Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Saturday, 20 October 2012

ጉዞ ኃይለ ማርያም - ከአረካ እስከ አራት ኪሎ

Saturday, 20 October 2012 00:00, By Yonas Abiye
በዮናስ አብይ
የ43 ዓመቱ ጐልማሳ መንገሻ መንዳዶ የተወለደባትንና አድጐ የተማረባትን አነስተኛዋን የአረካ ከተማን ለቆ መኖርያውን በአርባ ምንጭ ከተማ ካደረገ ከሁለት አሥርት ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡
ዛሬ የሥራ ጠባዩ በፈጠረለት አጋጣሚ ሙሉ ጊዜውንና ኑሮውን በአርባ ምንጭ ላይ በመመሥረቱ አልፎ አልፎ በአዕምሮው ውልብ ከሚሉበት ትዝታዎች በስተቀር ስለተወለደባት የአረካ ከተማ ሲያወሳ አይሰማም፡፡ ነገር ግን ስለተወለደባት ከተማ ከማይረሳቸው የልጅነት ትውስታዎቹ ውስጥ አንድ አስገራሚ ታሪክን ከተማሪነት ዘመኑ መዝዞ በፈገግታና ኩራት በተሞላበት ሁኔታ ሲያወጋ፣ ያድማጭን ጆሮ በጉጉት ሊያቆም እንደሚችል በቅድሚያ ከገጽታው ደማቅነት መረዳት ይቻላል፡፡ የታሪኩ ክስተት ወደኋላ 28 ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ 300 ኪሎ ሜትር በምትርቀው በአረካ ከተማና በነዋሪዎቿ ታላቅ የመደነቅ ስሜትን ስለፈጠረ  የአንድ ጎበዝ ተማሪን አስደናቂ ጉዳይ ያወሳል፡፡

መንገሻ በወቅቱ ከሚማርበት የአረካ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ይልቅ ከከተማዋ ዕምብርት ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ስለሚገኘው ዱቦ የካቶሊክ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ስላለ አንድ ተማሪ ጉብዝና መስማትና ማውራት ይመስጠው ነበር፡፡

“በዚያ የሕፃንነት ዕድሜ ሁሉም ሰው ስለሱ ጉብዝና ብቻ ሲወራ ትዝ ይለኛል፡፡ እኔም በእኛ ትምህርት ቤት ውስጥ ካሉ ጐበዝ ተማሪዎች ይልቅ በዚያኛው ትምህርት ቤት ስላለው ጐበዝ ተማሪ ብሰማም ባወራም አልጠግም ነበር፤” በማለት የሚናገረው መንገሻ አገለለጹና ገጽታው ይህ ታሪክ እንኳን 28 ዓመታት ቀርቶ አሥር ዓመት የሞላው አይመስልም፡፡

በነዚያ ዘመናት ውስጥ እነ መንገሻ ከሚኖሩበት ከተማ አልፎ በድፍን ቦሎሶ ሶሬ በጉብዝናውና በቀለም ትምህርት አያያዙ “ያሳድግህ” ተብሎ የሚመረቀው ታዳጊ ተማሪ ከአረካ ከተማ የሁለት ሰዓት ያህል የእግር መንገድ ከምትርቀው የደካ ቀበሌ ማኅበር ቢወለድም፣ ገና በጨቅላ ዕድሜው ነበር ከወላጆቹ እንዲለይ ትምህርት ያስገደደው፡፡ እንደዛሬው አረካም ልጆቿን ከአንደኛ ደረጃ በላይ ለማስተማር የሚያስችል ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ያልነበራት በመሆኑ፣ የልጆቿ ዕጣ ፈንታ በ8ኛ ክፍል ይገታል አልያም ወደ ሌላ አጐራባች ከተማ ስንቅ አስይዛ ትልካለች፡፡

በወቅቱ ከአረካ በስተደቡብ 30 ኪሎ ሜትር አለፍ ብላ ወደ ምትገኘው የሶዶ ከተማ ከላከቻቸው በጣት ከሚቆጠሩ ተማሪዎች አንዱ በጉብዝናው ጓደኞቹን እነ መንገሻን “አጀብ” ሲያሰኝ የነበረው ታዳጊ ብላቴ አንዱም ነበር፡፡ ይህ ታዳጊም ታዲያ በሶዶ ከተማ በሚገኘው ብቸኛው የሶዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ስሙንና ዝናውን  በአራት ዓመት ቆይታው ማስጠበቅ የተሳነው አልነበረም፡፡ የቤተሰብ ናፍቆት ሆነ ታዳጊነትን ተከትሎ የሚመጣ ጉርምስናም ቀለሜነቱን የሚያደበዝዙ አልነበሩም፡፡

ዝናባማዎቹ የ1976 ዓ.ም. ክረምት ወራት ሊገባደዱ ጥቂት ቀናት ሲቀሩ በሶዶ፣ በዓረካና ደካ በተባለችው ቀበሌ የሚገኙ ሁሉ ስለአንድ ነገር የሚያበስር ዜና ይጠባበቁ ነበር፡፡ የሁሉም ጉጉት ከቡዶ አንደኛ ትምህርት ቤት እስከ ሶዶ ሁለተኛ ደረጃ ስለሚወራለት ያ ታዳጊ ልጅ ቀደም ብሎ ከጥቂት ወራት በፊት ወስዶት ስለነበረው አገር አቀፍ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መልቀቂያ ፈተና ነበር፡፡

ብዙዎችን ሲያንቆራጥጥ የነበረው የፈተና ውጤት ጊዜውን ጠብቆ በወርኀ ነሐሴ የመጨረሻ ቀናት ውስጥ ወጣ፡፡ በወቅቱ የነበሩት ተፈታኝ ተማሪዎች፣ ወላጆቻቸውና ጓደኞቻቸው ከትምህርት ቤቱ መግቢያ በር ላይ ተለጥፏል ስለተባለውና የተማሪዎችን የውጤት ዝርዝር የያዘውን ወረቀት ለማየት ወደ ሶዶ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ጐረፉ፡፡ በእርግጥም ዝርዝሩ ወጥቷል፡፡ የሁሉንም ተፈታኞች ሳይሆን የጥቂት ተማሪዎች ዝርዝር ይታያል፡፡

የስማቸውም ዝርዝር ባገኙት የነጥብ ደረጃ ቅደም ተከተል መሠረት ተቀምጧል፡፡ ከእነዚህ ጥቂት ጐበዝ ከተባሉት ተማሪዎች ዝርዝር ውስጥ ከሁሉም በዕድሜ የሚያንሰውና ከቦሎሶሬ አፈር ተገኘ የሚባለው ታዳጊ ስሙ  በአንደኝነት ደረጃ የተቀመጠ ሲሆን፣ በስሙ ትይዩ 3.8 የሚል ደረጃን የሚያመለክት ቁጥር ተቀምጧል፡፡ ስሙም ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ቦሼ ይላል፡፡ ይህ ታዳጊ በይበልጥ “ኃይሌ” በሚለው አጭር ስያሜ ሲታወቅ በወቅቱ ከነበረው ዕድሜና ጉብዝና የተነሳ ብዙዎች በሴት ፆታ “አንቺ”፣ ‘እሷ’፣ “ይህቺ ትንሽ ልጅ” ብሎ መጥራትን ይመርጡ ነበር፡፡

