Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Friday 20 April 2012

‹‹እየተፈጸመ ያለው ስህተት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ማንነትና አንድነት ጥያቄ ውስጥ የሚከትና የሚሸራርፍ ነው››

Wednesday, 28 March 2012 14:21
By Henock Yare
-    አቶ አብርሃም ዓለሙ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ክፍለ ትምህርት ሊቀመንበር
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አዲስ አወቃቀርና አደረጃጀት በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ በቅርቡ ይፋ እንደሆነ በተነገረለት አደረጃጀት በሰብአዊ ሳይንስ (ሂዩማኒቲስ ፋኩልቲ) ሥር የሚገኘው የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ክፍለ ትምህርት መታጠፉ እየተገለጸ ነው፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ ሔኖክ ያሬድ የክፍለ ትምህርቱን ሊቀመንበር አቶ አብርሃም ዓለሙን አነጋግሯል፡፡

አቶ አብርሃም ከኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ዲፕሎማ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተመሳሳይ ትምህርት ቢኢ ዲግሪ ያገኙ ሲሆንና በውጭ ሥነ ጽሑፍ የማስትሬት ዲግሪ አላቸው፡፡ በሁለቱም ዲግሪዎቻቸው የመመርቂያ ድርሳናቸው በኦሮሞ ፎክሎር ላይ ያተኮረ ነው፡፡ በአሁን ጊዜ ከኔዘርላንድስ ላይደን አፍሪካን ስተዲስ ሴንተር የዶክትሬት ዲግሪ ዕጩ ናቸው፡፡ መመርቂያቸው በኦሮሞ ፎክሎር ላይ ‹‹ብሔረተኝነት፣ አካባቢያዊ ማንነትና ፎክሎር በደቡባዊ ምዕራብ ኦሮሞ አካባቢ፤›› በሚል ርእስ የሠሩ ሲሆን ከሁለት ወር በኋላ ለተቋቁሞ (ዲፌንስ) ይቀርባሉ፡፡  

ሪፖርተር፡- ክፍለ ትምህርቱ ስላለበት ሁኔታ ይግለጹልን፤

አቶ አብርሃም፡- የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ክፍለ ትምህርት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ2002 ዓ.ም. (2010) ባደረገው የአካዴሚና አስተዳደራዊ ክለሳ መሠረት ሰብአዊ ሳይንስ (ሂዩማኒቲስ) ፋክልቲ ሥር የተቋቋመ ነው፡፡ ቀደም ሲል የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ በመባል ይታወቅ የነበረውና በ1950ዎቹ መጀመርያ ላይ የተቋቋመው ክፍለ ትምህርት አካል ነው፡፡ ስለሰው ልጆች ማንነት፣ ሰው መሆን ምን ማለት እንደሆነ የሚያጠኑ የማኅበራዊ ሳይንስ ዘርፎች ጥናት ክፍል ውስጥ ያለ ነው፡፡ ፍልስፍናን፣ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎርን (የባህል ጥናት) ሥነ ልሳንን ይዟል፡፡ የሌላው ዓለም ሥነ ጥበብን፣ ታሪክን ሁሉን ይጨምራል፡፡ የሰብአዊ ሳይንስ ፋኩልቲ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር፣ የውጭ ሥነ ጽሑፍ፣ ፍልስፍናና ሥነ ልሳንን ይዞ ነው፡፡ አንድ የቅድመ ምረቃ ፕሮግራም በፎክሎር፣ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር የድኅረ ምረቃ ፕሮግራም፣ ሁለት የፒኤችዲ ፕሮግራሞች በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር በድምሩ አራት ፕሮግራሞችን የሚያስኬድ ክፍለ ትምህርት ነው፡፡ ባሉት 15 ቋሚ መምህራን እነዚህን አራት ፕሮግራሞች እያካሄድን ነው፡፡ የተማሪዎቹም ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ እየሠራን እያለን አዲሱ መዋቅር ይህን ክፍለ ትምህርት የሚያጥፍ ሆኖ የመጣ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ማጠፍ ያስፈለገው ለምንድን ነው?

