Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Tuesday 27 November 2012

የወቅቱ የአገራችን የፖለቲካ ሁኔታና የወደፊት የትግል አቅጣጫ – በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር

መግቢያ
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ
Dr. Negaso Gidada Ethiopian politicianየሁላችንም የረጅም ጊዜ ህልም፣ አንድነትዋ የተጠበቀ የበለፀገች ኢትዮጵያን ማየት ነው፡፡ ወደዚያ ለመድረስ ሁሉም ኢትዮጵያውያን አስተዋጽኦአቸውን የሚያበረክቱበት ለአገሬ እሠራለሁ ብለው በነፃ አየር የሚተነፍሱበት ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ምህዳር እንዲፈጠር ካሁኑ ጀምረው እንዲታገሉ ሁኔታን መመቻቸት ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህም የፖለቲካ ምህዳሩን ማየትና ወዳለምነው ግብ ለመድረስ የሚረዱንን አቅጣጫዎች መዳሰሱ ጠቃሚ ነው፡፡
ስለአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ሁላችሁም ታውቃላችሁ፤ ሆኖም የግለሰቦች አረዳድ ሊለያይ ስለሚችል፣ እኔ የራሴን ግንዛቤ ለመግለጽ እሞክራለሁ፡፡
-   የኔን ግንዛቤ ስገልጽ የኔን ሃሳብና አመለካከት ብቻ ተቀበሉ ለማለት ሳይሆን ዛሬም ይሁን በቀጣይ በሚካሄዱ ውይይቶች የኔም ግንዛቤና አመለካከት እንደአስተዋጽኦ እንዲወሰድ ምኞቴ መሆኑን ሳልገልጽ አላልፍም፡፡
-   ከኔ አመለካከት ጋር የማይስማሙ እንዳሉም እገነዘባለሁ፡፡ በበኩሌ ከኔ ጋር የማይስማሙትን አከብራለሁ፡፡ ሃሳባቸውንና አመለካከታቸውን ባልጋራምና ባልስማ ማባቸው እነሱንም ሆነ ሃሳባቸውን፣ አመለካከታቸውንና አቋማቸውን አዳምጣለሁ አከብራለሁ፡፡ የመረጃ ስህተት ካለ ስህተቴን ለመቀበልና ለማረም ዝግጁ ነኝ፡፡ የኔን ሃሳብ፣ አመለካከትና አቋም የማይጋሩት ግን እንዲያዳምጡኝና እንዲያከብሩልኝ አደራ እላለሁ፡፡
-   ስላገራችን የፖለቲካ ሁኔታ ዛሬ ሁሉንምና ዝርዝሮችን ለመተንተን አይቻልም፡፡ ስለሆነም በኔ እይታ መነካት አለባቸው የምላቸውን አንዳንድ ጉዳዮች ብቻ አነሳለሁ፡፡ የቤቱ ንቁ ተሳትፎ ውይይታችንን ያዳብራል ብዬ አምናለሁ፡፡ ስለሆነም በሠፊው እንድትሳተፉ አደራ እላለሁ፡፡ ይህ የኔ አስተያየት ለውይይታችን መነሻ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
  1. 2.   የአጋራችን የወቅቱ የፖለቲካ ሁኔታ
2.1    የሕዝብን  ሁኔታ፡-
-     ህብረሰባችንን ስናይ ብሶተኛና የማጉረመርም ደረጃ ላይ እንጂ ተናድዶ ንዴቱን በእንቅ ስቃሴ ለማሳየት ዝግጁ የሆነበት ደረጃ ላይ የደረሰ አይመስልም፡፡
-    ብዙ የማህበራዊና የኢኮኖሚ ችግሮች አሉበት፡፡ ይህንን ሰቆቃውንና ብሶቱን ያማርራል፡፡
-    በይፋና በአደባባይ አይገልጽም፡፡
-    ብሶቱ በማጉረምረም ደረጃ የሚገልጽ ነው እንጂ በአጠቃላይ ወደ ሕብረተሰባዊ ንዴት አልተለወጠም፡፡
-    ተናጠል ንዴቶች አልፎ አልፎ ቢገለፁም ሠፊና የአጠቃላይ ሕብረተሰቡ አልሆኑም፡፡

