Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Sunday, 15 July 2012

የኤክስፖርት ገቢ መቀነስ ለትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ፈተና ነው ተባለ

የዘንድሮ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከታቀደው በታች የቀነሰ በመሆኑ፣ ለአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽ ዕቅድ ለታሰበው ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ትልቅ ፈተና ሊሆን እንደሚችል ተጠቆመ፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ልማት ምርምር ተቋም በጋራ ባዘጋጁት ዓውደ ጥናት ላይ የተገኙት የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር አብርሃም ተከስተ ከሁለት ዓመት በላይ የሆነው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የወጪ ንግድ ገቢ ምን ያህል ሊሆን እንደሚገባው ተዘርዝሮ የተቀመጠ ቢሆንም፣ በተያዘው በጀት ዓመት በዕቅድ የተቀመጠውን ያህል ያለመሆኑ ሊያሳስብ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡

ባለፈው ማክሰኞ በተካሄደው በዚህ ዓመታዊ ጥናት ላይ በዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ የግሉ ዘርፍ ሚናና ተሳትፎን በሚመለከት በሚኒስትር ዴኤታው በቀረበው ጽሑፍ፣ የአገሪቱን ኢኮኖሚያው ዕድገት ለማስቀጠል የወጪ ንግዱ ትልቅ ቦታ ተሰጥቶታል፡፡

በ2003 ዓ.ም. የተገኘው የውጭ ምንዛሪ በ2002 ዓ.ም. ከተገኘው በ37 በመቶ ብልጫ ነበረው፡፡ የ2004 በጀት ዓመት አጠቃላይ መረጃው ባይደርስም በአሥር ወራት የተገኘው ገቢ ሲታይ ከአምናው ብልጫ ያለው ቢሆንም ከታቀደው ጋር ሲነፃፀር አነስተኛ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

የወጪ ንግድ ገቢው በዚህ ሁኔታ ከታቀደው በታች መገኘቱ በተከታታይ እየታየ ያለውን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከ2005 ዓ.ም. በኋላም ለማስቀጠል ትልቅ ፈተና ስለሚሆን፣ በዘርፉ ብዙ መሠራት እንዳለበት በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

በተለይ በአገሪቱ የወጪ ንግድ ዋነኛ ተሳታፊ የሆነው የግሉ ዘርፍ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለበት የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በታቀደው ልክ ለምን መላክ እንዳልተቻለና በተለምዶ ለረጅም ዓመታት ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ሳይቀሩ በተፈለገው መጠን ያለመጨመራቸው ምክንያት በአግባቡ መዳሰስ አለበት ብለዋል፡፡ የወጪ ንግድ ገቢ ቀነሰ ከተባለ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የግሉ ዘርፍ ተጠያቂ ሊሆን እንደሚችል ጭምር ገልጸዋል፡፡

ከወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የጨርቃ ጨርቅና ጋርመንት ምርቶች በዕቅድ ዘመኑ መጨረሻ ላይ አንድ ቢሊዮን ዶላር እንደሚገኝባቸው የታቀደ ቢሆንም፣ አሁን እየተገኘባቸው ያለው ገቢ ግን እጅግ አነስተኛ ሆኖ መገኘቱን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ መንግሥት በቀጥታ ምርት ወደ ውጭ እንደማይልክ ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ በዚህ ረገድ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት የግሉ ዘርፍ ነው ብለዋል፡፡ ሆኖም መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በጋራ እስካልሠሩ ድረስ የታሰበውን ዕቅድ ለማሳካት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡

እንዲህ ዓይነቱ ችግር ሊታሰብብት የሚገባና መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በጋራ መሥራት እንዳለባቸው ያመለከተ ከመሆኑም በላይ፣ በጋራ ለውጤት የሚያበቃ ምክክር ማድረግ አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ዶ/ር አብርሃም የዕድገትና ትራንስፎርሜሽነ ዕቅዱ ከግሉ ዘርፍ ጋር ስለሚኖረው ሚና አስመልክተው ሰፊ ማብራሪያ በሰጡበት በዚህ መድረክ፣ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ሰፊ ውይይት ተደርጐበት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀ በመሆኑ፣ የሕግን ያህል አስፈላጊና ከዚህም አንፃር ተጠያቂነት የሚያስከትል ዕቅድ ተደርጎ መታየት እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

ተጠያቂነት ሲባል ደግሞ ሁሉንም ዜጐች ተጠያቂ የሚያደርግ ዕቅድ ነው፡፡ ዕቅዱ የመንግሥት ብቻ ተደርጐ መወሰድ የሌለበትና የአገር ብሎም የሁሉም ዜጋ ዕቅድ መሆኑን በማመን፣ በተለይ የግሉ ዘርፍ አፈጻጸም ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል ብለውል፡፡

መንግሥት በተመረጡ ዘርፎች ላይ ብቻ የሚሳተፍ መሆኑን ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታው፣ መንግሥት በብረታ ብረት ኢንጂነሪንግ፣ በማዳበርያና በስኳር ልማት ብቻ ተሳታፊ ሲሆን፣ ሌላው ለግሉ ዘርፍ የተተወ በመሆኑ ለዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዱ ተፈጻሚነት ዋነኛ ተዋንያኑ የግሉ ዘርፍ መሆኑ መታወቅ ይኖርበታል ብለዋል፡፡

የግል ዘርፉን ለማበረታታት በዕቅዱ ውስጥ በርካታ ጉዳዮች እንዳሉና በተለይ በግሉ ዘርፍና በመንግሥት መካከል የሚደረገው የምክክር መድረክ ወሳኝ ቦታ ይሰጠዋል በማለት ገልጸዋል፡፡ የግሉ ዘርፍ በመንግሥት ላይ በጎ ተፅዕኖ የማሳደር፣ መንግሥትም ከግሉ ዘርፍ የሚነሳውን ሐሳብ በቅንነት በመቀበል ተግባራዊ እንዲሆን የማድረግ አሠራር እንዲኖረው በማድረግ፣ ከዚህ ቀደም ከተደረጉት የምክክር መድረኮች በተሻለ መንገድ እንዲካሄድ ይደረጋል ብለዋል፡፡ እንደ ምሳሌ ያቀረቡትም በኤክስፖርት ዘርፍ ምክክር ሲደረግ የተለመደው ዓይነት ሳይሆን እንሠራዋለን ተብሎ በዕቅድ የተያዘውን ማስፈጸም የሚያስችል ምክክር ዓይነት መሆን እንዳለበትና የጋራ ተጠያቂነት እንዳለበትም አስታውቀዋል፡፡

መንግሥት መሥራት ያለበትን ሥራ ካልሠራ፣ ባለሀብቱም ውጤት ካላስገኘ ለምን የሚባልበት የምክክር መድረክ መፈጠር ይኖርበታል ያሉት ሚኒስቴር ደኤታው፣ ለዕቅዱ አፈጸጸም መጓደል ሁሉም ወገኖች እንደ ድርሻቸው ተጠያቂ እንደሚሆኑ አሳስበዋል፡፡

No comments:

Post a Comment