Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Friday 20 July 2012

አልጋወራሽ እንምረጥ ወይስ?....ከዳዊት ዋስይሁን


የተከበረና ጀግናው አበበ ገላው የአቶ መለስን አንገት ካስደፋቸው አንስቶ የሰውየው ስም በየትኛውም ጎራ ባለ የመገናኛ አውታርም ሆነ የማህበራዊ መረብ እስከ አሁን ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በሪኮርድ ማለት ይቻላል በየለቱ የመወያያና የመነጋገሪያ ርእስ ሆኖ እንደሚገኝ የየለት ትዝብት ነው፣ ጉዳዩን ልዩ የሚያደርገው በየወቅቱ የሚፈጠር አዳዲስ ክስተት ሲሆን በሚገርም ሁኔታም አንዱን ተነጋግረንና አንሸራሽረን ሳንጨርስ ሌላ አዲስ ነገር ይወለዳል ይኽው እስካሁን አለን ስንባትል፣ በአገር ቤትም በውጭም በሁሉ ቦታ የደራ የሞቀ መነጋገሪያ ሆኖአል እንደውም ከሰሞኑማ አገር ቤት ያሉ ስርእት አደር የእምነት ተቋማት ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ለተፈጠረው ሁኔታ ሱባኤ ሊገቡ እያሰቡ እንዳለ የሚያሳይ ምልክቶች እየታዩ ነው እንግዲህ ይህ ነው እኔንም ብእሬን እንዳነሳ ያረገኝ።
መነጋገር መደማመጥና መቻቻል የአደገ ማህበረሰብ መገለጫዎች ሲሆኑ እኛም ይህንን በትእግስት አደረግነው ማለት ወደ አንድ ደረጃ ከፍ ማለታችንን ያሳያል እንደውም እንዲበዛልንና እንዲያድለን ተግተን ልንመኘው ልንለማመደው ያስፈልጋል፣ ነገር ግን በዚህ ሒደት ውስጥ በተለይ የአቶ መለስ ሁኔታ በፈጠረው ጉዳይ ላይ ጠንቀቅ ልንል ያስፈልጋል ምክንያቱም ትግልን ያማከለና ውጤትን ያነጣጠረ ስራ መሰራት ስላለበትና በ1997 የታጣው የህዝብ ጥያቄ ድጋሚ አሁንም በወያኔዎች ጮሌነት እንዳያመልጠን የሚነፍሰውን ንፋስ ለይተን ትግላችንን እንድንመራ ከማሰብ ነው።
ይህንን ስል እየታገልነው ያለው ስርአት ክፋትን፣ ሸርን፣ ተንኮልን፣ መርዘኝነትን፣ ዘረኝነትን፣ መከፋፈልን አንዲሁም በተለይ ትውልድን ባተሌ ማድረግ ለ21 አመት በአገራችን ፖሊሲ ነድፎ ያዋቀረና የተከለ ስለሆነ የምንሰማውን ወይም የሚፈጠረው አዲስ ነገር ሁሉ ልንደርስበት ካሰብነውና ካለምነው ለሰከንድ እንኳን ሊያጓትተን አይገባም፣ እንዲሁም መጠቀም ያለብንን እውቀት፣ ጉልበትና ሃብት አላስፈላጊ ቦታላይ እንዳናፈሰው መጠንቀቅ አለብን።
በተለይ ዋናውና ሃይለኛው የወያኔ ብልሃት ትውልድን ባተሌ ማድረግ ነው ይህ ስልት ከዚህ በፊት ያለፉ አሁንም ያሉ ወደፊትም የሚመጡ አስከፊ አምባገነኖች ሁሉ የሚጠቀሙበት ሃይለኛው መሳሪያቸው ነው። ህዝብን የወሬ ስራ መስጠት ማባተል፣ ህዝብ እንዲምታታ እዚህም እዚያም የተዘበራረቀ መረጃ መልቀቅ፣ የህዝብን የአስተሳሰብ ማእከላዊነት መበጥበጥ፣ በአንድ መረጃ ላይ ህዝብ ወጥ የሆነ አቋም እንዳይይዝና እንዳይፈታተናቸው የመዋከቡን ስራ ለሰፊው ህዝብ መተው በዚህ ሰአት እነሱ ለተንኮላቸውና ለእቅዳቸው መተንፈሻ ጊዜ ስለሚያገኙ የተነሱ ማናቸውንም አይነት አስተሳሰቦችና የለውጥ እንቅስቃሴዎች በእንጭጩ ማፈንን ይችላሉ። 