በእርግጥ ጐበዝ ተማሪዎች ዩኒቨርሲቲ መግባታቸው አዲስ ያልነበረና የተጠበቀ ቢሆንም፣ በወቅቱ “ኃይሌ” እያሉ የሚጠሩት ተማሪ ያስመዘገበው ውጤት ግን በአረካና አካባቢዋ “የመጀመሪያውና ታሪካዊው ከፍተኛ ውጤት” ያገኘ ተብሎ ተመዝግቧል፡፡

ከሶዶ እስከ አረካ የኃይሌ ዝናና ክብር በስፋት ተስተጋባ፡፡ ብዙዎችም በአደባባይ ወጥተው የአድናቆት ሆታን አቅልጠውለት ነበር፡፡ “ኃይሌ 3.8 ነጥብ አመጣ ሲባል ጓደኞቹና የአረካ ልጆች በመኪና አጅበውትና የመኪናው ጣራ ላይ አቁመውት ከሶዶ ሲመጡ እኛና የከተማው ሕዝብ አስፋልት ላይ ወጥተን እየጨፈርን ነበር የተቀበልነው፤” በማለት መንገሻ የያኔውን ክስተት ያስታውሳል፡፡

በዚያች ዕለት የኃይሌ ስም እንደ ደማቅ ኮከብ ፈክቶ ታየ፡፡ በቦሎሶ ሶሬ ለሚገኙ ወገኖቹ፣ ዘመዶቹና ለአካባቢው ሁሉ ኩራት ሆነ፡፡ በተለይ በትምህርት ደረጃቸው ከእሱ ያንሱ ለነበሩ ታዳጊዎች፣ ለነመንገሻና የአካባቢው ተማሪዎች “ጥሩ አርዓያ” (Best Model) ሆኖ መነሳሻ ሆኗቸው እንደነበር ትዝ ይለዋል፡፡

የአረካን ሕዝብ ያስፈነጠዘው የያኔው የኃይሌ የማትሪክ ውጤት በአንፃሩ ለቤተሰቡ ለየት ባለ ሁኔታ የተደበላለቀ ስሜትን የፈጠረ ነበር፡፡ በተለይ ኃይሌን በቅርበት የሚያውቁት የማትሪክ ውጤቱ የኃይሌን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በተለየ መልኩ እንዲቀየርና ወዴት እንደሚያመራ ያመለከተ ነው ሲሉ ይስማሙበታል፡፡

ታሪኩም እንዲህ ነው፡፡ ብዙዎች በጋራ ሆነው የኃይሌን ድንቅ ውጤት በደስታ በሚጋሩበት ሰዓትና ኃይሌም የልፋቱን ፍሬ በሚያጣጥሙበት ቅፅበት በካቶሊክ ትምህርት ቤት ውስጥ በበጐ ስማቸው የሚታወቁት የያኔው መምህርና የኃይሌ ወላጅ አባት የነበሩት አቶ ደሳለኝ ቦሼ፣ ከጥቂት ቀናት በፊት አልጋ ላይ ያዋላቸው ሕመም ፀንቶባቸው በስቃይ ላይ ነበሩ፡፡ ኃይሌም ደስታውን ከከተማ ወዳጆቹና ጓደኞቹ ጋር ተጋርቶ ሲጨርስ ወደ ተወለደባት ደካ ቀበሌ ለሁለት ሰዓታት ተጉዞ ለቤተሰቡ በተለይም በሕመም እየተሰቃዩ ለነበሩት አባቱ ደስታውን ሊያበስር ሩጫውን ቀጠለ፡፡ ነገር ግን የውጤቱ ማሳያ ሠርተፊኬቱን ይዞ ከአባቱ አልጋ ሲደርስ የሚወዳቸው አባቱ ሕመማቸው ቀድሞ ሲወጣ ካያቸው ብሶባቸው አገኛቸው፡፡ ያ ሁሉ ደስታው ወደ መሪር ሐዘን ተቀየረ፡፡ ደስታ ያፈነው የፊቱ ገጽታ በተቃራኒው በቀዝቃዛ ላብ ረጠበ፡፡

ድምፁን ቀስ አድርጐ የማትሪክ ውጤቱ 3.8 እንሆነ ያበስራቸዋል፡፡ ነገር ግን እሳቸው ቀደም ብለው ደስታቸውን በሆታና በጩኸት እንደገለጹት የአረካና የደካ ነዋሪዎች የመግለጽ አቅም አልነበራቸውም፡፡ ታማሚው አባቱና የቀድሞው መምህር ግን መቦረቅ ባይችሉም የልጃቸው የወደፊት ራዕይና የሕይወት መስመር ወዴት እንደሚያደርሰው በትክክል ለመተንበይ ግን የተኙበት አልጋ ሊገድባቸው አልቻለም ነበር፡፡

ቀና ብለው አዩት፡፡ ሁለት በስስትና ፍፁም አባታዊ ፍቅርን የተጐናፀፉ ዓይኖች በኃይሌ ላይ ቀና ብለው አፈጠጡ፡፡ ቀስ ብለው አፋቸውን ከፈት አደረጉ፡፡ ልቡ በሐዘን የተነካውም ኃይሌ አይኖቹ ቦዘው፣ ጆሮዎቹ ቆመው፣ ከአንገቱ ሰበር በማለት ከአባቱ የሚወጡ ቃላትን በአንክሮ ለማዳመጥ ወደ አልጋው ራስጌ ጐንበስ አለ፡፡

“ከዚህ በኋላ የቤቱ አስተዳዳሪ አንተ ነህ፡፡ ሰባቱን ወንድሞችህንና አንዲት እህትህን ከእንግዲህ አንተ ነህ የምትመራው፤” የሚል ታላቅ የሙት አደራ ወደ ኃይሌ ተወረወረ፡፡ በዚች ቅፅበት ትምህርትንና ታዳጊነትን ብቻ ተሸክመው የነበሩ የኃይሌ ትከሻዎች ክብደት ተሰማቸው፡፡ እንደገና አጠር ያሉ ነገር ግን ግልጽና ወደፊት ረጅም ጊዜያትን ተሻግረው አዲስ ሕይወትን የሚያሳዩ መልዕክቶች የያዙ ድምፆች ከመምህር አባቱ ለመጨረሻ ጊዜ ወጡ፡፡ “አንተ ትልቅ ሰው ትሆናለህ! አይዞህ!” የሚል ነበር፡፡