አቶ አብርሃም፡- የመዋቅር ክለሳ በየመሥርያ ቤቱ ይካሔዳል፡፡ መሠረታዊ ዓላማው ቢፒአር እንደሚባለው የዩኒቨርሲቲውን አሠራር፣ የትምህርት ጥራት ማሻሻል፣ ማፋጠንና ሒደቱን ማሳጠር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የክፍለ ትምህርቱ መታጠፍ እነዚህን የቢፒአር ዓላማዎች ወይም ደግሞ የዩኒቨርሲቲውን አሠራር ወደ ተሻለ ውጤት ያበቃዋል ወይ? ነው ጥያቄው፡፡ ይህ ጥያቄ ሲነሣ ክፍለ ትምህርቱ  በምንም መንገድ በየትኛውም መስፈርት ወደ ተሻለ መንገድ የሚያመጣ ሆኖ አላገኘውም፡፡ በመጀመርያ መግለጽ የምፈልገው እንደዚህ ዓይነት መዋቅራዊ ለውጦች ሲደረጉ ሁልጊዜ ከላይ ሳይሆን ከታች መነሣት ያለበት መሆኑን ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ክፍለ ትምህርቱ አልተጠየቀም?

አቶ አብርሃም፡- እኛ ምንም ዓይነት ሚና የለንም፡፡ ምንም ዓይነት ተሳትፎ የለንም፡፡ ያማከረን የለም፡፡ ስለ ሥነ ጽሑፍ፣ ስለፎክሎር ምንነት ስለ ኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ምንነትና ሥራ፣ ስለ ፕሮግራሞችም የጠየቀንና ያማከረን የለም፡፡ አንድ ክፉ ቀን በመጣ ደብዳቤ፣ ቀላጤ ብቻ ክፍለ ትምህርቱ ታጥፎ ከሌሎች ጋር መዳበሉን የሚገልፀው ደብዳቤ መጣ፡፡ የተላከው ደብዳቤ የሚያሳየው በመዋቅሩ ውስጥ የቀድሞ ሰብዓዊ ሳይንሶች ፋኩልቲ፣ የቋንቋዎች ጥናት ተቋምና የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን የሚባሉት ሦስቱ አንድ ላይ ተጨፍልቀው አንድ ኮሌጅ እንዲመሠርቱ፤ በውስጡም ሰባት ክፍለ ትምህርቶች እንዲኖር መደረጉን ነው፡፡

እነርሱም አንደኛ የአማርኛ ቋንቋ፣ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ክፍለ ትምህርት፣ ሁለተኛ የትግርኛ ቋንቋ፣ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ክፍለ ትምህርት፣ ሦስተኛ የኦሮምኛ ቋንቋ፣ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ክፍለ ትምህርት፣ አራተኛ የውጭ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፎች ክፍለ ትምህርት፤ ልብ በል! እላይ የኢትዮጵያ ተዘርዝሮ አማርኛ፣ ኦሮምኛ ትግርኛ ይላል፡፡ እዚህ ላይ ሲመጣ ፓተርኑን [ቅጡን] ይለውጣል፡፡ አምስተኛ ሥነ ልሳን፣ ስድስተኛው የጋዜጠኝነትና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ቤት ተብሎ ተዋቀረ፡፡ በዚህ አወቃቀር መሠረት ስናየው የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር የሚለው ክፍለ ትምህርት የለም፡፡ በኢትዮጵያ ፋንታ የሦስት ብሔሮችን ሥነ ጽሑፎች ፎክሎሮችና ቋንቋዎች የሚጠኑበት ብቻ ነው ያለው፡፡ ይኼ ነገር እንዴት ነው? ኢትዮጵያን በሦስት ብሔረሰቦች መወከል እንችላለን ወይ? የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ፎክሎር ስንል በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ የተጻፉና ያልተጻፉትን ሁሉ የምናጠናበት ነው፡፡ የሶማሌ፣ የአፋር፣ የሐዲያ፣ የወላይታ፣ የጉራጌ፣ የትግራይ፣ የአማራ፣ ኦሮሞ እና የሌሎችም፡፡

