Mon, 07/16/2012 - 11:07
የትግራይ ሕዝብ ነፃ አውጪ ግምባር ሠራዒ መጋቢ መሀንዲስ አቶ መለስ ዜናዊ በሠሩትና በሚመግቡት ምክር ቤት
ሲሰብኩና ተመጋቢዎቹ ጥያቄ እየጠየቁ ሲብራራላቸው ብዙ ጊዜ በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ሰምቻለሁ፤ አይቻለሁ።
ትርኢቱ የመምህርና የተጋባዥ ተማሪዎች ግንኙነትን የያዘ ሆኖ ስለሚቀርብ፥ ዜናው ሲደርሰኝ አዳማጮቹ ምን ዓይነት
ጥያቄ እንደሚያነሡ ከማወቅ ያለፈ ትኩረት አልሰጠውም ነበር። ግን አሜሪካን አገር አቶ አበበ ገላው ራሳቸውን
ያስደፋቸው ዕለት ሳይጠየቁ የሰጡት መልስ ልቤን ማርኮታል።
ጠያቂው አንድ አፍሪካዊ ነው። ጥያቄው “እድገትና ዲሞክራሲ አብረው ይሄዳሉ? ወይስ፤ እድገት ለማምጣት መጀመሪያ
ዲሞክራሲን መስፈን አለበት?” የሚል ነበር። መሀንዲሱ ላልተጠየቁት ጥያቄ የሰጡት መልስ በተለየ መልኩ የተሰማኝ
በአጋጣሚው ምክንያት ነው። “አጋጣሚ” ያልኩት እርሳቸው ሲመልሱ አቶ ሲሳይ አጌና “የቃሊቲው መንግስት” በሚል ርእስ
የጻፈውን መጽሐፍ እያነበብኩ ወደ ማገባደዱ ደርሼ በነበረበት ጊዜ መሆኑን ነው። መሀንዲሱ ሲመልሱ መጀመሪያ
እድገትና ዲሞክራሲ ምንም ግንኙነት እንደሌለው አብራሩ። ይኸን መልስ ስሰማ፥ የኢትዮጵያን ሕዝብ ለምን ዲሞክራሲን
እንደነፈጉት ማብራራታቸው መስሎኝ ነበር፤ አይደለም። መሀንዲሱ ዴሞክራሲን ለሕዝቡ ለመስጠት ሳይፈልጉ ከኢትዮጵያ
ምድር እንደሚለዩ መርሣት አልነበረብኝም።
ከዚህ ቀጥለው ላልተጠየቁት ጥያቄ መልሳቸውን አስከተሉ፤ “ይህ ማለት” አሉ፤ “ይህ ማለት፥ ያለ ዲሞክራሲ
በሰላም መኖር ይቻላል ማለት አይደለም። በተለየ እንደ ኢትዮጵያ ያለች ብዙ የተለያዩ ሕዝቦች በሚኖሩባት ሀገር ሰላም
ሰፍኖባት እድገትን ለማካሄድ እንዲቻል ዲሞክራሲ የግድ መስፈን አለበት” አሉ፥ ምንም ሳያወላውሉ፤ በሽብርተኝነት
ክስ ጥፋተኛ የተባሉት እነ እስክንድር ነጋ ከምድር ገሃነም ሆነው የሚጮሁት ዋይታ ምንም ሳይወቅሳቸው። (ጥያቀውና
መልሱ የተካሄደው በእንግሊዝኛ ስለነበረ የአማርኛ ትርጒሜ ስሕተት ካለበት መሀንዲሱ ሊያስተካክሉት ይችላሉ።)
ከአዳማጩ ማህል መልሳቸውና አገዛዛቸው ያልተገናኙ መሆኑ ያልገባው እሳቸውንም ግር እስኪላቸው ድረስ አጨበጨበ።
“መሀንዲሱ ምዕራባውያን መስማት የሚፈልጉትን መናገር ይችላሉ” የሚባለው ከመቸውም ግልጽ የሆነልኝ ይኸንን
