“የእናቷን ውበት ወርሳለች” ይሏታል። ርግጥ ነው፣ ወይዘሮ ላቀች ይህ ቀረሽ የማይባሉ ደርባባ ወይዘሮ ነበሩ።
የቀድሞ የወጣትነት ወዘናቸው ወደ ልጃቸው ተሻግሮ ማየት ችለዋል። በዚህም ተባለ በዚያ ልጅቱ የንጉስ ተክለሃይማኖት
ሴት ልጅ ናት። ስምን መልአክ ያወጣዋልና ስሟ ንግስት ይባላል። ስለዚህ ቆንጆ ናት። ከቁንጅናዋ በላይ ግን
ሊጠቀስላት የሚችል ቁምነገር ነበራት። ከደብረ ኤልያስ ገዳም በመጡ ሊቃውንት ፅህፈትና ቅኔ ተምራ ነበር። አባቷ እያሉ አጊጣለች። ርግጥ አሁን ፀሃይ ጠልቃባት ነበር…
ንጉስ ተክለሃይማኖት የልጃቸውን ወግ ማእረግ ሳያዩ አርፈው ነበርና ልእልቷን ለማጨት በክብር የሚጠየቅ ባለቤት፣
ወይም የሚከበርና የሚፈራ ወገን አልነበራትም። ስለዚህ ዘመኑ ያፈረጠማቸው ደጃዝማቾች የንጉሱን ሴት ልጅ ሚስት
ለማድረግ ጦር ወደ መስበቅ ተቃርበው ነበር። ወይዘሮ ላቀች ውሉ ጠፍቶአቸዋል። በግራና በቀኝ የሚጎነታተሉትን
ጉልበታም ባላባቶች ማስቀየም ተቸግረው፣ አንዱን መወሰን ሳይችሉ ብዙ ወራት አሳለፉ። የደጃዝማቾቹ የሽኩቻ ወሬም
በእረኛው በኩል በየመንደሩና በየመልካው ይናኝ ይዞአል፣
(“ስማኝማ! ልጅ መርእድ … ደፈጫ ሲበላ የከረመ ወይፈን አምሃ ብሎ ለንግስት ላከላት ይባላል”
“መርእድ ንግስትን ሊያገባ? ይሄ ጎሮጎሞ አጋሚዶ! ንጉሱ ቢኖሩ መች ይደፍር ነበር?”
“ደጃች ገሰሰ ‘ንግስት የኔ ካልሆነች ህይወቴ ታልፋለች’ ብሏል አሉ”
“አዬየ! ማርያም ትሁነን እንግዲይህ….ለከርሞ ጦር መስበቅ አይቀርም…”)
በየቤተክስያኑ ወሬው ይሄ ብቻ ነበር። ወይዘሮ ላቀች ለደጃች መርእድ “ቃል ሰጥተዋል” የሚለውን ወሬ ተከትሎ ደግሞ፣ ልእልቲቱ አኩርፋለች የሚል ወሬ ሹክሹክታ ብቅ አለ። ይሄም ቢሆን አነጋግሮአል፣
“እናቷ ተፈቀደች እሷ ምናገባት?”
