እውነት
ለመናገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህይወት እያሉ አምባገነን መሆናቸውና በርካታ ጥፋቶችን በዜጎች ላይ መፈፀማቸው ከማንም
የሚሸሸግ አይደለም፡፡ አብዛኛውን ህዝብ ባያስደስትም የተወሰኑ በጎ ተግባራትም ነበሯቸው፡፡ ይሁን እንጂ ከፈፀሟቸው
ጥፋቶች አንፃር በየመንደሩ፣ በየትራንስፖርት አገልግሎቱ፣ በየመስሪያ ቤቱ፣ በየቤተክርስቲያኑና በየመስጊዱ ስለሳቸው
ጥሩ ነገር አይወራም ነበር፡፡ ይሄን ደግሞ ጆሮ ጠቢዎቻቸው ገልብጠው ተቃራኒውን ካልነገሯቸው በስተቀር እርሳቸውም
ያውቁት የነበረ ይመስለኛል፡፡
ለዚህም ነው አንድም ቀን በአዲስ አበባም ሆነ በክልሎች በነፃነት ሳይንቀሳቀሱ ስንቱን
ንጹህ እስር ቤት እንዳላጎሩ እርሳቸውም ራሳቸውን በቤተ መንግስት በፈቃዳቸው አስረው በሞት የተለዩት፡፡ እኚህ ሰው
በነሐሴ 15 ቀን 2004 ዓ.ም መሞታቸው የተነገረው የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ ዜናዊ
ናቸው፡፡
ሞታቸው ሲሰማ ግን በካድሬዎቻቸው ፕሮፖጋንዳ ስንቱ
እንዳዘነላቸው ላየ ምነው ተነስተው ባዩ ያሰኛል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያዝንለትና
የሚያከብረው መሪ አጣ እንጂ በባህሪው ሩህሩህና አዛኝ ነው፡፡ በአቶ መለስ ሞት ይህንን የታዘብኩ ቢሆንም
ከየቀበሌው( ከየወረዳው) እና ከየመስሪያ ቤቱ በግድ ቤተ መንግስትና በተለያዩ የተዘጋጁ ቦታዎች ሄደው ልቅሶ
እንዲደርሱ የተደረጉ የአዲስ አበባና አጎራባች ከተሞች ነዋሪዎችን ላየ ይሄ ሁሉ ህዝብ ይወዳቸው ነበር እንዴ?
ያሰኛል፡፡
ያልተደፈረው ገነት
አዲስ አበባ አራት ኪሎ ያለው የኢትዮጵያ ታላቁ ቤተ
መንግስት ለዜጎች “ያልተደፈረ ገነት ነው” ይባላል፡፡ አንዳንድ ሰዎች የዚህን ምክንያት ሲገልፁ አዳም እጸ – በለስ
በልቶ ከገነት ሲባረር፤ የኢትዮጵያ ታላቁ ቤተ መንግስት ለመግባት ግን ያቺን፣ እፀ በለስ መብላት ግድ ይላል
ይላሉ፡፡ ምክንያቱም በሀገራችን ቤተመንግስት ገብቶ ስልጣን ላይ ያለ እስካሁን በህዝቡ መሃል በነፃነት ተንቀሳቅሶ
እንደተወደደ ከስልጣን የወረደ የለምና፡፡ በአሁን ሰዓት ደግሞ ማንም ሰው ለመሞትና መከራ ለመቀበል እፀ በለስ
የሚበላ የለምና፡፡ በዚህም ያልተደፈረው ገነት ተደፈረ፤ ስንቶች በአጠገቡ ሲያልፉ እንኳ ፊታቸውን ወደግቢው
እንዳያዞሩ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸው እንዳልነበረ ሁሉ ዛሬ በአቶ መለስ ዜናዊ ሞት በሰልፍ ተጎበኘ፡፡ በዚህም
ሞተው ዴሞክራት የሆኑ ይመስላል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሞት ተከትሎ ዘመድ ወዳጆቻቸውና
አድናቂዎቻቸው ሀዘናቸውን እንዲገልፁ ያ በአስፈሪ ድባብና በለመለሙ ዕፅዋቶች የተሞላው ቤተ መንግስት ክፍት ሆነ፡፡
ተገዶ የመጣውና ከልቡ ሀዘን ተሰምቶት በፈቃዱ የመጣ ሰው ሁሉ ተሰልፎ መግባት ጀመረ፡፡ አንዳንዶች ደግሞ የኢትዮጵያ
መሪዎች ገብተው በፈቃዳቸው “በቃኝ” ብለው የማይወጡት ለምንድን ነው? በሚል በዚህ አጋጣሚ ቤተ መንግስቱን
