ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ለፍርድ ቢቀርቡ ኢትዮጵያ ቀን ወጣላት
ብዬ አምን ነበር፡፡ የግብፅ ፕሬዘዳንት የነበሩት ሆስኒ ሙባረክ እስከዛሬ ፍርድ ቤት እየተመላለሱ የሚገኙት በ180
ሰዎች ግድያ ተጠያቂ ናቸው በሚል ተከሰው ነው፡፡ እኛም አገር በ1997 ዓ.ም በተደረገው ምርጫ ምክንያት በተፈጠረው
ቀውስ መንግስት ራሱ ባመነው መሠረት የ200 ሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ በእውነት የሕግ የበላይነት ሰፍኖ ቢሆን ኖሮ
አቶ መለስ በእነዚህ ሰዎች ግድያ ብቻ ፍትሕ አደባባይ በቆሙ ነበር፡፡ ሕጉ ቢፈርድባቸው ወይም ነፃ ቢለቃቸው
እንዴት ደስ በተሰኘሁ፡፡ ምክንያቱም የእኔ ዋናው የደስታዬ ምንጭ የሕግ የበላይነት በአገሬ ተከብሮ ማየት ነው፡፡
ገና በጠዋቱ ጠ/ሚኒስትሩ ታመሙ ሲባል ነበር የፈራሁት፡፡
ከወዳጆቼ ጋር ተቀምጠን ስንጫወት “እኔ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሞቱ በጣም ነው የምናደደው፡፡ በሕይወት ኖረው በፍትሕ
አደባባይ እንዳያቸው እናፍቃለሁ ያኔ አገሬ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደተሻገረች አምናለሁ፡፡ መሪዋን በሕግ መዳኘት
ችላለችና” የዘንባባ ዝንጣፊ ነበር ያልኩት፡፡ ግና የፈራሁት አልቀረም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሞቱ፡፡
ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል የዘንባባ ዝንጣፊ ይዘው ለተቃውሞ
አደባባይ በወጡ ልጆች ላይ ታንክ በማሰማራት በአልሞ ተኳሾች ሕይወታቸው የተነጠቀውን የአገሬ ታዳጊዎችና አባወራዎች
ደም ዛሬም ከምድር ወደ ሰማይ ይጮሀል፤ የፍትህ ያለህ ይላል፡፡ የተከበሩ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ለአዲስ ጉዳይ መፅሄት
በነሐሴ 19 እትም በሰጡት ምላሽ ያንን መራራ ወቅት እንዲህ ነበር ዕንባ እየተናነቃቸው የገለፁት፡፡ “እሳቸውን
ሳስታውስ በ1997 የሞቱትን ሰዎች አስታውሳለሁ፡፡ እኔ እንግዲህ ኦሮሞ እንደመሆኔ የመጣሁበትን ሀገርና ሰዎችን ነው
የማስታውሰው፡፡ በ97 በወለጋ ጦርነት ነው የተከፈተው፡፡ ይህንን ሁሉም ሰው ያውቃል፡፡ በዚህም ብዙ ሰዎች
ሞተዋል፡፡ ብዙ ሰዎች አዝመራቸው ተቃጥሎባቸዋል፡፡ የሚበሉት ምግብ እንኳ አልነበራቸውም፡፡ የእኛ ፓርቲ መኪናዎችን
ተከራይቶ ቦታው ድረስ በመጓዝ ነው ምግብ ያደረሰንላቸው፡፡ ምናልባት ዳቦና ሻይ ከማግኘታቸው ውጭ ፊታቸው አሳዛኝ
ገፅታ ለብሶ ነበር፡፡ አሁን የምናገረው ስለማውቃቸው ስለ ኦሮሞ ህዝቦች ነው እንጂ ሌሎች ክልሎችም የዚህ ገፈት
ቀማሽ እንደነበሩ ሰምቻለሁ፡፡ በ1997 ዓ.ም የደረሰው መጉላላት ስቃይ እስራትና ሞትን መርሳት አልችልም፤ እስከ
ዕለተ ሞቴ፡፡ አንዳንድ ፈረንጆች ውስጣችንን በደንብ የሚያውቁ ስለ ጠ/ሚኒስትሩ መልካም ነገር ሲናገሩ ላዳምጥ