ያልተጠየቁትን ጥያቄ ሲመልሱ ስሰማ ነው። እውነትም ፤ ተክነውበታል። ወደ አልተጠየቁት መልስ የተጣደፉት ምናልባት
አቶ አበበ ገላው ያስደፋቸውን አንገት ቀና ለማድረግ ይጠብቁት የነበረው ዕድል ስላጋጠማቸው ይሆናል።
ዲሞክራሲና መሀንዲሱ እንደማይተዋወቁ፥ ወደመጀመሪያው ላይ ተታልለን ይሆናል እንጂ፥ ከምርጫ 97 ወዲህ እቅጩን
ዐውቀነዋል። መግዛትን የጉልበተኛ ተራ ጉዳይ እንዳደረጉት መላ ዓለም አይቷል። ድምጽ መስጫ ወረቀቶች በአንዳንድ
ዲሞክራሲያዊ አገሮችም ይሰረቃሉ፤ ግን እንደዚህ ያለ ዝርፊያ የሚካሄደው ዲሞክራሲ በሌለበት አገር ብቻ ነው።
የምርጫ 97 ጉዳይ ከተነሣ፥ በዚያ ጊዜ ስለሆነው የምናውቀው ሕዝቡ በምርጫ ያገኘውን ድል መነጠቁንና አዝማቾቹ
ድሉን ስለመሩ ተወንጅ እስር ቤት መግባታቸውን እንጂ፥ አቶ ሲሳይ አጌና በዝርዝ እንደገለጠው እስረኞቹ በመሀንዲሱ
ትእዛዝ እንዲህ በምድር ገሃነም ውስጥ መሰቃየታቸውን መቸ ዐወቅን? ውይ፥ ውይ! እውነትም ሕገ-አራዊት! ከጭካኔዎቹ
ውስጥ አንዱን ለማንሣት ያህል፥ ሲመሽ ዘበኞቹ ከሦስት መቶ በላይ የሚሆኑ እስረኞችን አንድ ክፍል ውስጥ ዘግተውባቸው
በርቀት ሊቆሙ ይችላሉ። ማንም በምንም ምክንያት በሩን ቢያንኳኳ፥ የቱንም ያህል ከፍ ባለ ድምፅ ቢጮህ፥ ከመንጋቱ
በፊት የሚከፍትለት የለም። ሆዱን የጎረበጠው ሰው እዚያው በሁሉም ፊት ከመዋረድ ሌላ፥ ሁሉም ምነው አፍንጫ ባልኖረኝ
ሲያሰኝ ያነጋል። እሳት ቢነሣ ሁሉም ያልቁ ነበር።
የፍርድ ቤቱ ሂደት ድራማ ነበር፤ የዳኝነት ወምበሮች የተያዙት በገለልተኛ ሳይሆን የበላይ ትእዛዝ
በሚያወዛውዛቸው ገለልትኞችን በተኩ ዳኞች ነው። በሐሰት እንዲመሰክሩ ከታዘዙት መስካሪዎች ውስጥ አንዱ ሲጠየቅ፥
የመንግሥት ታዛዥ መሆኑን በኩራት ለማሳየትና በይፋ ለመመስገን፥ “ያየሁትም የሰማሁትም ነገር የለም፤ የመጣሁት
መንግሥት መስክር ብሎ ስላዘዘኝ የመንግሥት ትእዛዝ ለመፈጸም ነው” ብሎ መሰከረ።
በምርጫው ሳቢያ የመሀንዲሱ ፖሊሶች ሁለት መቶ የሚሆኑ ሰላማዊ ሰልፈኞች ገድለው ነበር። ሰዎቹ ለምን
እንደተገደሉ የሚመረምር አንድ ቡድን መንግሥት አቋቁሞ ነበር። ያም ሆኖ፥ መርማሪው ቡድን ጥፋቱ የመንግሥት መሆኑን
አረጋገጠ። መሀንዲሱ የፈለጉት ግን ሕዝቡን ጥፋተኛ ለማድረግ ነበር። ስለዚህ የቡድኑን አባላት እቢሮዋቸው ድረስ
ጠርተው ሪፖርቱን እንዲቀይሩ አስፈራሯቸው። አለዚያ እኮ በመሀንዲሱ ዘመን በኢትዮጵያ ዲሞክራሲ የለም ሊባል ነው።
