና በካታር የውስጥ ለውስጥ እየተደገፈ የሶርያ የነጻ አውጭ ወታደር እየተባለ የሚጠራው የፕሬዚደንት አሳድን መንግስት ለመጣል የሚደረገው የርስ በርስ ጦርነትና፣ በግምት ለሰላሳ ሺህ ሰዎች መሞት ምክንያት የሆነው ወዴት እንደሚያመራ ከአሁኑ በእርግጠኝነት ለመናገር ያስቸግራል። አንድ በእርግጠኝነት ለመናገር የሚቻለው ነገር ፕሬዚደንት አሳድ ቢወድቁ እንኳን የሶርያ ህዝብ እጣ የጨለመ ይሆናል። የርስ በርሱ ጦርነት ይቀጥላል። ምናልባትም ሶርያ ወደ ሶስት ቦታዎች የምትሽነሸንበት ሁኔታ ይፈጠር ይሆናል። ይህም ማለት የሶርያ ህዝብ የፈለገውን የዲሞክራሲ ምኞቱን በፍጹም አይቀዳጅም ማለት ነው።

በኬንያና በናይጀሪያ የተደረገው የፕሬዚደንትነት ምርጫ ያለውን ስርዓት የበለጠ ያጠናከረ እንጂ የህዝቡን መሰረታዊ ጥያቄ የፈታ አይደለም። በሁለቱም አገሮች ድህነት፣ እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ መኖር ባህላዊ የአኗኗር ስልት ሆኗል። በየአራት ወይም በየአምስት ዐመቱ የፈለገውን ያህል ምርጫ ቢካሄድም፣ ምርጫው በሁለቱም አገሮች የሰፈነውን የስራ አጥነት ብዛት ሊቀንስና ድህነትን ሊቀርፍ አልቻለም። የሀብት ክፍፍሉ እንዳለ በመቅረት በሀብታምና በደሃ መሀከል ያለው ልዩነት እንደሰፋና እንደተጠናከረ ነው። የናይጄሪያም ሆነ የኬንያ ህዝብ የየአገሮቻቸው ዕድል ወሳኞች መሆን እልቻሉም። ስለሆነም በሁለቱም አገሮች ያለው ህብረተሰብአዊ ግጭት፣ በተለይም ደግሞ በናይጄሪያ ከሃይማኖት ጋር ተሳቦ የሚካሄደው ተራን ህዝብ በቦምብ መግደል ቀጥሏል። ሁለቱም አገሮች ለረዥም ዐመታት በትርምስ ዓለም ውስጥ እንደሚኖሩ ከአሁኑ በእርግጠኝነት ለመናገር ይቻላል። ምክንያቱም ቀላል ነው። ምርጫ ተካሄደ ቢባልም በመሰረቱ፣ 1ኛ) የኃይል አሰላለፍ ለውጥ አልተካሄደም፤2ኛ) የየመንግስታቱ የመጨቆኛ መሳሪያዎች እልተወገዱም፤ የመንግስቱ መኪና ዲሞክራሲያዊ ይዘት እንዲኖረው በማድረግና በማደስ የህዝብን ጥያቄ መላሽ ሊሆን አልቻለም። 3ኛ) በሁለቱም አገሮች ሰፋ ያለ ህዝቡን የሚያሳትፍ ዲሞክራሲያዊ የኢንስቲቱሽን ሪፎርም አለተደረገም፤ 4ኛ)ሁለቱም መንግስታት የሚመሩበት የኢኮኖሚ ፖሊሲ አዲስ ሀብት የሚፈጥርና፣ ህዝቡን ወደስራ አሰማርቶ የተስተካከለና የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖር የሚያደርጉት አይደሉም። 5ኛ) ሁለቱም መንግስታት አሁንም የውጭ ኃይሎች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በውስጥ ፖሊሲዎቻቸው ጣልቃ ይገቡባቸዋል። ስለዚህም በሁለቱም አገሮች ያለው የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የባህላዊ፣ የህሊናና የሚሊታሪ ቀውስ ለረዥም ዐመታት እንዳለ ይቆያል፤ ወይም ደግሞ እየተባባሰበት ይሄዳል።


ወደ ስሜን አፍሪካው የጥቢው አብዮት ተካሄደባቸው በሚባሉት ወደቱኔዚያ፣ ሊቢያና ግብፅ ስንመጣ ተስፋ የሚያስቆርጥ ሁኔታን እንመለከታለን። ከአብዮታዊ ለውጥ ይልቅ የእስላም አክራሪዎች፣ በተለይም ሳላፊስቶች የበላይነትን የሚይዙበት ሁኔታ እየተመቻቸ ነው። ስሞኑን በግብፅ የሚደረገው የጥንት ፒራሚዶች ይውደሙ የሚለው

አደገኛ ቅስቀሳ በተለይም ለክርስቲያኑ የኮፕቲክ ማህበረሰብ ብቻ ሳይሆን ለጠቅላላው የግብፅ ህዝብ አስደንጋጭ ሁኔታን ፈጥሯል። በስልጣን ላይ ያሉት አገዛዞች ኢኮኖሚውን በአዲስ መልክ አደራጅቶ የስራ መስክ ፈላጊውን ወደ ስራ ከማሰማራት ይልቅ ካልጠበቁት አክራሪ ሁኔታ ጋር እንዲጋፈጡ ተገደዋል። አዲስ ሀብትና የስራ መስክ ለመፍጠር ያለመቻላቸውን ወደጎን ትተን፣ ወደ ነፃነት ጥያቄ ስንመጣ ከፕሬዚደንቶች ለውጥ በኋላ የሶስቱም አገር ህዝቦች ነፃነቶቻቸው በረቀቀ መልክ እየታፈነ የመጣበትን ሁኔታ እንመለከታለን። በተለይም ወጣቱና ሴቶች በአዲስ የእስላም እንቅስቃሴ መብታቸው እየተገፈፈ ነው። የፈለጉትን ልብስ እንዳይለብሱና አጋጊጠው እንዳይሄዱ የሚከለከሉበት ሁኔታ ሁሉ እየተዘጋጀ ነው። ሌሎች ሌሎች ነገሮችም፣ የምዕራቡን ሙዚቃ መስማትና ፊልም ማየት የሚከለከሉበት ሁኔታም ሩቁ አይሆንም። ይህ የሚያሳየን ምንድነው? አንድ ህዝብ ለነፃነት በሚያደርገው ትግል አንድ ድል ተቀዳጀሁ ካለ በኋላ ውስጥ ለውስጥ በተደራጁ ኃይሎች፣ ወይም ደግሞ በውጭ ኃይሎች ድጋፍ የራሳቸውን አጀንዳ ተግባራዊ የሚያደርጉ ስልጣንን በመንጠቅ የእንድን ህዝብ የነፃነትና የስልጣኔ ፍላጎት ዝብርቅርቁን እንደሚያወጡትና፣ እንደገና ደግሞ ወደ ሌላ ስቃይ ውስጥ በመክተት በድንቁርናና በድህነት ዓለም ውስጥ እንዲኖር እንደሚያደርጉት ነው።
ከዚህ ስንነሳ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመኘው፣ የሚያልመውና የሚጠይቀው ጥያቄ ግልጽ ነው። የዛሬው የወያኔ አገዛዝ በአንዳች ነገር ቢወድቅ ምኞቴን የሚያሟላልኝ፣ ህልሜን ዕውን የሚያደርግልኝ፣ ነፃነቴን የሚያስከብርልኝና፣ ተከብሬና ተዝናንቼ በአገሬ ውስጥ ለመኖር የሚያስችለኝ የተደራጀ ኃይል አለ ወይ? ካለስ እንዴትና በምንስ ዘዴ ነው ስር የሰደደውን የተወሳሰበ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊ፣ የጎሳ ችግር፣ የሃይማኖት ጥያቄ፣የሴቶችና የወጣቱን ጥያቄ፣ የባህልና ሌሎችንም መፍታት የሚችለው? እያለ ነው። ወደ ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ከመግባታችን በፊት፣ የአገራችን ሁኔታ ምን ይመስላል? የሚለውን እንዳስስ።
የአገራችን ሁኔታ ምን ይመስላል !
ሰሞኑን „አገርህን ዕወቅ“ በሚል አርዕስት በ27 ገጽ የተጠናቀረ የአገራችንን ሁኔታ ከሁሉም አቅጣጫ የሚዳስስ በጣም ግሩም ጽሁፍ ከአገር ቤት ለአንዳንድ ድህረ-ገጾች ተላልፏል። ዘጋቢው በዚህ ጽሁፉ ውስጥ የአገራችንን ሁኔታ እንዲህ ሲል ያትታል። „የኢትዮጵያ ሁኔታ በዓመቱና በችግሩ ብዛትና ስፋት መጨመር ይለይ እንደሆን እንጂ ከድሮው ለውጥ የለውም። ዘንድሮም እንደ አምናው፣ ዛሬም እንደ ትላንቱ አገሪቱ በጨካኞች መዳፍ ስር ወድቃ ትማቅቃለች። የዲሞክራሲ መብት ተነፍጎና ተገፎ ሕዝቡ በነጻ ሃሳቡን የሚሰነዘርበት መንገድ ሁሉ ተዘግቷል፤ በነጻ የመደራጀት፣ የመሰብሰብ፣ተቃውሞ የማሰማት መብት የለውም።ተምሮ ሥራ የማግኘት ቀርቶ ለመማር እራሱ የገዢው ቡድን ደጋፊና አጨብጫቢ ካልሆኑ በዜግነት የሚያገኙት መብት አልሆነም። በግልም ሆነ በመንግስት የስራ ዘርፎች ለመቀጠርና ለመቆየት እውቀትና ችሎታ ሳይሆን የግድ የመንግስት ደጋፊና የገዢው ፓርቲ አባል እንዲሁም በረከሰ ደረጃ ጎጠኛ መሆን እንደ መለኪያ መሳፍርት ተውስዶ በተግባር ይተረጎማል።“ አጠናቃሪው በመቀጠልም ህዝባችን በኢኮኖሚ ቀውስ ክፉኛ እንደተጎዳና፣ አገዛዙም የህዝቡን ችግር ተረድቶ የሚወስደው አስተማማኝ ፖሊሲ እንደሌለ ይጠቁማል። ሁኔታውን እንደዚህ በማለት ይገልጻል። „የአገሪቱ የኢኮኖሚ እድገት ጨምሯል እየተባለ ቢወራም በውጭ አገር በጎ አድራጊዎች የእህል ዳረጎት የሚተዳደረው ሕዝብ ቁጥር ሲጨምር እንጂ ሲቀንስ አይታይም። የማይበላው ከሚበላው እየበለጠ በቀን አንድ ጊዜ በልቶ ማደር ለብዙሃኑ እንደ ሎተሪ በጉጉት የሚጠብቁትና ሳያስቡት የሚያገኙት ዕድልና አጋጣሚ እየሆነ መጥቷል። በየመንገዱ ከየሆቴሉ የተሰበሰበ ትራፊ የጉርሻ ገበያ ተከፍቶ ደሃው ሕዝብ ገዝቶ ለመቅመስ ተሰልፎ ከሚታይበት ደረጃ ላይ ተደርሷል።“ አጠናቃሪው በዚህ ሳያቆም በአገራችንና በህዝባችን ላይ የሚደርሰውን ሰቆቃ ስዕላዊ በሆነ መልክ ይገልጻል። ለሰው ልጅ የቀን ተቀን የሚያስፈልጉት እህሎች፣ ዘይት፣ ሽንኩርት፣ በርበሬ፣ እንደ ምስርና ሌሎችም የጥራጥሬ እህሎች በበቂው አለመገኘታቸው ብቻ ሳይሆን፣ የሚገኙትን ገዝቶ ለመብላት እንደማይቻል ያትታል። በሌላ