ለመጎብኘት የተሰለፉም አሉ፡፡ እኔም ብሆን ከዚህኛው ጎራ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀዘኔን ለመግለጽ
ቤተ መንግስት መሄድ አይጠበቅብኝምና፡፡ እኔም ከተፈቀዱት ቀናት መካከል ባንዱ ታላቁን ቤተ መንግስት በጥቂቱ
ጎበኘሁት፡፡
ቤተመንግስት ገብቶ ሀዘኑን መግለጽ የሚፈልግም ሆነ
አጋጣሚውን ተጠቅሞ መጎብኘት የሚፈልግ ሰው መግቢያው በፓርላማው ጀርባ ባለው ግዙፍ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ጎን
ባለው አዳራሽ ሲሆን ሰልፉም በአርበኞች ህንጻ ፊት ለፊት የፓርላማው አጥር ጥግና ጀርባ ነበር፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ
ጽ/ቤት አዳራሽ እንደተገባም ሙሉ ጥቁር የለበሱ አስተናጋጆች ቦታ ይመራዎትና ይቀመጣሉ፡፡ ያኔ ከልቡ ያዘነ
የ”መጥቻለሁ” ልቅሶ ድምጽ ሲያሰማ ሌላው በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ስለእርሳቸው የተሰራውን “በጎ ጎን” ብቻ
የሚያመላክት ዘጋቢ ፊልም ያደምጣል፣ ይመለከታል፡፡ ቀሪው ደግሞ የአዳራሹን አሰራርና የሰውን ሁኔታ ይታዘባል፡፡
አንድ ሶስት ደቂቃ ያህል ከተቀመጡ በኋላ አስከሬናቸው
ወዳረፈበት “መኖሪያ ቤታቸው ወደነበረው” ቤተ መንግስት ግቢ ሁለተኛ አጥር ወደ ባህታና ግቢ ገብርኤል የተጠጋ ስፍራ
ተሰልፈው ይሄዳሉ፡፡ በቤተ መንግስቱ ግቢ ውስጥም እሳቸውን የሚያወድሱ ፅሑፎች ያሉባቸው በርካታ ፎቶዎቻቸው
ተለጥፈዋል፡፡
የአቶ መለስና ቤተሰቦቻቸው መኖሪያ ቤት ወደሆነውና
አስከሬናቸው ወዳረፈበት ስፍራ ሲሄዱ የቤተ መንግስ 3ኛ ግቢ በስተግራ በኩል በረጃጅም ቆርቆሮ ታጥሮ ይገኛል፡፡ እዛ
ግቢ ውስጥ ግዙፍ ያላለቀ የመኖሪያ ቤት ህንጻ ይታያል፡፡ ይሄንን ሳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞት ባይቀድማቸው ኖሮ
ስልጣን የመልቀቅ ፍላጎት እንደሌላቸውና፣ ከፈጣሪና መላዕከ ሞት ጋር ሳይነጋገሩ ለረጅም ዓመታት ቤተ መንግስት ግቢ
ውስጥ ለመኖር ያሰቡ ይመስላል፡፡ በዚህ ጊዜ የቅርጫ ምርጫን እያስታወስኩ የቀድሞ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኮ/ል
መንግስቱ ኃ/ማርያም የአጼ ኃይለስላሴ መኖሪያ የነበረ ውስጥ (3ኛው ግቢ) መኖር ባለመፈለጋቸው የምታምር የኤም
(M) ቅርፅ ያላት ባለ አንድ ፎቅ ያሰሩት መኖሪያ ቤት እንደሆነ የሚነገርለት ጋር ደረስን፡፡
ተሰልፈው የመኖሪያ ቤታቸው በረንዳ ሲደርሱ በስተግራ
መለስተኛ ድንኳን ተጥሎ ባለቤታቸው ወ/ሮ አዜብ መስፍን፣ ልጆቻቸው፣ የቅርብ የሥጋ ዘመዶቻቸውና አቶ ኃ/ማርያም
ደሳለኝን ጨምሮ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ተቀምጠዋል፡፡ አብዛኛውን ባለስልጣን ሲያዩ ‹‹በሀገሪቱ ሥራ የለም
እንዴ?›› ያስብላል፡፡
አስከሬናቸው የተቀመጠበት በረንዳ ከደረሱ በኋላ ሳይቀመጡ
እንደተሰለፉ በአሰተናጋጆች ወደቀኝ ይታጠፉና ከግቢ ይወጣሉ፡፡ ከፊት ለፊትዎ የኢቴቪና ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል
የካሜራ ባለሞያዎች ፊት ለፊትዎ እንደ አፈሙዝ ካሜራ ደቅነው ይጠብቆታል፡፡ ምክንያቱም ለፕሮፓጋንዳ ማድመቂያ
