Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Sunday 25 November 2012

የሱሉልታ ከተማ ኢንቨስትመንት ባለሥልጣናት ጉቦ ሲቀበሉ ተያዙ

-    የወረዳው ሥራ አስኪያጅ በእስራትና በገንዘብ ተቀጡ
በታምሩ ጽጌ
በኦሮሚያ ልዩ ዞን የሱሉልታ ከተማ ኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ጌታቸውና የከተማው ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ መሸሻ ዘውዴ፣ 200 ሺሕ ብር ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ በኮሚሽኑ የክትትል ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር የዋሉት አቶ ዮሴፍና አቶ መሸሻ፣ በሱሉልታ ከተማ የኢንቨስትመንት ቦታ የተረከቡ አንድ ባለሀብት ግንባታ ለመጀመር የግንባታ ፈቃድ ለማውጣት ላቀረቡት ጥያቄ የጠየቁትን ጉቦ ሲቀበሉ መሆኑን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

ባለሀብቱ በ2000 ዓ.ም. የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስደው ቦታው ተለክቶ ሳይሰጣቸው የ2,500 ካሬ ሜትር ቦታ ካርታ ተሠርቶ በቅድሚያ እንደተሰጣቸው የሚያብራራው የኮሚሽኑ መግለጫ፣ መሬቱ በመሐንዲስ ተለክቶ እንዲሰጣቸው ለሦስት ዓመታት ምልልስ ካደረጉ በኋላ ግንቦት 13 ቀን 2004 ዓ.ም. ተሸንሽኖና ተለይቶ እንደተሰጣቸው ኮሚሽኑ አስረድቷል፡፡

ባለሀብቱ ግንባታውን ለመጀመር በጥቅምት ወር 2005 ዓ.ም. ቦታውን ሲያጥሩ ሁለቱ ኃላፊዎች በቦታው በመገኘትና ሕገወጥ መሆኑን በመግለጽ እንዳያጥሩ ማገዳቸውን ኮሚሽኑ ገልጾ፣ ባለሀብቱ ከሥራ አጋራቸው ጋር በመሆን የቦታ ባለቤትነት ማረጋገጫና የግንባታ ፈቃድ ሰነዳቸውን ይዘው ወደ ማዘጋጃ ቤቱ ማምራታቸውን ኮሚሽኑ አስታውሷል፡፡

ማዘጋጃ ቤቱ አቤቱታቸውን ተቀብሎ መልስ ለመስጠት ለጥቅምት 12 ቀን 2005 ዓ.ም. የቀጠራቸው ቢሆንም፣ ባለሀብቱ በቦታው ላይ ግንባታ ለማካሄድ ከፈለጉ 200 ሺሕ ብር ጉቦ መስጠት ከቻሉ ብቻ መሆኑን ኃላፊዎቹ በሌላ ግለሰብ በኩል መልዕክት እንዳላኩባቸው ኮሚሽኑ አስረድቷል፡፡

ባለሀብቱ ጉቦ እንዲሰጡ የተላከባቸውን መልዕክት በመቀበል፣ ጉዳዩን ለፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን በማሳወቃቸው፣ ኮሚሽኑ ክትትል አድርጐ ባለሀብቱ ጉቦውን በኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊው አቶ ዮሴፍ ባለቤት በወ/ሮ አቦነሽ በንቲ አማካይነት፣ ሰሜን ሆቴል ውስጥ ሲቀባበሉ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን አስታውቋል፡፡ ኮሚሽኑ በወንጀሉ አፈጻጸም ዙሪያ የጀመረውን ምርመራ አጠናቅቆ መዝገቡን ሥልጣን ላለው የኦሮሚያ የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ማስተላለፉን አስታውቋል፡፡


በሌላ በኩል፣ የጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ አሥር ሥራ አስኪያጅ አቶ ዓለማየሁ ካሳ ገብሬ የተባሉ ግለሰብም፣ ጉቦ ሲቀበሉ እጅ ከፍንጅ ተይዘው በተመሠረተባቸው ክስ፣ አራት ዓመት ከስድስት ወራት እስራትና በአምስት ሺሕ ብር እንዲቀጡ መወሰኑን ኮሚሽኑ አብራርቷል፡፡

የኮሚሽኑ ዓቃቤ ሕግ የመሠረተውን ክስ የመረመረው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 15ኛ ወንጀል ችሎት፣ ግለሰቡ ኅብረተሰቡን እንዲያገለግሉ መንግሥት የሰጣቸውን ሥልጣን አላግባብ በመጠቀም፣ አንዲት ግለሰብ ሰነድ አልባ ይዞታ ሕጋዊ እንዲሆንላት ጥያቄ በማቅረቧ፣ ሕጋዊ እንዲሆንለት ከፈለገች 150 ሺሕ ብር ጉቦ እንድትከፍላቸው በተደጋጋሚ ሲጠይቋት፣ ለኮሚሽኑ ጠቁማ 50 ሺሕ ብር በዘመዷ አማካይነት እንዲሰጣቸው በማድረጓ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን በውሳኔው ተገልጿል፡፡

No comments:

Post a Comment