Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Saturday, 15 September 2012

አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር ሆኑ: የሕወሓት ሊቀመንበርነት እስካሁን ምርጫ እልተካሄደበትም

Sat Sep 15, 2012 4:19 pm
በዘካርያስ ስንታየሁ

(Reporter) - ባለፈው ዓርብና ቅዳሜ በዝግ የተካሄደው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ስብሰባ የግንባሩን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር በሙሉ ድምፅ በመምረጥ ተጠናቀቀ፡፡

ከአራቱ አባል ድርጅቶች የተውጣጡ 180 አባላት ያሉት የኢሕአዴግ ምክር ቤት አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን በሊቀመንበርነት ሲመርጥ፣ አቶ ደመቀ መኮንን ደግሞ ለምክትል ሊቀመንበርነት ተመርጠዋል፡፡ በድርጅቱ ልምድ መሠረት ሊቀመንበሩ ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ ምክር ቤቱ ሲስማማ፣ ምክትል ሊቀመንበሩም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲሆኑ መወሰኑ ታውቋል፡፡

ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩትን የግንባሩን ሊቀመንበር አቶ መለስ ዜናዊን እንዲተኩ በኢሕአዴግ ሕገ ደንብ መሠረት በምክር ቤቱ አባላት የተመረጡት አቶ ኃይለ ማርያም፣ የደኢሕዴን ሊቀመንበርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን በማገልገል ላይ ነበሩ፡፡ ለግንባሩ ምክትል ሊቀመንበርነት የተመረጡት አቶ ደመቀ የብአዴን ሊቀመንበርና የትምህርት ሚኒስትር ናቸው፡፡

ቅዳሜ ምሽት ላይ በሒልተን ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ በረከት ስምኦንና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕዝብ አደረጃጀትና ተሳትፎ አማካሪ አቶ ሬድዋን ሁሴን እንዳስታወቁት፣ ሦስት ተወዳዳሪዎች ለምክር ቤቱ ቀርበው ሁለቱ ተመርጠዋል፡፡ ቅዳሜ ከቀኑ 10 ሰዓት እስከ ምሽቱ 12፡30 ድረስ በተካሄደው የድርጅቱ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር ምርጫ ሥነ ሥርዓት የቀረቡት ሦስቱም ዕጩዎች በኢሕአዴግ የመተካካት ፖሊሲ መሠረት በትጥቅ ትግሉ ያልነበሩና የአዲሱ ትውልድ አመራር መሆናቸውን አቶ በረከት ገልጸዋል፡፡ የሦስተኛውን ዕጩ ማንነት ግን ለመግለጽ ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡

የኢሕአዴግ ምክር ቤት የመረጣቸው ሁለቱ የግንባሩ ሊቀመናብርት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ፡፡ በዚህ መሠረት አቶ ኃይለ ማርያም የራሳቸውን ካቢኔ የመምረጥ ሙሉ መብት ሲኖራቸው፣ በእሳቸው ተይዞ የነበረውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ቦታም እንደሚሾሙበት አቶ በረከት አስታውቀዋል፡፡ የግንባሩ ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት የአቶ ኃይለ ማርያም ጠቅላይ ሚኒስትርነት በይፋ የሚፀድቀው በመስከረም የመጨረሻ ሳምንት ሥራውን በሚጀምረው ፓርላማ አማካይነት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ሥነ ሥርዓት አሠራሩን ለመጠበቅ እንጂ ድርጅቱ ሙሉ ለሙሉ ሥልጣኑን አፅድቆላቸዋል፡፡ ሁለቱ ተመራጮች እስከሚቀጥለው ምርጫ ድረስ እንደሚቀጥሉ አቶ በረከት ገልጸው፣ ኢሕአዴግ ምርጫውን ካሸነፈም በሥልጣን ላይ እንደሚቆዩ ተናግረዋል፡፡

በአቶ መለስ የተያዘው የሕወሓት ሊቀመንበርነት እስካሁን ምርጫ እንዳልተካሄደበት አቶ በረከት አስረድተው፣ ድርጅቱ ወደፊት በሚያደርገው ምርጫ ተተኪው እንደሚመረጡ አስታውቀዋል፡፡

