Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Wednesday 12 September 2012

የመርዶው ሕዝባዊ ምላሽ – ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ

Dr. Dagagnachewየዚህ ጽሑፍ ዋና ቅጂ  በኢትዮጵያ እንዳይነበብ በታገደው የዞንዘጠኝብሎግ ላይ ይገኛል፡፡እኛም ለጋዜጣ በሚመች መልኩ አሰናድተነዋል
የዞን ዘጠኝ ጦማር ጽሁፉን የሚጀምረው በዚህ መልኩ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ የፍልሰፍና መምህርና ከጥቂት የአደባባይ ምሁራን አንዱ የሆነውን ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋን አነጋግረን ስለወቅቱ ማሕበራዊ እና ፖለቲካዊ ጉዳዮች የተለያዩ  ሐሳቦችን ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ አሁን ደግሞ የአቶ መለስን ‘ድንገተኛ!?’ ሞት  ተከትሎ በድኅረ-መለስ  አትዮጵያና በሌሎች ተያያዥ ጉዳየች ዙሪያ እንደተለመደው ገዢ ሐሳቦቹን ሰጥቶናል፡፡ መልካም ንባብ
የመርዶው ሕዝባዊ ምላሽ
እንደሚታወቀው ለሀያ አንድ ዓመታት በሙሉ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥኑን መስኮት አጣበው  የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ናቸው፡፡ እንዲሁም በከፍተኛ ሁኔታ ተክለ ስብዕናቸውና ስራቸው በሚዲያው ሲገነባላቸው ከቆዩ በኋላ የጠቅላይ ሚኒስተሩን ድንገተኛ  ህልፈተ ህይወት ህዝቡ ሲሰማ  ድንጋጤና ሀዘን ተፈጥሮበታል፡፡ ይህንንም የህዝብ  ሀዘን በሁለት አቅጣጫ ልናየው እንችላለን፡፡ የመጀመሪያው አስከሬናቸው ከውጭ ሀገር በገባበት ምሽት ከተጠበቀው በላይ ህዝብ ወጥቶ ብሶቱንና ሀዘኑን የገለፀበት ነው፡፡ ምናልባትም ህዝብ ላሳየው የሐዘን ጎርፍ አንድ ወሳኝ የሆነ ነገር መገንዘብ የምንችለው ህዝቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ፓርቲው ከሚያራምደው የጎሳና የነገድ ፖለቲካ ውጪ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊና እንደግለሰብ አይቶ እንዳዘነላቸው ለመረዳት አያስቸግርም፡፡ በተጨማሪም  እሳቸው በህይወት እያሉ ለያይተው ያዩት ህዝብ ሲሞቱ ግን እርስ በርስ ሳይለያይ በህይወት እያሉ ያላያያዙትን ህዝብ በሞታቸው ሊያያይዙት ችለዋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ እየተመለከትን ያለነው ኢህአዴጎች የህዝቡን ስሜት ለፖለቲካ ግብአታቸው ለመጠቀም ስትራቴጂ ነድፈው፣ በተደራጀ መልኩ እንቅሰቃሴ ውስጥ መግባታቸውን ነው፡፡ ከዚህም አኳያ መንግስት ሊያደርግ የሚፈልገው አቶ መለስ ኖሩም አልኖሩም ህዝቡ የስርዐቱን መቀጠል እንደፈለገና ተቀባይነትም እንዲኖረው ማድረግ ነው፡፡ ይህንንም ለመተግበር በብሔራዊ የቀብር ስነ ስርዓት አስፈጻሚው ኮሚቴ ስም የህዝቡን ስሜት ወደፈለጉት አቅጣጫ ተቆጣጥረው ለማዞር በሚያስችል መልኩ እየተሰራ መሆኑን ነው፡፡ በመሆኑም መልስ አዘል ጥያቄ በማቅረብ ህዝቡ እንዲናገር በማድረግ፣ በየሰፈሩ ድንኳን በመትከል፣ በካድሬዎች አማካኝነት በየመስሪያ ቤቱ መመሪያ በመስጠት ወዘተ… የህዝቡን ስሜት ለፖለቲካ ግብዐት እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡ ለማጠቃለልም ብዙ ሐዘንተኞች የተጀመረው ፕሮጀክት ከፍፃሜ  እንዲደርስ በርግጥ ቢጠይቁም የመንግስት ኮሚቴ እንደተመኘው  የኢሕአዴግን ስርዓት ቅጥያ ሲጠይቁ አልተደመጡም፡፡ ምን አልባትም ህዝቡ በፕሮጀክትና በስርዐት መካከል ያለውን ልዩነት የተረዳ ይመስላል፡፡
የስልጣን ሽግግር
የድኅረ መለስ መንግስት ምን ዓይነት የፖለቲካ መንገድ እንደሚይዝ ከመተንተናችን በፊት  ወደኋላ መለስ ብለን ከቅርብ ታሪካችንና ከፖለቲካ አንጻር ጥቂት እንበል፡፡
. ከታሪክ ማህደር
በዶ/ር ሌቪንን “Wax and Gold” የተሰኘው መጽሐፍ ገጽ 152 ላይ  እንዲህ ይላል፡፡
“Successors to the throne were not determined according to fixed rule like primogeniture. Membership in the Solomonian line was normally a prerequisite……Usually however there were several legitimate candidates for the position and the absence of fixed procedures for choosing among the meant that the death of an emperor was often a time of confusion and political improvisation.” 