ወገን ደግሞ ጥቂት አለፈልን የሚሉ ምድር አልበቃ ብሎአቸው በኑሮአቸው እንደሚንደላቀቁና፣ በደሀና በሀብታም መሀከል ያለው የገቢና የኑሮ ልዩነት በጣም የሰፋ መሆኑን ያብራራል። ሰሞኑን አዲስ አበባ ውስጥ የተሰበሰበው የተለያዩ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በአንድ ጥላ ሥር ያሰባሰበው የኢትዮጵያ ፍትህና ዲሞክራሲ ኃይሎች ግንባር(ኢፍዲኃግ) እንደዚሁ አገሪቱ የምትገኝበትን የውጭና የውስጥ ውጥረት በሰፊው ከዘረዘረ በኋላ፣ በደሀና በሀብታም መሀከል ያለው ልዩነት በጥይት ዐይነት ፍጥነትም መደረስ እንደማይቻልበት ሲያትት፣ ይህ ሁኔታ እርማት ካልተደረገበት አገሪቱ ከፍተኛ ህብረተሰብአዊ ቀውስ ውስጥ በመውደቅ ህዝቡ ፍዳውን እያየ አንደሚኖር ያረጋግጣል።
በተጨማሪም የ27 ገጽ ጽሁፍ አጠናቃሪው የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ አሰቃቂነት እንደዚህ በማለት ያትታል። „ በሰዎች የኑሮ ደረጃ ዕድገት መሻሻል/human development and living standard/ ኢትዮጵያ ከ179 አገሮች የ169ኛውን ቦታ ይዛለች።“ ይልና፣ ወደታች ወረድ ብሎ ደግሞ የህዝባችን ኑሮ በጣም ወደኋላ የቀረ መሆኑን ቁልጭ አድርጎ ያስቀምጣል። „ከጠቅላላው ሕዝብ መሃል 66% የሚሆነው የተጣራ ውሃ አያገኝም። 11% የሚሆነው በቅጡ ያልተሟላ የመጸዳጃ ዕድል ሲኖረው፣ 89% የሚሆነው ደግሞ ከእንስሳት ባልተሻለ ደረጃ ጫካና ሜዳን ተገን አድርጎ የሚጠቀም ነው። 44.2% የሚሆነው ከድህነት ወለል መስመር በታች ይኖራል። የዓመት አማካኝ ገቢው ከ$324 ዶላር አይበልጥም። የገቢው መጠን በነፍስ ወከፍ በቀን $2 ዶላር ነው። በህግ የተደነገገ የደመወዝ ተመንና ገደብ የለም። የመንግስትም ሆነ የግል መሥሪያ ቤት የመሰላቸውን አነስተኛ የደመወዝ ጣሪያ በማስቀመጥ ይገለገሉበታል። አብዛኛው ተቀጣሪ በወር $25 ዶላር ሲያገኝ፣ በባንክ የሚሠራው ደግሞ በወር የሚያገኘው ደሞዝ $26.5 ዶላር አይበልጥም። በቁጥር ጥቂት የሆነው ብቻ በከተማዎች በተለይም በአዲስ አበባ ከተማ በበቂ የወር ገቢ ተቀጥሮ ይሠራል። የሳምንቱ የሥራ ሰዓት 48 ነው። ግን እንደመብት የተወሰደ ሳይሆን በግዴታም ሊራዘም እንደሚችልና በአሠሪው ፍላጎት ላይ የተቀመጠ ውሳኔ ነው። በዚህ ዝቅተኛ በሆነ ደሞዝ ሠርቶ ለማደር የታደለው በጣም ጥቂቱ ነው።“ በዚህ መልክ ህዝባችን የሚኖርበትን አሳዛኝ ሁኔታ ቁልጭ አድርጎ ያስቀምጣል።
አገርህን እወቅ የሚለው ሀተታ በዚህ ሳያቆም፣ የአገሪቱ ብሄራዊ ነፃነት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ እንደደረሰና፣ ኢትዮጵያዊነት የረከሰበትና የውጭ ዜጋ ደግሞ የሚከበርበትን ሁኔታ ያመለክተናል። በተለይ አገሪቱ በአዲስ ኢንቬሰተር ነን በሚባሉ እንደተሸነሽነችና እንደተያዘች፣ እንዲሁም ደግሞ ምስኪኑ ደሀ ህዝብ ከቀዬው ተፈናቆሎ ወደባሰ ድህነት ውስጥ እንደተገፈተረና እንደሚገፈተር ያስረዳናል። የአገሪቱን የኢኮኖሚ ሁኔታ በአሃዝ ካመለከተ በኋላ፣ ዛሬ አገራችን የምትገኝበት ሁኔታ የሶስት ሺህ ዐመት ታሪክ ነበራት የማያስብላት ብቻ ሳይሆን፣ በ21ኛው ክፍለ-ዘመን በህዝባችን ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ እጅግ አስከፊ ከመሆኑ የተነሳ፣ በዚህ ዐይነት ሁኔታ መኖር እጅግ አሳፋሪ መሆኑን ያሳስበናል።
ይህ አሰቃቂና አሳዛኝ ሁኔታ የሰፈነው እንደሚታወቀው “የዴቬሎፕሜንታል መንግስት” የኢኮኖሚ ዕድገት ይካሄዳል በሚባልበት አገር ነው። ዛሬ ለሁላችንም ግልጽ የሆነው ነገር፣ የወያኔ አገዛዝና ጥቂት ካድሬዎቹ በተለይም ስትራቴጂክ የሚባሉ የኢኮኖሚ ሴክተሮችን በመቆጣጠር ህዝቡን መፈናፈኛ ያሳጡበት ሁኔታ በግልጽ ይታያል። ካለነሱ ፈቃድ ማንኛውም ግለሰብ በኢኮኖሚ ዘርፍ ውስጥ ገብቶ መሳተፍ አይፈቀድለትም። ተወዳዳሪ የሚባልና ለአገሪቱ ጠቃሚ የሆነ የኢንቬስትሜንት ፕሮጀክት የሚያካሂድ የረዥም ጊዜ የቀረጥ ውዝፍ አለብህ እየተባለ በብዙ መቶ ሺህ ወይም በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንዲከፍል በማድረግ ከኢኮኖሚ ጨዋታ ውስጥ እንዲወጣ ይደረጋል። ለዛሬው የዋጋ መናር ዋናው ምክንያት አንዳንዶች እንደሚሉት ገንዘብ በብዛት በኢኮኖሚው ውስጥ በመሽከርከሩ ሳይሆን፣ አገሪቱ ውስጥ የሚመረተው፣ ከአተር እስከባቄላ፣ ከሽምብራ እስከ ምስር፣ ጅንጅብልና ቁርፍንድ፣ እንዲሁም የአትክልትና የፍራፍሬ ምግቦች ድረስ በወያኔ እየተጋዙ የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት ሲባል ወደ ውጭ ስለሚላኩ ነው። በሌላ ወገን ደግሞ በጥራታቸው እጅግ ዝቅተኛ የሆኑ፣ የበቀሉና በውሃ የተዘፈዘፉ እህሎች ገበያ ላይ ወጥተው

ይሸጣሉ። በርበሬ ውስጥ የተፈጨ ቀይ አፈር(ለሸክላ የሚሆን) ይቀላቀልበታል። ቅቤ ውስጥ ሙዝ ይታከልበታል። ቁርፍንድና ምስር ለክብደት እንዲያመቹ ተደርገው ውሃ ውስጥ ተነክረው ይሸጣሉ። እዚህ ያለንበት አገር ለህክምናም ሆነ ዘመዶቻቸውን ለመጠየቅ የሚመጡ ኢትዮጵያውያን የሚነግሩን የኢትዮጵያ ገበሬ እንደዚያ በስንት ልፋት የሚያመርተውን ጥቂቱ ካልሆነ በስተቀር ሰፊው ህዝብ ገዝቶ እንዳይበላ የተረገመ ይመስላል እያሉ ነው። በሌላ አነጋገር የዛሬው አገዛዝ ለራሱና በአካባቢው ለተሰበሰቡና ለውጭ ኃይሎች የቆመ እንጂ የኢትዮጵያን ህዝብ ጥቅም የሚያስጠብቅና፣ ሊያስጠብቅ እንደማይችል በገሃድ እያረጋገጠ ነው፤ አረጋግጧልም። ከሞላ ጎደል የአገራችን ሁኔታ ይህንን ይመስላል። የሚነሳው ጥያቄ አገዛዙ እንደዚህ በግልጽ ከህዝቡ አፍ ላይ እየነጠቀ ወደ ውጭ የሚሸጥ ከሆነ፣ ህዝባችንን ከመሬቱ እያፈናቀለ መሪቱን ለውጭ ኢንቬስተሮች ለሚባሉት የሚሰጥ አገዛዝ ከሆነ፣ በዘመናዊ የስለላ መሳሪያ በመታጠቅ ህዝባችንን ፍዳውን የሚያሳይ ከሆነ፣ በአገራችን ምድር ረጋ ያለ በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ሰፊውን ህዝብ የሚያዳርስና የሚጠቅም የኢኮኖሚ ዕድገትና ስልጣኔ እንዳይመጣ በግልጽ የሚታገል ከሆነ፣ በሽምግልናና፣ እናስታርቃችሁ በማለት፣ ወይም በምርጫ ላይ በሚካሄድ ውድድር ህዝባችን የሚመኘውን ዕውነተኛ ስልጣኔን ሊቀዳጅ ይችላል ወይ? በዚህ ዐይነቱ የውሸት ሽንግልና በአገራችን ምድር ዕውነተኛ ሰላምና መረጋጋት ይመጣል ወይ? „ህጋዊ መንገዱን“ ተከትለን በማሽነፍ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመኘውን ዕድገትና ሰላም እናመጣልሃለን የሚሉት የተለያዩ ተቃዋሚ ኃይሎች ትግላቸው ከልብ የመነጨ ነው ወይ? ወይንስ ትግላቸው የአገዛዙን ዕድሜ ለማቆየትና የህዝባችንን ሰቆቃ ለማርዘም ነው? በባልና በሚስት መሀከል ያለ ጸብ ይመስል „እናንተ ኢትዮጵያውያን ናችሁ ተስማምታችሁ ስሩ፣ እናስታርቃችሁ“ እያሉ እዚህና እዚያ ሽር ጉድ የሚሉት በእርግጥስ በአገራችን ምድር የሰፈነውን አስከፊ ሁኔታ ተገንዝበውታል ወይ? ከአሜሪካም ሆነ ከአውሮፓ ወደ አገር ቤት ሲመላለሱ ወደ ውስጥ በመግባት ህዝባችን የሚኖርበትን አስከፊ ሁኔታ ይመለከታሉ ወይ? እነሱ እንደሚሉት በእርግጥስ በሽምግልና አማካይነት የአገራችን ሁኔታ አንዳች ዐይነት ለውጥ ያያል ወይ ? በምርጫ ተወዳድሬ አሸንፌ ስልጣን ይዛለሁ የሚለውንና ለሽምግልና እዚህና እዚያ ጉድ ጉድ የሚለውን እኔ ብቻ ሳልሆን ሰፊው ህዝባችን የሚጠይቀውና መመለስ ያለበት በእርግጥስ አገዛዙ ራሱን መጠየቅ የሚችል ነው ወይ? አገሪቱ ወዴት እንደምትጓዝ የገባው ኃይል ነው ወይ? ማመዛዘን ይችላል ወይ? ወደታች በዝርዝር እንመልከት።
ሰፊው ህዝብ የሚለው ! ችግሬን በሚገባ የተረዳለኝ ሰው የለም!
እንደ አስተዳደጋቸው፣ እንደ ዕውቀት አቀሳሰማቸውና እንደ አመለካከታቸው የተለያዩ ሰዎች የአንድን አገር ሁኔታና የህዝቡን ኑሮ በተለያየ መልክ ሊረዱቱና ሊተረጉሙት ይችላሉ። አንዳንዶቹ ችግሩ ተፈጥሮአዊ ስለሆነ በዚህ መቀጠል አለበት በማለት የራሳቸውን የቅንጦት ዓለም ብቻ እየኖሩ ህብረተሰብን አዝረክርከው ታሪክን ሳይሰሩ ያልፋሉ። ሌሎች ደግሞ በተለይም በአሁኑ ኢንፎርሜሽን የሚባለው ነገር በተትረፈረፈበት ዘመንና፣ ዕውነትን ከውሸት ነጥሎ ማወቅ በማይቻልበት ዓለም የአንድን ህዝብ ዕድል ቀድሞውኑ በተዘጋጀ የሃሳብ ክልልና የኃይል አሰላለፍ ውስጥ ብቻ መፍታት እንደሚቻል ያስተምራሉ። አንድ አገዛዝ የፈለገውን ያህል አረመኔ ተግባር ቢፈጽምም እሱን እሹሩሩ በማለትና የዓለም አቀፍ ኮሙኒቲ የሚባለውን በመማፀን አንዳች ዐይነት ለውጥ የሚመጣ ይመስላቸዋል።
እንደሚታወቀው በአ.አ ከ1989 ዓ.ም ጀምሮ ዓለም ወደ መንደርነት እየተለወጠች የመጣችበት ዘመን ነው እየተባለ ነበር ይሰበክ የነበረው። ስለሆነም የዓለም ህዝብ በርዕዮተ-ዓለም መከለሉን አቁሞ ሁሉም በመፈቃቀር በዚህች ዓለም በብልፅግናና በሰላም የሚኖርባት ዘመን መጣ እየተባለ ነው ይነገር የነበረው። ከ20 ዐመት የግሎባላይዜሽና የነፃ ገበያ ሰበካ በኋላ የዓለም ህዝብ በሰላምና በብልጽግና ሲኖር

አይታይም። የባሰውኑ ጦርነት፣ አለመረጋጋት፣ የሀብት መባከንና የጥቂቶች መበልጸግ፣ የእስላም አክራሪዎች የተባሉ ተፈጥረው በእነሱና እነሱን እንዋጋለን በሚለው የምዕራቡ ዓለም ከፍተኛ ፍጥጫ መፈጠር፣ በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ሴቶችና ወጣቶች አስከፊ በሆነ የስራ መስክ በመሰማራት ለኢንዱስትሪ አገሮች የሚያመርቱበትና እንደባሪያ የሚታዩበት ሁኔታ...ወዘተ. የዚህ የዓለም ወደ አንድ መንደርነት መለወጥ ገጽታዎች ናቸው። የሰው ልጅ እንደ ዕቃ የሚታይበትና፣ የሰው በሰው ግኑኝነትም ወደ ገንዘብ ግኑኝነት የተለወጠበትና፣ የሰውነት ኦርጋኖች ሳይቀሩ ወደተራ ሸቀታሸቀጥነት በመለወጥና በመሽጥ የግሎባል ካፒታሊዝምን አስከፊ ባህርዩን የምንመለከትበት እንጂ፣ የዓለም ማህበረሰብ በደስታና በብልጽግና የሚኖርበትን ዘመን አይደለም የምናየው። ከዚህም በመነሳት በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች ዲሞክራሲያዊ ስነ-ስርዓቶች ሳይሆኑ የሰፈኑት፣ ጭቆናና የህዝብ መፈናቀል፣ እንዲሁም ድህነትና የአካባቢ መበላሸት የምስኪን ህዝቦች ዕጣ በመሆን ብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ አገራችንንም ጨምሮ ታሪክ የሚሰራባቸው መሆናቸው ቀርቶ ወደተራ የቆሻሻ መጣያነት የተለወጡበትን ሁኔታ አንዳንዶቻችን በቁጭትና በፀፀት እንመለከታለን፣ ሌሎቻችን ደግሞ ይህንን ለማየት አቅቶን በዚህ በተወናበደና ሰውን በሚያወናብድ ዓለም ውስጥ ገብተን እንከንፋለን። ጥቂቶች ደግሞ ለህዝብ ዲሞክራሲያዊ መብት እንታገላለን በማለት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚካሄደውን አልአግባብ ድርጊት ዝም ብሎ በማለፍና የህዝብን አስተሳሰብ ወደሌላ አቅጣጫ እንዲያመራ በማድረግ የአንድ ህዝብ የነፃነት ትግል ዕውነተኛውን ፈር እንዳይዝ ያደርጋሉ። ይህም ማለት እንደ ዕውቀት አቀሳሰማችን፣ እንደሰብአዊነትና ኢሰብአዊነት ባህርያችንን ይህችን ዓለም በተለያየ መነፅር ነው የምንመለከታት። በተለይም ገንዘብና ስልጣን ከፍተኛ ሚናን በሚጫወቱበት ዓለም ውስጥ ለዲሞክራሲ እንታገላለን የሚሉ ኃይሎች ከዕውነተኛ ምሁራዊ እንቅስቃሴና ዕውነተኛ ነጻነት ይልቅ የራሳቸውን ጥቅም በማስቀደም የአንድን ህዝብ የስልጣኔ ጥም ያራዝሙታል። ታሪክን እንዳይሰራ፣ ዕውነተኛ ነፃነትን እንዳይቀዳጅና ተከብሮ እንዳይኖር መሰናክል ይሆኑበታል። ይህ በኛ የተጀመረ አይደለም። ከሶስት ሺህ ዐመት ጀምሮ በተለይም የአውሮፓን ምሁር ሲያናክስ የነበረ ነው። ዕውነተኛውን የስልጣኔ ፈለግ በሚከተሉና እሱን በሚቃወሙ መሀከል የጦፈ ትግል ተካሂዷል። በዘመነ ግሎባላይዜሽንና የኒዎ-ሊበራል ዓለም በተለይም ለእንደኛ ላለው የምሁር ደካማነት ለሰፈነበት አገር የአገራችንን የችግር መነሻ፣ በየጊዜው ጥልቀት ማግኘትና ውስብስብ መሆን ለመረዳት ደግሞ እጅግ አስቸጋሪ እንደሚሆን መረዳቱ ከባድ አይደለም። ያለፈውን የ21 ዓመቱን ትግል፣ በተለይም ደግሞ በምርጫ 97 ዓ.ም የተከሰተውን ሁኔታ ስንመለከት የቱን ያህል አዲሱ የዓለም ሁኔታ ሁላችንንም እንደ አዘናጋን መገንዘቡ ከባድ አይሆንም።
ይህ ዐይነቱ የርዕዮተ-ዓለም ውዥንብርነትና የዓለምን ሁኔታ በጠባቡ መመልከት ነው ለዕድገታችንና ለስልጣኔ እንዲሁም ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት መገንባት እንቅፋት የሆነው። የተማረው ኃይል የሃሳብ ጥራትን በማግኘት የህዝብ አለኝታ ከመሆንና አኩሪ አገር ከመገንባት የታገደው በዓለም ላይ የተነዛው የተሳሳተ ዕውቀትና ኢንፎርሜሽን ጭንቅላቱንና ዐይኑን ስለጋረደው ነው። እዚህ ላይ የዳንቴን የአምላኮች ኮሜዲ የሚለውን ግሩም ስነ-ጽሁፍ መመልከቱ በጣም ጠቃሚ ነው።የሰው የማሰብ ኃይል ከመደብዘዙ የተነሳና፣ መጥፎ ነገሮችን እንደደህና ነገር አድርጎ በመውሰድ ለታዳጊውና ለመጪው ትውልድ አፀያፊ ባህል በማስፋፋት ላይ ነው።ዝሙተኝነት መስፋፋት፣ ውሸት፣ ለገንዘብ መንሰፍሰፋና፣ ለገንዘብ ብሎ የሌላውን ሰው ህይወት ማጥፋት፣ ጉቦተኝነት፣ በስራ ማላገጥና ዲስፕሊን መጉደል... ወዘተ. የአገራችን ገጸ-ባህርዮች ሆነዋል። በተለይም በአለፉት 7 ዐመታት ህዝባችን የሚወተውተው ችግሬን የተረዳልኝ የለም በማለት ነው። ዛሬ በአገራችን ምድር አፍጦና አግጦ የሚታየው አሰቃቂው ሁኔታ የመነጨውና በየቀኑ የሚመረተው ተማርን በሚሉ ሰዎች፣ ግን ደግሞ የተሳሳተ ዕውቀትን አንግበው በእልከኝነት ወደ ፊት በሚሸመጥጡ ነው። በአገራችን ምድር የሚታየው ግፍና አስቀያሚ ሁኔታ ከላይ ዱብ ያለ ወይም የእግዚአብሄር ቁጣ አይደለም። የዚህ ሁሉ ዋናው መሰረታዊ ችግር በሰፊውና በጥልቀት ለማሰብ ካለመቻል የመጣ ነው። ይህም ማለት፣ 1ኛ) እጅግ ጠባብ በሆነ አስተሳሰብና አመለካከት መመራት፣ 2ኛ) የአንድን ህብረተሰብ ሁኔታና የተጓዘበትን ጠመዝማዛ ጉዞ በቅጡ ለመመርመር አለመፈልግና፣ 3ኛ) በየጊዜው ለሚነሱት ችግሮች