ከቢሮዋቸው ሲወጡ፥ ከአባላቱ አንዳንዱ ሪፖርቱን እንቀይር አለ፤ ሌላው (ከመቃጠል) እናቃጥለው አለ፤ አንዳንዶቹ
ከአባልነቱ በፈቃዳቸው (ያለፈቃዳቸው) ለመሰናበት ተገደዱ፤ ሌሎቹ የመጣው ይምጣ ብለው በቃላቸው ረጉ። መፍትሔው
ለመሀንዲሱ ቀላል ነበረ፤ ከዚህ ሁሉ ጭቅጭቅ እራሳቸው እንደፈለጉት ጽፈውም ይሁን አስጽፈው፥ የቡድኑ ሪፖርት ሆነ፤
አለቀ ደቀቀ።
የሽማግሌዎቹ ሚና ከማስገረም ይልቅ የሚያስቅ ነው። ሊቀ መንበሩ ስለሽምግልና ባህላችን በሰፊው ያብራራል።
ያደረገው ግን መሀንዲሱ ያሉትን ተቀበሉ (ጥፋተኞች ነን በሉ) ብሎ ከጫማቸው ላይ መውደቅ ነበር። አስፈታኋቸው ብሎ
ስም ለማትረፍ መሆን አለበት። አወይ ባህላችን!! በመጨረሻ፥ ከእስረኞቹ አንዱ፥ “የጎበዝ በር እንልቀቅለት” ብሎ
ባቀረበው ሐሳብ (ይኸንን ከሲሳይ መጽሐፍ ሳይሆን ከሌላ ነው የሰማሁት) ተስማምተው የመሀንዲሱን ወንጀል ግማሹን
ወስደውለት ተፈቱ። ሲፈቱ ከመሀንዲሱ ተከታዮች አንዱ “ሕገ-አራዊት ሲሉ ያጣጣሉትን ሕገ-መንግስትንም እንደሚቀበሉ
በማረጋገጥ ተንበርክከው ይቅርታ ጠይቀዋል” ብሎ ፎከረ፤ ጊዜ ስለሰጠው ብቻ የኢትዮጵያ ዓይኖችን በማሰቃየቱና
ክብራቸውን በመንካቱ መግቢያ ቀዳዳ እስኪጠፋው በማፈር ፈንታ በአነጋገሩ እውነትም ሕገ-አራዊት መኖሩን መልሶ
አረጋገጠ።
ተረቱ የታወቀ ቢሆንም አጋጣሚው እንድደግመው ይጋብዘኛል፤ አሽከር ጠዋት የጌታውን ጫማ ሊጠርግ ሲያነሣው አይጥ
በልታለት አገኘው። “አወይ፥ አወይ! ወይ ጉድ፥ ወይ ጉድ!” እያለ ሲጮህ፥ ጌታው ሰምቶት፥ “ምን ጉድ ተፈጠረ?”
ብሎ ጠየቀው። የሆነውን ሲነግረው፥ “ምን ሞኝ ነህ እባክህ? ጉዱ ጫማው አይጧን ቢበላት ነበር እንጂ፥ አይጥ ቆዳ
መብላቷማ የተፈጥሮ ጠባይዋ ነው” አለው ይባላል። መሀንዲሱ ባላቸው የማይለወጥ ጠባይ የተነሳ በደል በፈጸሙ ቊጥር
እንደ አዲስ ነገር ማየታችንን አቁመን ነፃነታችንን በምናገኝበት ዘዴ ላይ ብቻ ማተኮር አለብን። “ወይ ጉድ!”
ማለታችንን ከምናቆምበት ዘዴ አንዱ የመወያያ አርእስት እነሱ ሲሰጡን አለመቀበል ነው። አለዚያ አንድ የማንወደውን
ነገር ጣል ያደርጉልንና እሱን ማስተባበል የሚገባ ቢሆንም፥ ማስተባበሉን በመጠኑ ካላደረግን በመፍትሔው ላይ የመሰለፍ
አቅማችንን እናጠፋበታለን። የመሀንዲሱ “ክልል”፥ “አንቀጽ 39”፥ “የብሔሮች ጥያቄ”፥ “ወዘተ” ስንት ጊዜ
አከራከሩን!!