የ18 ዓመቱ ኃይሌ ከአባቱ የመጨረሻ “ዕዳ” ወይም ‘በረከት’ ተቸረው፡፡ በተመሳሳይ ጊዜና ቅፅበት ደብልቅልቅ ስሜትና ድብልቅልቅ ክስተቶች አጋጠሙት፡፡ ሕይወት የምህዋሯን እንቅስቃሴ በመምህሩ በአባቱ አቶ ደሳለኝ ላይ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አቆመች፡፡ በተቃራኒው የሐዲድ አቅጣጫዋን አስፍታ ኃይሌን ይዛ መንጐድ ጀመረች፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ - አምስት ኪሎ
ወጣቱ ኃይሌ ገና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለ የራሱ የሆነና እንደ ማንኛውም ተማሪ ትልቅ ግብና ህልም እንደነበረው ራሱም ሆነ የሚያውቁት ሁሉ የሚመሰክሩት ቁምነገር ነበረ፡፡ ድንገት አባቱን በሞት ከመነጠቁ በፊት ዩኒቨርሲቲ ገብቶ የሕክምና ሳይንስ (Medicine) ለማጥናትና ከዚያም ተመርቆ ቤተሰቡን በተለይም በሥነ ምግባር አንፀው ያሳደጉትን የአባቱን ውለታ ለመክፈል ትልቅ ህልም ነበረው፡፡ ነገር ግን ሕይወት እነዚያን ግብና ህልም በሚፈልገውና ባቀደው መልኩ እንዲሄድ ዕድል ከመስጠት ይልቅ በሌላ አቅጣጫ እንዲጓዝ የራሷን መንገድ ቀይሳ ይዛው ነጐደች፡፡

በወርኀ መስከረም 1977 ዓ.ም. በወቅቱ የነበረው አገር አቀፍ የፈተናዎች ድርጅት ቀደም ባለው ዓመት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ፈተና ወስደው ወደ ከፍተኛ ተቋማት የሚገቡት ተማሪዎች ይፋ ሲያደርግ፣ ከፍተኛ ጭፈራ የተደረገለት የያኔው ኃይሌ፣ አሁን በይበልጥ ኃይለ ማርያም በመባል የሚጠራው ወጣት ቦሎሶ ሶሬን ትቶ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እንደሚያመራ አወቀ፡፡

በታላቁ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወይም የቀድሞው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሥር ከሚገኙት አንዱ በሆነው የአራት ኪሎ ካምፓስ ለአንድ ዓመት ቆየ፡፡ ከአንድ ዓመት የአራት ኪሎ ቆይታ በኋላ ኃይለ ማርያም አምስት ኪሎ በሚገኘው ካምፓስ በሲቪል ምህንድስና የትምህርት ክፍል (Department of Civil Enginerring) ተመድቦ ተጨማሪ አራት ዓመታትን አሳለፈ፡፡

ከአረካ ከተማ እስከ ሶዶ ድረስ በቀለም ትምህርት አያያዙና በበጐ ምግባሩ የሚታወቀው ኃይለ ማርያም ለአምስት ዓመታት በቆየበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ተመሳሳይ ታሪክን መድገም ችሏል፡፡ ከ1980 ዓ.ም. ተመራቂ ተማሪዎች መካከል ኃይለ ማርያም የከፍተኛ ማዕረግ ተሸላሚ ሆኖ ተመረቀ፡፡ በዚያው በከፍተኛ ማዕረግ፡፡

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በከፍተኛ ማዕረግ በየዓመቱ ከሚያስመርቃቸው ተማሪዎች ጋር በተያያዘ በርከት ላሉ ዓመታት ከሚታወቁ ልምዶቹ መካከል እነዚህን ተማሪዎች እዚያው አስቀርቶ ለረዳት መምህርነት (Assistant Instructor) መቅጠር፣ ወይም ለሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት አወዳድሮ ዕድል መስጠት ነበር፡፡ ይህንንም ታዲያ ኃይለ ማርያም ከመመረቁ ቀድሞ ያውቅ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ እንደተመረቀም እዚያው እንደሚቀጠርም ጥርጥር አልነበረውም፡፡ ታዲያ ምን ያደርጋል ከሕፃንነት የትምህርት ዕድሜው አንስቶ እስከ አዋቂ ዕድሜው ድረስ የኃይለ ማርያም የውጤት ስኬት ሁሌም መጨረሻቸውን መገመት በማይቻልበት ሁኔታ ወዳልታሰበ አቅጣጫ እንደወሰዱት ነው፡፡ እናም የ1981 ዓ.ም. የዓመቱ የከፍተኛ ትምህርት ቤት የትምህርት ዘመን ሲጀምር እዚያው በተማረበት የአምስት ኪሎ ምህንድስና ፋኩልቲ እቀጠራለሁ ብሎ የጠበቀው ተመራቂው ኃይለ ማርያም ባልተለመደ ሁኔታ ከአዲስ አበባ 500 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው አርባ ምንጭ ከተማ በሚገኘው የወቅቱ አርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በጀማሪ መምህርነት ተቀጠረ፡፡ ብዙዎች በከፍተኛ ማዕረግ ከተማረበት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ወደ ሌላ ኮሌጅ የተላከ “የመጀመሪያው ሰው” አድርገው ይቆጥሩታል፡፡

ሞቃታማዋ አርባ ምንጭ - መንፈሳዊነት ወይስ ታላቅ ኃላፊነት?
ቢሾፕ ህዝቅኤል ጐዴቦ የትውልድ ቦታቸው ከሆነው ወላይታ ዳሞት ጋሌ ከምትባል ሥፍራ ለቀው ወደ አርባ ምንጭ ከተማ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሄዱት ከ36 ዓመታት በፊት ነበር፡፡ እስከ ዛሬ ድረስም ኑሯቸውንና ሙሉ ሕይወታቸውን በዚያችው በሞቃታማዋ አርባ ምንጭ አድርገው ዘጠኝ ልጆችና ቤተሰቦችን አፍርተዋል፡፡

ቢሾፕ ህዝቅኤል ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ከሚያስተዳድሩበት መኖሪያ ቤታቸው ጋር አያይዘው “በጋሞ ጐፋ ሀገረ ስብከት የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን” ተብላ የተሰየመችውን የአምልኮ ቤት አሠርተው ለ36 ዓመታት እየመሯት ይገኛሉ፡፡ መቀመጫቸውን አርባ ምንጭ ላይ ያድርጉ እንጂ ለብዙ ዓመታት ወደተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በመዘዋወር ሃይማኖታዊ አገልግሎቶችን ሲያከናውኑ ኖረዋል፡፡ በእርግጥ ዛሬ የዕድሜ ጫና እንቅስቃሴያቸውን ካለፉት ዘመናት ቢቀንሰውም በተደጋጋሚ የወንጌል ስብከትን ያከናውኑባቸው ከነበሩ ሥፍራዎች መካከል አዲስ አበባን ደጋግመው ጐብኝተዋል፡፡ በተለይም ከተለያዩ የደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ተሰባስበው በአዲስ አበባ የተለያዩ የትምህርት ተቋማት የሚገኙ ተማሪዎችን የማስተማርና የማፅናናት ሃይማኖታዊ ተልዕኮን ሲወጡም ቆይተዋል፡፡