በሦስቱ ስናሳጥረው እንደምን አድርገን ነው ከ80 በላይ የሚሆኑ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሥነ ጽሑፎች ባህሎች የምናጠናው?  ይኼ ነገር በጭራሽ ሊታሰብ የሚችል ነገር አይደለም፡፡ ብዙ ሰው ይኸን ስናገር ለማመን ይከብደዋል፡፡ እንዴት ሊሆን ይችላል? ይህንን ከላይ የወረደብንን ረቂቂ ስናየው ደንግጠን ይኼ እንዴት ሊሆን ይችላል? በምን ዓይነት ተጠየቃዊ አካሔድ ሊፈጠር ይችላል ብለን አንሥተን በክፍለ ትምህርቱ የመምህራን ጉባዔ ላይ ተወያይተንበታል፡፡ ጠቅላላ የክፍለ ትምህርቱ መምህራን ይኼ እንዴት ሊሆን ይችላል?  አንድ ኢትዮጵያዊ ሊቀበለው ከሚችለው በላይ ነው፡፡ እንዴት የኢትዮጵያ የሚባለው ቀርቶ ወደ ሦስት ብቻ ይጠባል፡፡ የውጭ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፎች ከተባለ ለምንድን ነው የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፎች ያልተባለው? ምናልባት የቋንቋውንና የሥነ ጽሑፉን አከፋፈል ተቃውሞ ቢኖር እንኳ እንደ ዱሮው እንደተማርንበት የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፎች ክፍለ ትምህርት ተብሎ በሥሩ ብዙ ዩኒቶችን ወይም በኮሌጅ ደረጃ ፋኩልቲ አቋቁሞ በተለያዩ ክፍለ ትምህርቶች መክፈት ይችል ነበር፡፡ ይኸም አልሆነም፡፡ እነዚህ ሦስቱን ክፍለ ትምህርቶች ሲያቆም የተደረገው የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር የሚለው ለወደፊት እንዳይኖር ነው፡፡ ስለዚህ የመምህራኑ ጉባኤ ይኸ ነገር ልክ አለመሆኑን ተነጋግሮ ለሚመለከተው ክፍል ለፋኩልቲውም ለዩኒቨርሲቲውም አስታውቋል፡፡ በፕሬዚዳንቱ በሚመራው ስብስባ ላይም ትክክል አለመሆኑን ተቃውሟችንን አሰምተናል፡፡ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ገልጸናል፡፡ ምንም መልስ አላገኘንም፡፡ ሲቸግረን በመጨረሻ ያደረግነው ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቦርድ ሰብሳቢ ለሆኑት የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ጁነዲን ሳዶ ደብዳቤ ጽፈን አስገብተናል፡፡ ያገኘነው መልስ ግን የለም፡፡ ይህን ሁሉ ካደረግን በኋላ ዩኒቨርሲቲው በሐሳቡ ጸንቶ ይኸን ክፍለ ትምህርት ለመዝጋት ተነሥቷል፡፡

ሪፖርተር፡- የመታጠፉን ምክንያት አልደረሳችሁበትም?