አልቻልኩም፡፡ ፓርቲዬም አልቻለም፤ ኦሮሞዎችም አልቻሉም፤ ይህንን ስል ዕንባ እየተናነቀኝ ነው” በማለት ነበር የልብ
ስብራታቸውን የገለፁት፡፡
ይህ እንግዲህ ለናሙና የቀረበ ምሳሌ ሆኖ እንጂ ጠ/ሚኒስትሩ
ሕግፊት የሚቆሙበትና የሚጠየቁበት ሌሎች ግዙፍ ጉዳዮች ሳይኖሩ ቀርተው አይደለም፡፡ ግን ሌሎቹን ሁሉ ለጊዜው ትቼ
ቢያንስ በዚህ ብቻ እንኳ እንደ ሆስኒ ሙባረክ በፍትሕ ሊዳኙ በተገባ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፤ ምክንያቱም አገሪቱ
ኢትዮጵያ ስለሆነች ነዋ፡፡
በዘር ላይ የተመሠረተውን ሥርዓታቸውን ትቼ፣ በኢትዮ ኤርትራ
ጦርነት በከንቱ ደማቸው የፈሰሰውን ዜጎች ህይወት ሳላነሳ፣ የበደኖውንና የጋምቤላውን እልቂት ዝም ብዬ፣ በሚሊዮን
የሚቆጠሩ ሕዝቦች በርሀብ በሚማቅቁባት አገር ጥቂት ግለሰቦች ግን ኢኮኖሚውን ተቆጣጥረው የአገሪቱን ሀብት
መቀራመታቸውን ችላ ብዬ፣ ከእውቀት ይልቅ በፖለቲካ ታማኝነት ላይ የተገነባውን መንግስታቸውን አልፌ፣ በሰብአዊ መብት
ጥሰትና የፕሬስ ነፃነትን በማፈን ተጠያቂ መሆናቸውን ሳልጽፍ የፍትህ አካላትን እንዳሻቸው በመዘወር ሕግ ማለት
እሳቸው እስኪመስሉ ድረስ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትንና ጋዜጠኞችን ወደ ስደትና ወደ እስር ቤት መወርወራቸውን
ሳልጠቅስ፣ አቶ መለስ በአደባባይ አምነው በተቀበሉት የ200 ሰዎች ግድያ ብቻ እንኳ ፍርድ ቤት ቢቆሙ ምንኛ ታላቅ
ደስታ ነበር፡፡ አገሬ ኢትዮጵያ መሪም ሆነ ተመሪ ከሕግ በታች ሲውሉ አይታ ቢሆን ኖሮ ምንኛ ሐሴት ባደረገች ምንኛ
እንደ ሰባ እምቦሳ በዘለለች፣ ምንኛ በደስታ እንባ በታጠበች ነበር፡፡
ክቡር ጠ/ሚኒስትሩ በሞት ምክንያት ከፍርድ በማምለጣቸው ዕድለኛ
ናቸው ሊባል ይችል ይሆናል፤ አገሪቱ ግን እድለኛ ልትባል አትችልም፡፡ አምባገነን መሪዋን በሕግ የምትዳኝበት እድሏን
አጥታለችና ነው፡፡ ይገርማል እግዚአብሄርም ያበረ ይመስል፤ በሕግ እንዳንጠይቃቸው ወደ ራሱ ሰበሰባቸው፡፡ ምን
ይደረግ እሱን አንጠይቀው ነገር ‹እኔን ለምን እንዲህ አደረግህ ብሎ የሚጠይቀኝ ማነው?› ሲል መልሶ ይጠይቀናል፡፡
እግዝአብሔርን በመጠየቅ የሚገኘው መልስ ጥያቄ ነው፡፡
የጠ/ሚኒስትሩ አስክሬን ወደ አገር ሲገባና ልጆቻቸውን ስመለከት
ዕንባ ተናንቆኛል አንዳች የማላውቀው ስሜት ወሮኛል፤ እኚህ አስፈሪ መሪ ለልጆቻቸው ግን የሚሳሱ አባት ናቸው፤
ማንኛውም ልጅ አባቱን ሲያማ ያስለቅሳል፤ ያሳዝናል፤ ይረብሻል፤ ግን ይህው ስሜት በ1997 ምርጫ አባታቸውን ያጡ
ልጆች ዕምባ እንዲሁ አስለቅሶኛል፤ ለእነዚያ ልጆች አባት ግን ማንም ሰልፍ ወጥቶ አላለቀሰላቸውም፤ ማንም በየቀበሌው
ድንኳን አልጣለላቸውም፤ እነዚህ ሰዎች እንዲገደሉ ትዕዛዝ ያስተላለፉት ጠ/ሚ መለስ ግን በክብር እየተለቀሰላቸው
ነው፡፡ ለእኔ ሕዝቡ እንዲህ በነቂስ ወጥቶ ያዘነላቸው ሥራቸውን አድንቆ ነው ብዬ አላምንም፡፡ በይቅርታ የታነፀ
ታላቅ ሕዝብ መሆኑን ማሳየቱ ነው፡፡ ኢህአዴግ ቢገባው ሕዝቡ ባሳየው ጨዋነትና አክብሮት ሊያፍር በተገባው ነበር፡፡