በ1980ዎቹ የመጀመሪያ ዓመታት ቢሾፕ ህዝቅኤል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከሚማሩ ተማሪዎች የሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን አማኞችን ለማግኘት ብቅ ብለው ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ እሳቸው ከተወለዱባት የዳሞት ጋሌ አካባቢ በቅርብ ርቀት ከምትገኘው ቦሎሶ ሶሬ ተወልዶ በአምስት ኪሎ የቴክኖሎጂ ፋኩሊቲ ተማሪ የነበረውን ኃይለ ማርያምን ከአማኝ ተማሪዎች ጋር በአካል አገኙት፡፡ ሕፃን ሆኖ በዝና ብቻ የሚያውቁትን ወጣቱን ተማሪ በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ አሁንም ድረስ ያስታውሱታል፡፡

“አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሳገኘው በርግጥ ትውውቃችን እዚህ ግባ አይባልም ነበር፡፡ ግን በወሬና በዝና በደንብ አውቀው ስለነበር በአካል ሳገኘው በጣም ደስ ብሎኝ ነበር፤” በማለት ያስታውሱታል፡፡

አዲስ አበባ በምትገኘው ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ከሃያ ዓመታት በፊት የተገናኙት ሰባኪው አዛውንትና ተሰባኪው ተማሪ ግንኙነት እስከ አርባ ምንጭ ከተማ በምትገኘው ቤተ ክርስቲያን ድረስ የዘለቀና አድጐ የቀጠለ ሆኗል፡፡ ለረዥም ጊዜ የተለያዩት ነገር ግን በአንዲት ቤተ ዕምነት የተሳሰሩት መምህርና ደቀ መዝሙር ግንኙነታቸው ጠብቆ ዛሬ በዝምድናም ተሳስረዋል፡፡

ቢሾፑ ዛሬ ላይ ቁጭ ብለው ሲያስታውሱት የሚያስገርምና “ድንቅ የእግዚአብሔር ተዓምር” በማለት የቆየ ታሪካቸውንና ቀረቤታቸውን ያጋራሉ፡፡ ይሁን እንጂ ከሁሉም በላይ ዛሬ ላይ ሆነው ሲያስቡት ከሚያስደንቃቸው ታሪኮች ሁሉ ፈገግታ በተመላበት ገጽታ የሚያወሱት ያልተጠበቀውን የኃይለ ማርያምን በመምህርነት ወደ አርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መመደብ ሲሆን፣ “እኔን እንዲያገለግል እግዚአብሔር አመጣው፤” ብለው ያምናሉ፡፡ ከዚህም በላይ ኃይለ ማርያምን ለታላቅ ሃይማኖታዊ አገልግሎትና ሥልጣን እስከማጨትም ደርሰው ነበር፡፡

“እኔ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እያለ በጣም ጐበዝ ተማሪ ሰው ሆኖ ነው የማውቀው፡፡ በዚያን ጊዜ ደግሞ ጐበዝ ተማሪዎች ሲመረቁ እዚያው የተማሩበት ዩኒቨርሲቲ ሰቅለው እንደሚቀሩ ነው፡፡ ሁሌም የሚገርመኝ እሱ በከፍተኛ ደረጃ ተመርቆ፣ ሁሉንም ትምህርቶች ‘A’ አግኝቶ የጨረሰን ተማሪ እዚህ ጋሞ ጐፋ ተመድቦ ሲመጣ በጣም ደንቆኛል፡፡ ጋሞ ጐፋ ተመድቦ የሚላከው ሌላ ሌላው እንጂ እንደሱ ዓይነት ሰው አልነበረም፡፡ ይኼ ሰው እኔን እንዲረዳ እግዚአብሔር ልኰት ነው ብዬ ነበር ያመንኩት፤” በማለት በሳቅ በታገዘ ስሜት ይናገራሉ፡፡

መንፈሳዊነትና መምህርነት የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች
አፍላ ወጣት፣ አዲስ ምሩቅና ጀማሪ መምህር የነበረው ኃይለ ማርያም ኑሮን በአርባ ምንጭ ‘ሀ’ ብሎ ሲጀምር ሙሉ ጊዜውን ተመድቦ በተላከበት የትምህርት ተቋም ላይ ቢያደርግም፣ የአፍላነት ጊዜውንና አገልግሎቱን ከአሥር ዓመት በላይ ለቆየባት ቤተ ክርስቲያንም አልነፈጋትም፡፡

ከመሀል ከተማዋ በአዲስ አበባ መግቢያ በኩል አራት ኪሎ ሜትር ራቅ ብሎ በከተመውና የከተማዋ ታላቅ በሆነው ተቋም ውስጥ ሙሉ ቀን የማስተማር ሥራውን ያከናውናል፡፡ ዘወትር ከሥራ ሰዓት ውጪና ቅዳሜና እሑድን ጨምሮ በቤተ ክርስቲያን በትጋት ያገለግላል፡፡ ከእነዚህ ሁለት የትምህርትና የዕምነት ተቋማት ውጪ እንደሌሎቹ ወጣቶች ሌሎች ነገሮች ለኃይለ ማርያም ግድ አይሰጡትም ነበር፡፡

በተቋሙ ውስጥ በተቀጠረ በሁለተኛ ዓመቱ ኃይለ ማርያም ከማስተማሩ ጐን ለጐን ከተቋሙ የሬጂስትራር ክፍል ውስጥ በተደራቢነት ሲያገለግል ነበር፡፡ ምንም እንኳ ወጣቱ መምህር የብዙ ዓመታት የሥራ ልምዶች ባይኖሩትም፣ በወቅቱ ከነበሩ ባልደረቦቹና የሥራ አጋሮቹ መልካም ግንኙነትንና ተቀባይነት በፍጥነት ለማግኘት አልተቸገረም፡፡ ይልቁንም አብረውት በሥራ የቆዩትና ተቋሙ ወደ ዩኒቨርሲቲነት ደረጃ እስካደገበት ጊዜ ድረስ በሥራ ቦታ ላይ ከ20 ዓመታት በፊት ጀምሮ የሚያውቋቸው ኃይለ ማርያምን በተመሳሳይ መልኩ ይገልጿቸዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚ ፕሮግራም ግምገማና ትግበራ ክፍል ዳይሬክተር ሆነው የሚያገለግሉት አቶ ዘነበ ዘውዴ አቶ ኃይለ ማርያም ከተቀጠሩበት ጊዜ ጀምሮ ያውቋቸዋል፡፡ ዳይሬክተሩ የያኔውን ባልደረባቸውን እስካሁን ድረስ ኃይሌ በማለት ቀረቤታቸውን በሚያመላክት ስሜት ነው አሳጥረው ስማቸውን የሚጠሩት፡፡ “አቶ ኃይሌ እዚህ ግቢ መጀመርያ መጥቶ ከተዋወቅንበት ጀምሮ በደንብ የማውቀው በራስ መተማመኑና  በውሳኔ ሰጪነት ችሎታው ነው፤” የሚሉት አቶ ዘነበ፣ ‹‹እሱ ከሚታወቅበት ሌላ ባህሪያቶች ውስጥ ከተራ መምህርነት አንስቶ የተቋሙ ዋና አስተዳደሪ (ዲን) ሆኖ ግቢውን እስከለቀቀ ድረስ ሁሉንም ሰው አክባሪና ትንሽ ትልቅ ብሎ ሰው መለየትን የማያውቅ ነበር፤” በማለት ይገልጿቸዋል፡፡