“አውሬ ድመት ናት ይላሉ”
“ጠበል መውሰድ ነው እንግዲይህ…”
ወይዘሮ ላቀች በልጃቸው ጉዳይ ክፉኛ ተቸግረው እንደነበር መፃህፍት ያወጋሉ። በርግጥ የመኳንንቱ ግፊት ቢበረታ፣
እናትየው “መርእድ ያንሳት” ሲሉ መስማማታቸው እውነት ነበር። ሆኖም የጎጃሟ ልእልት፣ “መርእድን አላገባም”
በማለቷ በሁለቱ ደጃዝማቾች መካከል ውጥረቱ ከረረ። በልጅ መርእድና በደጃች ገሰሰ ወገኖች መካከል ግጭት የማይቀር
መሆኑ ሲታወቅ፣ ጉዳዩ ወደ አጤ ምኒልክ እንዲደርስ ተደረገ። ለአንድ አመት ያህልም አጤ ምኒልክ ጣልቃ ገብተው
ሲሸመግሉ ቆዩ። በመጨረሻ ግን ጉዳዩ እልባት አገኘ። ደጃች ገሰሰ የንጉሱን ልጅ እንዲያነሳ ከተወሰነ በሁዋላ፣ አጤ
ምኒልክ ልጅ መርእድን ወደ አዲስአበባ አስጠሩት።
* * *
ልጅ መርእድ አዲሳባ ደርሶ ደጅ እየጠና መሆኑ ሲነገራቸው አጤ ምኒልክ በፍጥነት ወደ እልፍኝ እንዲቀርብ አዘዙ። ልጅ መርእድ ከንጉሰ ነገስቱ ዙፋን ፊት ቀርቦ በደንቡ መሰረት ለጥ ብሎ እጅ ነሳ።
“አረፍ በል” አሉት።
እየተርበተበተ ወንበር ያዘ።
“…ያልወደደችህን ልጅ ወዳኛለች ብለህ ጦርነት ልታነሳ ነበር” አሉት ቆጣ ብለው።
“ጃንሆይ! እንደሱ አይደለም…”
“እንደሱ ነው’ንጂ! ምን እንደሱ አይደለም ትለኛለህ?”
“እናቷ ወይዘሮ ላቀች ፈቅደውልኝ ነበር…”
“እናቷን ነው የምታገባ ልጅቷን?”
ልጅ መርእድ የሙግት ስልቱን ቀየረ፣
“ጃንሆይ! ደጃች ገሰሰ አስፈራርቶ ነው የወሰዳት…”
“አትቀላምድ!” ብለው ተቆጡ ንጉሱ፣ “….ዳኛ ሆነው እንዲፈርዱ ግራዝማች ወልደዮሃንስን ሾሜ ነበር። ግራዝማች
ግን ዳኝነቱን ትተው ለአንተና ለአባትህ ወገን ሆኑ። እሷን፣ ‘ከጃንሆይ እናጣላሻለን’ ብላችሁ አስፈራርታችሁ አሳቧን
ልትገለብጡ ፈለጋችሁ…”
“ጃንሆይ! እኔ ይሄን አላውቅም።”
“አንተ ይሄን አታውቅም? እንግዲያው አባትህ አልነገረህም ይሆናል። ንግስት ራሷ ወረቀት ጥፋ የሰደደችልኝ እጄ ላይ አለ። ‘መርእድን አልፈልግም፤ ገሰሰ ይሻለኛል’ ብላለች። ምን ትላለህ እንግዲህ?”
ልጅ መርእድ ተስፋ ባለመቁረጥ ይሟገት ቀጠለ…
“ጃንሆይ! ንግስት ሚስቴ እንድትሆን ተመኝቼ ነበር…”
“ልጅ መርእድ! በግድ ይሆናል እንዴ ታዲያ? እሷ እንደወደደችህ ነው’ንጂ፣ እገሌን ታግባ፣ እገሌን አታግባ
የምለው እኔ ምን አግብቶኝ ነው? አንተስ ቀድሞውኑ የሷን ልብ ሳትይዝ እንዴት እጇን ለመያዝ ትቃጣለህ?”
“ጃንሆይ! አምሃ ብዬ ደፈጫ እየበላ ያደገ ወይፈን ልኬላት ነበር!”
“ወይፈን ሰጥተህ ልቧን ለማግኘት ተመኘህ? እንዴት ይሆናል? አባቷ ሞተባት እንጂ የንጉስ ልጅ ናት እኮ!