አንቀጽ 39ን እንተወው፤ እንደማየው፥ የመሀንዲሱ ቡድን በሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ ይህ አንቀጽ ኢትዮጵያን
አያሰጋትም። ሕገ መንግሥቱ ውስጥ የገባው በአንድ በኩል ሀገር ወዳዱን ለማስፈራራትና የመወያያ ርእስ ለመስጠት
ሲሆን፥ በሌላ በኩል ለመገንጠል የሚጓጓውን ለመደለል ነው። እንደእውነቱ ከሆነ ግን በመሀንዲሱ ሕገ መንግሥት
መሠረት፥ አንድ ክልል የሚገነጠለው ራሱ መሀንዲሱ የሚያስገነጥሉ ብለው የዘረዘራቸውን ምክንያቶች መንግሥት ሲያጓድል
ነው። የሚያስገነጥሉትን ምክንያቶችን እሳቸው መርጠው ከሰጡ፥ እነዚያንም ቢሆን ተገንጣይ ወገን “መንግሥት
አላሟላልኝም” ቢል ማነው የሚሰማው? የመሀንዲሱ መንግሥት ነው? እስቲ ተሰምተው እንደሆነ የመገንጠል ጥያቄ ያነሱትን
እንጠይቃቸው! ኢትዮጵያ የወያኔ ጒልት ሆናለች፤ ማን ይድላው ብሎ ነው ወያኔ ሳይገደድ ጒልቱን የሚያስቈርሰው?
መሀንዲሱ ስለጒልቱ መልማትም በሰፊው ያስወራሉ። ወያኔና ሻዕቢያ በጣምራ ባይወጥሯቸው የንጉሡ መንግሥትና የደርግ
መንግሥት የእድገቱ እርምጃ የትና የት ይሄድ ነበር! አርበኞች ባያስቸግሩት ኖሮ የዱካ ዳዎስታ አገዛዝ ኢትዮጵያን
በእድገት ከኢጣልያ ጋር ያወዳድራት ነበር። ፕላኑን ያየ ይደነቃል። ግን ጥያቄው መጀመሪያ ነፃነትን ማግኘት ስለሆነ
ማንም አልተባበራቸውም። በኃይል ገዝተው ሲያቅታቸው አልፈዋል። ነፃነት የሁሉ መጀመሪያ እንጂ ለምንም ነገር ሁለተኛ
አይሆንም። ነፃነት አምሳያ የሌለው ሰውን በሰው ደረጃ የሚያስቀምጥ የአምላክ ስጦታ ነው። አንድን ሰው ነፃነቱን
ነፍጎ ቢያበሉት እንኳን፥ ሰውየው እንደ ከብት ቅልብ ነው የሚሆነው፤ ጌታ ሰው በእንጀራ ብቻ አይኖርም ያለው ስለዚህ
ነው። እንጀራን የምንፈልገው ላለመሞት ሲሆን ነፃነትን የምንጠይቀው ለመኖር ነው። ያሁኖችም ኃይላችሁ
እስከፈቀደላችሁ በኃይል ገዝታችሁ ታልፋላችሁ፤ ነፃነቱን ከገፈፋችሁት ሕዝብ ጋራ ሳትጣጣሙ።
መሀንዲሱ ስለሕግ የበላይነት በሰፊው ያስወራሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ፥ የሕግ የበላይነት ወደታችነት የወረደው
በደርግና በወያኔ የጭቆና አገዛዝ ዘመን ብቻ ነው። ፍርድ ቤቶች እስከዛሬ የሚሠሩት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን
በታወጁ ሕጎች ነው። የዚያን ጊዜው ዳኝነትና ሽምግልናው ከዛሬው ጋር ሲተያይ ምድርንና ሰማይን፥ ጭለማንና ብርሃንን