ረጅም ዓመታትን ካስቆጠረው የትውውቅ ጊዜያት ውስጥ አቶ ዘነበ ከሚያስታውሱት መሀል “የሚገርመኝ” ብለው የሚገልጹት ታሪክ አላቸው፡፡ “እዚህ ሁለት ዓመት ካስተማሩ በኋላ የማስተርስ ዲግሪያቸውን ለመሥራት ወደ ፊላንድ ሄደው ሲመለሱ አንድ ጉዳይ ነበር፡፡ እዚያ ፊላንድ  ባደረጉት የትምህር ቆይታ በሳኒቴሪ ኢንጂነሪንግ ትምህርታቸውን  ሲያጠናቅቁ የወርቅ ተሸላሚ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ወዲያው ስለተመለሱ ሽልማታቸውን እዚህ ፊንላንድ ኤምባሲ ተጠርተው ነበር የተቀበሉት፤” በማለት ያስታውሱታል፡፡

በተመሳሳይ አቶ  ተክለ ማርቆስ ኃይለ ጊዮርጊስ ከ21 ዓመት በፊት ወደ ተቋሙ መጥተው በአስተዳደርና ፋይንስ መምርያ ኃላፊ ሆነው ከተመደቡበት ጊዜ ጀምሮ አቶ ኃይለ ማርያምን በቅርብ ጓደኝነትና በኋላም አቶ ኃይለ ማርያም አለቃቸው ሆነው በሚገባ ያውቋቸዋል፡፡ “እሱ ሁለተኛ ዲግሪውን ሠርቶ ሲመጣ ጀምሮ እንተዋወቃለን፡፡ ተራ መምህር ሆኖም ከዚያም የሬጂስትራር ኃላፊና በመጨረሻም አለቃዬ ሆኖ አውቀዋለሁ፡፡ እሱ ከለቀቀበት የመጨረሻዋ ዕለት ጀምሮ ስምንት ያህል አለቆች አይቻለሁ፡፡ ለእኔ ግን ከሌሎቹ በዕድሜ ወጣቱ እሱ ስለነበር ነው መሰል እሱ ከሌሎቹ በተለየ መልኩ ለሠራተኞች ተደራሽ ነው፡፡ ማንንም ሰው በፈለገበት መንገድ አግኝቶ ያናግር ነበር፡፡ እሱም ከላይ እስከታች ወርዶ ምን ጎደለ? ምን ቸገራችሁ? ብሎ ይጠይቅ ስለነበር ሠራተኞችን በቅርብ ያገኝ ነበር፡፡ ርቆ ራሱን የሰቀለ ሰው አልነበረም፤” በማለት ይመሰክራሉ፡፡ “እኔ አይመለከተኝም የሚባለውን በአገራችን የተለመደ አባባል ፈጽሞ  የማያውቁና  የመኮፈስ ባህሪ የሌላቸው ነበሩ፡፡ በወቅቱ በዚህ ግቢም ሆነ በአገሪቱ ከነበሩት ጎበዝ መምህራንና በተማሪዎቻቸው ዘንድም ጥሩ ከሚባሉ ሦስት አስተማሪዎች ውሰጥ አንዱ እሳቸው ነበሩ” በማለት በአክብሮት ይገልጻሉ፡፡

የኃይለ ማርያም  “ወንድ ልጅ”

በቀድሞው ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሊቀመንበር በመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ዘመን 1979 ዓ.ም የተቋቋመው የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ከተቋምነት ወደ ዩኒቨርሲቲነት ደረጃ ለማደግ ከአሥር ዓመታት በላይ ቆይቷል፡፡ ተቋሙ ወደ ዩኒቨርሲቲነት ለመሸጋገር ያበቁት ብዙ አገራዊ ምክንያቶች ቢኖሩም፣ የአቶ ኃይለ ማርያም ጥረት “ጉልህ” የሚባል ድርሻ እንዳለው የሚናገሩት አሁን በሥራ ላይ የሚገኙት የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ብዙ ናቸው፡፡ በከባድ ሾፌርነት በማገልገል ላይ የሚገኘው አለማየሁ መኮንን ታደሰ አርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲን ለዚህ ደረጃ ካበቁት ውስጥ ትልቁን ድርሻ ለአቶ ኃይለ ማርያም ይሰጣል፡፡ “ጋሼ ኃይሌ  ሕፃኑን እንደ ሕፃን፣ ትልቁን እንደ ትልቅ አይተው የሚያከብሩ ናቸው፡፡ በዚህም ላይ ትልቅ ራዕይ የነበራቸውና ይህን ግቢ ትልቅ ለማድረግ ሲሠሩ የኖሩ ናቸው፤” የሚለው ሾፌር፣ እስካሁን “ጋሼ”› በማለት  የሚጠራቸውን የድሮ አለቃውን “ጠቅላይ ሚኒስትር” ብሎ ለመጥራት እንደሚቸገርና ገና ለመለማመድ ጊዜ እንደሚወስድበት ሳይደብቅ ስሜቱን ይገልጻል፡፡

ሾፌሩ አለማየሁም ሆነ አብረውት የሚሠሩት ጓደኞቹ ከቀድሞው የዩኒቨርሲቲው ዲን ጋር ያላቸውን ፍቅርና አክብሮት በቀጥታ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ያስተሳስሩታል፡፡ ዩኒቨርሲቲውን እንደ መተዳደደሪያቸው ብቻ ሳይሆን የሚያዩት ለአቶ ኃይለ ማርያም ካላቸው ፍቅር ጋር በቀጥታም ሲያገናኙት ይስተዋላል፡፡ ይህ ሐሳብ በአሁኑ ወቅት በሚያስተምሩ መምህራንም ላይ ይንፀባረቃል፡፡

የዚህ ታሪክ መነሻው ከራሳቸው ከአቶ ኃይለ ማርያም በአንዲት ቀን ከተደረገ ንግግር የተፈጠረ ነው፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም በዲንነት ሲያስተዳደሩ በተቋሙ ግቢ በሚገኘው ኳስ ሜዳ ላይ ተማሪዎችን፣ መምህራንና ሠራተኞችን ሰብስበው ንግግር ያደርጉ ነበር፡፡ የንግግራቸው ጭብጥ ያተኮረው “መላው የተቋሙ ማኅበረሰብ በምን መልኩ ተቋሙን ለማሳደግ መነሰሳሳት እንዳለባቸው” በሚለው ላይ ነበር፡፡ ከአቶ ኃይለ ማርያም አንደበት እንዲህ የሚል ንግግር ወጣ፡፡ “በአጋጣሚ ያሉኝ ሦስቱም ልጆቼ ሴቶች ናቸው፡፡ ለእኔ ይኼ ግቢ ‘ወንድ ልጄ’ ነው፤” ሲሉ በሁሉም ሠራተኞች ጆሮ ጠልቆ የገባ ታላቅ ንግግር ነበር፤ ሠራተኞቹ እንደሚመሰክሩት፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም  ተቋሙን ከለቀቁ ብዙ ጊዜያት አልፈዋል፡፡ ዳግም ላይመለሱም ርቀት ሄደዋል፡፡ ነገር ግን በነአለማየሁና በመምህራን ጭንቅላት ውስጥ ግን “ወንዱ ልጄ ይህ ነው” የሚለው ቃል አሁንም እንደሚታወስ ይናገራሉ፡፡

