Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Sunday, 15 April 2012

በኢትዮጵያ ከፍተኛ ረሃብ ሊከሰት እንደሚችል ተገለፀ


ብስራት /ሚካኤል
በኢትዮጵያ እጅግ አስከፊ ረሃብ ሊከስት እንደሚችል ተጠቆመ፡፡ በተለይ ወቅቱን ጠብቆ ይመጣል የተባለው የበልግ ዝናብ ባለመዝነቡ በደቡብ እና በአማራ ክልል ድርቅ ሊፈጠር እንደሚችልና በዚያም ምክንያት የአካባቢው ማህበረሰብ ለርሃብ ሊጋለጥ እንደሚችል የተለያዩ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን መዘገባቸው ይታወሳል፡፡ በደቡብ ክልል በሚገኘው የሰሜኑ ክፍል የበልግ ዝናብን በመጠቀም የክረምቱን ወቅት መሸጋገሪያ ይሆናቸው ዘንድ ድንች ስኳር የመሳሰሉትን በቶሎ የሚደርሱ የምግብ እህሎችን ያመርቱ ነበር፡፡ ነገር ግን የተለያዩ ሪፖርቶች እና ጥናቶች እንዳረጋገጡት ከሆነ የበልግ ዝናብ ወቅቱን ጠብቆ ባለመምጣቱ ለቀጣዮቹ ወራት እስከ ክረምት ርሃብ ሊከሰት ስለሚችል ከወዲሁ የኢትዮጵያ መንግስት ጥንቃቄ ሊያደርግ እንደሚገባ ተጠቁሟል፡፡ የዝናብ እጥረቱ በምስራቅ ኦሮሚያና በትግራይ ክልል እንዲሁም በኢትዮጵያ ማዕከላዊ ቦታዎች ላይ መከሰቱንና አሁን ያለውም ዝናብ ከሚጠበቀውና መደበኛ ከነበረው ያነሰ መሆኑን የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ቃል አቀባይ የሆኑት ጂዲዝ ሼለር ነግረውናል ሲል IRIN ዘግቧል፡፡ የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማትና የረሃብ ቅድመ ማስጠንቀቂያ ድርጅት በበኩሉ የበልግ ዝናቡ እጥረት እስከ ሰኔ መጀመሪያ ድረስ ሊቀጥል እንደሚችል ጠቁሟል፡፡ በዘርፉ ከፍተኛ ልምድ ያላቸው እጥኚዎች በበኩላቸው በኢትዮጵያ እየተከሰተ ያለውን የዝናብ እጥረት ተከትሎ ከመጋቢት እስከ ግንቦት 2004 . የአፍሪካ ቀንድ መካከል ከፍተኛ ድርቅ ሊከሰት እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልፀዋል፡፡ በተለይ የበልግ ዝናብን በመጠቀም አምራች የሆኑት የደቡብ ክፍልን ጨምሮ የዝናቡ ሁኔታ ወደፊት በምን መልኩ ሊቀጥል እንደሚችል ጥርጣሬ እንዳላቸው የኢትዮጵያ ሜትሪዮሎጂ ኤጀንሲ የቅድመ ትንበያ ክፍል ዳይሬክተር አቶ ድሪባ ቆርጫ መናገራቸው ተገልጿል፡፡ የግብርና ሚኒስቴር ከፍተኛ ኦፊሰር የሆኑት አልማዝ ደምሴ በበኩላቸው ገበሬዎች ለረጅም ጊዜ መተካት የሚያስችላቸውን በቀሎና ማሽላ እንዲያለሙ ማስገንዘባቸውን አስታውሰዋል፡፡ ይህም የሚከሰተው የምግብ ሰብል ምርት እጥረት በጥራጥሬ እህሎች ዋጋ መጨመር ላይ ከፍተኛ አስተዋፅዖ እንደሚኖረው፤ የዋጋ ግሽበትም አሁን ካለበት 36.3% ሊጨምር እንደሚችል በመጠቆም በሀገሪቱም ባለፉት 5 ዓመታት ታይቶ የማይታወቅ የምግብ ዋጋ መናር ባልተጠበቀ ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችልም የዓለም የምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ቃል አቀባይ የሆኑት ሼለር መናገራቸው ተጠቁሟል፡፡ መንግስት በበኩሉ ችግሮቹ በተከሰቱበት አካባቢዎች በተለይ በደቡብና አማራ ክልል ከየካቲት አጋማሽ ጀምሮ ከፊል አስቸኳይ የምግብ ዋስትና ዳሰሳ በመጪዎቹ ሳምንታት በማድረግ ችግሮቹን መቆጣጠር እንደሚችል አስታውቋል፡፡ የኢትዮጵያ የአደጋና የምግብ ዋስትና ቢሮ አስተዳደር ቃል አቀባይ አክሎግ ንጋቱ በበኩላቸው መንግስት ችግሩን ለመቆጣጠር ማቀዱን አስታውሰዋል፡፡ አያይዘውም ለገበሬዎች ችግኞችን እንዳዘጋጁና አርሶ አደሩም ለሚፈልገው መልሶ ማልማት እንዲችል ተደርጓል፣ ችግሮቹ አሉ በተባሉበት አካባቢም የአደጋና ዝግጁነት ግብረ ኃይል ተመድቦ በመጠባበቅ ላይ እንዳለ ገልፀውልኛል ሲል IRIN አስታውቋል፡፡ በቅርቡ መንግስት በኢትዮጵያ ድህነት ቀንሷል ብሎ መግለፁ የሚታወቅ ሲሆን የድርቅና ረሃቡ ስጋት ከጀመረ ግን አንድ ወር 15 ቀን እንዳለፈው ተጠቁሟል፡፡ ከሰሞኑ ያንዣበበውን የረሃብና ድርቅ አስመልክቶ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት የሚሰጡን የተለየ መረጃ ካለ ብለን ጥረት ብናደርግም ለጊዜው አልተሳካም፡፡

No comments:

Post a Comment