መልስ ለመፈለግ አለመሻት፣ 4ኛ) እንዲሁም ደግሞ የአንድን የህብረተሰብና የባህል ችግሮች ኢምፔሪሲስቲያዊ በሆነ ዕውቀት ለመመርመር መቻኮል፣ 5ኛ) ከዚህም በመነሳት የራስን ጥቅም በማስቀደም ለዕውነተኛ ነፃነትና ለአጠቃላይ ለሆነ ማህበረሰብአዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት መደረግ የሚገባውን ትግል በዚህም በዚያም ብሎ ለማጨናገፍ መሞከር፣ 6ኛ)በራስ ሎጂክና በራስ ጥቅም በመመራት በተለያየ መልክ ከውጭ የሚመጣውን ህብረተሰብን የሚያፈራርስ ኢኮኖሚያዊ ፖሊሲ ልክ ከቀና ስዎች እንደመጣና ከሱ በስተቀር ሌላ አማራጭ የሌለ ይመሰል ተግባራዊ በማድረግ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ሁኔታዎችን ማዛባትና ማዘበራረቅ ነው የአገራችንን ሁኔታ ውስብስብ ያደረገውና፣ ህዝባችን የሚመኘውን ሰላምና ደስታን እንዳናጎናጽፈው ሊያግደን የቻለው። ህዝባችን የሚለው ድሮ የውጭ ጠላት ከባድ መሳሪያና የመርዝ ጋዝ በማንገብ ነበር ሊወረን የሚመጣው፤ የዛሬው ግን እጅግ የረቀቀና በተወሳሰበ መልክ በመምጣት የሚፈታተነንና፣ እንደ አገርና እንደህብረተሰብ፣ ወይም ደግሞ እንደ ማሀበረሰብ እንዳንኖር የሚያደርገን ኃይል ነው ከፊታችን ተደንቅሮ የሚፈታተነን እያለ ነው እቅጩን የሚነግረን። ስለዚህም ይላል የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ዛሬ በአገራችን የሰፈነው የጭቆና አገዛዝ፣ ፋሺሽታዊ ድርጊቱ፣ ሀብትን መቆጣጠር፣ አብዛኛውን ህዝብ ደግሞ ደሀና አቅመቢስ ማድረግ፣ የአገሪቱን ሀብት መዝረፍና የተወሰነውን የህብረተሰብ ክፍል በ21ኛው ክፍለ-ዘመን ለፊናንስ ካፒታል ባርያ እንዲሆን ማድረግ፣ አጠቃላይ የሆነ የኢኮኖሚ ድቀት መስፈንና የአብዛኛውን ህዝብ አስተሳሰብ በንግድና ቶሎ ቶሎ ገንዘብ ወደሚያገኝበት እንዲያዘነብል ማድረግ፣ የወጣቱን መንፈስ በተለያዩ ድረጎች ማደንዘዝና፣ ለብሄራዊ ነፃነትና ለሀገር ፍቅር ያለውን ፍላጎት ሙሽሽ እንዲል ማድረግ፣ በተለይም ለአሜሪካ ፍቅር እንዲኖረው ማድረግና፣ ማንኛውም ነገር ከአሜሪካ ፍላጎት ውጭ ሊመጣና ሊካሄድ እንደማይችል እንዲያስብ ማድረግ፣ ባጭሩ እግዚአብሄር የፈጠረለትን የማሰብ ኃይል በመጠቀም ለዕውነተኛ ስልጣኔ እንዳይታገል ማድረግ፣ እነዚህ ሁሉ ባለፉት 21 ዐመታት እየተጠናከሩ የመጡና፣ አገራችን በሁሉም አቅጣጫ እንድትዳከምና ብሄራዊ ነፃነታችን እንዲንሸረሸር ያደረጉ ናቸው።
ለምንድነው ያ የተሰበከለት፣ የተደሰኮረበት የነፃ ገበያና ግሎባላይዜሽን እንደተለፈፈው ዕውነተኛ ዕድገትን ሊያመጣ ያልቻለው ? ግራ የተጋባው ህዝባችን እየደጋገመ የሚጠይቀው፣ አፄ ኃይለስላሴ ከወደቁ በኋላ ይሰበክልና ይለፈፍ የነበረው በአብዮትና በሶሻሊዝም አማካይነት የብልጽግናውን ዓለም ታያላችሁ፣ ጭቆናን ለአንዴም ለመጨረሻም ጊዜ በማስወገድ በሰላምና በብልጽግና ትኖራላችሁ እየተባለን ነበር። በሱ ፈንታ ግን መተራረድና መመሰቃቀል እንዲሁም፣ ህገ-አልባነት ሰፍኖ ስንትና ስንት መቶ ዐመታት የተጓዝንበትን የአገር ግንባታ በአንድ ምሽት እንድናወድም ተደርጓል። ይህ ቀን መቼ ያልፋል ብለን ስንጠባበቅ የወያኔ አገዛዝ ከሰማይ እንደወረደ ዱብዳ በገበያ ኢኮኖሚ አማካይነት ለመጨረሻ ጊዜ ብልጽግናን አመጣላችሁ አለን። ሁላችንም የነፃ ገበያን ዘፈን መዝፈን ጀመርን። ይሁንና ግን ከገበያ ኢኮኖሚ የተረፈን የባሰ ድህነት፣ በኑር ውድነት መሰቃየትና በውጭ ዕርዳታ መኖር ነው። በእነ አይ ኤምፍና በዓለም ባንክ ረቆ የቀረበው የነፃ ገበያ ፖሊሲ ለምን የተፈለገውን ውጤት ሊያመጣ አልቻለም?1ኛ) የአገራችንን የማቴሪያልና፣ የህዝባችንን የህሊና አውቃቀርና ዕውነተኛ ፍላጎት የሚያንፀባርቅ አልነበረም። እንዲያው እያንዳንዱ አገር ካለው የማቴሪያል ሁኔታ ባሻገር በገበያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ ሊጠቃለልና፣ የኢኮኖሚ ዕድገትም ሊመጣ ይችላል ከሚለው ተራ ስሌት የመነጨ በመሆኑ ከመጀመሪያውኑ እንደዚህ ዐይነቱ ፖሊሲ ህብረተሰብአዊ ቀውስ እንደሚያመጣ የታወቀ ነበር። 2ኛ) ፖሊሲው ተግባራዊ በሚሆንበት ጊዜ የትኛው የህብረተሰብ ክፍል ነው እንደ እንቀሳቃሽ ኃይል ሆኖ ኢኮኖሚውን መልክ ሊያሲዘው የሚችል? የሚለውን ያጠና አልነበረም። እንደሚታወቀው የገበያን ኢኮኖሚ ለማዳበር የግዴታ ብቃት ያለውና የቴክኖሎጂ ትርጉምን የተረዳ የህብረተሰብ ክፍል ያስፈልጋል። እንደዚህ ዐይነቱ የህብረተሰብ ክፍል በሌለበት አገር ውስጥ ከቴክኖሎጂያዊ ምጥቀትና ሰፋ ካለ የገበያ ኢኮኖሚ ይልቅ የግዴታ በንግድና በሌሎች የአገልግሎት መስኮች ላይ ርብርቦሽ የደረጋል። ይህም ማለት በዚህ መልክ ተግባራዊ የሚሆነው የገበያ ኢኮኖሚ የሀብት መባከንን ያስከትላል። 3ኛ) ፖሊሲው ህብረተሰብን ከሁሉም አንጻር ከመገንባት(Nation Building) ጋር

የተያያዘ አይደለም። ስለሆነም በአገሪቱ ውስጥ የሚገኘውን ሀብት በሙሉ፣ የሰውንም ኃይል ጨምሮ ለማንቀሳቀስ የሚያስችል አይደለም። እንዲያው በደፈናው ሁሉም ነገር ከገበያ ኢኮኖሚ አንፃር ብቻ የታየና፣ የሰው ልጅ ፍላጎት በተወሰነ ነገር ላይ ብቻ እንዲሽከረከር በማድረግ ህብረተሰቡን ለመበወዝ የሚያመች ሁኔታን ነው የፈጠረው።
ስለሆነም ከነፃ ገበያ በስተጀርባ የተጠነሰሰውን አደገኛ መርዝ ለመመርመር አንድም የቃጣ ኃይል አልነበረም። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የነፃ ገበያ የሚባለው ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ጀምሮ፣ ህብረተሰብአዊ ሀብት እየተዘረፈ በጥቂ ሰዎችና አንድ ኩባንያ ስር የሚጠቃለልበት ሁኔታ ሲፈጠር ዝም ብሎ ማየት የተቃዋሚውን ኃይል ትዝብት ውስጥ ከቶታል። ከዚህም ባሻገር በዚህ ዐይነቱ የነፃ ገበያ ኢኮኖሚ አማካይነት ህዝባችን የባሰውኑ ወደድህነት ዓለም ሲገፈተርና አቅመ-ቢስ ሲሆን ከህዝባችን ጎን ቆሞ ይህንን ዐይነቱን ምስቅልቅልና አገር አፍራሽ ሁኔታን በጋራ ሊቋቋም የሚችል ኃይል ብቅ ሊል አልቻለም። ስለሆነም ህዝባችን እየደጋገመ የሚለው የአንድ ተቃዋሚ ኃይል የህዝብ አለኝታነት ሊረጋገጥ የሚችለው በእንደዚህ ዐይነቱ ባህላዊና ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀል ወቅት ችግራችንን ተረድቶ ሊታገልና ሊያታግል የሚችል ኃይል ሲኖር ብቻ ነው። ይሁንና በአገራችን ምድር ይህንን ሁኔታ ሊጋፈጥ የሚችል ኃይል ብቅ ሊል አልቻለም በማለት ነው ሮሮውን የሚያሰማው። በእርግጥም ከሌሎች የአፍሪካ አገሮች ጋር ስንወዳደር በአገራችን ለሰፊው ህዝብ የሚያስብና፣ ከጎኑ የቆመ የበሰለ ምሁር ማግኘት ከባድ የሆነበት ሁኔታ ተፈጥሯል ማለት ይቻላል። አብዛኛው ምሁር ነኝ ባይ አያገባኝም እንደማለት የሚታዩ ነገሮችን ዝም ብሎ የሚያልፍ እንጂ አንድ ህዝብ በዚህ ዐይነት መልክ መኖር የለበትም በማለት ሊጋፈጥ የተዘጋጀና የሚዘጋጅ አይደለም። ማህበራዊና ህብረተሰብአዊ ንቃተ-ህሊናው በጣም ደካማ ነው ማለት ይቻላል። ከዚህም በመነሳት ሰፊው ህዝብ የሚለው አንድ ተቃዋሚ ነኝ የሚል ፓርቲ ዋና ዐላማው ለስልጣን መታገል ብቻ ሳይሆን፣ በየጊዜው በህብረተሰብ ውስጥ የሚከሰቱትን አደገኛ ነገሮች በመመርመርና ለህዝብ በማሳወቅ አጥብቆ እንዲታገለውና በመንግስት ላይ ግፊት በማድረግ አስቸኳይ እርምጃ እንዲወስድ ማድረግ ነበር። ይህ ሲሆን ብቻ ይላል የኢትዮጵያ ህዝብ፣ ለዕውነተኛ ነፃነት የሚደረገው ትግል ትክክለኛውን ፈር ለመያዝ ይችላል በማለት እቅጩን ይነግረናል።
ከዚህም በመነሳት ህዝባችን የሚለው ብዙ ነገሮች እየተድበሰበሱ በመሄድና በመከማቸታቸው ዕውነትን ከውሸት መለየት የማንችልበት ሁኔታ ተፈጥሮአል። ማን ከኛ ጋር ተስልፎ እንደሚታገል፣ ዓላማውስ ምን እንደሆነ ለማወቅ ግራ የተጋባንበት ሁኔታ ተፈጥሯል በማለት ያለበትን እጅግ አስቸጋሪ ሁኔታ ያሰማል። አዲሱ ትውልድም ሆነ ከአብዮቱ የተረፈው ታጋይ የአገራችንን ሁኔታ በሰፊው በመገምገም አማራጭ መፍትሄ በመስጠት ህዝቡን ሲያስተምርና ታሪካዊ ሚናውን በመረዳት ለነፃነቱና ለክብሩ እንዲታገል የሚያግዙት ስትራቴጂ ሲሰጥ አይታይም። በተለይም አንድ ሰሞን ሶሻሊዝም እያለ ይታገል የነበራውና ከአብዮቱ የተረፈው ዛሬ በምን የቲዎሪ መሰረት ላይ ተንተርሶ ለየትኛው ዓላማ እንደሚታገል ግልጽ አይደለም። በአጠቃላይ ሲታይ ተቃዋሚ ነኝ የሚለው በአብዮቱ ውስጥ በንቁነት ያልተሳተፈውና፣ አዲሱ ትውልድና ከአብዮቱ የተረፈው ኃይል አጠቃላይ ከሆኑ ነገሮች አልፈው በመሄድ በአዲስ አስተሳሰብ በመመራት ምን ለሚመስል ህብረተሰብና፣ በምንስ ዐይነት የኢኮኖሚ ቲዎሪና ፍልስፍና በመመራት ነው አገራችንን መገንባት የምንችለው የሚለውን ከባድ ጥያቄ በማንሳት ሲወያዩና ሲከራከሩ አይታይም፤ አይሰማም። እንደሚታወቀው ዓላማው ግልጽ ያልሆነና በቲዎሪ ተመስርቶ የማይደረግ የትግል ዘዴ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እንደሚከት ከብዙ የሶስተኛው አገሮች ልምድ መቅሰም ያስፈልግ ነበር። ስለሆነም ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል በሙሉ ግልጽ የሆነ በሃሳብ ላይ የተመረኮዘ ውይይትና ክርክር ካላደረገ ትግላችን መና ሆኖ መቅረቱ ብቻ ሳይሆን፣ በአገዛዙና በውጭ ኃይሎች መሀከል ያለው ያልተባረከ ጋብቻ ተጠናክሮ በመቀጠል እቺ የሶስት ሺህ ዐመት ታሪክ አላት የምትባል አገር ለመጭው ትውልድ የምታስተላልፈው የታሪክ ቅርስ አይኖራትም። ከዚህ በመነሳት የኢትዮጵያ ምሁር፣ በተለይም ደግሞ ወጣቱ ደፍሮ መወያየትና መከራከር ያለበት ጉዳይ በሚቀጥሉት ነጥቦች ላይ ነው።