እስከ ዛሬ ደስታችሁን ለብቻችሁ ብትካፈሉትም ሀዘናችሁን ግን ተካፈለ፡፡ ክፉን በክፉ አልመለሰም፤ ክፉን በመልካም
አሸነፈ እንጂ፡፡
ጠ/ሚኒስትሩ በሕግ ፊት እንዲቆሙ መፈለግ ቂም በቀል አይደለም፤
እንዳውም አገርን በአስተማማኝ መሠረት ላይ ማነጽ ነው፡፡ ማንኛውም ሰው በሕግ ፊት እኩል መሆኑን ማሳየት መጪውን
ትውልድ በሕግና በሥርዓት እንዲመራ በአስተማማኝ መሠረት ላይ እንደመገንባት ነው፡፡
ሚዲያው ሰብአዊነትና ማንነት ተምታቶበት እያምታታ ነው፤ አቶ
መለስ በመሞታቸው ማዘንና ተግባራቸውን መዳኘት የተለያዩ ናቸው፡፡ ስብዕናንና ሥራን እየደባለቁ ማቅረብ አለማወቅ
ወይም አውቆ አጥፊነት ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰሯቸው ስህተቶች በመሞታቸው ምክንያት ብቻ ስህተቶቻቸው ትክክል
አይሆኑም፡፡ አንድ ክፉ ሲሰራ የኖረ ሰው ስለሞተ ብቻ መልካም አይሆንም፤ በአጭሩ ሞት ፃድቅ አያደርግም፡፡ ቅዱስ
የሆነው መጽሐፍ እንኳን እስራኤል ታላቅ መሪ የነበረውን ንጉስ ዳዊትን ያስነበበን ሙሉ ማንነቱ ነው፡፡ ከሀያልነቱ
እስከ አሳፋሪ ከእነ ልብሱ እስከ እርቃኑ በግልጽ አስነብቦናል፡፡ ሚዲያው ስለአቶ መለስ የመጀመሪያውን ገጽ አንብቦ
ከዚያ ሀምሳ ገፅ ይዘልና ሀምሳ አንደኛውን ገፅ ያነብልናል፡፡ ኧረ ተው አንተዛዘብ፡፡
መሪን ማክበር ማለት እውነትን መሸሸግ ወይም መካድ ማለት
አይደለም፡፡ ሚዲያው እንዲህ የሚያደርገው አቶ መለስን ያከበረ መስሎት ከሆነ በጣም ተሳስቷል፡፡ እንዳውም እውነቱን
መደበቅ አለማክበር ነው፡፡ ለዚያውም የህዝብ በሆነ ሚዲያ ላይ ሕዝብን መዋሸት ነውር ነው፡፡ ደግሜ እላለሁ ሕዝብ
ግልብጥ ብሎ መውጣቱ ስራችሁን እንዳፀደቀላችሁ አስባችሁ ከሆነ ተሳስታችኋል፡፡ ለክፉ ስራችሁ በመልካም እያሸነፋችሁ
ነው መልዕክቱ ይኽው ነው፡፡ ግን አሁንም የገባችሁ አይመስልም ወይም ያደቆነ ሰይጣን እንዲሉ አሁንም እብሪቱ
አለቀቃችሁም “አቶ መለስ ስለ ሞቱ ምንም የስርዓት ለውጥ አይኖርም” ማለት ምን ማለት ነው? ጥፋቴ እንደሚያጠፉኝ
ባውቅም በጥፋቴ እቀጥላለሁ ማለት መቼም የጤና ሊሆን አይችልም፡፡ ኧረ የአቶ መለስ ዕድል ላይገኝ ይችላል፡፡ ነገ
አንገት ደፍቶ ፍርድ ቤት በአፍረት መቆም ሊመጣ ይችላል፡፡ እሱም ከተገኘ ነው፡፡ የጋዳፊም አይነት ዕድል አለ
እኮ፡፡
አቶ በረከት ስምዖን “ጠ/ሚኒስትሩ በ80 ሚሊዮን ሕዝብ
ተተክተዋል” ሲሉ ደነገጥሁ፤ ፈራሁም፡፡ ይታያችሁ 80 ሚሊዮን አምባገነን ሕዝብ ምን ዓይነት አገር ሊፈጥር
እንደሚችል? ደግነቱ ትውልዱ ከእንግዲህ አቶ መለስን የሚያውቃቸው በክፉና በመልካም ታሪካቸው ብቻ በመሆኑ
እፅናናለሁ፡፡ ከእሳቸው ይማራል እንጂ እሳቸውን አይተካም፡፡ ለማንኛውም ገዢ መሪያችንን /Lord leadership/
ለመቅበር እንደታደልነው ሁሉ መሪዎቻችንንም በፍትህ አደባባይ የምንዳኝበትን ቀን እናፍቃለሁ፡፡ ሰማዕቱ ደራሲ
እንዳለው “ተስፋ ማድረግ ጥሩ ነው ተስፋ በሌለበት ቦታም ቢሆን”፡፡
No comments:
Post a Comment