Mon, 07/16/2012 - 11:06
አንድ
የአሜሪካ ፈላስፋ የሚተርከው ገጠመኝ አለው፤ አንድ ቀን በእግሩ ሲንሸራሸር ሰዎች አንድ ዛፍ ከብበው ሲጨቃጨቁ
ያያል፤ ይጠጋና ሲያዳምጥ ክርክሩ በአንዲት ዛፉ ላይ ባለች የዛፍ አይጥ (የዛፍ አይጥ እኔ ያወጣሁላት ስም ነው፤
በእንግሊዝኛ ስኮረል ትባላለች ረጅም ጭራ ያላት ጸጉራማ ፍራፍሬ ለቃሚ ነች፤) የተነሣ ነው፤ አንዱ ሰው ይቺን የዛፍ
አይጥ እዞራታለሁ ይላል፤ ሌላው ደግሞ የለም ዛፉን ትዞራለህ እንጂ አይጥዋን ልትዞራት አትችልም ይላል፤ እዞራታለሁ
የሚለው ሰው ለማስረዳት ዛፉን ይዞራል፤ አይጥዋም በዛፉ ላይ ትሽከረከራለች፤ የተሰበሰቡት ሰዎች በዚህ ጉዳይ
ለሁለት ተከፍለው ይጨቃጨቃሉ፤ ፈላስፋው ሲደርስ የሱን አስተያየት ይጠይቁታል፤ ክርክሩ በመዞር ትርጉም ላይ ልዩነት
መሆኑን እንደሚከተለው ያስረዳቸዋል፤ አይጥዋን መዞር ማለት አይጥዋን በተለያዩ አቅጣጫዎች፣ ማለትም አንድ ጊዜ
ከፊትዋ፣ ሌላ ጊዜ ከግራዋ፣ እንዲሁም ከቀኝዋና ከኋላዋ ማየት ነው ወይ? ወይስ አይጥዋ ዛፉ ላይ ስላለች ሰውዬው
ዛፉን በመዞሩ አይጥዋንም ይዞራል?
እሁድ ማታ ሰዎች ደወሉልኝና በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ስለአክራሪነት የሚተላለፈውን ፕሮግራም እንድመለከት አስታወቁኝ፤ ተመለከትሁት፤ በጥንቃቄ በተመለመሉት ሰዎች መሀከል ነጻነት፣ መቻቻል፣ አክራሪነት የሚሉት ቃላት እንደልብ ይወረወሩ ነበር፤ በእነዚህ በጣም ቁልፍ በሆኑ ቃላት ላይ ክርክር አልተከፈተም ሊከፈትም አይቻልም፤ ክርክር ሊነሣ የሚችለው በአእምሮአቸውና በኅሊናቸው እየተመሩ፣ ምንም ዓይነት የውጭ ኃይል አስተሳሰባቸውን ሳያዛባባቸው ለመነጋገር በተሰለፉ ሰዎች መሀከል ነው፤ የተለያየ ካባ የለበሱና የተለያየ ሃይማኖት አለን የሚሉ ካድሬዎች በአንድ ቀጭን ክር ይታሰሩና ቋንቋቸው አንድ ይሆናል፤ አስተሳሰባቸው አንድ ይሆናል፤ ሀሳባቸው አንድ ይሆናል፤ ኦርቶዶክስ፣ እስላም፣ ካቶሊክ፣ ፕሮቴስታንት፣ መናፍቅ መሆን ወግ ብቻ ይሆናል።
ፕሮግራሙ ለእኔ ያስተላለፈልኝ መልእክት በእውነትና በድፍረት ከፍርሃትና ከጥቅም በላይ ሆነው ክርስቲያንነትንም ሆነ እስላምነትን፣ ወይም መናፍቅነትን በማስረዳት ብዙዎቹ ከጠቀሱት ሕገ መንግሥት ጋር እነሱን ሁሉ የሚያስተሳስራቸው ምን እንደሆነና እንዴትስ እንደሚተሳሰሩ በግልጽ አላወጡትም፤ እነዚህን ሁሉ የሚያስተሳስራቸውና ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የሚያደርጋቸው ዜግነት ነው፤ ዜግነት የሚል ነገር በቀበሌ መታወቂያ ላይ እንኳን አይገባም፤ የሚደንቀው ሃይማኖትም ከጉዳይ ተቆጥሮ በቀበሌ መታወቂያ ላይ አለመግባቱ ነው፤ ጎሣ የለኝም ብሎ በኢትዮጵያዊነት ለመመዝገብ አይቻልም ነበር፤ ከዛሬው የተሻለ ፍርድ ቤት በነበረበት ጊዜ ልጅ ይስሐቅ ክፍሌ በፍርድ ቤት ከስሶ ነው በኢትዮጵያዊነቱ የመታወቅን መብት ያረጋገጠው፤ አሁንም ቢሆን በቀበሌም ሆነ በየመሥሪያ ቤቱ ቅጽ ሲሞላ ጎሣ የለኝም የሚል ሰው ክርክር ይገጥመዋል፤ ሁሉንም ሰው በግድ በጎሣ ከረጢት ውስጥ ለማስገባት ጥረት ይደረጋል።