የአገር ጉዳይ!
ለምንድነው የኢትዮጵያ ህዝብ ከአንዴም ከሁለቴም በላይ ከውጭ የመጣበትን ጠላት እየተጋፈጠ መክቶ የመለሰው? ለምንድነው እጁን አንስቶ በመስጠት አገሩ እንዲደፈር ያላደረገው? ምክንያቱም ቀላል ነው። ምክንያቱም የውጭ ኃይል ባርነትን ማስፈሩ ብቻ ሳይሆን፣ ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፉ የታሪክና የባህል ቅርሶችን በማውደም አገራችን እንደ አገር የሚያስጠራት የታሪክ ቅርስ እንዳይኖራት ስለሚያደርግ ነው። ይህ ማለት ግን፣ ዕድገትን የሚያግዝ፣ ህብረተሰብአዊ መተሳሰርን የሚያድስና ዕውነተኛ ግለሰብአዊ ነፃነትን የሚያመጣን ከውጭ የሚመጣን መንፈስን የሚያድስ ባህል መቃወሙ አልነበረም። እንደሚታወቀው ከአስራዘጠነኛው ክፍለ-ዘመን ጀምሮ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መልክ የተካሄዱት ወረራዎችና ሰተት ብሎ መግባቶች ለህዝቦች ዕውነተኛ ነፃነትን ለማምጣት አልነበረም። ስለዚህም በዚያን ጊዜ ማንም የሚጋፈጠኝ ኃይል የለም ብሎ መሳሪያውን አንግቦ የሚመጣን ኃይል ለመቋቋምና መክቶ ለመመለስ ከባድ አልነበረም። በዘመነ ግሎባላይዜሽንና በነፃ ገበያ ዘመን ግን ትግሉ በቀጥታ በመጋፈጥ መክቶ መመለስ የማይቻልበት ሁኔታ ተፈጥሯል። የግሎባል ካፒታሊዝም ውስብስብነትና ኃያልነት፣እንዲሁም በረቀቀ መልክ ገብቶ አንድን አገር ምስቅልቅሉን ማውጣት ብዙዎቻችንን አቅመ-ቢስ ወደ ማድረግ አድርሷል። በሌላ ወገን ደግሞ ይህንን ዐይነቱን በረቀቀ መልክ የሚካሄድን ወረራና አገርን ማውደም አንዳንዶች በጊዜው ሲያሳስቡ የድሮውን ነገር ቀሰቀሳችሁብን፣ ይህ ዐይነቱ የትግል ዘዴ አክራሪነት ነው በማለት አንዳንዶች ዘመቻ በማድረጋቸውና በማዘናጋታቸው ቀደም ብሎ በቲዎሪ ወይም በምሁር ደረጃ ሊደረግ የሚገባውን መከላከልና ዝግጅት ማድረግ የማይቻልበት ሁኔታ ሊፈጠር ቻለ።
ከዚህ ስንነሳ ይህንን የተወሳሰበውን ዓለም የሚረዱ በጣም ጥቂቶች ናቸው። ይህ ብቻ ሳይሆን አንድ አገር በሁለንታዊ መልኩ የሚገለጽና፣ በተለይም ደግሞ በጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረት ላይ ካልቆመ በውጭ ኃይል የሚጠቃ መሆኑን ሊረዱ የሚችሉ እምብዛም ይደሉም። እያንዳንዱ ምሁር ነኝ ባይ አንድ አገር ማህበረሰብአዊ፣ ባህላዊ፣ ስነምግባራዊ፣ ሞራላዊና ህብረተሰብአዊ እንደመሆኑ መጠን እንደዚህ ዐይነቱ በተከታታይ ጥናት በሚደረግ ዝግጅት ነው መልክ ሊይዝና በፀና መሰረት ላይ ሊገነባ የሚችለው ብሎ ካላስተማረ የብዙዎቻችን ጉዞ የጭፍኖች ዐይነት ጉዞ ነው የሚሆነው። በተለይም ደግሞ የብሄረ-ሰብ ትግልና ነፃነት የሚለው አስተሳሰብ በሰፈነበት አገር፣ የህብረተሰብን በሁለንታዊ መልክ መገለጽ ለመጠየቅ፣ ለመመራመርና ለመረዳት የሚፈልግ የለም። በአንድ አስተሳሰብ ግን ደግሞ ሳይንሳዊ ይዘት በሌለው ነገር ላይ የሚደረግ ትግል አለመደማመጥን፣ እንዲያም ሲል አክራሪነትን በማስቀደም መመለስ የሚገባውና ማንኛውንም ግለሰብ የሚጠቅም መልስ ተድበስብሶ እንዲቀር ይደረጋል። በተጨማሪም የአድርባይነት ባህል በተስፋፋበት፣ ከአገር ይልቅ ግለሰቦችን በማስቀደም ዕውነተኛ ህዝባዊ ነፃነት ለማምጣት በማይታሰብበትና ከጭንቅላት ጋር ባልተዋሃደበት አገር፣ ለብዙዎች የአገርን ትርጉምና ምንነት ለማስረዳት እጅግ አስቸጋሪ ይሆናል። ከዚህ ሌላ አሁን የተያዘው ፈሊጥ ደግሞ አንዳንዶቻችን የኢትዮጵያን አገርነት በአሜሪካ መነፅር የማየቱ ጉዳይ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል። የኢትዮጵያ ህዝብ ዕድልና፣ ኢትዮጵያም እንደአገር የመኖሯ ጉዳይ ከአሜሪካ ስትራቴጂያዊ ስሌት ውጭ ሊታሰብ እንደማይችል ቀድሞውኑ እንዳንዶች ጭንቅላታቸው ውስጥ የቀረጹ ይመስላሉ። ባለፉት ዐመታት ለፕሬዚደንት ኦባማም ሆነ ለወይዘሮ ክሊንተን የተጻፉትን የልምምጥና የሮሮ ደብዳቤዎች ለተመለከተ አንድ ግንዛቤ ውስጥ ሊከተን ችሏል፤ ይኸውም የኢትዮጵያ ህዝብ የነፃነት ጥያቄ ከአሜሪካ ጥቅም ጋር የተሳሰረ ነው እንደማለት ነው። ይህ ዐይነቱ አካሄድ ደግሞ የኢትዮጵያን የሶስት ሺህ ዘመን አኩሪ ታሪክ የሚፃረር ብቻ ሳይሆን፣ የኢትዮጵያ ህዝብ ከአንዴም ሁለቴም በላይ በጋራ በመነሳት መክቶ የመለሰውን ጠላት ከቁጥር ውስጥ እንዳናገባ የሚያደርግ እጅግ አደገኛ አካሄድ ነው። በዚህ ዐይነት ለኢትዮጵያችን በምናደርገው ትግል ግራ የተጋባን ብቻ ሳንሆን፣ ለአገራችን ነጻነት ቆመናል የምንል ሰዎች ከሁለት አንዱን በመምረጡ ላይ ችግር ውስጥ ገብተናል። ለምሳሌ የዛሬው የአገራችን አገዛዝና አሜሪካ እጅና ጓንቲ ሆነው እንደሚሰሩ የታወቀ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ከሃያ

አንድ ዐመት ጀምሮ በአገራችን ምድር የተካሄደው አረመኔያዊ ሁኔታን፣ በሀብት መባለግ ከአሜሪካ ፖሊሲና ጣልቃ-ገብነት ውጭ ተነጥሎ በፍጹም ሊታይ አይችልም። አሜሪካ እንደዚህ ዐይነቱን አረመኔያዊ አገዛዝ የደገፈና የሚደግፍ ከሆነ በምን ተዐምር ነው የዲሞክራሲና የእኩልነት ጠበቃ ሊሆን የሚችለው? እንደሚታወቀው ዲሞክራሲና እኩልነት ዓለማዊ ህጎችና መሰረተ-ሃሳቦች እንደመሆናቸው መጠን ለአንዱ የሚሰጡና ለሌላው የሚከለከሉ አይደሉም። አንድ ለዲሞክራሲና ለእኩልነት ቆሜያለሁ የሚል ኃያል መንግስት ደግሞ በአንድ አገር ውስጥ በአገዛዙ በደል የሚፈጸም ከሆነ፣ ከእኩልነት ይልቅ በደሀና በሀብታም መሀከል መረን የለቀቀ ልዩነት ከተፈጠራና፣ በዚያውም ነፃነት ከታፈነ ይህ እንዲቆም የግዴታ መጎትጎትና፣ ማስቆም የማይችል ከሆነ ደግሞ ልዩ እርምጃ በመውሰድ ለነፃነት እንታገላለን የሚሉትን ኃይሎች መደገፍ ነበረበት። በአሜሪካ የውጭ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ግን አሜሪካ ለነፃነት እንታገላለን በሚሉ ኃይሎች ጎን የቆመበት ጊዜ ታይቶ አይታወቅም። እንዲያውም ዕውነተኛውን ነፃነት ሲያፍንና ብሄራዊ ነፃነትን ሲቀናቀን እንደነበር የአንዳንድ የላቲንና የአፍሪካ አገሮች የትግል ታሪክ ህያው ምስክር ነው።ይህንን የሚክድ በአሜሪካ ፍቅር ያበደ ብቻ ሳይሆን፣ የአንድን ህዝብ የነፃነት ፍላጎት የሚክድና፣ ለዕውነተኛ ነፃነትና ለአገር ልዕልነት የሚደረገውን ትግል ለማጨናገፍ የሚሞክር ነው።
ከዚህ ስንነሳ የአገራችን እንደ አገር የማየቱና የመገንባቱ ጉዳይ ከአሜሪካን ስትራቴጂያዊ ጥቅም ውጭ ማየት የሚያስፈልግ ይመስለኛል። የአሜሪካን መንግስትና የኢትዮጵያ ህዝብ ህልም እሳትና ጭድ ሆነው መታየት ያለባቸው እንጂ፣ የለም ካለሱ ሊሆን አይችልም ብለን የምንታገል ከሆነ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ፀረ-ኢትዮጵያ ትግል ነው የምናካሂደው ማለት ነው። በመሆኑም የአሜሪካንን ጣልቃ-ገብነት የሚቃወም ሁሉ በሌላ ዐይን እየታየ ፍዳውን የሚያይበት ምንም ምክንያት የለም። የብዙዎቻችንም ችግር የዓለምን የተወሳሰበ ሁኔታ በየዋህነት መነፅር ማየታችን ብቻ ሳይሆን፣ በዚህ ዓለም ላይ የሚፈፀሙት በደሎች በሙሉ ጥቂት አሸባሪዎችና አምባገነን ኃይሎች የሚፈጥሩት ችግር ነው የሚል የፖለቲካ ሳይንስን ህግ የሚፃረር አካሄድ ነው። በሌላ አነጋገር ዛሬ በዓለም ላይ የሚፈፀሙት የአስተዳደር በደሎች፣ ጭቆናዎች፣ የኃይል አሰላለፍ ሁኔታ፣ በጥቂት ሰዎች እጅ የሀብት ክምችትና በመሳሪያ ታጥቆ አንድን ህዝብ ማሰቃየት ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ የተፈጠሩና እየተጠናከሩ በመምጣት ስር እየሰደዱ ናቸው። ይህ ደግሞ ካለምክንያት አይደለም። በብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም በአፍሪካ ውስጥ የነቃና ሰፋ ያለ፣ እንዲሁም ደግሞ ለነፃነትና ለዕድገት የቆመ ኃይል በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጠር ባለመቻሉ ኋላ ቀር ኃይሎችን በስለላና በመሳሪያ በማሰልጠን የጭቆና አገዛዝን ለማስፈን አመቺ ነበር። ስለ ኢኮኖሚ ዕድገት፣ ስለነፃ ገበያና ስለ ዓለም አቀፍ የስራ ክፍፍል ትምህርት የተማረ ወዲያውኑ ሊገነዘብ የሚችለው፣ የአብዛኛዎቹ የአፍሪካ መንግስታት ተልዕኮ ወደ ውስጥ ጭቆናን ማስፋፋትና ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን መግታት ሲሆን፣ በዚያውም መጠን ደግሞ አገሮችን በአሜሪካን ስትራቴጂያዊ ስሌት ስር ጥገኛ እንዲሆኑ በማድረግ የባርነት ዘመኑን ማራዘምና የአገርን ትርጉም ማሳጣት ነው። ይህ ዐይነቱ የፀረ-ዕድገትና የፀረ-ነፃነት ትግል በዘመነ ግሎባላይዜሽን እጅግ በረቀቀ መልክ የሚካሄድ ሆኗል።
ስለሆነም የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ፣ ለምንድነው ይህ ተማርኩ የሚለው ኢትዮጵያዊ ግራ ተጋብቶ ግራ የሚያጋባኝ? በማለት እሮሮውንና ሀዘኑን ያሰማል። ከምሰማው፣ ከአገር ከሚመጡ ተራ ስዎች ከሚመስሉ ጋር ቁጭ ብዩ ለብዙ ቀናትም ሆነ ሰዓታት ሳወራ የማገኘው ልምድ ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ጠላቱንና አገሩን የሚያውድመውን ኃይል ጠንቅቆ የሚያውቅ መሆኑን ነው። የአሜሪካን ኢምፔሪያሊዝም ጠላቱና አጥፊው እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል። በዚህ ኃያል መንግስትም በየጊዜው የተሰነዘረበትን የረቀቀ አገር አውዳሚ ሴራ ተገንዝቧል። የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር ተቃዋሚ ነኝ የሚለውንና እዚህና እዚያ የሚሯሯጠውን ኃይል የመረዳቱ ላይ እንጂ፣ ከሃያ ዐመት በላይ በወያኔና በግብረ-አበሮች የተቀነባበረበትንና የተሰነዘረበትን ሴራ የመረዳቱ ላይ አይደለም። በመሆኑም ተቃዋሚው ኃይል አገር የሚለው ግዙፍ ፅንሰ-ሃሳብ እስካልገባው ድረስ ትግል የሚባለው ነገር ትርጉም አይኖረውም። በየጊዜው ፕሮራም በመጻፍና
 