አቶ አብርሃም፡- በመጀመርያ ደረጃ የውጪ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፎች ክፍለ ትምህርት እንዲኖር ሲደረግ እንደምን ኅብረ ባህላዊውና ኅብረ ብሔራዊው የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ክፍለ ትምህርት እንዳይኖር ተደረገ? የመዘጋቱ ዓላማውና ግቡስ ምንድን ነው? የሚሉ ጥያቄዎች በተደጋጋሚ አንሥተናል፡፡ ቀጥተኛ መልስ ግን ማግኘት አልቻልንም፡፡ ከዩኒቨርሲቲው እስከ ቦርድ ብንጠይቅም መልስ አላገኘንም፡፡ በቀጥታና በአደባባይ የሚነገር መልስ የለም፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ የውይይት መድረኮች ሲነገሩ ከምንሰማቸው እንደዚሁ አንዳንድ ወጎችና ሕዝባዊ ኢንተርኔት ሲነገር እንደምንሰማው፤ አንድም የመንግሥት የአሁን ጊዜ ትኩረት ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ስለሆነ ለእቅዱ ግብ መምታት አስተዋጽዖ የማያደርጉ ክፍለ ትምህርቶች መኖር የለባቸውም የሚል አስተሳሰብ አለ፡፡ በዚህ ረገድ ልማት ቅድሚያ የሚሰጠው ሆኖ ሥነ ጽሑፍና ባህል ልማታዊ አይደሉም የሚል የተሳሳተ አስተሳሰብ አለ፡፡ 

በመጀመርያ ደረጃ ባህልና ልማት ሊነጣጠሉ የሚችሉ ጉዳዮች አይደሉም፡፡ የልማት መነሻው ፍላጎቱ ነው፡፡ የፍላጎቱ ማስፈጸምያና ተግባራዊ ማድረጊያ መሣርያ እንዲሁም የመጨረሻ ግቡ ባህል ነው፡፡ ባህል የሰው ልጅ አኗኗር ነው፡፡ የምታለማው የኢትዮጵያን አኗኗርና ሕይወት ነው፡፡ ለመለወጥ መነሻህ ራሱ የሕዝቡ አኗኗር መሆን አለበት፡፡ ልማትና እቅድን ተግባራዊ ማድረግ የምትችለው ባለህ ሀብት ነው፡፡ ያም ሰው ነው፡፡ ስለዚህ ባህልና ልማት የሚነጣጠሉ ነገሮች አይደሉም፡፡ የልማት መነሻውም ግቡም ባህል ነው፡፡ ስለዚህ የባህል፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የፎክሎር ጥናት ልማታዊ አይደሉም የሚለው አስተሳሰብ የሚያስኬድ አይደለም፡፡ ሁለተኛው ምክንያት በግልጽ የማይነገር ግን በአንዳንድ ውይይቶች የሚነገረው የኢትዮጵያ ባህል፣ የኢትዮጵያ ፎክሎር፣ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ የሚባል ነገር የለም፡፡ ከዚያ ይልቅ ያለው የብሔር፣ ብሔረሰቦች ሥነ ጽሑፍና ፎክለር ነው ያለው፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ የሚለውን ድፍን ነገር እንተወውና ባሉት በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በትግርኛ ቋንቋዎች እንዲኖር እናድርግ የሚል አካሔድ ነው ያለው፡፡ ይህ እየተፈጸመ ያለው እጅግ በጣም ከፍ ያለ ስህተት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ማንነትና አንድነት ጥያቄ ውስጥ የሚከትና የሚሸራርፍ ነው፡፡