ማስተያየት ይሆናል። የታሪክ ምንጮች እንደሚመሰክሩት፥ የጥንት ነገሥታትም ቢሆኑ የሚገዙት በሕግ ነበር። ነገሥታቱን
ከሚያጅቡት ባለሥልጣናት ማህል ትልቁን የክብር ቦታ የሚይዙት ሕግ ዐዋቂዎችና ዳኞች ነበሩ። ለምሳሌ፥ ነገሥታቱ
ርስት ለገዳማት ሲጐልቱ፥ በሃይማኖት ጭቅጭቅ ጊዜ ዳኝነት ሲቀመጡ፥ በዓላት ሲያከብሩ፥ ከመኳንንቱ ጋር ለምስክርነትና
ሕግ ለመጥቀስ ሕግ ዓዋቂ ታላላቅ ሰዎች በቦታው ይገኛሉ። ይህም ነገሥታቱ ለሕግ የቱን ያህል አክብሮት
እንደነበራቸው ያሳያል። የፍርድ ጒዳይ ከንጉሡ ችሎት ሲደርስ ንጉሡ ብቻውን አይፈርድም። ከችሎት ላይ የሚቀመጡ
መኳንንትና ሊቃውንት የክብር ተራቸውን ጠብቀው ከታች ወደላይ ይፈርዳሉ። ንጉሡ ሁሉን አዳምጦ የማይሻረውን
የመጨረሻውን ፍርድ ይሰጣል።
ገዢዎቹ ሃይማኖተኞች ስለነበሩ ጭካኔያቸውን ለመቆጣጠር ሃይማኖታቸው ከዲሞክራሲ የበለጠ ኀይል ነበረው። ሕግን
ከሚፈራ እግዚአብሔርን የሚፈራ ይሻላል። በአንድ ዘመን ንጉሡ ይሙት በቃ የፈረደበትን ሰው እንዲምረው ሽማግሌዎች
ቢለምኑት እምቢ ብሎ ነበር። ድንገት በዚያው ጊዜ ፀሐይ ብርሃኗን ነፈገች። ይህ የሆነው በእሱ እምቢተኝነት መሆኑን
ያመኑ ንጉሡን ስላሳመኑት፥ ይሙት በቃ የፈረደበትን እስረኛ ነፃ ለቀቀው። ትልቁ ችግር ነገሥታቱ ፍጹም ጻድቃን
ሲሆኑ፥ ወይ መንፈሳዊነቱ ላይ ብቻ ያተኲራሉ፤ ወይም ገዳም ገብተው ይመነኲሳሉ።
ከዓሥራ ሰባተኛው ምእት ዓመት ጀምሮ እስከ ሃያኛው ምእት ዓመት ድረስ የሃገሪቱ መተዳደሪያ ሕግ ፍትሐ ነገሥት
ነበር። ፍትሐ ነገሥት ስለ ንጉሥ ሲናገር፥ “ከዙፋኑ ላይ ሲቀመጥ፥ በእድሜ ልኩ አብሮት የሚኖር አምላካዊ
(የተግሣጽ) ጽሑፍ ካህናት ይጻፉለት፥ ያንን እያነበበ ፈጣሪውን እግዚአብሔርን መፍራት እንዲማርና ትእዛዞቹን
እንዲያከብር” ይልና፥ “በመንጋው ላይ በትክክል ይፍረድ፤ ለራሱም ሆነ ለሌሎች፥ ለልጆቹም ሆነ ለዘመዶቹ፥ ወይም
ለባዳ አያዳላ” ይላል። ጦርነት ሲታወጅ ጠላት እንዲያሸንፍ የሚያጋልጥ፥ የተመከረውን ምክራችሁን የሚያወጣ፥ ወይም
ወደነሱ ሄዶ መሣሪያ የሚሸጥላቸው ይሰቀል፤ ይቃጠልም” ይላል። ኢትዮጵያን ለመገነጣጠል እንደ ታጠቀው እንደ ሻዕቢያ
ካለ የሀገር አንድነት ጠላት ጋር የዶለተ ማለት ነው።
የጎንደር ቤተ መንግሥት ዘርፈ ብዙ ወግና ሥርዓት በጥንቃቄ ስለተመዘገበ፥ የረቀቀ ሥልጣኔያችንንና በቤተ
መንግሥት የዜጎች መብት እንደ ታቦት ይከበር እንደነበረ ለማሳየት በግዕዝ የደረሰንን አጭር ሰነድ ወደአማርኛ