በመደርደር አገርም መገንባት አይቻልም ነው የሚለው ህዝባችን። ምክንያቱም ቀላል ነው፤ የአንድ አገር ትርጉም ከፕሮግራም በላይ የሆነና በተወሳሰቡ መልኮች የሚገለጽ ብቻ በመሆኑ ነው። ስለሆነም አንድ ፕሮግራም ትርጉም የሚኖረው ይህ የተወሳሰበ የአገር ጉዳይ ከቁጥር ውስጥ የገባ እንደሆን ብቻ ነው። ከዚህ በመነሳት እስቲ አገር ማለት ምን ማለት እንደሆነ በመጠኑም ቢሆን ለመቃኘት እንሞክር። ለምንድነው አንድ ህዝብ አገሬ ብሎ ለአገሩ የሚዋደቀው? አገርስ ማለት ምን ማለት ነው ? አንድ አገርስ ወደ ብሄረ-ሰብነት ሊቀነስ ይችላል ወይ? እነዚህን ጥያቄዎች በመጠኑም ቢሆን ለመመለስ አንሞክር።
በመጀመሪያ ደረጀ ማንም ሰው በአንድ አገር ውስጥ መወለዱ ወዶት ወይም አቅዶት የሚያደርገው ነገር አይደለም። በተጨማሪም ከዚህኛው ወይም ከዚያኛው ብሄረ-ሰብ መወለዱ ያጋጣሚ ጉዳይ እንጂ ከመጀመሪያውኑ የሚታቀድ አይደለም። ስለዚህም አንደኛው አማራ፣ ሌላው ትግሬ፣ ሌላው ደግሞ ኦሮሞ ስለሆነ በኩራት ወይም በዝቅተኛ ስሜት ራሱን የሚያስጨንቅበት ምክንያት የለውም። የዚህ ዐይነቱ የመናናቅና የመጠላላት ስሜት የሚመነጨው በመሰረቱ ሰፋ ያለ ጭንቅላትን ብሩህ የሚያደርግ ዕውቀት(Enlightenment) ስላልተስፋፋና፣ ከዚህም ሆነ ከዚያኛው ብሄረ-ሰብ ተወለድኩኝ የሚል ግለሰብ ራሱን ስለማይጠይቅና ስለማይመራመር ሁልጊዜ በመጠራጠር ዓለም ውስጥ እንድንኖር ተገደናል ። ሰፋ ያለ በሁሉም አቅጣጫ የሚገለጽ ዕውቀት አለመዳበር የግዴታ አገር የሚለውን ስም ወይም ደግሞ ኢትዮጵያን እንድንጠላ ሊያደርገን በቅቷል። ኢትዮጵያ የሚለው ስም ከጭቆናና ከብዝበዛ ጋር በመያያዝ የህብረተሰብአችንን የተወሳሰበ የታሪክ ሂደት እንዳንረዳን በማድረግ የሚያሳፍር ሆኗል። ብሄረተኝነት እንዳይዳብርና ለአገር በጋራ ተነስተን እንዳንሰራ እንቅፋት ሆኗል። የብዙዎቻችን ችግር፣ በተለይም በብሄረ-ሰብ መነፅር የታወርን ማንነታችንን ለመግለፅ የምንሞክረው የመጣንበትን አካባቢ አጉልቶ በማሳየት እንጂ፣ እያንዳንዳችን በአንድ ትልቅ ኮስሞስ ውስጥ ተጠቃለን የምንገኝና፣ ማንነታችንም ሆነ ምኞታችን በጠባቡ ኮስሞስ ውስጥ ሳይሆን በሰፊው ኮስሞስ ውስጥ ብቻ ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችል አይደለም የምንገነዘበው። የብዙዎች በብሄረ-ሰብ መነፅር የታወሩ ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች ዋናው ችግር የተፈጥሮን ህግ በፍጹም ያለመረዳት ችግር ነው። ለምሳሌ አንድ ልጅ ከተፀነሰ በኋላ እዚያው እናቱ ማህፀን ውስጥ ለዘለዓለም ሊኖር አይችልም። ከዘጠኝ ወር በኋላ ተረግዞ ሲወለድ ሊያድግ የሚችለው፣ ሙሉ አካል ኖሮት ሊያስብና ዕውነተኛ ነፃነቱንም ሊቀዳጅ የሚችለውና ፈጣሪ የሚሆነው ሰፋ ባለው ኮስሞስ ውስጥ አየር መተንፈስና ሙቀት ማግኘት ሲችል ብቻ ነው። ይህ ዐይነቱ ባይሎጂካዊ ክንውን ለአገርና ለህብረተሰብ ግንባታም ያገለግላል። ብሄረ-ሰቦችና ጎሳዎች የሚባሉት ነገሮች ዕውነተኛ ነጻነታቸውን መቀዳጀት የሚችሉት በሰፊው ዕውነተኛ ነፃነትና ብርሃን በሚፈናጣቅበት ኮስሞስ ውስጥ ገብተው መዋኘት የቻሉ እንደሆን ብቻ ነው። ይህም ማለት ከጠባቡና ከማያፈናፍነው ጥቃቅኑ የብሄረ-ሰብ ዓለም ሰፊው አገር ለማንኛውም ግለሰብም ሆነ፣ የዚህ ወይም የዚያኛው ብሄረ-ሰብ አባል ነኝ ለሚል የበለጠ ለመዳብር ያመቸዋል። በሌላ ወገን ደግሞ በአንድ ትልቁ ኮስሞስ ውስጥ የተጠበቀው የፀሀይ ብርሃንና ነፃነት መፈናጠቅ የማይችል ከሆነ፣ ለምን እንደዚህ ዐይነቱ ነፃነትን አፋኛና ዕድገትን የሚቀናቀን ሁኔታ ሊፈጠር ቻለ? ብሎ በህብረተሰብ-ሳይንስ ዘዴና በፍልስፍና መነፅር መመርመሩ እጅግ አስፈላጊ ነው። ይህን ከማድረግ ይልቅ በጥላቻ ተነስቶ አንድን የህብረተሰብ ሁኔታ በጨቋኝና በተጨቋኝ በመክፍል አጉል ትግል መጀመርና ማካሄድ ወደ ዕውነተኛው ነፃነት ከማምራት ይልቅ ትግሉን ውስብስብ በማድረግ የጭቆናው ዘመን እንዲራዘም ያደርጋል። ካሊያም ደግሞ ጥራት የጎደላቸው ኃይሎች ስልጣን ላይ በመውጣት ከነፃነት ይልቅ ሌላ የረቀቀ ጭቆናንና ህብረተሰብአዊ መመሰቃቀልን ያስከትላሉ።
ከዚህ በመነሳት አገር ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን በመጠኑም ቢሆን ለመቃኘት እንሞክር። አገር ሲባል አንድ ሰው የተወለደበት ቀዪ ብቻ ሳይሆን ትዝ የሚለው፣ ለአቅመ-አዳም እስኪደርስ ድረስ ያሳለፈባቸውን ጊዜያት፣ መጥፎም ይሆኑ ጥሩ ነገሮች ወደ ኋላ ዞር ብሎ ሲያገናዝብ የሚሰማው ትዝታ ነው። ተራራው፣ የወጣበት ዛፍ፣ እንጨት ወይም ችቦ ለመልቀም የተጓዘበት ዱር፣ የተሻገረበት ወይም የዋኘበት ወንዝ፣ የተጫወታቸው ጫወታዎች፣ የኖረበት ኑር፣ ከሰው ጋር የነበረው ግኑኝነት፣ የተማረበት ትምህርት ቤት፣ እያደገ ሲሄድ ደግሞ ኳስ የተጫወተበት ሜዳ፣ ሲጎረምስ
 
የደነሰበት ዳንስ ቤት፣ መጎናተል የጀመረበት፣ እንዲያም ሲል ሰው መናቅ የጀመረበት፣ ከአጭር የጉርምስናው ጊዜ ሲላቀቅ ደግሞ ራሱን ማግኘት የጀመረበት ጊዜና፣ ይንቅ የነበረውን ሰው እንደገና ማክበር የጀመረበት ዘመን፣ ...ወዘተ. የአንድ ሰው የአገርነት መግልጫዎች ናቸው። አንድ ሰው ለሰላሳና ለአርባ ዐመታት ውጭ አገር ቢኖርም እየተመላለሱ ጭንቅላቱን የሚያስጨንቁት፣ ደስታና ስቃይ የሚፈራረቁበት፣ በተለይም በወጣትነት ዘመኑ ያሳለፈባቸውን ጊዜያት ትዝ ሲሉት ነው።
በእርግጥ የአንድ አገር ትርጉም በዚህ ብቻ የሚገለጽ አይደለም። እንደ ንቃተ-ህሊናችን የአንድ አገር ትርጉም ወደ ኋላ ዞር ብለን ስንመረምርና በታሪክ ወይም በህብረተሰብ አገነባብ መነፅር ስንመለከት የተጓዘችበትን ጠመዝማዛ ሂደት የቱን ያህል አስቸጋሪ እንደነበር የተገነዘብን እንደሆን ነው። ስለሆነም አንድ አገር ሊወራትና የራሱ ተገዢ ሊያደርጋት የመጣን ኃይል ባለ በሌለ ኃይሏ መክታ ስትመልስና፣ ህዝቡ ተደራጅቶ በአንድ ባንዲራ ስር ሲገዛና፣ አገር ሊገነባ ተፍ ተፍ ሲል የአንድ አገር ጣዕምነት የበለጠ እየታወቀ ይመጣል። ስለዚህም አንድ አገር አንድን ህዝብ በሚያስተሳስር ባንዲራ የሚገለጽ ነው። በአንድ የመግባቢያ ቋንቋ የሚገለጽ ነው። ህብረተሰቡን በሚያሰተሳስር ልዩ ልዩ ባህላዊ ነገሮች የሚገለጽ ነው። ተረት ተረት፣ ልዩ ልዩ የህብረተሰቡን ግኑኝነቶች የሚገልጹ ግጥሞች፣ እንደ ዕድገታችን ደግሞ በሙዚቃና በስዕል የሚገለጽ ነው። ይህም ማለት የአገር ትርጉምነት በግልጽ የሚታይ ሲሆን፣ በሌላ ወገን ደግሞ እጅግ በረቀቀ መልክ የሚገለጽ፣ በልዩ ልዩ ህብረተሰብአዊ ድሮች የተሳሰረና በስነ-ጽሁፍና በግጥም የሚተነተን ነው።
ስለሆነም በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ከዚህኛውም ሆነ ከዚያኛው የብሄረ-ሰብ ክፍል ተወለድን የምንል፣ ለዚህኛው ወይም ለዚያኛው ርዕዮተ-ዓለም አደርን የምንል፣ የዚኽኛው ወይም የዚያኛው ህብረተሰብ ክፍል አካል ነን የምንል፣ በተለይም ባለፉት አርባ ዐመታት አገራችንን ስንፈታተናት ከርመናል። በሰፊው ካለማሰብ የተነሳና በራስ ወይም በድርጅት ፍቅር በመወጠር አገራችንን ዛሬ ላለችበት አደገኛ ሁኔታ የየበኩላችንን አስተዋፅፆ አድርገናል። በተለይም ደግሞ ሳንወድ በግድ የርዕዮተ-ዓለም ሰለባ በመሆን፣ ከአገራችን ፍቅር ይልቅ ሌላ አገር ፍቅር በማሳየት፣ ብዙም ሳይገባን ህዝባችንና አገራችንን በመናቅ በጣም በተወሰነ አጅግ አደገኛ ዘመናዊ ዕውቀት በመታወር የአገርን ትርጉም አሳጥተናል። በተጨማሪም ደግሞ ይህች የተወሳሰበች የመጣችውን ዓለም ሁኔታ በቅጡ ካለመረዳት የተነሳና፣ የአገራችንን ዕድል በኛ ኃይልና ዕውቀት ላይ ካማድረግ ይልቅ በውጭ ኃይሎች ላይ በማድረግ ለነፃነት የሚደረገውን ትግል ውስብስብ አድርገናል። በአሻጥር ዓለም ውስጥ በመግባትና ግለሰቦችን በማሳደድ ለዕውነተኛ ነፃነት የሚደረገውን፣ ለህዝብ ፍቅርና ሰላም የሚያመጣውን ዕውነተኛውንና ቀናውን መንገድ አሰናክለናል።
የኛ ለአገራችን ያለን ፍቅር እንዲያው አገሬ አገሬ እያልን ስላለቀስንና ስለጮህን አይደለም የሚገለጸው። በአውሮፓ ምድር ውስጥ ለአንድ አገር ዕድገት፣ አንድ አገር እንደህብረተሰብና እንደማህበረሰብ እንዲተሳሰርና፣ ህዝቡም በአገሩ ላይ ፍቅርና ዕምነት እንዲኖረው የተደረገውን ትግል ስንመረምር የአገር ግንባታ እንዲያው በተራ ዕውቀት እንደማይካሄድ በቀላሉ መረዳት ይቻላል። የአውሮፓ ምሁራን ለአገራቸው ነፃነት ትግል ሲጀምሩ የህዝቦቻቸውን የኑሮ ሁኔታ በዚያን ጊዜ ከነበሩበት ሁኔታ ነጥለው በፍጹም ያዩበት ጊዜ አልነበረም። ይህም ማለት፣ የህዝቡ የማሰብ ኃይል ሁኔታ፣ ተፈጥሮን በቁጥጥሩ ስር ለማድረገ ያለው ችሎታና ያለመኖር ጉዳይ፣ እንደማህበረሰብ የመደራጀቱና ያለመደራጀቱ ጉዳይ፣ በየጊዜው ብቅ ጥልቅ የሚሉት ገዢዎች ንቃተ-ህሊና ጉዳይ፣ ወዘተ... ወዘተ. በመመርመር ነበር። ከሶስት ሺህ ዐመት ጀምሮ አገርን እንደማህበረሰብ ለመገንባት የተደረገውን የአውሮፓውን ህዝብ የትግል ታሪክ ስንመረምር ትግላቸው በአቦሰጡኛና፣ በዚያን ጊዜ የነበረን ኃያል መንግስት በመማፀን የሚደረግ ትግል ሳይሆን በከፍተኛ የጭንቅላት ስራ በመመራትና በመመካት ብቻ ነበር ይካሄድ የነበረው። እንደሚባለውም ዕውነተኛ ነፃነት ሊገኝ የሚችለው በጠብመንጃ ኃይል ሳይሆን በዕውቀት ኃይል ብቻ ነው። የመጨረሻ መጨረሻም የአንድ አገር እንደ አገርነት መታወቅ የሚችለው አንድ ህዝብ ቀስ በቀስ ነፃነቱን መቀዳጀት ሲችል፣ ወይም ደግሞ የራሱን ዕድል ራሱ ወሳኝ መሆኑ ሲረዳ ብቻ ነው። ለዚህ ደግሞ ንቃተ-ህሊና ወይንም ዕውቀትና የራስን ሚና መረዳት ያስፈልጋል።

