ይህው
እንግዲህ ፆም ሊፈታ ነው። ተስፋዬ ካሳ በአንድ ቀልዱ ላይ ሁለት ችግር ያላቸው…! (“ር”ን ረዘም ያድርጉልኝ)
እናም ሁለት ችግርርርር … ያላቸው ባልና ሚስቶች ብላችሁ አንብቡልኝ፤ ስለ ፆም ፍቺ ያወሩትን እንዲህ ነግሮን
ነበር፤
ሚስት “እንግዲህ አሁን ፆሙ ሊፈታ ነው። ምን ይሻለናል?” ብላ ትጠይቀዋለች።
ባል ታድያ ምን አላት፤ “አይዞሽ ሌላ ፆም እንይዛለን” ብሎ “አፅናናታ”
ተስፋዬን ደግሞም ደግሞም ነብሱን ይማርልን!
አሁንም ፆም ሊፈታ የቀሩት ጥቂት ቀናት ናቸው። ገና አመት በዓሉ ሳይቃረብ የጀመረው አስማታዊ የዋጋ ውድነት
አሁንም ከልካይ አላገኘም። ከሳምንት በፊት የአዲሳባ ወዳጆቼ እንደነገሩኝ ከሆነ ዶሮ፣ ቅቤ፣ በግ እና አጠቃላይ
የአመት በዓል “አክሰሰሪዎች” ዋጋ ሰማይ ነክቷል።
ለምሳሌ ዶሮ አንድ መቶ ሰማኒያ ብር ቅቤ አንድ መቶ ስድሳ ብር ከገቡ ቆይተዋል። አሁን ደግሞ በዓሉ ሲቃረብ ስንት ይገባሉ የሚለውን ሸማች ይወቀው።
እንግዲህ አመት በዓልን አመት በዓል የሚያደርጉት በርካታ ነገሮች አሉ። እንደ አስተያየት ሰጪዎች ከሆነ
“በአሁኑ ግዜ ከአመት በዓል እሴቶቻችን ውስጥ የቀረን “ሞቅታ” ብቻ ነው” ሲሉ ይደመጣሉ። እርሱም በማር ጠጅ የመጣ
ሞቅታ አይደለም፣ በገብስ ጠላም የተፈጠረ አይደለም… (እነርሱማ የት ተገኝተው…!?) እንግዲያስ ከወዴት የመጣ
ሞቅታ ነው…? ያሉ እንደሆን፤ እንክርዳድ የበዛው ኑሯችን ያመጣብን፤ በዓል አዘቦት የማይለይ ሞቅታ ነው ይሉዎታል።
እናም የዘንድሮን በዓል በርካቶች ሳይበሉ ሳይጠጡ ብስጭት ባመጣው ሞቅታ ለማለፍ ተገደዋል እያሉ የሚያወጉ በርክተዋል።
“ማማረር ምናባቱ!” ያሉ የፈጠራ ክህሎት የታደሉ ነዋሪዎች ደግሞ የአመት በዓል ደስታዎችን ለማግኘት የሚያስችል
ዘዴ ሲያስቡ ሰንብተው አንድ ማስታወቂያ ማውጣታቸውን ሰምቻለሁ። የስራ ማስታወቂያ ነው ነገሩ። እንዲህ ይላል።
የስራ ማስታወቂያ
የስራው መደቡ መጠሪያ ….. ተዋናይ
የትምህርት ደረጃ……. የፈለገው ይሁን
የስራው መግለጫ አንድ
እንደ ዶሮ እና በግ የሚተውን፤ መኖርያ ቤታችን እስከ ዛሬ ድረስ መጣ የተባለውን አመት ባዕል በሙሉ በተቻለ
አቅም፤ ዶሮ ሳይታረድ ጠቦት ሳይጣል አልፎ አያውቅም ነበር። ከቅርብ ግዜ ወዲህ ግን እነዚህን ማሟላት አልተቻለም።
ቢሆንም ግን፤ በመኖርያ ቤታችን ቢያንስ ቢያንስ የዶሮ እና የበግ ድምፅ መሰማት አለበት ብለን ቆርጠን ተነስተናል።
ስለሆነም አመልካቾች የዶሮ እና የበግ ድምፅን አመሳስሎ በመጮህ ለመሮሪያ ቤቱ ድምቀት መስጠት ይጠበቅባቸዋል።
(ስራው ትልቅ የማስመሰል ጥበብ የሚፈልግ በመሆኑ ባለፈው ግዜ በልማታዊው እግር ኳስ ላይ የተሳተፉ አርቲስቶች ይበረታታሉ!)
የስራ መግለጫ ሁለት
እንደ ዘመድ ሆኖ የሚተውን፤ ከዚህ በፊት በነበረን ልምድ ለአመት ባዕል በመኖሪያ ቤታችን ዘመድ ተሰባስቦ
በልቶ፣ ጠጥቶ ሙያችንንም አድንቆ ይሄድ ነበር። ዘንድሮ ግን ዋናዎቹ ዘመዶቻችን በቤታችን ምንም እንደሌለ እና
ገበያውንም ደፍረን እንደማንሸምት ይረዱታል ብለን እናምናለን! ይህንን ሁሉ ችላ ብለው እንኳ ቢመጡ ተሳቀው ከመመለስ
ውጪ ቀድሞ የለመዱት አይነት መስተንግዶ ለማድረግ አቅም የለንም። በመሆኑም እንደ ዘመድ ሆኖ የሚጫወት ተዋናይ
ማግኘት አስፈላጊ ሆኗል። አመልካቾች ምንም ሳይበሉ ሰይጠጡ ጎረቤት ጉድ እስኪል ድረስ የቤታችንን ሞያ እያደነቁ
ድምፃቸውን ከፍ አድወርገው ማውራት ይኖርባቸዋል። ከቤት በሚወጡ ግዜም አረማመዳቸውም ሆነ ጨዋታቸው “እሁድ የቁብ
ጠላ ስለጋ ስለጋ…” እንደሚለው ዘፋኝ መሆን ይጠበቅበታል።
አመልካቾች ለመመዝገብ በሚመጡበት ግዜ ለበዓሉ ማድመቂያ የማይመለስ፤ ቄጤማ፣ ጠጅ ሳር፣ እንዲሁም እንደ እጣን የመሳሰሉ ጢሳጢሶችንም ይዘው እንዲመጡ ይመከራሉ።
የደሞዝ ሁኔታ…
ውይ ለካ ይሄም አለ… በቃ ተዉት እንደሚሆን እንደሚሆን እናልፈዋለን!
No comments:
Post a Comment