በመጀመርያ ደረጃ እኛ ኢትዮጵያውያን፣ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የምንለያይባቸው የማንመሳሰልባቸው የየግላችን ብሔረሰባዊ ማንነት ቢኖርም፣ ትልቅና ሰፊ ብሔራዊና ኢትዮጵያዊ ማንነት እንዳለን ሊታወቅ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ የምትባል አገር፣ ኢትዮጵያውያን የሚባሉ ሰዎች፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዳለ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ይኼ የብሔራዊ ማንነታችንና አንድነታችን መሠረት የሆኑ የጋራ ጉዳዮችና እሴቶች እንዳሉን ሊታወቅ ይገባል፡፡ ልክ የአሜሪካ ሥነ ጽሑፍ፣ የአሜሪካ ሙዚቃ፣ የአውሮፓ፣ ወዘተ. እንደሚባለው እንዳለ ሁሉ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ፣ የኢትዮጵያ ፎክሎር፣ የኢትዮጵያ ሙዚቃ የሚባልም የጋራ እሴቶች መፍጠርያና ማጠናከርያ መገለጫ ጥበባት እንዳሉ ማወቅ አለብን፡፡ ኢትዮጵያውያን የምንጋራቸው እንደ አንድ አገር ሕዝብ በአንድነት እንድንቆም የሚያደርጉን የምንመሳሰልባቸውና የምንጋራቸው የጋራ ጉዳዮችና እሴቶች አሉን፤ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ አንድ በሰላም፣ በፍቅር በአንድነት አብረን የምንኖርባት አገር አለችን፤ አኩሪ ታሪክ ያላት- አነጋጋሪና አከራካሪ ሊሆን ቢችልም-ግን ታሪክ ያላት፣ የረዥም ዘመናት ህልውና ያላት ምናልባትም ጥንታዊ ከሚባሉት አገሮችም ሆኑ ሥልጣኔዎች ምንጮች አንዷ የሆነች አገር፣ የጋራ ፌዴራላዊ መንግሥትም አለን፡፡ በጋራ የምንተዳደርበት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት አለን፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች የምንጋራቸው ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጀግኖች አሉን፤ በዘር በሃይማኖት በቋንቋ ሳንከፋፈል ሁሉንም ጀግኖች የምናከብርበት ብሔራዊ ክብረ በዓላት አሉን፡፡ የጋራ ቋንቋም የፌዴራላዊ መንግሥት የሥራ ቋንቋ የሆነው አማርኛም አለን፡፡ ወደድንም ጠላንም በታሪክ አጋጣሚ ይህ ቋንቋ በጋራ ቋንቋነት፣ በሥነ ጽሑፍ፣ በባህል ምርምር ቋንቋነት ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የተሻለና ያደገ ቋንቋ ሆኗል፡፡ በዚህም ምክንያት ዛሬ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ክፍለ ትምህርት የሚባለው የማስተማርያና የምርምር ቋንቋው አማርኛ ነው፡፡ በእንግሊዝኛም እናስተምራለን፡፡

አልፎ አልፎ በየውይይት መድረኩ የሚሰማው የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ክፍለ ትምህርት ይባል እንጂ ክፍለ ትምህርቱ የሚያስተምረው በአማርኛ፣  ትኩረቱም አማርኛ ላይ ነው የሚሉ ወቀሳዎች አሉ፡፡ የክፍለ ትምህርቱ የማስተማርያ ቋንቋው የአገሪቱ ፌዴራላዊ መንግሥት የሥራ ቋንቋ አማርኛ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ትኩረቱን የአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ማለት አይደለም፡፡ ይህ ስህተት መሆኑን ለማረጋገጥ ባለፉት ከ1950ዎቹ ጀምሮ በክፍለ ትምህርቱ ሥር የተሠሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የቢኤና የኤምኤ ቴሲሶችንና ሌሎች ጥናቶችን ማየት ይቻላል፡፡ ትኩረታችን በኢትዮጵያ ሕዝቦች ልዩ ልዩ ቋንቋዎች፣ ሥነ ጽሑፎች፣ ፎክሎሮችና ባህሎች መሆኑ የተሠሩት የሶማሌ፣ የአፋር፣ የጉሙዝ፣ ሲዳማ፣ ቡርጂ፣ ወላይታ፣ ከፋ፣ እና የሌሎች ብሔረሰቦች ጥናቶች አመልካቾች ናቸው፡፡