ወይፈን ብቻ ሳይሆን፣ ጊደርና በቅሎ ጨምረህ ልትሰጣት ይገባ ነበር። እዚያው አባቷ አገር ጉልት ሰጥታችሁ መለማመጥ
በተገባ። ሲሆን ሁለት ጉልት፣ ካልሆነ አንድ ጉልት ሰጥተህ አቆላምጠህ ባታለልካት ነበር እንጂ፣ እሷ ‘አይሆንልኝም፣
የወደድሁትን አገባለሁ’ ስትል እኔ ምን አደርግልሃለሁ? የንጉስ ተክለሃይማኖትን ልጅ እንደ ገረድ አንቄ ልሰጥህ
ነው? ምን ይሁን ማለትህ ነው?”
“ጃንሆይ! መጀመሪያ ላይ እሺ ብላኝ ነበር እኮ…”
“አትቀላምድ! እሺ አላለችህም”
“ቆርቦ ያንሳኝ ብላ ነበር…”
“ጅላጅሎ! ቆርቦ ያንሳኝ ማለቷ ምን ማለት ነው? አንተ ባንድ እንደማትረጋ አውቃለች። ቆርበህ እንደማታነሳት አውቃ እምቢ ማለቷ ነው። ይሄ አይገባህም?”
በመጨረሻ ልጅ መርእድ ተሸነፈ።
“ተሳስቻለሁ ጃንሆይ! ይቅር ይበሉኝ” አለ።
ጃንሆይ ግን ተቆጥተውበት ስለነበር፣ “ተነስ ተከተለኝ” አሉትና ከዙፋናቸው ተነሱ።
በጃንሆይ ዙሪያ ነበሩት ሁሉ የሳቅ ድምፅ አሰሙ። ቀጥሎ የሚሆነው የገባው ልጅ መርእድ (ምናልባት እድሉን
እያማረረ) ጃንሆይን ተከትሎ ወደ ጓዳ ገባ። በግራና በቀኝ ጠባባብ መስኮቶች ያሉት ሰፊ ክፍል ነበር። መካከሉ ላይ
ካለው ጠረጴዛና አንድ ወንበር በቀር በክፍሉ ውስጥ አንዳችም እቃ አልነበረም። ግድግዳው ላይ የተለያዩ ዱላዎች
ተንጠልጥለዋል። አጤ ምንሊክ ከሽመሎቹ አንዱን እየመረጡ እንዲህ አሉት፣
“ቀላምደህ ጦርነት ልታነሳ ነበር። ላጠፋኸው ጥፋት ጥሩ ፍትፍት መቅመስ አለብህ?”
“ጃንሆይ! አጥፍቻለሁ ብያለሁኮ!”
“ቢሆንም፣ ጠጅ ሳትቀምስማ አትወጣም…”
እንደ ራቻ እያገላበጡ ይገርፉት ጀመር። አጥንቱንና ክፉ ቦታ እንዳይመቱት እየተጠነቀቁ፣ ልክ አባት ልጁን
እንደሚቀጣው አስጎንብሰው ጀርባ ጀርባውን በዱላ ዠለጡት። ይህችን የጃንሆይ የዱላ ፍትፍት ብዙዎች ፊታውራሪዎችና
ራሶች ጭምር እንደቀመሷት ስለሚያውቅ፣ ልጅ መርእድም ድምፅ ሳያሰማ ቀጨሞውን በፀጥታ ጠጣ። አጤ ምኒልክ ዝቅተኛውን
ቅጣት 12 ዱላ ካቀመሱት በሁዋላ ዱላውን እነበረበት ቦታ ሰቀሉ። እናም እንደገና ልጅ መርእድን አስከትለው ወደ
እልፍኛቸው ተመለሱ። በቤተመንግስቱ ደንብና ስርአት መሰረትም ምኒልክ በዙፋናቸው፣ ልጅ መርእድም በቦታው ተቀመጡ።
በመጨረሻ እንዲህ ሲሉ አሰናበቱት፣
“…እስቲ ለማን እንደምንድርህ እናያለን። እዚሁ አካባቢ ቆይ!”
(የትረካ ምንጭ፡ ጳውሎስ ኞኞ፣ (አጤ ምኒልክ)፣ Count Gleichen – With the Mission to Menilik, ደጃዝማች ከበደ ተሰማ)