Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Tuesday, 11 September 2012

በኢትዮጵያ ባንኮች በጠቅላላ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በከፍተኛ ደረጃ በመከሰቱ ደንበኞቻቸውን ማስተናገድ እንደተሳናቸው ተዘገበ

ጳጉሜን ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ሪፖርተር፦”የዶላር ያለህ!” በሚል ርዕስ ባጠናቀረው ዘገባ የውጪ ምንዛሬ እጥረቱ ከተከሰተ የሰነበተ ቢሆንም፤ በአሁኑ ጊዜ ግን ችግሩ የከፋ ደረጃ ላይ መድረሱን አመልክቷል።
ከወራት በፊት በቂ የውጭ ምንዛሪ ያለ መሆኑ ቢገለጽም፣ አሁን በተጨባጭ የሚታየው እውነታ ግን በተቃራኒው ሆኗል-ብሏል ጋዜጣው።
የውጭ ምንዛሪ ለማግኘት የባንኮችን ደጃፍ የሚረግጡ  አስመጪዎች፤ <ሌተር ኦፍ ክሬዲት> ለመክፈት እና
ማስመጣት የሚገባቸውን ምርት ለማምጣት ባለመቻላቸው፤ ሥራችን እየተስተጓጐለ ነው በማለት እያማረሩ ነው::
ባንኮች ደንበኞቻቸውን ማስተናገድ ባለመቻላቸውም ዶክመንቶቻቸውን ተቀብለው <ወረፋ ጠብቁ> ከማለት ወጪ ወረፋው መቼ እንደሚደርሳቸው እንቆቅልሽ ሆኗል ያለው ጋዜጣው፤ ችግሩ ቀስ በቀስ ከፍተኛ የሆነ ተፅዕኖ እያሳረፍ ለመሆኑ አንዳንድ ምልክቶችም እየታዩ ናቸው”ብሏል።
ትልቁ የአገሪቱ ባንክ  የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሳይቀር፤ ከግል ባንኮች የተሻለ የውጭ ምንዛሪ አለው ቢባልም፣
ለግለሰቦች የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ አዎንታዊ መልስ ሊሰጥ አልቻለም።
ጋዜጣው እንዳለው፤በግል ባንኮች ያለው የውጭ ምንዛሪ ድርቅ ፤ለባንኮቹ ሳይቀር ራስ ምታት ሆኗል::
ረዥም ተራ በመጠበቅ በሚገኘው ዕድል እንኳን  የሚሰጠው የውጭ ምንዛሪ አነስተኛ በመሆኑ፣ ለዕለት ፍጆታ የሚሆኑና አስፈላጊ ናቸው የተባሉ ምርቶችን አስመጥቶ ወደ ገበያ ለማስገባት አልተቻለም::
<በዚህን ወቅት ለምን የዶላር እጥረት እንደተፈጠረ  ግልጽ አለመሆኑም ብዙ ሊያነጋግር ይችላል፤ ችግሩ
በግልጽ የመታየቱን ያህል -መፍትሔ ለመስጠት እየተደረገ ያለው ጥረት ምን እንደሆነ አይታወቅም::”ብሏል ጋዜጣው።
አክሎም፦”ችግሩ ጊዜያዊ ነው እንዳይባል፤ ችግሩ ማጋጠም  ከጀመረ ሳምንታት ሳይሆን ወራት ተቆጥረዋል። መቆሚያው መቼ እንደሆነም ለመተንበይ እንኳን አልተቻለም:: ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የመንግሥት አካልም በውጭ ምንዛሪ ዙሪያ የተፈጠረውን ክፍተት  አስመልክቶ ምንም ዓይነት መረጃ እየሰጠ አለመሆኑ፣ ችግሩ ነገም ሊቀጥል ይችላል የሚል ስጋት እያሳደረ ነው::”ብሏል።

ይህም ፤የሸቀጦችን ዋጋ በማናር፤ እንዲሁም በእጥረቱ ሳቢያ የሚፈለገውን ያህል ምርቶች አለመግባታቸው የምርት እጥረት እንዲከሰት በማድረግ አጠቃላይ ኢኮኖሚውን ያቃውሰዋል ተብሎ ተፈርቷል።
አቶ መለስ በህመም ሳቢያ ከስልጣን ቦታቸው መሰወራቸውን  ተከትሎ የታየው የመንግስት ሥራ መቀዛቀዝና የኢኮኖሚ መዋዥቅ፤ ሞታቸው በይፋ  ከተነገረ ወዲህ ይበልጥ እየባሰበት መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ።
በተለይ ገዥው ፓርቲ  የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት በማሰብ የ 15 ቀናት የሀዘን ጊዜ አውጆና ከአገሪቱ ጫፍ እስከ ጫፍ ድንኳን አስተክሎ ህዝብን  ሲያስለቅስባቸው በሰነበቱት ሁለት ሳምንታት በሁሉም ሴክተሮች የታየው ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ እጅግ ከፍ ያለ መሆኑ፤እንዲሁም ገንዘብ በባንክ አስቀምጠው ነበሩ በርካታ ሰዎች አለመረጋጋቱን ተከትሎ ገንዘባቸውን በስፋት ወደ ውጪ ማሸሽ መጀመራቸውና የባለሀብቶችም  እንቅስቃሴ መገታቱ፤ወትሮም በቋፍ ላይ የነበረውን የምንዛሬ እጥረት ክፉኛ እንዳላሸቀው ተመልክቷል።
የውጪ ምንዛሬ ከአገሪቱ ካዝና ጨርሶ በመሟጠጡ የቻይና መንግስት በቅርቡ ቀውሱን ለማረጋጋት በሚል መጠነኛ የገንዘብ ድጋፍ እንዳደረገ መዘገባችን አይዘነጋም።
ሆኖም ከተፈጠረው ከፍተኛ እጥረት አኳያ ከቻይና የተገኘው ድጋፍ፤ ጥቂት ርቀትም ሊያስኬድ አልቻለም።
ወደ ሥልጣን እየመጣ ያለው አዲሱ አመራር ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር በመነጋገር እንዲሁም  የፕሬስ ነፃነትን ጨምሮ ለሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበር ያለውን ቁርጠኝነት በማረጋገጥ አዲስና ተስፋ ሰጭ ሽግግር እንዲያደርግ የሚፈልጉ አንዳንድ ለጋሽ አገሮች፤ አመራሩን የሚሄድበትን መንገድ እስኪያውቁ ድረስ የእርዳታ እጃቸውን መሰብሰባቸውን ለኢሳት የደረሱ መረጃዎች ያመለክታሉ።

No comments:

Post a Comment