ስለዚህ ይህ ወቀሳ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ስም አማርኛን ነው የሚያስፋፉት የሚለው ወቀሳ መሠረት የሌለው ነው፡፡ አንድም የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ብለን በ80ዎቹ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ክፍሉ ውስጥ ማስተማር አንችልም፡፡ በየትኛውም ዓለም ተደርጎ አይታወቅም፡፡ በአውሮፓ የአውሮፓ ሥነ ጽሑፍ የሚባል ዲፓርትመንት አለ፡፡ እያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ የአውሮፓን ሥነ ጽሑፍ የሚያስተምርበትን የአገሪቱን ቋንቋ ይመርጣል፡፡ ፈረንሣይ ብትሔድ ፈረንሣይኛ ነው፡፡ ጀርመንም ሆነ እንግሊዝ የየራሳቸውን ዋነኛ ቋንቋ ይጠቀማሉ፡፡ በየአገሩ ያለው ቋንቋ እነሱ ብቻ ናቸው ማለት ግን አይደለም፡፡ አንድ ቋንቋ የግድ ትመርጣለህ፡፡ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ብለንም ለማስተማር 80ዎቹን ቋንቋዎች ክፍሉ ውስጥ ማምጣት አንችልም፤ የማይመስልም ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ክፍለ ትምህርት እንዲዘጋ የተወሰነበት ምንም መሠረታዊ የሆነ ምክንያት ያለው አይመስለኝም፡፡

በሌላ በኩልም ስናየው፣ ከቅድመ ልደት ክርስቶስ ጀምሮ የካበተ የግእዝ ሥነ ጽሑፍ አለ፡፡ ከአፍሪካ የራሷ ፊደል፣ የጽሑፍ ሥርዓትና የዘመን አቆጣጠር ያላት አገር ሆና ሳለ በአሁኑ የዩኒቨርሲቲው ዕርምጃ ይህንና ሌሎች የብዙኀኑ ሥነ ጽሑፍ በአጀም (ዓረብኛ ፊደል) የተጻፈውን ሁሉ ለማጥናት አያስችልም፡፡ ስለ ኢትዮጵያ ስናወራ የኢትዮጵያን ታሪክ ማንሣት አስፈላጊ አይደለም የሚል በግልጽ የማይነገር አስተሳሰብና አመለካከት ያለ ይመስላል፡፡ የትኛውም አገር ታሪኩን ሳያጠና፣ ታሪኩን መሠረት ሳያደርግና የኋላውን ሳያይ ወደፊት መሔድ አይችልም፡፡ በምንም መንገድ ሁልጊዜ በእጃችን ያለው ዕውቀታችን መነሻችን ነው፡፡ የወደፊቱን አካሔድ የምንቃኝበት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የኖረውን የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ እዚያ ውስጥ ያለው ዕውቀት ሀብት፣ ፍልስፍና ሳናጠናና ሳናውቅ አዲስ ዕውቀት መፍጠር አንችልም፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ለማጥናት ከውጭ የሚመጡ ተመራማሪዎች አያያዝስ እንዴት ይታያል?

አቶ አብርሃም፡- አስቸጋሪ ነው፡፡ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ክፍለ ትምህርቶች ጋር ግንኙነት አለን፡፡ ለምሳሌ ከደቡብ አፍሪካ ዩኒቨርሲቲ ጋር ኢንተርዲፓርትመንታል [በይነ ክፍለ ትምህርታዊ] አቻ ግንኙነት እየመሠረትን ነው፡፡ ከአሜሪካም ሆነ ከአውሮፓ ዩኒቨርሲቲዎች የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ለማጥናት የሚመጡ አሉ፤ በአሁኑ አካሔድ ይኸ ሁሉ ነገር ለማከናወን የሚቻል አይደለም፡፡ ይኸ ብቻ ሳይሆን ባሉን አራት ፕሮግራሞች (በቢኤ፣ ኤምኤና ፒኤችዲ) እየተማሩ ያሉ በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ላይ ጥናታቸውን እያካሔዱ ያሉ ተማሪዎች የወደፊት እጣ ፈንታ ምን ሊሆን እንደሚችልም መገመትም አንችልም፡፡ ምክንያቱም በሦስቱ ቋንቋዎች (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ) ላይ የሚያተኩሩ ችግር ላይገጥማቸው ይችላል፡፡ ወደየክፍለ ትምህርቱ ሊሔዱ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን በቤንሻንጉል፣ ሶማሌ፣ አሪ፣ ከምባታ፣ ጉራጌ፣ ሐዲያና በሌሎች ላይ የሚሠሩ ተማሪዎች አሉ፡፡ የእነዚህ ተማሪዎች የወደፊት እጣ ፈንታቸው ምን ሊሆን እንደሚችል በበኩሌ አላውቅም፤ ማንም ማወቅ የሚችል አይመስለኝም፡፡