እየተረጐምኩ ላቅርብ፤
ግራና ቀኝ ወምበሮች ለፍርድ በችሎት ሊቀመጡ ሲሉ፥ መጀመሪያ በቅዱስ ያሬድ ቃል በዜማ እንዲህ ብለው ይጸልያሉ፤
“ሃሌ ሉያ፤ ዕዳ በሚከፈልባት በዚያች ዕለት፥ ፍርድ በሚሰጥባት በዚያች ዕለት፥ በዚያች በእግዚአብሔር ዕለት
ነፍሳችንን ምን እንላታለን? . . .” ይኸንን ጸሎት ሦስት ጊዜ እስከመጨረሻው ይሉና ትርጓሜውን ከጽራግ ማሠሬ
(ከንጉሥ አልባሽ) እና ከሊቀ ማእምራን (ከትልቁ ሊቅ) ይሰማሉ። ከዚያ በኋላ (ዳኞቹ) በንጉሥ ሰቀላ ቤት ለፍርድ
በቀኝና በግራ ይቀመጣሉ። ከበሽተኞች፥ ከሴቶች፥ ከመምህራን በቀር ትንሹም ትልቁም ሹምም ብሕትወደድም ደጃዝማችም
ተቀምጦ አይፋረድም። ቁጭ ብሎ የሚፋረድ ባለሥልጣን የአክሱም ነብርድ ብቻ ናቸው።
“ትርጓሜ” የሚለው በግዕዝ የተነበበውን እንደዚህ እኔ ወደ አማርኛ እንደተረጐምኩት ጥሬ ትርጒም ማለት
አይደለም። የምጽአት ዕለት ነፍስ በታላቁ ዳኛ ፊት ቆማ፥ እያንዳንዱ ሰው የሠራው ሥራ በጎውና ክፉው ይመዘናል።
የሰውየው የዘላለም ሕይወት የሚወሰነው በሚመዘነው ሥራ ነው። ሚዛኑን የሚይዙት መላእክት ስለሆኑ፥ ተዳላብኝ የሚል
አይኖርም። ማንም ሰው ወደፈለገበት ሕይወት ለመሄድ ዕድሉ አሁን እንደሆነ ሊቃውንቱ ያስረዷቸዋል። ለዳኞቹ በተለየ
የሚጠቅሱላቸው፥ “እንዳይፈረድባችሁ በአድላዊነት አትፍረዱ” የሚለውን የክርስቶስ ቃል ነው። አባ አበክረዙን የሚባሉ
መነኲሴ የገዳማቸው አለቃ (አበ-ምኔት) እንዲሆኑ ሲጠየቁ፥ እምቢ ለማለት፥ “እርጉሞች ሆይ፥ ወዲያ ለሰይጣንና
ለሠራዊቱ ወደተዘጋጀው እሳት ሂዱ” የሚለውን የጌታ ቃል ጠቅሰው፥ “ከዚህ ቃል በቀር ሰውን እንደማዘዝ የሚያስፈራኝ
ሌላ ነገር የለም” ማለታቸው የዕለተ እግዚአብሔርን አስፈሪነት በማስታወስ ነው። ከድርሰቶቻቸው እንደምገምተው፥
አባቶቻችንና እናቶቻችን እግዚአብሔን ያከብራሉ፤ ፍርዱንም እንደማይስት ተወርዋሪ ጦር ይፈሩ ነበር።
የሰው ልጅ፥ በተለየም ገዢ፥ ሌላውን እንዳይበድል የሚቆጣጠረው፥ አንደኛ፥ ፈሪሃ እግዚአብሔር ሲያድርበት፥
ሁለተኛ፥ በትምህርት የዳበረ የተፈጥሮ ርኅራኄ ሲኖረው፥ ሦስተኛ፥ የመንግሥት የጸጥታ ኀይል በጎኑ ሲቆም፥ አራተኛ፥
ገዢውን የሚያሰጋ የተደራጀ የሕዝብ ኀይል ሲኖር ነው። በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ሕዝብ እምነቱ ከነዚህ ውስጥ
በየትኛው ነው?
No comments:
Post a Comment