ስለ ጌታቸው አሰፋ ወይም ደብረፅዮን ምንም ልፅፍ አልችልም። ጌታቸውን በቅርብ አላውቀውም። የአማረ አረጋዊ የቅርብ ጓደኛ ስለነበር፣ አንድ ሁለት ጊዜ በአጋጣሚ ቡና ጠጥተናል። ጌታቸው አሰፋ ነባር የህወሃት አመራር አባል ሲሆን፣ በአቅም ደረጃ ሲመዘን ከላይኛው የህወሃት አመራር አባል አንዱ መሆኑ የሚታወቅ ነው።
ደብረፅዮንን በቅርብ አውቀው ነበር። ደርግ ከመውደቁ በፊት በሃገረሰላም የህወሃት ሬድዮ ጣቢያ በአንድ አካባቢ ነበርን። ሆኖም ደብረፅዮን ሰሞኑን እንደሚፃፍበት፣ ተራ የሬዲዮ ኦፕሬተር አልነበረም። የሬድዮ ስርጭቱ የቴክኒክ ሃላፊ ነበር። ደርግ ከወደቀ በሁዋላ ወዲያውኑ የተቋረጠ የዩንቬርሲቲ ትምህርቱን እንደቀጠለ አስታውሳለሁ። ከደብረፅዮን አንድ የሜዲያ ኮሚቴ ውስጥ አብረን ሰርተን ነበር። ብሩህ አእምሮ የነበረው፣ ባተሌ አይነት ሰው ነበር። ደብረፅዮንን የህወሃት ምክትል እና የፀጥታው መስሪያ ቤት ሁለተኛ ሰው አድርገው ማምጣታቸው በአጋጣሚ አይመስለኝም። ተጠንቅቀው አስበውበት ያደረጉት ነው። ደብረፅዮን በግማሽ ጎኑ ኤርትራዊ ስለመሆኑ ሰምቻለሁ፣ በጋብቻ ከስብሃት ነጋ ጋርም እንደሚዛመድ የተፃፈ አንብቤያለሁ። ርግጠኛ መረጃ ስለመሆኑ ግን አላውቅም።
ስለ ጌታቸው እና ስለ ደብረፅዮን ከዚህ በላይ ማለት የምችለው የለም። ይልቁን ከአጠቃላይ ነገር በመነሳት እነዚህ ሁለት ሰዎች ከሚመሩት ቢሮ ጋር በተያያዘ አንድ ብጫቂ ወግ ማንሳት ፈልጌያለሁ።
እንግዲህ በቅርቡም ሆነ ዘግይቶ አዜብ መስፍን ቤተመንግስቱን ለሃይለማርያም አስረክባ መውጣቷ የማይቀር ነው። ህወሃት ወዶም ሆነ ተገዶ የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ወንበር ለሃይለማርያም ሲያስረክብ የፀጥታውን መስሪያ ቤት እና መከላከያን በመያዙ በመሆኑ ላይ ስምምነት አለ። የሃይለማርያምን እንቅስቃሴ በመቆጣጠር ረገድ ዋና ሃላፊነቱ የሚወድቀው፣ በጌታቸው እና በደብረፅዮን ቢሮ ላይ ነው። አደጋ እንዳይደርስበት ይጠብቁታል። ባንፃሩ አደጋ እንዳያደርስ ይሰልሉታል። ሃይለማርያም ሊሰለል ከሚችልባቸው መንገዶች ዋናው፣ ቢሮውን እና መኖሪያ ቤቱን በድምፅ መቅጃ መጥመድ ነው።