ሪፖርተር፡- ምን ይደረግ?

አቶ አብርሃም፡- ይኸ በጣም ቀላል ነገር ነው፡፡ ይህ አዲሱ አደረጃጀት የሚያስከትላቸውን አሉታዊ ተጽዕኖዎች በክፍለ ትምህርቱ የመማር፣ ማስተማርና የምርምር ሥራ ላይ ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ብሔራዊ ማንነትና አንድነት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያስከትል ይችላል የሚል ሥጋት እንዳለን በተደጋጋሚ ገልጸናል፡፡ ይኼ ሥጋት መሠረት ያለው ነው ወይስ የሌለው ነው ብሎ ቆም ብሎ ማሰብና በዚህ በማሰብና በዕውቀት፣ በጥናትም ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ማስተላለፍ የሚያስፈልገው ይመስለኛል፡፡ ይኸን ክፍለ ትምህርት ማጠፍና ወደ ሦስቱ ብሔር ብሔረሰቦች ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ክፍለ ትምህርት ማጥበብ በእርግጥ የተሻለ ውጤት ያስገኛል ወይ? ይኼ ብዙ ምርምር የሚያስፈልገው አይደለም፤ አይመስለኝምም፡፡ ሰፋ ያለ አመለካከት ብቻ ይዞ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያውያን ኅብረ ባህላዊ ማንነትና አንድነት መሠረት ያደረገ ውሳኔ ማስተላለፍ ብቻ መፍትሔ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲው በአዲሱ መዋቅር ዲፓርትመንት ወይም ክፍለ ትምህርት የሚለውን ደንግጓል፡፡ እንደ ክፍለ ትምህርት የሚያስቆጥረው 1ኛ ሲያንስ አንድ ቅድመ ምረቃና አንድ ድኅረ ምረቃ ፕሮግራም የሚያካሒድ፣ 2ኛ ቢያንስ የቅድመ ምረቃና ድኅረ ምረቃ ሥራውን ለማስኬድ የሚያስችሉ ቢያንስ 10 ቋሚ መምህራን ያሉት መሆን አለበት ብሎ ይደነግጋል፡፡