ኢሕአዴግ ከአንድ በላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮችን ይሾማል ወይ ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ በአሁኑ ወቅት ከአንድ በላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር መሾም ድርጅቱ አስፈላጊ እንዳልሆነ አምኖበታል ብለዋል፡፡ “በአሁኑ ጊዜ ከአንድ በላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር መሾም አልታየንም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይም ኢሕአዴግ የጠራ አቋም አለው፡፡ ሁልጊዜም በኅብረት ሥራ የሚያምን ድርጅት ነው፡፡ በከተማው የሚወራውን ወሬ እንሰማለን፡፡ ኢሕአዴግ ግን በሚወራው ወሬ አይመራም፤” ሲሉ አቶ በረከት አስረድተዋል፡፡ ከአቶ መለስ ሕልፈት በኋላ አቶ ኃይለ ማርያም በተጠባባቂ ጠቅላይ ሚኒስትርነትና በቀድሞው ሹመታቸው ለምን ተጠሩ? አሁንስ ምን ተብለው ይጠራሉ? ተብለው ተጠይቀው፣ “የማዕረጋቸው አጠራር የሚጨምረውና የሚቀንሰው ነገር የለም፡፡ አሁን የሰጠናቸው ኃላፊነት እጅግ ከባድ ነው፡፡ በአቶ መለስ ወንበር ላይ ነው ያስቀመጥናቸው፡፡ እንደ ድርጅት ሥራ ላይ ስለምናተኩር ኢሕአዴግ የሚያስበው የሕዝብን አደራ እንዴት አሳካለሁ የሚለውን ብቻ ነው፤” ብለዋል፡፡

በዕድገትና በትራንስፎርሜሸን ዕቅድ አፈጻጸም ላይ አጭር ግምገማ ያካሄደው ምክር ቤቱ፣ የ2005 ዓ.ም. የትኩረት አቅጣጫዎችን የሚመለከት ሰነድ በመመርመር ውሳኔዎችን ማሳለፉ ታውቋል፡፡

በሁለቱ ቀናት ስብሰባው በድርጅትና በፖለቲካ ሥራዎች ዙሪያ በመምከር መሠረታዊ አቅጣጫዎችን ምክር ቤቱ ማስቀመጡን የገለጸው ኢሕአዴግ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አመራርና በድርጅቱ የተጀመረውን የኢትዮጵያ ህዳሴ ለማስቀጠል መስማማቱን አስታውቋል፡፡ የድርጅቱን የአመራር ግንባታ በተመለከተ በተዘጋጀው ሰነድ ላይ በመወያየት ውሳኔ ማሳለፉም ተገልጿል፡፡

በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ የኢሕአዴግ አጋር ድርጅቶች ሊቀመናብርትና የክልል አስተዳዳሪዎች መገኘታቸው ታውቋል፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም ሐምሌ 12 ቀን 1957 ዓ.ም በደቡብ ክልል ወላይታ ዞን ውስጥ የተወለዱ ሲሆን፣ የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዚያው አካባቢ ተምረዋል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሲቪል ምሕንድስና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ካገኙ በኋላ፣ በአርባ ምንጭ የውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሠርተዋል፡፡ በአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለሁለት ዓመት ከሠሩ በኋላ ፊንላንድ ከሚገኘው ቴምፕር ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ቴክኖሎጂ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በሳኒቴሽን ምሕንድስና አግኝተዋል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ሊቀመንበር ሲሆኑ፣ ከ2002 ብሔራዊ ምርጫ በኋላ የአገሪቷ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲሠሩ ቆይተዋል፡፡

አቶ ደመቀ መኮንን በአማራ ክልል አዊ ዞን ቻግኒ የተወለዱ ሲሆን፣ በአማራ ክልል የአስተዳደርና ፀጥታ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊነት፣ በክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንትነትና በአቅም ግንባታ ቢሮ ኃላፊነት ሠርተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ የትምህርት ሚኒስትር ናቸው፡፡

No comments:

Post a Comment