ስለዚህ እንግዲህ እዚህ ጋር ነው የኔ ፍርሃት ጠዋት ወዳጆቼን ሰላም ሰል አፋችንን የምንከፍተው የበረከት ስምኦን እና የደብረጽዮን ገ\ሚካኤል ቢሮ በፈጠረልን ስራ እንጠመዳለን ሰውየው ሞተ፣ አገርቤት ገባ፣ ከሳ፣ አበጠ፣ ጀርመን ነው ያለው አይደለም ቤልጅየም …. ትክክል ልንነጋገርባቸው ይገባል፣ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት በጀግናው አበበ ገላው ተለኩሶ  እየተቀጣጠለ ያለው የለውጥ እንቅስቃሴ በዝባዝንኪ ብትቶ ወሬ ተጠምደን እድሉ ሊያመልጠን አይገባም እንደውም በምንም መስፈርት እነኝህ የጉዳያችን ዋና አጀንዳ አርእስት ሊሆኑ አይችሉም፣ ወያኔ በተወናበደና በተምታታበት ሰአት በተጠናከረና በተቀናጀ መንገድ ለለውጥ ወደፊት ማየት ይገባናል አሁን ሰአቱ የበለጠ የሚታሰብበትና ብረቱ እንደጋለ የሚቀጠቀጥበት ወቅት ነው።
ስለዚህ በፊት ለፊታችን ሁለት አማራጮች አሉ፣ አንድኛ በአሁኑ ሰአት ወያኔ ያላሰበው ትልቅ ክስረት ገጥሞታል ተምታቶበታል፣ ተርበትብቷል፣ ምንእደሚያረግ ግራ ገብቶታል፣ በትክክል እስከዛሬ ህዝብን እያባተለበት ያለው መንገድ በውስጡ ፈንድቷል ምክንያቱም አስፈሪው የስርአቱ ማእዘን ተመትቶ የማያስፈራ ደረጃ ላይ ደርሷል፣ ስለዚህ አሁን ሕውሓት በቀን ቅዠት ላይ ነው ያለው፣ ራሱ የፈለፈላቸው ብአዴን፣ ደኢሕዴን፣ ኦሕዴድ……. ነገ ምን ሊያረጉ እንደሚችሉ ስለማያውቅ ይፈራቸዋል ምክንያት ብዙ ናቸውና፣ በመቀጠል ሆድ አደር አባላቱን ይፈራል፣ ከመሬት ያፈናቀላቸው ገበሬውን ይፈራል፣ ህዝቡን ይፈራል፣ እራሱን ይፈራን ምክንት የሕውሓት ባህል መበላላትና መጠፋፋት ነውና፣ የውስጥና የውጭ ተቃዋሚዎችን ይፈራል ሲያስባቸው ይንቀጠቀጣል፣
እንግዲህ ውነታው ይህ ነው በተቃራኒው ህዝቡ አዲስ ነገር ይጠብቃል ተስፋም ያደርጋል ለዚህ ሰአት መፍትሄ የሚሆን የለውጥ እርሾ ይፈለጋል፣ አዲስ ራእይ ይዞ ወደዚህ ህዝብ ሄዶ ህዝቡን ወደትግል ለመምራት ከተቃዋሚዎች አንድ መሆንን እና ቁርጠኝነት ይጠበቃል፣ እስከዛሬ ደካማ የተከፋፈሉ እያለ ሲያሾፍና ሲቀልድ የነበረው ወያኔ አሁን ግን ይህ በሽታ ከመቅስፈት አጥቅቶታል ስለዚህ ይህ ታሪካዊ ወቅትና አጋአሚ ድጋሚ እንዳያመልጠን ሁላችንም ልዩነታችንን ወደኻላ ትተን ለአንዴና ለመጨረሻ በህዝባችን ጠላት ላይ እንነሳ፣
ወይም ሁለተኛው ምርጫችን እጃችንን ሰጥተን ወያኔ በሚሰጠን የቤት ስራ እየባተልን ከነሱ ጋር ሆነን የቀጣዩን አልጋወራሽ እንምረጥ፣ እየሰራንላቸውም እኮ ነው፣ ለለውጥ ማሰብ እና መነቃቃት ሲገባን እንቁ የሆነ ጊዜያችንን ሰለ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም ወይም ኃይለማርያም ደሳለኝ አነጋገስ ላይ ስንለፋ እንገኛለ::  
  
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!
ፀሓፊውን ለማግኘት zoloaba112@yahoo.com

No comments:

Post a Comment