ሾፌሩ አለማየሁ ተቀጥሮ ከሚሠራበት ዩኒቨርሲቲ ሥራውን ካጓደለ ወይም ኃላፊነቱን በአግባቡ ካልተወጣ የሚወደው የድሮ አለቃው ልጅ ላይ “ክፋት” እንደሠራ ይቆጥረዋል፡፡  በተጨማሪም ይህ ሾፌር የቀድሞ አለቃውን የሥራ ፍቅርና ቅንነት በራሱ ላይ በአንድ ወቅት ካጋጠመው ተሞክሮ በመነሳት እንዲህ ሲል ይገልጸዋል፡፡ “አንድ ጊዜ ለግቢ ሥራ የሌሊት ተረኛ ሆኜ ተመድቤ ነበር፡፡ ከሌሊቱ 9፡30 አካባቢ የካፍቴሪያ ሠራተኞችንና ሻይ አፊዮችን ከየቤታቸው እየዞርኩ ለመጥራት ከተማ ወጥቼ መኪናው መንገድ ላይ ተበላሸብኝ፡፡ የተማሪዎች ቁርስ ሰዓት ከመድረሱ በፊት ሠራተኞችን መሰብሰብ ነበረብኝ፡፡ የመኪናው መበላሸት ግራ አጋብቶኝ አማራጭ ሳጣ በቀጥታ ወደ ጋሼ ኃይሌ መኖሪያ ቤት ሄጄ በሌሊት ቀስቅሼ ችግሬን አስረድቼ መኪናቸውን እየፈራሁ ካዋሱኝ ብዬ ሄድኩ፡፡ እንደፈራሁት ሳይሆን ‘ችግር የለም አንተ ሄደህ መኪናህን ጠብቅ እኔ ሄጄ ሠራተኞችን አመጣቸዋለሁ’ ብለው ሲነሱ ማመን ነው ያቃተኝ፡፡ አንድ ሥራ አስኪያጅ የሆነ ሰው እንዴት እንዲህ ያደርጋል? ብዬ እስካሁን ድረስ ይገርመኛል፡፡ እኔም ታዲያ አሁን ድረስ ይህ ዩኒቨርሲቲ የጋሼ ኃይሌ ወንድ ልጅ እንደሆነ እንዳስብ በደንብ ነው ያሳመነኝ፤” በማለት ይገልጸዋል፡፡

በድኅረ ኃይለ ማርያም ያረበበው መንፈስ
1993 ዓ.ም. ከቀድሞ ዓመታት ሁሉ በአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንትቲትዩት ውስጥ ላሉ መምህራንና ሠራተኞች በጣም አሳዛኝና የአብዛኞችን ስሜት የነካ ዓመት እንደነበር የሚገልጹት ጥቂቶች አይደሉም፡፡ ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ሠራተኞች በአስተዳደር ክህሎታቸውና በቀና ባህሪያቸው የሚያደንቋቸውንና የሚወዷቸውን አለቃቸውን የሚያጡበት ‹‹ጥቁር ቀን›› የሆነባቸው ዓመት ነበር፡፡

ለፖለቲካ ኃላፊነት በሹማምንት ተመርጠው አቶ ኃይለ ማርያም “ወንድ ልጃቸው” የሆነውን ተቋም ለቀው አዲሱን ኑሮአቸውንና የሥራ መስካቸውን ወደ ሐዋሳ አደረጉ፡፡ የደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  ክልል ምክትል አስተዳዳሪ ሆኑ፡፡  ይህ ያልተጠበቀ ዝውውር  የአቶ ኃይለ ማርያምን ለታላቅ ኃላፊነት የሚያበቃ፣ ወደፊት ለታላቅ አገራዊ ኃላፊነት የሚፈለጉ ግለሰብ ለመሆናቸው ፍንጭ ተደርጎ በብዙዎች የተገመተ ቢሆንም፣ ለተቋሙ አስደንጋጭ መርዶ መስሎ ታይቶ ነበር፡፡

ከክልል አስተዳዳሪነት እስከ ፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን እርከን ድረስ የተረማመደው የኃይለ ማርያም ፈጣን ግስጋሴና ስኬት፣ ለዛሬዎቹ የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኞች አስደሳች ክስተት ብቻ ሳይሆን “ኩራታቸውም” ጭምር እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

አብዛኞቹ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኞች ስለ ቀድሞ ባልደረባቸውና አለቃቸው  ተመሳሳይ ቋንቋ እንደሚናገሩ በግልጽ መታዘብ ይቻላል፡፡ “እጅግ ቅን”፣ “ሰው አክባሪ”፣ “ጥልቅ የሥራ ፍቅር ያላቸው”፤ “ሁሌም ለአዲስ ነገር የሚተጉ” እና ብዙ ተመሳሳይ የሙገሳና የአድናቆት ቃላት የኃይለ ማርያም መገለጫ ባህሪዎች ሆነው የቀሩ አገላላጾች ናቸው፡፡ ዛሬም በሁሉም ዘንድ በአንድ ቋንቋ ይነገራሉ፡፡

በዩኒቨርሲቲው የተገነቡ የማስፋፊያ ሕንፃዎች እንደ አንድ መገለጫዎቻቸው ተደርገው ይታያሉ፡፡ ለዘመናት የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ማነቆ የነበረው የመምህራን ፍልሰት ሲሆን፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ አቶ ኃይለ ማርያም የወሰዱዋቸው ዕርምጃዎች አሁንም ድረስ ይጠቀሳሉ፡፡ በአርባ ምንጭ ከተማ የሚገኘውን ብቸኛ የማኅበረሰብ ትምህርት ቤት ያሠሩት አቶ ኃይለ ማርያም መሆናቸው ሲነገር፣ በወቅቱ በከተማው ውስጥ በየቤቱ በእግራቸው እየዞሩ ወላጆችንና የከተማ ነዋሪዎችን ለማሳመን ብዙ እንደደከሙ  ይናገራሉ፡፡ “ዛሬ በዚህ የማኅበረሰብ ትምህርት ቤት   የሚማሩ ተማሪዎች ዩኒፎርም ለብሰው በከተማው ሲንቀሳቀሱ ሳይ ዕንባዬ ይመጣል፤” በማለት አቶ ኃይለ ማርያም ይናገሩ እንደነበር የሚያጫውቱን የድሮ ባልደረቦቻቸው ናቸው፡፡

የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ ግንባታ ሲጠናቀቅ በወቅቱ በነበሩት ኮንትራክተር ለአቶ ኃይለ ማርያም ምን እናድርግልዎት በማለት ለቀናነታቸው፣ ለሥራ አክባሪነታቸውና ለአስተዳደራዊ ተግባራቸው እንደ ውለታ ተቆጥሮ እጅ መንሻ ይቀርብላቸዋል፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም ግን በግላቸው ለዋሉት ውለታ ምንም ነገር ተቀብለው ወደ ኪሳቸው ማስገባትን አልፈለጉም፡፡ ይልቁንም ለተቋሙ መምህራንና ለተራ ሠራተኞች ሳይቀር ለልጆቻቸው መማሪያ የሚሆን ግቢው ውስጥ መዋዕለ ሕፃናት እንዲገነቡላቸው ይጠይቃሉ፡፡ ኮንትራክተሩም ይህን ለማድረግ ወደ ኋላ አላሉም፡፡ ዛሬ የሁሉም ሠራተኞች ልጆች በተሠራላቸው መዋዕለ ሕፃናት እየቦረቁ በጨዋታና በመዝናናት  የጨቅላነት ዕድሜ ትምህርን ይቋደሱበታል፡፡  በዚህ አነስተኛ መዋዕለ ሕፃናት ውስጥ ከመጀመርያዎች ተማሪዎች ውስጥ የራሳቸው የኃይለ ማርያም ልጆችም የመጀመሪያዎቹ ተመራቂ ሕፃናት ነበሩ፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም እጅግ በጣም ብዙ የሚነገርለት ታሪክና አሻራቸውን ጥለው ሄደዋል፡፡ ሥራ ወዳድነታቸው አሁንም ድረስ የሚዘከር ቢሆንም ብዙዎቹ ከባለቤታቸው አንደበት እንደሰሙት ያስታውሳሉ፡፡

በ1993 ዓ.ም ዩኒቨርሲቲው ለአቶ ኃይለ ማርያም ደማቅ የመሸኛ ዝግጅት አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በዚህ የሽኝት ሥርዓት ላይ ከተገኙ እንግዶች አንዷ በወቅቱ ብዙም ያልተነገረላቸው ወይዘሮ ሮማን ተስፋዬ የአሁኗ ቀዳማዊት እመቤት ነበሩ፡፡ ስለ ባለቤታቸው አስተያያት እንዲሰጡ ዕድል የተሰጣቸው ወይዘሮ ሮማን፣ “አቶ ኃይለ ማርያም ሙሉ ጊዜውንም ሆነ የዕረፍት ሰዓቱን በሥራው ላይ ስለሚያተኩር ለልጆቹና ለቤቱ ጊዜ የለውም፡፡ እኛም በዚህ የተነሳ በጣም ተቸግረናል፤” ብለው የተናገሩትን አሁንም ሠራተኞቹ ያስታውሱታል፡፡

ኃይለ ማርያም ተክለውት ያለፉት ስምና አሻራ ከዚያ በኋላ ለሚመጡ ኃላፊዎችም ልዩ ትርጉም የሚሰጥና ራሳቸውን እንዲፈትሹ የሚያደርግ መሆኑን ደግሞ የሚገልጹት የአሁኑ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ፈለቀ ወልደየስ ናቸው፡፡ የዛሬ 11 ዓመት ዶክተር ፈለቀ ወደ ዩኒቨርሲቲው ሲመጡ አቶ ኃይለ ማርያም ሐዋሳ ከተማ የደቡብ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሆነው እየሠሩ ነበር፡፡ “አቶ ኃይለ ማርያም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸው ለዚህ ዩኒቨርሲቲ ታላቅ ክብር ነው፤” ይላሉ፡፡

የኃይሌ መክሊት ቄስነት ወይስ አገር መሪነት?
ኃይለ ማርያም በብዙ ሁኔታ በተቋሙና በአርባ ምንጭ ከተማ እያሳዩት የመጡት ተፅዕኖና የገነቡት መልካም ስም በተለያዩ ወገኖች አስተሳሰብ ለብዙ ቁምነገሮች እስከ መታጨት አድርሷቸው ነበር፡፡ ከዚህም አንዱ ቢሾፕ ህዝቅኤል የሚያስተዳድሩት ቤተ ክርስቲያን አንዱ ተጠቃሽ ነው፡፡ በዚህ መሰል ጉዳዮች የአሁኑን የአገሪቱ መሪ ብዙ ያልተነገሩ ወጎችን መስማት ያስፈልጋል፡፡

ጊዜው 1983 ዓ.ም. ነው፡፡ ቢሾኘ ህዝቅኤል ኃይለ ማርያም  በዕምነቱ ያለውን ቀናኢነትና የአገልግሎት ብቃት በደንብ ይገመግሙና አንድ ነገር ማድረግ እንዳለባቸው ውሳኔ ላይ ይደርሳሉ፡፡ ይህም የኃይሌን የዕምነት አገልግሎት ላቅ ወዳለ ደረጃ ማሳደግና ፍፁም የሃይማኖት ሰው ማድረግ ነበር፡፡ እናም በውሳኔያቸው መሠረት ቢሾፑ በተጠቀሰው ዓመት በወርኃ ጥር የቤተ ክርስቲያኒቷን ዋና ዋና አገልጋዮች፣ አስተዳዳሪዎችና ቀሳውስትን ሰብስበው አንድ አዲስ ነገር ለማብሰር ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡ በሐሳባቸው መሠረት በአገልግሎቱ የተማመኑበትና የመረጡት ደቀ መዝሙራቸው የሆነውን ኃይለ ማርያም “ቄስ” አድርገው ሊቀቡት ነበር ዝግጅታቸው፡፡

በቤተክርቲያኗ ሕግና ትውፊት መሠረት አንድ አገልጋይ በቄስነት ማዕረግ ከተቀባ በተለያዩ ዓለማዊ የሥስራ መስኮች እንደ ፖለቲከኛ፣ ነጋዴነት፣ ወዘተ የመሳሳሉት ነገሮች ውስጥ መሳተፍ አይችልም፡፡

ብዙውን ጊዜ በተለያዩ አጋጣሚዎች የተሞላው የኃይለ ማርያም ሕይወት ግን  “ቄስ” የመሆን መክሊት የነበረው አይመስልም፡፡ ለመቀባት አንድ ወር ሲቀረው በወርኀ ታህሳስ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን ለመማር ወደ ፊንላንድ ሄደ፡፡ “እኔ ለቄስነት ባስበውም እግዚአብሔር ግን በራሱ መንገድ ወሰደው” ይላሉ ቢሾፕ ህዝቅኤል፡፡