የመንበሩ ወራሾች በተደነገገ ቋሚ መመሪያ አልነበረም የሚወሰኑት፡፡ በሰለሞናዊ ስርወ መንግስት መስመር ውስጥ አባል መሆን በጥቅሉ እንደቅድመ ሁኔታ የተቀመጠ ነውበተለምዶ፣ ምንም እንኳን ቦታውን የሚመጥኑ ብዙ ሕጋዊ (ሰለሞናዊ) እጩዎች ቢኖሩም፣ አንዱን ለመምረጥ የሚያስችል ውሱን መስፈርት ባለመኖሩ የንጉሠ ነገሥት ሞት ሁልጊዜም ውዥንብር እና ፖለቲካዊ ጥበብን ይጠይቃል፡፡” (ትርጉም የዞን ዘጠኝ)
በኢትዮጵያ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ሰላማዊና ሕጋዊ የሆነ የስልጣን ሽግግር በአብዛኛው ተካሄዶ አያውቅም፡፡ እንደ ዕውቁ ሶሾሎጂስት አገላለጽ ይህም የሆነበት ምክንያት፡-
  •   አንደኛ የስልጣን ሽግግር ህጉ በደንብ አለመቀመጡ፣
  •  ሁለተኛ ስልጣን ለመያዝ (ዘውድ ለመጫን)  የሰለሞናዊ ስርወ-መንግስት የግዴታ ተወላጅ  መሆንና፣
  •   በአንድ ጊዜ  ከሰለሞናዊው ስርወ መንግስት ተወላጅ የሚሆኑ ብዙ ተወዳዳሪዎች ለቦታው ብቁ ሆነው መገኘታቸው ነው፤
  • በመሆኑም ወደ ኢህአዴግ ዘወር በምንልበት ጊዜ ከላይ የጠቀስናቸውን ታሪካዊ ክፍተቶች ዛሬም እንደትላንቱ ኢህአዴግም በዘረጋው ስርዓት አልተሻገራቸውም፡፡ ይህንንም የምንለው በሕገ መንግስቱ በግልጽ የሰፈረ   ቋሚ የስልጣን ሽግግር ህግ በለመኖሩ ጭምር ነው ፡፡ በተጨማሪም ትላንት ዘውድ ለመጫን የሰለሞናዊው የዘር ሀረግ አስፈላጊ እንደነበረው አሁን ደግሞ ስልጣን ለመጨበጥ የኢህአዴግ አመራር መሆን የግድ ነው፡፡ በመሆኑም ለሰለሞናዊው የሽግግር ጥያቄም ሆነ ለአሁኑ ጊዜ በርካታ ተቀራራቢ ዕጩዎች ወይም ተወዳዳሪዎች መኖራቸው ሽግግሩን ውስብስብና አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡
. ከፓለቲካ ዳራ  አሁን ለተነሳው የሽግግር ጥያቄ መልስ ለማግኘት የጠቅላይ  ሚኒስቴር መለስ ዜናዊ አመራር ምን አይነት  መልክ የያዘ ነበር የሚለውን ማወቅ ይገባናል፤ ምክንያቱም በየትኛውም የዓለማችን ክፍል እንደሚታየው የስርዓቱ ዲሞክራሲያዊ ወይንም ኢ-ዲሞክራሲያዊ መሆን  በስልጣን ሽግግሩም ላይ ወሳኝ ሚና ይጫወታል፡፡ ምንአልባት ይህንን ሐሳብ የበለጠ ለማብራራት የሀኛያው ክፍለ ዘመን የፓለቲካ ፍልስፍና መምህርት ከነበረችው ሐና አረንት  (Hanna Arendt) ትንሸ እንውሰድ፡፡እንደ ሐና አረንት አመለካከት የዴሞክራሲያዊ ስርዓት አገዛዝ የ’ስልጣን መርህ’ (authority principle) ሲከተል  ኢ-ዲሞክራሲያዊ አገዛዝ በአንጻሩ ደግሞ በ’መሪ መርህ’ (leadership principle) ይተዳደራል፡፡ በ’ስልጣን መርሕ’ የስልጣን ተዋረዱና ክፍፍሉ  በሀገሪቱ ህግ በዝርዝርና በግልጽ ተለይቶ ይቀመጣል፡፡ በሌላ በኩል በ’መሪ መርሕ’  የሚተዳደሩ ሀገሮች  ይህን በተመለከተ የስልጣን ተዋረድ የላቸውም፡፡ ስልጣኑ ተጠቃሎ በመሪው እጅ ይገኛል፡፡ ከመሪው ቀጥሎ ሁለተኛ የሚባል ለይስሙላ ይቀመጣል እንጂ መሪው አንድ ነገር ቢሆን በሁለተኛ ደረጃ የተሰየመው ሰው ይተካዋል ማለት አይደለም፡፡ ለማጠቃለል የሀና አረንት አቀራረብ የሚያስተምረን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ማለት ከ’መሪ መርህ’ ወደ ‘ስልጣን መርህ’ መሸጋገር  ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሕገ መንግስታዊ ሰርዓት ሲዘረጋ ይህ ታስቦ ቢሆንም የዲሞክሪያሲያችን ጨቅላነት የመሪዉን ጫንቃ መሸከም ስላቃታት ዴሞክራሲው በአጭሩ ተቀጭቶ በ’መሪ መርህ’ ለመመራት በቅተናል፡፡