ስለሆነም የአውሮፓ ምሁራን ትግላቸውን የጀመሩት የብሄረ-ሰብን ጥያቄ በማንሳትና፣ አንደኛው ከሌላው ይለያል ወይም ይበልጣል ብለው አጉልተው በማንሳት ሳይሆን፣ የአንድ ህዝብ የዕድገት እንቅፋቱና የነፃነት እጦት የትክክለኛ ዕውቀት አለመኖርን መሆኑን በመረዳት ብቻ ነው። ከዚህ በመነሳት የአውሮፓ ምሁራን ወደዚህ ዐይነቱ የእብዶች ፈሊጥ ወደሆነው የብሄረ-ሰብ ጥያቄና የርዕዮተ-ዓለም ትግል ላይ መምጣትና ጭንቅላታቸውን በዚያ መወጠር አስፈላጊያቸው አለነበረም። የነሱ ጭንቀት እንዴት አድርገን የተፈጥሮንና የህዋን ምስጢርና ህግጋት መረዳት እንችላለን፤ ከዚያስ በመነሳት እንዴት አድርገን አዳዲስ ነገሮች በመፍጠር እያንዳንዱ ግለሰበ የራሱ ባለቤት እንዲሆን ማድረገ እንችላለን? የሚለው ነበር የሚያስጨንቃቸው። ሀቀኛ የአውሮፓ ምሁራን በፍጹም ለስልጣን የታገሉበት ጊዜ አልነበረም። ዕውነተኛ ምሁራን የቀን ተቀን ኑሮአቸውን ዕውነትን ከመፈለግ ጋር በማጣመርና፣ አዲስ ዕውቀት በመፍጠር የሰው ልጅ በተፈጥሮ ላይ የተወሰነ ቁጥጥር እንዲኖረውና የሰለጠነ ማህበረሰብ እንዲመሰርት ነበር ትግላቸው። ስለዚህም ነው ፍልስፍናን፣ የቲዎሎጂ ምርምርን፣ በተፈጥሮ ሳይንስ ላይና በኋላ ደግሞ ኢኮኖሚክስ የሚባል አዲስ ዕውቀት በመፍጠር አንድ አገር ርስ ብርሱ ሊተሳሰር የሚችልበትን ሁኔታና፣ በአንድ አገር ውስጥ ተከብሮ እንዲኖር መሰረት መጣል የጀመሩት።ይህ ዐይነቱ ሰውነታዊ ፖለቲካ(Body politics) በመባል ይታወቃል። ማለትም ሰውነታችን በብዙ ሺህ ነርቦች የተሳሰረና፣ በተለያዩ ኦርጋኖች በመደገፍ እንደሚንቀሳቀስና እንደሚያስብ ሁሉ፣ አንድ አገርም በውጭ ኃይል እንዳትጠቃና ህብረተሰቡ በፀና መሰረት ላይ እንዲቆም ከተፈለገ፣ በተለያዩ ዕውቀቶችና የዕድገት መሰረቶች መተሳሰር አለባት። ሰፋ ያለ የስራ-ክፍፍል በመዳበር ህብረተሰቡ መተሳሰር አለበት። በተለያዩ የአውሮፓ አገሮች ውስጥ አንደኛው ከሌላኛው ለመብለጥ ሲል ትግልና ወረራ ቢካሄድም፣ በጊዜው ደካማ የነበሩና ወደ ማሀበረሰብ ግንባታ ያላመሩ አገሮች ቶሎ ብለው ግንዛቤ ውስጥ የገቡት ለአንድ አገር መገንባት ዋናው ቁልፉ ዕውቀት መሆኑን መረዳት፣ ከዚያም ወደሳይንስና ወደቴክኖሎጂ ማምራትና ተከብሮ መኖርን በመገንዘብ ነው። ይህ ነው የአውሮፓው የአገር ግንባታና የህብረተሰብ ምስረታው መንገድ። ይህ ዐይንቱ ሳይንሳዊ መንገድ ነው አንድ አገር እንደ አገር ሊያስጠራት የሚችለውና ለተከታታዩ ትውልድ ከላብዙም ውጣ ውረድ እንድትተላለፍ የሚያድርገው።
ወደኛው አገር ምሁር ስንመጣ ግን አገርን አገር ነው የሚያስብላት ላይ ከፍተኛ አለመግባባት አለ። አንዳንዶች ለስልጣን እንታገላለን የሚሉ እንዲያውም የአንድን አገር ሁኔታ በዕውቀት መነፅር ሳይሆን የሚመለከቱት፣ እንዴት አደርጌ ተሽለኩልኬ ስልጣን መያዝ እችላለሁ ከሚለው እጅግ አደገኛና በጣም ጠባብ ስሌት በመነሳት ነው። ይህ ዐይነቱ አጉል አመለካከት በሁላችን መንፈስ ውስጥ በመቀረጽና የዕውቀትን ትርጉም ባለመረዳት፣ እንዲያውም ትግል የሚባለውን ነገር ወደ ተራ አሻጥርነት፣ አንዱን በማቅረብ፣ ሌላውን በማግለል፣ የአንዱን ስም በማጥፋት፣ ሌላውን በማወደስ፣ ከዚያም በመነሳት የወገናዊነት ስሜት ማዳበርና በቡድን ቡድን እየተካለሉና እየተዳራጁ ትግሉን ጥምዝምዝና አስቸጋሪ ማድረግ፣ ዛሬ የዚህኛው ድርጅት አባል መሆን፣ ነገ ደግሞ ከዚያ ተገልሎ በመውጣት የቀድሞውን በመወንጀል የታሪክ ወንጀል መስራት፣ የአንድን ህዝብ የስልጣኔ ህልም ድምጥማጡን ማጥፋት ዋናው መለያችንና የሚያሳፍረን ሆኗል። ከዚህ ስንነሳ የፈልግነውን ያህል አገር አገር እያልን ብንጮህም ዕውነተኛ የሰብአዊነት ባህርይና አገርን የመገንባት ተልዕኮ ከሰውነታችን ጋር ስላልተዋሃደ እየመላለስን ጭቃ ውስጥ እንድንጨማለቅ አድርጎናል። በተለይም ባለፉት አርባ ዐመታት ጎጠኝነት፣ አድርባይነትና ሰላይነት ዋናው መለያችን በመሆን ለአገር ነፃነት፣ ለሰላምና ለዕድገት የሚደረገው ትግል እጅግ አስቸጋሪ እየሆነ መጥቷል። ከምንግዜውም በላይ ተወናብደናል። በውዥንብር ዓለም ውስጥ በመዋዠቅና ሌላውን በማሳሳት አገራችንን እንደ አገር እንዳትኖር እያደርገን ነው። ይህ ዐይነቱ ሩጫችን ግን ለሁላችንም ግልጽ የሆነ አይመስልም።ምክንያቱም በአጭር ጉዞ ህልም የታወርን ስለሆን ከሌላው ዓለም የትግልና የህብረተሰብ ግንባታ ታሪክ ትምህርት ለመቅሰምና ሌላው የሚለንን ለመስማት የምንፈልግ አይደለንም።
ከዚህ አጭር ሀተታ ስንነሳ ህዝባችን የሚለው ገና የበሰለና የታሪክን ሂደትና ትርጉም የተረዳ ትውልድ አልተፈጠረም ነው። በዚህም በዚያም ብሎ ስልጣን ላይ ቁጥጥ

በማለትና፣ የዚኽኛው ወይም የዚያኛው ኃይል መንግስት አቀንቃኝ በመሆን ሊያስጨንቀኝ የሚፈልግ እንጂ፣ እንደ አንድ ህዝብ ተነስተን፣ በወንድማማችነትና በመከባበር አገር ለመገንባት የሚያስችለን ኃይል አይደለም የተፈጠረው ነው የሚለው። እንደዚህ ዐይነቱ ትውልድ በተለይም ከጣሊያን መባረር በኋላ የተፈጠረና፣ በአጉል የዘመናዊነት አስተሳሰብ ያደገ በመሆኑ ስራው ሁሉ የተወሳሰበ አስተሳሰብንና ቀና አመለካከትን ከማዳበርና ለአገር ክብር ከመታገል ይልቅ አገርን ወደሚያፈራርስ ሁኔታ እንዲያመራ የተገደደ ነው። እንዲያውም አንዳንዱ አራዳ ነኝ ባይ ስለ አገር ነገር ሲነሳበት በሰው ላይ በማሾፍ አገር የሚለው ግዙፍ ፅንሰ-ሃሳብ ትርጉም እንደሌለው ከቁም ነገር ለመሸሽ ይሞክራል። ህዝባችን የሚጠይቀው በተለይም አዲሱ ትውልድ ከእንደዚህ ዐይነቱ አገርንና ታሪክን፣ እንዲሁም ባህልን ከሚያፈራርስ አደገኛ ስሌትና አስተሳሰብ መራቅ አለበት ነው። ቀናውን መንገድ ለማግኘት በዕውቀት ዓለም መዋኘት አለብህ ነው የሚለው። በተለይም በአሁኑ ዘመን ዓለማዊ አገዛዝ (World Governance) ለመፍጠር የሚደረገውን አጉል የኢምፔሪያሊስቶችን አሻጥር በመረዳት የትግልህን ሂደት አሻሽል ነው የሚለው። ስለዚህም ፖለቲካን በሁለንታዊ መልኩ በመረዳትና ወገናዊነትን ባለማስቀደም፣ ወይም ደግሞ የዚህኛው ወይም የዚያኛው ፓርቲ አባል ነኝ በማለት አጉል ግብ ግብ ውስጥ በመግባት የታሪክ ወንጀል መፈጸም የለብህም ነው የሚለን። ህዝባችን ህልሜ ዕውን ሊሆን የሚችለው በአረጀው ትውልድ አጉል የትግል ስልት ሳይሆን፣ አዲስ የሰብአዊነትን መንፈስ ከሰውነቱ ጋር ያዋሀደ ኃይል ብቅ ያለ እንደሆን ብቻ ነው የሚለው። ህዝባችን በአንድ በኩል ይህ ፍላጎቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንደማይሆን ይገነዘባል። በሌላ ወገን ደግሞ ይህ አስጨንቆ የያዘው ኃይል ከጫንቃው ላይ እንዲላቀቅለት ይፈልጋል። ህዝባችን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ነው የወደቀው ማለት ነው። ከዚህ ስንነሳ የሁላችንም ትግል የህዝባችንን ጥያቄና ግራ የተጋባበትን አስቸጋሪ ሁኔታ መመርመሩና መመለሱ ላይ ነው። ይህም ማለት ዋናው ትግል ስልጣን ከመያዝ ባሻገር መታየት ያለበት ሲሆን፣ ዕውነተኛው ነፃነት በምንም ዐይነት በአጉል ምርጫ እንደማይገኝ መገንዘብ ያስፈልጋል። በተለይም በአሁኑ ወቅት አንድ አመፀኛ አገዛዝ ሁሉን ነገር በሚቆጣጠርበትና፣ አላላውስም ባለበት ሁኔታ ውስጥ በምርጫ ዕውነተኛ ነፃነትን መቀዳጀት አይቻልም ነው የሚለው ህዝባችን። ከዚህ በመነሳት የማህበርንና የህብረተሰብን የመመስረቱ ሁኔታ ላይ አጠር ባለመልክ እንሂድበት።
የህብረተሰብና የማህበረሰብ ጉዳይ !
የአገርን ጉዳይና ምንነት የመረዳቱ ላይ ግራ የተጋባነውን ያህል፣ ማህበራዊና ህብረተሰብ በሚሉት ጉዳይም ላይ ከፍተኛ አለመግባባት አለ። ከዚህ በመነሳት ህዝባችን በየጊዜው እየደጋገመ የሚጠይቀውና ተማርኩኝ የሚለውና ተቃዋሚው ኃይል መመለስ ያለባቸው ጥያቄ፣ ህብረተሰብ ማለት ምን ማለት ነው? የሚለውን ግዙፍ ጥያቄ ነው።
ግለሰብ-አዊነትና፣ ማንኛውም ሰው የራሱን ጥቅም ብቻ ነው ማሳደድ ያለበት በሚለው ሆበሳዊ አስተሳሰብ በተስፋፋው አጉል ፍልስፍና ምክንያት የተነሳ የህብረተሰብና የማህበራዊ ጉዳዮች በጣም ተጣመው ይቀርባሉ። ብዙዎቻችንንም አሳስተዋል። በአንድ በኩል ህብረተሰብን በማዋቀርና አገርን በመገንባት መሀከል ያለውን ዲያሌክቲካዊ ግኑኝነት፣ በሌላ ወገንም ደግሞ በግለሰብ ነጻነትና፣ በማህበራዊና እንዲሁም በህብረተሰብአዊ ነፃነት መሀከል ያለውን መተሳሰር፣ እንዲሁም መተሳሰብ አለመረዳትና አለመግባባት ላይ ችግር አለ። አንድ ሰሞን አዲስ አበባ ውስጥ የእነ አቶ ልደቱ ፓርቲ ያስፋፋው አጉል ፈሊጥ ነበር። ይኸውም ማንኛውም ሰው ለራሱ ጥቅም ብቻ ነው የሚታገለው፤ ችግራችንም ቀደም ብለን የሊበራሉን የትግል መንገድ አለመያዛችን ዛሬ ልንወጣ የማንችለው ሁኔታ ውስጥ ከቶናል የሚል ከሳይንስና ከህብረተሰብ ዕድገት ጋር ያልተያያዘ አባባል መስበክ ነው የጀመሩት። በመቀጠልም፣ ኢዴፓ የሚባለው የእነ አቶ ልደቱ ፓርቲ ለኢትዮጵያም ሆነ ለተቀሩት የአፍሪካ አገሮች ከሊበራሊዝምና ከነፃ ገበያ ሌላ የሚያዋጣ መንገድ የለም በማለት ከየአገሮች የማህበረሰብ አወቃቀር ጋር ሊጣጣምና፣ ወደፊትም ሊመሰረት የሚችለውን ህብረትሰብአዊ ፕሮጀክት የሚያጨናግፍ አጉል ሰበካ ማስፋፋት ጀምረው