አዜብ ቤተመንግስቱን ስትለቅ፣ ሃይለማርያም ከመግባቱ በፊት፣ ቤተመንግስቱ ሙሉ እድሳት ይደረግለታል። እድሳቱን ማን ሊረከብ እንደሚችል አይታወቅም። ከቻይና ወይም ከሱር ኮንስትራክሽን አያልፍም። የፀጥታው መስሪያ ቤትም ከእድሳት ስራው ጎን ለጎን ስራዎች ይኖሩታል። በዋናው መኝታ ቤት፣ በልጆች መኝታ ቤት፣ በጥናት ክፍል፣ በመፀዳጃ ቤቶች፣ በክበብ፣ በእንግዶች መቀበያው፣ በሲኒማ ቤቱና በፀጉርቤቱ ሳይቀር የድምፅ መቅጃ እና ማስተላለፊያ የረቀቁ ዘመናዊ የስለላ መሳሪያዎች ይቀበራሉ። ህወሃት በዚህ ስራ ተክኖአል። ከህወሃት የተገነጠሉትን እነ ስዬ አብርሃን የተጫወተባቸው በዚሁ ዘዴ ነበር። ቢተው በላይ መኖሪያ ቤት ይሰበሰቡ ነበር። ክንፈ ደግሞ ቢሮው ሆኖ የሚያወሩትን ሁሉ ይሰማል። ቅንጅቶችንም በከፊል በዚህ ዘዴ ገብተውባቸው ነበር። በመጪው ዘመን ሃይለማርያም ከዚህ አያመልጥም። አሳዛኙ ነገር የድምፅ መቅጃ መሳሪያዎቹ የግል ጉዳይ እና የስራ ጉዳይ መለየት አለመቻላቸው ነው።
የሳቅ፣ የለቅሶ፣ የንግግር፣ የመሳሳም፣ የመደባደብ፣ የማንኮራፋት፣ የመገላበጥ ድምፆችን ሳይቀር እያግበሰበሱ ይልካሉ። እነዚህን ድምፆች እያበጠሩ፣ መረጃ የሚመዝኑ ሰዎች ፍሬውን ከገለባ ለይተው ለሃላፊዎች ያቀርባሉ። በቀድሞው አሰራር እነዚህ ጭማቂ መረጃዎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይላኩ ነበር። አሁን ግን ለማን እንደሚላኩ ገና አልታወቀም። ምክንያቱም የሃይለማርያምን ለሃይለማርያም መልሰው ሊልኩ አይችሉም። የቄሳርን ለቄሳር የሚለው አባባል የስለላ ስራ ላይ አይሰራም።
ከዚህ አደጋ ለመዳን ሃይለማርያም ሶስት ምርጫዎች አሉት። የመጀመሪያው ቤተመንግስቱን በገለልተኛ ባለሙያ ማስመርመር ነው። ይህን ሊፈፅም አይችልም። ሁለተኛው ቤተመንግስት አለመግባት ነው። ይህን ሌላ ምክንያት ፈጥሮ ሊፈፅመው ይችላል። ሶስተኛው መድሃኒአለምን አምኖ ዝም ብሎ መግባት ነው። አዘንኩለት። እንኳን እኔ በሱ ቦታ አልሆንኩ።
ርግጥ ነው፣ የህዝብ ድጋፍ የሌለው አምባገነን ስርአት በስለላ፣ በጠመንጃ እና በገንዘብ ሃይል ብቻ ለዘላለም ህያው ሆኖ መኖር አይቻለውም። የጋዳፊን ያህል ዘመናዊ የስለላ ቴክኖሎጂ መጠቀም የሚችል ከቶ ማነው? የሴሴሴኮ ቢሊዮናት ዶላሮች የትም ባክነው ቀርተው የለምን? ለመሆኑ የገናናው የኮሎኔል መንግስቱ ጦር ዛሬ የት ነው?
ማንዴላ የሃገሩን ነጮች ልብ ያሸነፈው እነዚህ ሶስት ሃይል ሰጪ መሳሪያዎች ሳይኖሩት ነው። በርግጥ ማንዴላ መተኪያ አልባ ሌላ ሃይል ነበረው – የህዝብ ፍቅር።
No comments:
Post a Comment