ድኅረ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያ (Post; Capital ‘P’ or Small ‘p’)
የእንግሊዘኛውን ‘post’ የሚለውን ቃል ለሁለት ከፍለን ብንመለከተው ለትንተናችን ያመቸናል፡፡  ካፒታል ‘ፒ’ እና ስሞል ‘ፒ’ ብለን እንከፍለዋለን፡፡ ካፒታል ‘ፒ’ ተጠቅመን ድኅረ (Post) ስንል consequential መሰረታዊ የለውጥ ሂደቶችን  ያካተተ ማለት ሲሆን ባንፃሩ ደግሞ ስሞል ‘ፒ’  ስንጠቀም መሰረታዊ ያልሆነና ፋይዳ ያለው ለውጥና ሽግግር የማይታይበት ሆኖ እናገኛዋለን፡፡  ለምሳሌ በአረብ ሀገራት በቅርቡ የተነሳው አብዮት  መሰረታዊ የስርዓት ለውጥ ስላስከተለ ካፒታል ‘ፒ’   ነው፡፡ በሌላ በኩል  ከአንዋር ሳዳት ወደ  ሙባረክ  የነበረው ሽግግር ግን ምንም ዓይነት የስርዓት ለውጥ ስላልታየበት  ስሞል ‘ፒ’  ነው፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ከላይ በትንሹ ልንጠቅሰው እንዳሰብነው አሁን አመራር ላይ ያሉት ባለስልጣናት የድኅረ መለስን ስርዓት እንዳለ እንዲቀጥልና ሽግግሩም ስሞል ፒ’  እንዲሆን ይፈልጋሉ፡፡ ለዚህም ነው አስቀድመው “የፓርላማ አባላቱን በአስቸኳይ ሰብስበን አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ከጊዜያዊ ጠቅላይ ሚኒስቴርነት  ወደ ቋሚ ጠቅላይ ሚኒስቴርነት እንለውጣለን” የሚል ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት፡፡መንግስት እንዳሰበው የስርዓቱ ሕልውና በምንም መልኩ ጥያቄ ውስጥ የገባ እንዳልሆነ በየጊዜው የሚነግረን ቢሆንም ብዙ የአደጋ ቀጠናዎች እንዳሉ ግን እየተገነዘብን ከላይ ወደ አነሳነው  ወደ  አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ መመረጥ ፖለቲካ አንድምታ ላይ እንመለስ፡፡በአቶ ኃይለማርያም ምርጫ ዙሪያ ሁለት ጥያቄዎች ማንሳት እንችላለን፡፡ አንደኛ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ የኢህአዴግ መሪዎች ‘የስልጣናችን ምንጭ (legitimacy) የሚፈልቀው በትጥቅ ትግሉ ውስጥ በከፈልነው መስዋዕትነት’  ሲሉ ቆይተው በዚህ ጎዳና ያላለፈ ሰው መምረጣቸው፤ ሁለተኛ  ደግሞ ሌሎች አንጋፋ ፓርቲዎች እያሉ ኢህአዴግ አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ የተመሰረተ ፓርቲ አባል መሆናቸው ስለሳቸው ሳይሆን በግንባሩ የፖለቲካ ህይወት  ወሳኝ  ሚናን ስለሚጫወቱት አካሎች የሚነግረን ነገር አለ፡፡ይህንን ለመረዳት ከሁለት ዓመት በፊት ከኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር መካከል አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንዴት የምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርነትን ሹመት እንዳገኙ ማስታወስ ይገባናል፡፡ በዚህ ወቅት ፓርቲው  በመተካካት ጥያቄ እና በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ጤና መቃወስ ምክንያት ተወጥሮ ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ በጣም የሚያስገርመውና የሚያስደምመው የህወሓት ልሂቃን ሁለት አማራጭ ይዘው ቀረቡ፡፡ አንደኛ በአገሪቱ ላይ ዴሞክራሲ እንዳይቀጭጭ ከተፈለገና እኛ የምንወክለው የሕዝብ ቁጥር አነስተኛ ስለሆነ የጠቅላይ ሚኒስቴሩን ቦታ  ከብአዴንና ኦህዴድ ብንመርጥ የግንባራችንን የኃይል ሚዛን ስለሚያዛባው  በኛ በኩል ተቀባይነት የለውም የሚል ሐሳብ አቀረቡ፡፡ ሁለተኛ የጠቅላይ ሚኒስቴሩን ጽ/ቤት ለሦስት ወይንም ለሁለት በመክፈል የስልጣን ክምችቱን (premiership ) ብናሰራጨው የተሻለ ይሆናል አሉ፡፡ በመሆኑም የመጀመሪያው ሐሳብ በግንባሩ ተቀባይነት በማግኘቱ ከሁለቱ ብዙኃን ፓርቲ ውጪ የሆነ ሰው በምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርነት ለመምረጥ በቅተዋል፡፡  ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ ሀገሪቱን ለሌሎች ስጋቶች ስለሚያጋልጣት ተቀባይነት አላገኘም፡፡
አሁን ለጊዜው የሀገሪቱ የፖለቲካ አቅጣጫ ወይም የሽግግር ሁኔታ ካፒታል ‘ፒ’ ወይንም ስሞል ‘ፒ’ ይሆናል ለማለት አስቸጋሪ ቢሆንም በዚህ ጉዳይ ላይ ተጽእኖ የሚፈጥሩ አራት ዐበይት  ወቅታዊ ጉዳዮች አሉ፡፡
ከአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የፖለቲካ ደረጃ አጠያያቂነት በራሳቸው አመራር እንዳይሄዱ ሰርዓቱ የማይፈቅድላቸው በመሆኑ፣
  1. በኦሮሚያ ክልል ፕሬዘዳንት አቶ አለማየሁ አቶምሳ  መታመም  ክፍተት በመፈጠሩ እና ከዚህም ጋር ተያይዞ የሚነሳው ውዝግብ፣
  2. በኢትዮጵያ ሙስሊሞችና በመንግስት መካከል የተነሳው ውዝግብ እልባት አለማግኘቱ፣
  3. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክን ህልፈት ተከትሎ ቀጣዩን ፓትርያርክ የመምረጥ ሂደት
መደምደሚያ
እንደሚታወቀው ኢህአዴግን የሚያዋቅሩት የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉም እኩል  ናቸው ቢባልም በኦርዌሊያን (George Orwell) አነጋገር “ሁሉም ፓርቲዎች እኩል ናቸው አንዳንድ ፓርቲዎች ግን የበለጠ እኩል ናቸው” እንዳለው ልክ ከጠቅላይ ሚኒሰቴር ጽ/ቤት ባላነሰ የህወሓት ሊቀመንበር ቦታ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ህይወት ላይ ወሳኝ ሚና እንደሚኖረው አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይሄ ፓርቲ የበላይነቱንና የገዢ ስፍራውን ለረጅም ጊዜ ማስቀጠል ይፈልጋል፡፡ ይሄንን ለመተግበር አሁን ለማደረግ እንደተፈለገው  ከሌላ (ማለትም ብዙኃን ቁጥር ከሌለው) ፓርቲ በመሾም አሊያም ከራሱ ፓርቲ ሰው መልምሎ በማቅረብ በምንም መልኩ የስልጣን ባለቤትነቱን ለማረጋገጥ ይፈልጋል፡፡

No comments:

Post a Comment