ያስፈልጋሉና፡፡ በጣም የሚገርመው በግምት እድሜው ከ4 ዓመት የማይበልጥ ህፃን ስለ አቶ መለስ ሞት የተሰማውን ሀዘን
እንዲገልፅ በጋዜጠኞች ሲጠየቅ እናትየው “እንዲህ በል” ብላ ስታስጨንቀው ማይክራፎን የተሰጠው ህፃን ሲደናገጥ
ለማየት በመቻሌ ገርሞኛል፡፡ ያ ህፃን እንኳን ስለማያውቃቸው አቶ መለስ ቀርቶ ስለወላጆቹም ሆነ ስለራሱ መግፅ
ይችላል ተብሎ አይታሰብም፡፡ ታዲያ ምን የሚሉት ፕሮፓጋዳ ይሆን? እኔ ግን የህፃኑ ጭንቀት አሁንም ድረስ
ያስጨንቀኛል፡፡
ያልተደፈረው ገነት በአቶ መለስ ሞት በብዙ ዜጎች
መጎብኘቱ ምናለ የህዝቡን ጨዋነት ተነስተው ቢያዩ ያስብላል፡፡ ምክንያቱም በህይወት እያሉ እንኳን ታላቁ ቤተ
መንግስት ቀርቶ ከባህር ማዶ ጉዞ ሲያደርጉ መንገዶች እንዴት ከሰዎችና ሌሎች ተሽከርካሪዎች እንደሚፀዳ የደረሰበት
ያውቀዋል፡፡ዛሬ ግን ሞተው ዴሞክራት መሪ መሆን ችለዋል፤በህይወት ላሉ ዜጎች ባይጠቅምም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በህይወት እያሉ ያላመኑትን የኢትዮጵያን
ህዝብ ጨዋነት ሞተው ማመናቸው አንገታቸውን አቀርቅረው ላየኋቸው ተተኪው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝና
ግብረ አበሮቻቸው ትምህርት የሚሰጥ የቤት ሥራ ይመስለኛል፡፡
የሥራ ዕድል
አቶ መለስ በህይወት እያሉ ለቻይናውያን ፣ ለህንዳውያን
በኢትዮጵያ የስራ ዕድል መፍጠራቸው አይዘነጋም፡፡ ለተማሩ ዜጎች ደግሞ በኮብል ስቶን ድንጋይ ጠረባም ቢሆን የስራ
ዕድል እንዲፈጠር ማድረጋቸው በተደጋጋሚ መነገሩ ይታወሳል፡፡
ሰሞኑን ከሞቱ በኋላ በርካታ የስራ እድል የፈጠሩ ሲሆን
ይህም የተለያዩ ፎቶግራፎቻቸው ለደጋፊዎቻቸው ከአንድ ብር እስከ አስር ብር እንዲቸበቸብ አድርገዋል፡፡ በዚህም ሥራ
አጥ ወጣቶች ለጊዜውም ቢሆን ለዕለት ጉርስ የሚሆን የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡ ሌላው የልብስ መደብሮች ጥቁር
ልብሶችን ለ‹‹ሀዘን›› በሚል ባልተለመደ ሁኔታ እንዲለበስ ተደርጓል፡፡ በዚህም የተዘጋጁ ልብስ ሻጮች እስከ ቀብር
ስነ ስርዓታቸው ድረስ ይሸጣል በሚል በሱቆቻቸው ውስጥ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፎቶ ያለበትን ጥቁር ካናቴራን ሰቅለው ላየ
የሀገራችን የንግድ ስራ ሁሌ በመልካም ነገር ሆኖ እንዲህ ቢቀላጠፍ ያሰኛል፡፡
ሌላው ተሽከርካሪዎች ከየመስሪያ ቤቱ በግድ ለቅሶ እንዲደርሱ በአለቆቻቸው የኮንትራት መኪና እንዲዘጋጅ በመደረጉ እና የተለያዩ ወጣቶች በአስተናጋጅነት እንዲያገለግሉ ማድረግ ተችሏል፡፡
የሚገርመው ግን በኢቴቪ የኢህአዴግ ተሻDሚዎችና ጋሻ
ጃግሬዎች “የጠቅላይ ሚኒስትሩን ራዕይ እናሳካለን” የሚል መፈክር ቢያሰሙም አንዳንድ መስሪያ ቤቶች ግን በልቅሶ
ሰበብና ስም የዓመት ፈቃድ የወጡ ይመስል ከመደበኛ ስራቸው የጠፉ በርካቶች እንደሆኑ እየተነገረ ይገኛል፡፡ በዚህ
ደግሞ ሀገሪቱ ኪሳራዎችንና የጊዜ ብክነቶችን እንድናስተናግድ አስችሏታል፡፡ ለማንኛውም ለቤተሰቦቻቸውና ለወዳጅ
ዘመዶቻቸው ፈጣሪ መፅናናትን እንዲሰጣቸው እመኛለሁ፡፡
No comments:
Post a Comment