ነበር። በዚህ መልክ ብዙ ወጣቶችን ወደ ማሳሳት ደርሰዋል። ከዚህ ጋር የነፃ ገበያ የሚባለው አጉል ፈሊጥ በመግባቱና ተግባራዊ በመሆኑ የግለሰብአዊ ነፃነትን ትርጉም መጣመሙ ብቻ ሳይሆን፣ የወፈፍራሞች ዓለም ተፈጥሮ አቅመቢሱን የሚደቁስበት፣ በመሳሪያ እየታጠቁ ቤት የሚያፈራርሱበትና፣ ሺህ በሺህ የሚቆጠርን ህዝብ መንገድ ላይ እንዲወረወርና እንዲያድር በማድረግ ማህበራዊ ሁኔታዎች የተበጣጠሱበትን ሁኔታ እንመለከታለን። ከዚህ በመነሳት ህዝባችን የሚለው እንደማህበረሰብ ለመኖር የማንችልበት ሁኔታ ሲፈጠርና ሜዳ ላይ ስንጣል ይህንን ችግራችንን ተረድቶ ከጎናችን በመቆም የሚታገልልናና የሚያታግለን የለም የሚል ነው። በዚህ ዐይነቱ የጎጠኞች ዓለምና፣ ዐይናቸውን በጨው በታጠቡ ግለሰቦችና ቡድኖች በተፈጠረው የጋራ ግምባር ትግል ህብረተሰባችን ብጥስጥሱ እንዲወጣ እየተደረገ ነው። ህዝቡ ህሊናው እንዲዳሽቅ ሆኗል። ባህሉ እንዲወድም ተደርጎበታል። ማህበራዊና ህብረተሰብ እንዳይመሰርት በልማት ስም መሬቱ እየተሸነሸነ ለውጭ ከበርቴዎች በመሰጠቱና ከቀየው በመበተኑ እንደማህበረሰብ እንዳይኖር፣ የስራ-ክፍፍል እንዳያዳብር፣ ከዚህም በመነሳት በንግድና በኢንዱስትሪ፣ እንዲሁም በዕደ-ጥበብ አማካኝነት የንግድ ልውውጥ በማድረግ እንደ አንድ ህዝብ እንዳይተሳሰርና ህብረሰብአዊ ኃይል እንዳይሆን ከፍተኛ መሰናክል ተፈጥሮበታል። እየተፈጠረበትም ነው።
የአንድ አገር ትርጉምነት የሚገለጸው፣ አንድ ህዝብ በነፃነት ሊኖር የሚችለው፣ አገሬን አገሬ ብሎ ሊጠራና ሊዝናና የሚችለው፣ ቤተሰብ መስርቶ ልጅ ወልዶ ሊያሳድግና ለአቅመ-አዳም አድርሶ ደስታን መጎናፀፍ የሚችለው፣ አዳዲስ ባህሎች የሚያፈልቀውና ታሪክን መስራት የሚችለው፣ የህብረተሰብና የማህበራዊ ጉዳይ ግንዛቤ ውስጥ ሲገቡና በጭንቅላት ውስጥ ሲቋጠሩ ብቻ ነው። የአንድ አገር ምንነት ከማህበራዊና ከህብረተሰብአዊ ግንባታ ውጭ ትርጉም ሊኖረው በፍጹም አይችልም። በተለይም ተከታታይ ሶስዮሎጂያዊ ጥናት በማይካሄድበት አገር ውስጥ፣ በየጊዜው የሚከሰቱትን የሀብት ፈጠራና ክፍፍል ሁኔታ፣ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የገቢና የአኗኗር ሁኔታ በቲዎሪና በኢምፔሪካል ጥናት ተጠንተው መወያየት ልምድ በሌለበት አገር፣ ስለህብረተሰብ አገነባብ ግንዛቤ ማግኘት በጣም ያስቸግራል። ስለዚህም ሁሉም ከማህበራዊና ከህብረተሰብአዊ ኃላፊነት በመሸሽ፣ በአንድ በኩል ከትውልድ ወደ ትውልድ የተላለፈ ግኑኝነት እንዲበጣጠስ ያደርጋል፣ በሌላ ወገን ደግሞ መንፈስን የሚያድስና ህዝብን ሊያስተሳስር የሚችል አዲስ ባህል ማዳበር ያስቸግራል። የዛሬው የአገራችን ሁኔታ በዚህ እስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኝ ነው።
የሰው ልጅ ከእንስሳ የሚለየው ከፍተኛ የሆነ የማሰብ ኃይል ስላለው ብቻ ሳይሆን፣ የስራ-ክፍፍል በመፍጠርና በማዳበር፣ እንዲሁም ተፈጥሮን እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ ከቁጥጥሩ ስር በማዋል ህብረተስብአዊ ግኑኝነትና ማህበራዊ ሁኔታ መፍጠር ስለሚችል ነው። በመሆኑም እያንዳንዱ አገር ህብረተሰቡን እሱ በመሰለው፣ ግን ደግሞ ሳይንሳዊ በሆነ መልክ ማደራጀት መብቱ ነው። ይሁንና ግን በአጠቃላይ ሲታይ አገሮች ማህበራዊና ህብረተሰብ የመመስረት መብት ቢኖራቸውምና፣ ይህም የተፈጥሮ ህግ ጉዳይ ቢሆንም አጠቃላይ የሆነ ለሁሉም ማህበረሰቦች የሚያገለግል ዩኒቨርሳል ህግ የለም። በሌላ ወገን ግን አንዱ አገር ከሌላው አገር ልምድ ይቀስማል፤ ለአገርና ለማህበረሰብ ግንባታ የሚሆኑ ልዩ ልዩ ዕውቀቶችን ሊወሰድ ይችላል፤ መውሰድም አለበት። ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ትልቁ መወናበድ በአንድ በኩል በተለያዩ አገሮች መሀከል መኖር የሚገባውን የባህልና የንግድ ልውውጥ፣ በሌላ ወገን ደግሞ በነፃ ገበያ ስም የሚደረገውን የረቀቀ ወረራና አገሮች እንደህብረተሰብ እንዳይኖሩ የሚሸረበውን አሻጥር ያለመረዳቱ ብዙ ደካማ አገሮችን አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እየከተታቸው ነው። ብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮችና መንግስታት የህዝቦቻቸው አለኝታ መሆን ያልቻሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። በየአገሩ የተመሰረቱት መንግስታት የታጠቁትን መሳሪያና የገነቡትን የስለላ መዋቅር ተገን በማድረገና ከውጭ ኃይሎች ጋር በመመሰጣጠር ህዝቦቻቸው አርፈው እንዳይቀመጡና እንዳያስቡ በማድረግ የህብረተሰብን ግንባታ ሂደት እንዲያጣምሙት ተገደዋል። ስለዚህም በአገራችንም ሆነ በብዙ የአፍሪካ አገሮች ያለው የመንግስት አወቃቀርና የሚካሄደው ፖለቲካ ከየአገሮች ፍላጎትና፣

ህብረተሰብንና ማህበረሰብን ከመገንባት አንፃር ሳይሆን፣ ሳይታስብ በአቦሰጡኝ የሚካሄድ አደገኛ ሂደት ነው የሰፈነው።
ከዚህም በመነሳት ብዙ አገሮች፣ አገራችንም ጨምሮ እንደማህበራዊና እንደህብረተሰብ የማይታዩበት፣ ማንም እየገባና እየወጣ የሚፈነጭበት፣ ህዝቦች ወደ ባርነት ሁኔታ የተቀየሩበትን ሁኔታ እንመለከታለን። አንድ የአስራ ስምንት ዐመት ኮረዳ ለአውሮፓ ሴቶች አበባ የመትከል ግዴታ አለባት ወይ? ጤንነቷ በተባይ መርዝና በማዳበሪያ መቃወስ አለበት የሚል የተፈጥሮ ህግ አለ ወይ? ለዓለም ገበያ እየተባለ ገበሬው ለራሱ የሚጠቅመውን ሰብል ከማምረትና ወደ ሰለጠነ ተግባር ከመሸጋገር ይልቅ ቡና መትከል አለበት የሚል የተፈጥሮ ህግ አለ ወይ? ከዚህም አልፈን ስንሄድ፣ የደቡብ አፍሪካው ወዝ አደር ሌሊት እየተነሳ ብዙ ኪሎ ሜትሮችን በእግሩ በመጓዝ አንድ ሺህ ሜትር ያህል ወደ ታች በመውረድ ወርቅ እየቆፈረ በማውጣት ብቻ ነው ህብረተሰብ መገንባት የሚችለው የሚል የተፈጥሮ ህግ አለ ወይ? በዚህ ዐይነቱ ብዝበዛ የጥሬ-ሀብትን የሚቆጣጠረው የውጭ አገር ኩባንያ በብዙ ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ሲያተርፍና ከአገር ውስጥ ሲያስወጣ ሰራተኛው የባርያ ደሞዝ እየተከፈለው ዘለዓለሙን ፍዳውን ማየት አለብህ የሚል የእግዚአብሄር ቃል አለ ወይ? የምዕራቡ ካፒታሊዝም በፈጠረው አጉል የስራ ክፍፍል(International Division of Labour) በመታወርና በመታለል ብዙ የሶስተኛው ዓለም አገሮች፣ በተለይም አፍሪካ ወደጥሬ-ሀብት አምራችነት በመወርወር ህዝቦቿ እንደማሀበረሰብና እንደህብረተሰብ እንዳይኖሩ ታግደዋል። ወደ ዘለዓለማዊ ባርነት ተለውጠዋል። የለም ከዚህ የተሻለ ሌላ አማራጭ አለ ብለው የሚጋፈጡትን ኃይሎች እንደ አክራሪ እየተወነጀሉ ፍዳቸውን እንዲያዩ እየተደረጉ ነው። ስለዚህም ለአገርና ለህብረተሰብ ግንባታ የሚደረገው ትግል ውስብስብ ከመሆኑ የተነሳ በቀላሉ መፍትሄ የሚያገኝ አይደለም። በሌላ ወገን ግን ፍላጎትና ቆራጥነት፣ እንዲሁም የዓላም ፅናት ካለ ጉዞውን ማቀላል ይቻላል።
ዛሬ የኢትዮጵያን ህዝብ በሰላም የመኖር፣ የመስልጠንና በጋራ አገርን በፀና መሰረት ለመገንባት መፈለጉን የሚቃወሙ ወያኔና የውጭ ኃይሎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ተቃዋሚ መስለው ሰተት ብለው በተቃዋሚ ጎራ ውስጥ በመግባት የውስጥ ለውስጥ ትግል የሚያደርጉትም ኃይሎች ጭምር ነው። ይህ ዐይነቱ ችግር በእኛ አገር ብቻ የተከሰተ ሳይሆን በሌሎች የሶስተኛው ዓለም አገሮችም የሚታይ ዳካማ አስተሳሰብ ነው። ምክንያቱም ቀላል ነው። የሌላው ሰው ኑሮን መሻሻል አጥብቀው የሚጠሉና፣ የሌላው ሰው ኑሮ መሻሻል የነሱን ጥቅም የሚነካ የሚመስላቸው በየአገሩ አሉ። ስለዚህም በሆነው ባልሆነው አንድ አገር ማህበረሰብና ህብረተሰብ እንዳይመሰርት የሆነ ያልሆነ መሰናክል በመፍጠርና የግለሰቦችን ስም ለስለላ ድርጅቶች አሳልፈው በመስጠት አገርን ለመበታተን ሌት ተቀን ይሰራሉ። እዚህ ላይ ፕላቶን እንዳለው የሰው ልጅ ችግር የዕውቀት ችግር ወይም አርቆ የማየት ችግር ነው። ምክንያቱም አንዳንድ ግለሰቦች በራሳቸው ጠባብ ዓለም ውስጥ ስለሚኖሩ ሰፊውንና ቆንጆውን የሆነውን፣ የሁሉም ሰው ደስተኝነት የሚገለጽበትን የኮስሞስ ዓለም ስለሚጠሉ ትግላቸው ሁሉ ማህበረሰብና ህብረተሰብን የመገንባቱን ጉዳይ ማጫናገፍ ነው።
ከዚህ ስንነሳ ህዝባችን የሚጠይቀውንና የሚመኘውን ዕውን ለማድረግ ብዙ ውስብስብ ነገሮችን ማየት አለብን።የውጣ ውረድ ጉዞ ማድረግ አለብን። በተጨማሪም አገራችን በላፉት አርባ ዐመታት የተጓዘችበትን ኢ-ሳይንሳዊ የህብረተሰብ አገነባብ፣ ማለትም የከተማዎችና የመንደሮች አመሰራረት፣ ዕቅደ-አልባና ጥበበ-ቢስ መሆን፣ ተፈጥሮን የሚፃረር የአኗኗር ስልትና በተፈጥሮ ላይ ዘመቻ በማድረግ አገርን ማራቆት ግንዛቤ ውስጥ በማግባት ለሰፊ ውይይት መዘጋጀት አለብን። ለዚህ ደግሞ ግልጽነት፣ በነፃ ማሰብ፣ ደፋርነት፣ በዩልኝታ አለመገዛት ዋናው የትግል መሳሪያዎች መሆን አለባቸው። አንድን አገርና ህብረተሰብን የመገንባቱ ጉዳይ በዩልኝታና፣ አጉልና አጠቃላይ በሆነ ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ቢሰበሰቡ በሚል ሳይንሰ-አልባ የትግል ዘዴ መልክ ሊይዝ የሚችል አይደለም። ስለዚህም የድሮውን የትግል ዘዴያችንን እርግፍ አድርገን በመጣል ወደ ተወሳሰበ የትግል ዘዴ፣ ግን ደግሞ ግልጽ ወደሆነ መሽጋገር አለብን። ከላይ እንዳልኩት ለዚህ ሁሉ ደግሞ በተለያየ መልክ የሚገለጽ አንድን ህዝብ ነፃ ሊያወጣና ማንነቱን