የሃይማኖት ሰዎች ነን የሚሉት ሕገ መንግሥቱን ሲጠቃቅሱ የሚያምኑበትን የእግዚአብሔርን ሕግ ለመጠቃቀስ የደፈሩ አይመስሉም፤ አንድ ጊዜ በጀኔቭ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ላይ ሱዳን የሰብዓዊ መብቶች የሚረገጡበት አገር ተብሎ ሲወቀስ፣ የሱዳኑ መልእክተኛ እኛ የምንከተለው የአላህን ሕግ ነው እንጂ የሰውን ሕግ አይደለም፤ ብሎ መለሰ፤ የእግዚአብሔር ሕግ የተባለው ውስጥ ሰብዓዊ መብቶች የሉበትም የማለት ዝንባሌም እንኳን ማሳየት ሃይማኖቱንም እግዚአብሔርንም የሚያስቀይም አይሆንም?
ለእኔ አክራሪ ማለት ለእግዚአብሔር ጠበቃ እቆማለሁ የሚል ኦርቶዶክስ፣ ለእግዚአብሔር ጠበቃ እቆማለሁ የሚል ካቶሊክ ወይም ፕሮቴስታንት፣ ለአላህ ጠበቃ እቆማለሁ የሚል እስላም፤ ሃይማኖት ሁሉ ድንቁርና ነው የሚል ደንቆሮ… እነዚህ ሁሉ ክፉ አክራሪዎች ናቸው፤ በእግዚአብሔር የሚያምኑት የእግዚአብሔርን ኃያልነት ጠዋትና ማታ እየሰበኩ፣ እግዚአብሔር ራሱን ያልቻለ፣ ጠበቃና ፌዴራል ፖሊስ ጠባቂ የሚያስፈልገው አድርገው የሚገምቱት ሃይማኖተኞች ይባላሉ ወይስ መናፍቅ? እግዚአብሔር በየትኛውም ስም ቢጠራ የኃያሎች ኃያል ነውና ከፈለገ እንኳን እሱን ራሱን ጎረቤታቸውንና ደሀዎችን የሚበድሉትን በማናቸውም ጊዜና በየትኛውም ቦታ ፍርዳቸውን ለመስጠት የሚችል መሆኑን የማይቀበል ሃይማኖተኛ ያለ አይመስለኝም፤ ታዲያ እግዚአብሔርን አዋረደ፣ ወይም ናቀ ብሎ በዚያ ሰው ላይ የኃይል እርምጃ መውሰድ የእግዚአብሔር መንበር ላይ መቀመጥ አይሆንም? በእግዚአብሔር መንበር ላይ ለመቀመጥ ከመንጠራራት የበለጠ የአክራሪነት ዕብሪት ምን አለ?
በአክራሪው ግምት እግዚአብሔርን የሚያስቀይም ንግግር ሲሰማ፣ ወይም እግዚአብሔር የማይወድደው ነገር ሲደረግ ሲያይ፣ እግዚአብሔር አይሰማም፣ አያይም፣ በማለት ነው አክራሪዎቹ ለእግዚአብሔር ጠበቃ ቆመናል ብለው ሰውን የሚያጠቁት? ይህ እግዚአብሔርን መስደብ አይሆንም ወይ? እስቲ እግዚአብሔር የሰጠንን አእምሮ ተጠቅመንበት እናስበው፤ የሁለት የተለያዩ ሃይማኖቶች አክራሪዎች በእግዚአብሔር ስም ቢጨፋጨፉ ሁሉም እግዚአብሔርን ያስቀይማሉ? ሁሉም እግዚአብሔርን ያስደስታሉ? ወይስ አሸናፊው እግዚአብሔርን ያስደስታል? ወይስ መናፍቃንን ያስደስታል?
መቻቻልንና ነጻነትን እያብላላናቸው እንቆይ።

No comments:
Post a Comment