ትንሽ ምክር ስለ ፖለቲካ
የአርባ ምንጭ ውኃ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በከተማዋ የልማት ጉዳዮች ላይና ለክልሉ በሚያበረክተው እገዛ ምክንያት የኃይለ ማርያምን አስተዋጽኦና የአስተዳደር ክህሎት የፖለቲካ ሽማምንትን ቀልብ ገና በጠዋቱ ገዝቶት ነበር፡፡ እናም ኃይለ ማርያም በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደአሕዴን) አባል ሆኖ ክልሉንና ሕዝቡን እንዲያገለገል ጥያቄዎች ይቀርቡለት ጀመር፡፡ የአካዳሚክና የዕምነት ሰው ብቻ ለነበረው መምህር ይህን ዓይነቱን ጥያቄ መቀበል ከፈጣሪው ጋር እንደመጋጨት አድርጎ ይቆጥረው ነበር፡፡ ጥያቄው ያልተፍታታና ለመወሰን ያስቸገረው ፈተና ሆኖበት ነበር፡፡

በእርግጥ ብዙ ጊዜ ኃይለ ማርያም እንዲህ ያሉ ጉዳዮች በራሱ ለመወሰን ሲያስቸግሩት እንደ አባቱ የሚቆጥራቸውን የሃይማኖት አባቱን ማማከር ይወድ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት ወደሳቸው ቀርቦ “ና ወደ ፖለቲካ ግባ፣ እዚህ የአንተ አገልግሎት ያስፈልገናል አገርህን እርዳ እያሉ ይጠይቁኛል፤” ብሎ እንደነገራቸው ቢሾፕ ህዝቅኤል ያወሳሉ፡፡ “ኃጢአት አይሆንብኝም?” ሲላቸው የቢሾፑ መልስ ምን ነበር? “እንደዚያ ብለው ጠሩህ? እንዲያስ ከሆነ ሂድ እግዚአብሔርን ባለሥልጣን ሆኖም ማገልገል ይቻል፡፡ አንተንም ይረዳሃል፤” በማለት አበረታቱት፡፡

መጽሐፍ ቅዱሳዊ መረጃዎችን በመጠቃቀስ አገርን ማስተዳደር እንደሚቻል ለኃይለ ማርያም አባታዊ ምክርና ማበረታቻቸው ተቸረው፡፡ “ዳንኤል የባቢሎን ጠቅላይ ሚኒስትር ነበር፣ መርዶክዮስ ጠቅላይ ሚኒስትር ነበር፡፡ ሳኦልንም ዳዊትንም መመልከት ትችላላለህ፤” በማለት ያስረዱታል፡፡ ቢሾፑ በኃይለ ማርያም ችሎታና ኃላፊነት የመወጣት ብቃት ይተማመኑበታል፡፡ “ማንኛውንም ጠባብ ነገር እሱ ዘንድ ሲመጣ ሰፊ ይሆናል፤” ይላሉ፡፡

የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሕልፈት ተከትሎ በአገሪቱ በቅርቡ የተደረገውን የሥልጣን ሽግግር በተመለከተ ቢሾፕ ህዝቅኤል የሚሉት አላቸው፡፡ “እሱን (ኃይለ ማርያም) ለማምጣት ይመስለኛል የፖለቲካ መተካካት ፖሊሲ የመጠው፤” በማለት ይናገራሉ፡፡

ቢሾፑ ግን የኃይለ ማርያም ለጠቅላይ ሚኒስትርነት መመረጥ ብዙም አላስደነቃቸውም፡፡ ምክንያቱም በፊት የሚጠብቁት ነበርና፡፡ “ለእኔ አስደንጋጩ የመለስ ዜናዊ በድንገት መሞት ነበር እንጂ ኃይለ ማርያም አሁን ይመረጣል ብዬ ቀድሜ ባልገምትም፣ ከሦስት ዓመት በኋላ በሚደረገው ምርጫ ግን እሱ የአገሪቱ መሪ እንደሚሆን እርግጠኛ ነበርኩ፤ ይላሉ፡፡

“የእሱ ቅንንት ለአገር የሚበቃ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ አሁን ሥጋትም የለኝም፤” የሚሉት ቢሾፕ ህዝቅኤል፣ “እሱም ፀልዩልኝ ትልቅ አገራዊ ሸክም ተሸክሜያለሁ ብሎኛል፤” ብሎ እንደነገራቸውም ያወሳሉ፡፡ 

አቶ ኃይለ ማርያም ሐዋሳ የክልሉ አስተዳደሪ ሆነው ትልቅ  ፈተና ከሆኑባቸው ጉዳዮች አንዱ በሲዳማና በወላይታ መካከል የተፈጠረው ሽኩቻ አንደነበር ቢሾፕ ህዝቅኤል ከቤታቸው በረንዳ ላይ ቁጭ ብለው ያስታውሱታል፡፡ “አንድ ጊዜ በዚህ በሐዋሳ ጉዳይ አሁን አስቸጋሪውን ጉዳይ ለመወጣት እየሞከርኩ ነው ያለሁትና ፀልዩልኝ ብሎኝ ነበር፤” የሚሉት ቢሾፑ፣ አቶ ኃይለ ማርያም እንዴት ከክልል ወደ ፌዴራል መንግሥት በአቶ መለስ ዜናዊ ጥሪ መሠረት እንደሄዱ ያብራራሉ፡፡

“በዚህ ጉዳይ ላይ በጣም ተቸግሮ ነበር፡፡ እናም ይህ የወላይታና የሲዳማ ጉዳይ እንዳስቸግረው ለመለስ ነግሬዋለሁ አለኝ፡፡ መለስስ ምን አለህ ብዬ ጠየቅኩት፡፡ አንተ እዚያው እኖራለሁ ብለህ ካላሰብክ በል ሁሉንም ነገር አስረክብና ዛሬ ና ብሎኛል ሲለኝ፣ በእሱ ልብ ውስጥ ገብተሃል ማለት ነው ስለዚህ ብትሄድ ይሻላል አልኩት፤” በማለት ወቅቱን ያስታውሳሉ፡፡

አቶ ኃይለ ማርያም በአራት ኪሎ በሚገኘው ታላቁ የምኒሊክ ቤተ መንግሥት መኖሪያቸውንና በአቅራቢው መሥሪያ ቤታቸውን ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አራት ኪሎ ታላቁ ቤተ መንግሥት እንዳሉም ይቆጠራል፡፡  ቢሾፕ ህዝቅኤልም አርባ ምንጭ በረንዳቸው ላይ ተቀምጠው ስለ ኃይለ ማርያም ስኬት ፈጣሪያቸውን በማመስገን ይደመማሉ፡፡ ስለ ኃይለ ማርያም ጉዞ ሲያስቡ ካንገታቸው ቀና ብለው ወደ ሰማይ ይመለከታሉ፡፡ ከመኖሪያ ቤታቸው ፊት ለፊት ባሠሩት ቤተ ክርስቲያን ጣራ ላይ ወዳለው ወደ መስቀሉም ቀና ብለው ይመለከታሉ፡፡ ከፍ ባለው እይታቸውም የኃይለ ማርያምን ወደላይ ማደግ በኩራት እያመለከቱ፣ የመንፈስ ልጃቸው አገሪቱን በሰላም እንዲመራ እግዚአብሔርን ይማፀናሉ፡፡

No comments:

Post a Comment