እንዲያገኝ የሚያደርግ ዕውቀት በየጊዜው እየተዘጋጀ መቅረብ አለበት። ስለሆነም ምርጫችን ከሁለት አንዱ መሆን አለበት። ይኸውም ዛሬ እንደምናየው የተዝረከረከና ርስ በርሱ የሚተናኮስ ህዝብ፣ ወይንም በጠንካራ ድር የተሳሰረ ማህብረሰብና ህብረተሰብ መገንባት አለብን የሚለው ነው። ከሁለቱ አንዱን መምረጥ አለብን። ሁለተኛውን የምንመርጥ ከሆነ ደግሞ ስንዴውን ከእንክርዳዱ መለየት አለብን። በአጠቃላይና ትርጉም በሌላቸው ነገሮች ላይ ከመረባረብ ይልቅ የነገሮችን ውስብስብነት በመረዳት ጠለቅ ብለን በመግባት ለህብረተስብ ግንባታ የሚያመቸውን መንገድ ማነጠፍ አለብን።
በአጭሩ ህዝባችን እንደማህበረሰብና እንደ ህብረተሰብ እንዲጠነክር ከተፈለገ፣ 1ኛ) ከአጉል ሽኩቻና ኃይልን ከሚጨርስ የትግል ዘዴ መላቀቅ አለብን። 2ኛ) የሃሳብ ጥራትና ግልጽነት በጣም አስፈላጊ ናቸው። ከዚህ ጋር ተያይዞ ምሁራዊ ውይይትና ክርክር እጅግ አስፈላጊ ናቸው።3ኛ) የገበያ ኢኮኖሚ ያለህ እያሉ ትርምስ ከመፍጠር ይልቅ፣ ሰፋ ያለ የስራ-ክፍፍል፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ምርምር በሚሉት ላይ ርብርቦሽ ማድረግ። 4ኛ)ለአንድ አገር ጥንካሬና ለህብረተሰብ ግንባታ የግዴታ የባህል-ሬናሳንስ ወይም አብዮት ማካሄድ ያስፈልጋል። እነዚህ በጭንቅላት ውስጥ እንደመሰረተ-ሃሳብ ሲያዙ መንገዱ ሁሉ ቀና ይሆናል። ለማንም ጠላት መፈናፈኛ መንገድ ማሳጣት ይቻላል።
ከዚህ አጭር ሀተታ በመነሳት፣ በገጽ አራት ላይ ከንዑስ አርዕስት በላይ በመጨረሻው ፓራግራፍ ላይ ያቀረብኩትን ጥያቄዎች በመጠኑም ቢሆን ለመመለስ ልሞክር። በመጀመሪያ ደረጃ ዛሬ በአገራችን ያለው ዋናው ችግር ተቃዋሚ ነኝ በሚለውና በአገዛዙ መሀከል ያለ ችግር አይደለም። በባልና በሚስት መሀከል፣ ወይም በሁለት ጓደኛሞች መሀከል እንደሚፈጠር ጠብ ዐይነት አይደለም ያለው ችግር። ችግሩ ስልጣኔን በሚጠላው የወያኔ አገዛዝና፣ ስልጣኔንና ዕውነተኛ ዕድገትን በሚፈልገው የኢትዮጵያ ህዝብ መሀከል ያለ፣ በቀላል ቋንቋና በማስታረቅ ሊፈታ የማይችል ትንቅንቅ ነው። አገዛዙ ከኔ በስተቀር ብቻ በዚህች አገር ውስጥ ሊዋኝ የሚችል ኃይል የለም ብሎ ቆርጦ የተነሳና በከፍተኛ መሳሪያ የታጠቀ፣ ገንዘብና ኃይል ልቡን ያደነደነና ጭንቅላቱን ያሳወረ ነው። ስለዚህም ይላል አገዛዙ፣ እቺን አገር እንደፈልግሁኝ ልበውዛት፣ ልሸጣት፣ ላከፋፍላት፣ ላተረማምሳት፣ ብሄረ-ሰብን ከብሄረ-ሰብ በማጋጨት አገዛዜን ማራዘም እችላለህ፤ ይህ ህዝብ ለዲሞክራሲ የበቃ ስላልሆነ እንደፈልግሁኝ እጫወትበታለሁ የሚል ነው። በመሰረቱ በአገራችን ምድር ውስጥ መንግስት የሚያስብለው መንግስታዊ አካል የለም። ራሱ በፈጠረው ህግ፣ የራሱን ህግ በመጣስና የአገሪቱን ሀብት በመዝረፍ ሌሎች በኢኮኖሚው ክንውን ውስጥ ገብተው እንዳይሳተፉ የሚያግድ ኃይል ነው። ዛሬ በአገራችን ያለው አገዛዝ በማንኛውም የአፍሪካ አገር የሌለና፣ እጅግ በዝቅተኝነት ስሜት አገር የሚያፈራርስና በቂም-በቀለተኝነት የተወጠረ ነው። ስለዚህም አንዳንድ ሽማግሌዎች ዋሽንግተንና አዲስ አበባ ሼራተንና ሂልተን በማደርና በመስብሰብ ተቃዋሚውንና አገዛዙን „ለማስታረቅ“ በሚያደርጉት አጉል መሯሯጥ ችግሩ የሚፈታ አይደለም። እንደዚህ ዐይነቱ የያዙኝ ልቀቁኝ መሯሯጥ ትግሉን የሚያሳስት ብቻ ሳይሆን የአገዛዙን ዕድሜም የሚያራዝም ነው። ይህንን የሚያደርጉት አንዳንድ ግለሰቦች ብቻ ሳይሆኑ፣ ጋዜጠኛ ነኝ በማለት የህብረተሰብን ህግጋት ባለመረዳት ግለሰቦች እየፈለጉ ቃለ-መጠይቅ የሚጠይቁ ጋዜጠኞችም ለስልጣኔውና ለነፃነቱ ትግል እንቅፋት እየፈጠሩ ነው። ሁለተኛው ጥያቄ ደግሞ ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ኃይል በየአራት ዐመቱ በሚደረግ „ምርጫ“ ለመሳተፍ መጣደፍና አገዛዙ የፖለቲካ ቀዳዳ ይስጥ እያሉ መለማመጥ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገውንና የሚመኘውን ነገር እንዳይቀዳጅ የሚያደርግ አሳሳች ዘዴ ነው። በመሰረቱ ዛሬ ለምርጫ ምዝገባ የሚጣደፉ ኃይሎች ያልገባቸው ሳይንስ አለ። ይኸውም በአገራችን ምድር ዛሬ የምርት ኃይሎችን የሚቆጣጠር፣ ወይም ደግሞ የህብረተሰቡን ሀብት በቁጥጥሩ ስር አድርጎ ሁሉን ነገር ያጠረ ኃይል ለዕድገት እንቅፋት መሆኑን ከግንዛቤ ውስጥ ያላደረገ አጉል አካሄድ ነው። እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ተቃዋሚ ነን የሚሉ ኃይሎችን በመምረጥና ፓርሊያሜንት ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ እነሱና መንግስት ቲያትር ሲሰሩ እንዲያይ አይደለም የሚፈልገው። የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር በምርጫ የመሳተፍና ያለመሳተፍ፣ ወይም የሚፈልገውን የመምረጥና ያለመምረጥ ችግር ሳይሆን፣ መሰረታዊው የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን የሚፈታለት፣ የስራ መስክ የሚከፍትለት፣ ለነፃ ውድድር ያሚያመች ሁኔታ
 
የሚፈጥርለትና፣ ራሱም በአገር ግንባታ ውስጥ የሚሳተፍበትን ሁኔታ የሚያዘጋጅለትን ዲሞክራሲያዊ ኃይል ነው የሚፈልገውና የሚመኘው። ስለዚህም በእንደዚህ ዐይነቱ በተልከሰከሰና በስግብግብነት በሚካሄድ ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚመኘውን ዕውነተኛ ነፃነት አንዲትም የቅንጣቢ ያህል ሊያገኝ አይችልም። በመሆኑም ለኢትዮጵያ አስባለው የሚል ሁሉ ከእንደዚህ ዐይነቱ አደገኛ አካሄድ መቆጠብ አለበት። አንድ ነገር ከመሰንዘሩ በፊት በሰፊው ማጥናት አለበት።
ከዚህ ስንነሳ የዛሬው አገዛዝ ችግር የራሱን ሁኔታ ወደጭንቅላቱ ውስጥ ዞር ብሎ በማየት የአገራችንን ሁኔታ በቅጡ ለመመርመር የሚችል ኃይል አይደለም።ለማድረግም የማይችል ኃይል መሆኑን ባለፉት ሃያ ዐመታት አረጋግጧል። ቀደም ብዬ ላይ እንዳልኩት የሰው ልጅ ከእንስሳ የሚለየው የስራ-ክፍፍልና ማህበረሰብ በመገንባት የሚረጋገጥ ብቻ ሳይሆን፣ ድርጊቱን በየጊዜው መመርመር የሚችል ከሆነ የሰውነት ባህርይ ይኖረዋል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ አንድን ሰው ሰው የሚያሰኘው፣ ለሌላው ፍቅር ሲኖረው፣ የሌላው ሰው ህመምና ችግር ሲገባውና፣ ከቻለ የሚያቃልልለት ከሆነ ዕውነትም ይህ ዐይነቱ ግለሰብ የሰለጠነ ነው ማለት ይቻላል። በተጨማሪም የአንድ ሰው ውይም ቡድን መሰልጠኑ የሚታወቀው፣ ለመወያየት፣ ለመከራከርና በሚያስማሙ ነገሮች ላይ በጋራ መፍትሄ ለመፈለግ ዝግጁ የሆነ እንደሆን ብቻ ነው። በሌላ ወገን ግን ሌላውን ለመጉዳት ሲል የሚሆን የማይሆን መሰናክል ከፈጠረ፣ የራሱን ህግ አውጥቶ ህዝብን የሚያስርና የሚያሰቃይ ከሆነ፣ በከፍተኛ መሳሪያ በመታጠቅ ኑ ግጠሙኝ የሚል ከሆነ፣ ባጭሩ እሱ ሽብር እየፈጠረ ሌላውን አሸባሪዎች የሚል ከሆነ እንዴት አድርጎ ከዚህ ዐይነቱ አገዛዝ ቀና ነገር መሻት ይቻላል? ይህንንስ ኃይል እንዴት ተደርጎ እንደሰለጠነ ይወሰዳል? ተቃዋሚ ነኝ የሚለው ወይም ደግሞ በዚህም በዚያም ፖለቲካ አለገባችሁም ብሎ ሌላውን የሚወነጅለውን የምጠይቀው ይህንን የተምታታ ሎጂክ እንዲያስረዳኝ ነው። ስለሆነም ሃሳቦች ስናቀርብ፣ ለምርጫ እንወዳደራለን ስንል፣ ዓለም አቀፍ ኮሙኒቲው ጋ ዕውቅና እንዲሰጥ እያልን የምንጎተጉትና የምንሯሯጥ፣ የምንሰራቸውን ስራዎችና፣ የምናካሂዳቸው ትግሎች ኮመን ሴንስንና ሎጂክን የተከተሉ መሆናቸውን መመርመር አለብን። በራሳቸን ስሜት እየተነሳን ወዲህና ወዲያ ማለትና ሌላውን ማሳሳት የትግሉን ሁኔታ ያባብሰዋል እንጂ የነፃነቱን መንገድ ቀናና ለስላሳ አያደርገውም።
የኢትዮጵያ ህዝብም የሚለው የነገሮችን ሂደትና ዕድገት በደንብ የሚመለከትልኝ ኃይል መፈጠር አለበት ነው የሚለው። ብሶቴ፣ ችግሬ፣ ሃዘኔና ስቃዬ የገባው ኃይል ብቅ በማለት ልዩ ዐይነት የዕውነተኛ ነፃነትን ብርሃን የሚፈነጥቅ ኃይል ብቅ በማለት የስልጣኔውን ፋና ያሳየኝ ነው የሚለው። ሰላም፣ መፈቃቀር፣ ዕውነተኛ ዕድገት እያለ ነው የኢትዮጵያ ህዝብ በናፍቆት የሚጠባበቀው። ይህንን ምኞቱን፣ ህልሙንና ፍላጎቱን ነው እያንዳንዱ ለማሟላት እዚህና እዚያ መሯሯጥ ያለበት እንጂ በሽወዳና የውጭ ኃይሎችን በመለማመጥ አይደለም ወደ ስልጣን ላይ ለመውጣት መሯሯጥ ያለበት። ይህንን ማድረግ ባንችል እንኳ ላለማሳሳት ስንል እጅን አጣጥፎ መቀመጡ ትግሉን እንደማገዝ ይቆጠራል። ጥልቀት ያለው ኢንፎርሜሽን ሳይኖር፣ ወይም ደግሞ ሳያወጡና ሳያወርዱ፣ እንዲሁም ደግሞ በሎጂክ መነጽር እየመረመሩ የማይደረግ ትግል የአንድን ህዝብ ህልም ደብዛውን ያጠፋውል። ስቃዩን ያራዝመዋል።መልካም ንባብ !!
ፈቃዱ በቀለ
fekadubekele@gmx.de

No comments:

Post a Comment