በዚህ መሠረት ካየኸው የኛ ክፍለ ትምህርት አራት ፕሮግራሞች ያካሒዳል፡፡ ሁለት ፒኤችዲ፣ አንድ የኤምኤ፣ አንድ የቢኤ ፕሮግራሞችን ለማካሔድ የሚችሉ 15 ቋሚ መምህራን አሉት፡፡ በእነዚህም ሁለቱ ብቻ ረዳት ሌክቸረር ሲሆኑ (እነሱም እየተማሩ ነው፤ በዚህ ዓመት መጨረሻ ሙሉ ሌክቸረር ይሆናሉ፡፡) 13ቱ ሌክቸረርና ከዚያም በላይ ረዳትና ተባባሪ ፕሮፌሰሮች ናቸው፡፡ የፒኤችዲ ጥናትም እያካሔዱ ያሉባቸውም አሉ፡፡ ስለዚሀ በየትኛውም መሥፈርት ይኸንን ክፍለ ትምህርት ሊያዘጋ የሚችል ምንም መሠረት የለም፡፡ ስለዚህ ይህን ነገር ቆም ብሎ አጢኖ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ማስተላለፍ የሚገባ ይመስለኛል፡፡ ክፍለ ትምህርታችን ያቀረበው ሐሳብ አንድም የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ ጽሑፍ ፋኩልቲ ወይም ኮሌጅ አቋቁሞ በዚያ ሥር ልዩ ልዩ ክፍለ ትምህርቶችን ማድረግ ይቻላል፡፡ ወደ ኮሌጅ ደረጃ ማሳደግ ይከብዳል ከተባለ ደግሞ በአሁኑ አካሔድ የቋንቋዎች ክፍለ ትምህርት (አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግርኛ) እንዳሉ ሆነው፤ ነገር ግን ይህን ኅብረ ባህላዊ የሆነውን የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር የሚያጠና አንድ ክፍለ ትምህርት የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍና ፎክሎር ክፍለ ትምህርት እንዳለ በሥራው እንዲቀጥል ማድረግ የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- የአገሪቱ የባህል ፖሊሲ አለ፡፡ እየተከለሰም መሆኑ ይነገራል፡፡ ከክፍለ ትምህርታችሁ ጋር ሊኖረው ከሚችለው ግንኙነት አንፃር እንዴት ይታያል?  አንዱ ግብአት ከክፍለ ትምህርቱ እንደሚገኝ ይታመናልና፡፡ በሌላ በኩል በሚሌኒየም ልማት ግብ ስለ ባህል አስቀድሞ ትኩረት ባይሰጠውም በኋላ ላይ እ.ኤ.አ. 2001 ላይ እንደ አራተኛ የልማትና ዕድገት ምሶሶ ሆኖ የቀረበበት መልክ አለ፡፡ የባህል ፖሊሲውን ከመተግበር አንፃር እንዴት ይታያል? 

አቶ አብርሃም፡- በአገር ብሔራዊ አንድነት፣ በባህል ልማት አንፃር አሉታዊ ተጽዕኖዎች ይኖሩታል የምንለው ስለዚህ ነው፡፡ አንድም እነዚህ ሽርፍራፊ ማንነቶችን ማጉላት (Fragmented Identities) ትኩረት የሚሰጥ ነው የሚመስለው፡፡ ከሙሉው ከሰፊው ማንነትና አንድነት ይልቅ ለሽርፍራፊ ማንነቶች ነው ትኩረት የሚሰጠው፡፡ በመጀመርያ ኢትዮጵያውያን በጋራ የሚመሳሰሉበት ጉዳዮች እንዳሉ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ የኢትዮጵያ ልዩ ልዩ የቋንቋና ባህል ባለቤቶች የሚለያዩባቸው ነገሮች እንዳሉ ሆነው የሚጋሯቸውና የሚመሳሰሉባቸው እሴቶች እንዳሉ ግን ይዘነጋል፡፡ በዚህ ረገድ የባህል ፖሊሲንም ሆነ የባህሎቻችን እኩልነት የቋንቋዎችንና የሕዝቦችን የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት ከሚደነግገው ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓታችንና ሕገ መንግሥታችን ጋር ሁሉ የሚጋጭ ይመስለኛል፡፡ በዚህም ምክንያት ነው በተደጋጋሚ ይኼ ውሳኔ በጥሞና እንደገና እንዲጤን የምንወተውተው፡፡ እስከ ዩኒቨርሲቲው ቦርድ ድረስ አመልክተናል፡፡ ይህም አልሆነም፡፡ የመጨረሻውን ሙከራ ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አቤት ለማለት አስበናል፡፡ በጥሞና እንዲታይልን እንጠይቃለን፡፡ በዩኒቨርሲቲው ውጤቱና ግቡ አዎንታዊ ስለማይመስለን ውሳኔው ይሻራል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

No comments:

Post a Comment