-    እነዚህ ተናጠልና ትናንሽ ንዴቶች ወደ ተደራጀና የተቀናጀ ሕዝባዊ እምቢተኘነት እና የእምቢተኘነት እንቅስቀሴዎች አልተለወጡም፡፡ በሌሎች አገሮች በዳቦ ወይም በነዳጅ ዋጋ ላይ ትንሽ ጭማሪ ከታየ የህብረተሰቡ ንዴት ይገነፍላል፡፡ በኛ ህዝብ ዘንድ ግን ይህ አይታይም፡፡ ምልክት ከታየም ጥቂት፣ ተናጠል፣ ያልተደራጁና ያልተቀናጁ ናቸው፡፡
2.2  ገዢው ፓርቲ Authoritarian ነው አምባገነን ነው
-    ኢህአዴግ ለሕዝብ ፍላጎት ደንታ የማይሰጥ ድርጅት ነው ፡፡
-    የሕዝብን ፍላጎት አያዳምጥም፡፡
-    ሕዝብ እሱን ብቻ መስሎ እንዲያድር የሚፈልግ ነው፡፡
-    ከሀገርና ከሕዝብ ይልቅ ፓርቲውን ያስቀድማል፡፡
-    በሕገ-መንግሥቱ የተረጋገጡትንና በአንቀጽ 29፣ 3ዐ፣ 31፣ እና 38 የተዘረዘሩትን መብቶች አፍኖአል፡፡
-    ተቃዋሚዎችን ለማጥቃት ብሎ ህጎችን በማውጣት፣ ሕግን አስከብራለሁ እየለ ሰብአዊ መብቶችን ይጥሳል፡፡
-    ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዳይኖሩ አድርጎአል፣ ሦስቱም የመንግሥት አካላት ለሕዝብ አገልጋዩች  ሳይሆኑ የፓርቲው መሣሪያ  ሆነዋል፡፡
-    ገዢው ፓርቲ ሕገ-መንግሥቱን አያከብርም በሕገ-መንግሥቱ የተከበሩ መብቶች ተግባራዊ ይሁኑ ሲባል አይፈቅድም፡፡ ሕገ-መንግሥቱ የሚሻሻልበትን መንገድ ከመክፈት ይልቅ በሚያወጣቸው ሕጎች በእጅ አዙር ያሻሽላል፡፡ በአሠራሩ የሕገ-መንግሥታዊ አስተሳሰብን ዋጋ አሳጥቷል፡፡
2.3  የፓርቲ ሥርዓታችን ዴሞክራሲያዊ አይደለም
-    በሕገ-መንግሥት ቢደነገግም ዴሞክራሲያዊ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ባገራችን የለም፡፡
-    እንደሚታወቀው በንጉሱ ዘመን በፓርቲ መደራጀት ክልክል ነበር፡፡
-    በደርግ ዘመን በመጀመሪያ ዓመታት ለደርግ ታማኝ የሆኑ ለስሙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢወለዱም በመጨረሻ ግን አገሪቱ በአንድ ፓርቲ ብቸኛ ሥርዓት (ኢሠፓ)ሥር ወደቀች፡፡
-    ኢህአዴግ  የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ይመሠርታል ተብሎ ቢጠበቅም እሱ ግን የአውራ ፓርቲን ሥርዓት የሚከተል ሆነ፡፡
-    ይህም አውራ ፓርቲነት እንደ አሜሪኮና እንደ ታላቋዋ ብርታንያ ዴሞክራሲያዊ የሆኑ የሁለት ፓርቲዎች አውራነት  ቢሆን ባልገረመን፤   ወይም እንደ ጃፓንና እንደ እነ እስራኤል ዴሞክራሲያዊና መድብለ ፓርቲ ሥርዓት በሰፈነበት አውራ ሆኖ ቢወጣ እንቀበል ነበር፡፡ እርሱ ግን በአስገዳጅነት አንድ አውራ ፓርቲ ሆኖ ሌሎች ግን እንደ   ጫጩት እንኳ እንዳይኖሩ አድርጓል፡፡
-    እሱን የሚገዳደሩ ጠንካራ ፓርቲዎች እንዳይኖሩ በሙስና አሠራር  በ Patronage እና በልዩ ልዩ ተጽእኖ ለማዳ ያደርጋቸዋል ወይም ከነጭራሸ እንዲጠፉ ያደርጋል፡፡
2.4  ብልሹ የምርጫ ሥርዓት አለን
-   የምርጫ ሥርዓታችን ለአገራችን ውስብስብ ሁኔታ ምቹ  አይደለም፡፡ ብዙ ብሔር ብሔረሰቦች፣ ብዙ ኃይማኖቶችና የተለያዩ ርዕዩተ ዓለመች ባሉበት ሀገር አሸናፊው ሁሉን የሚወስድበት (First-Past-the Post)  ሥርዓት አይመችም ፡፡
-   ማህበረሰባዊ ውክልና፣ ተጠያቂነት እና አሳታፊነት  (Participatory) መርህን የተከተለ የተመጣጠነ Proportional ሥርዓት እንዲኖር አይፈለግም፡፡
-   ይባስ ብሎ በምርጫዎች መሀከልና በምርጫዎች ወቅት ያለው የፖለቲካ ሜዳ (ምህዳር) የተስተካከለ አይደለም፡፡  ዴሞክራሲያዊ ፍትሐዊና ነፃነት የተሞላበት አይደለም፡፡
- በዚህ የምርጫ ሥርዓት ውስጥ ተሸናፊ ፓርቲዎችን የሚመርጥ ብዙ ሚሊዮን የሕዝብ ክፍል በፖርላማ  ደረጃ ድምጽ አልባ ይሆናል ማለት ነው፡፡
2.5 የፖለቲካ ልዩነቶች /ችግሮች አፈታታችን ልምድ መፍትሔ ሰጪ ሳይሆን የሚያባብስ ነው
-   ባገራችን የፖለቲካ ችግሮች የሚፈቱት በሠላማዊ መንገድ በውይይትና በድርድር ሳይሆን፤ በአስተዳደራዊ፣ ወይም በጉልበት ነው፡፡
-   ብዙውን ጊዜ በግለሰቦችና በድርጅቶች ዘንድ ህዝብንና ሀገርን ከማስቀደም ራስን ማስቀደም ይታያል፡፡
-   በግለኝነት (የራስን ፍላጎት ማስቀደም) ላይ የተመሠረቱ ልዩነቶችን፣ (የሥልጣን ፍላጎት፣ ለራስ ዝና፣ ገንዘብ/ሀብት ለማግኘት) መፍታት በጣም አስቸጋሪ ናቸው፡፡
-   ያገራችን የፖለቲካ ኃይሎች ልዩነቶችን ለመፍታት፤ የሕዝብ ወሳኝነትን ለመቀበል አይፈልጉም፡፡   ህዝብ ፡-
- በምርጫ፣ ወይም
- በህዝበ ውሳኔ፡፡ (Referendum) ችግሮችን እንዲፈታ አይፈለግም፡፡
-   ብዙውን ጊዜ ውይይቶች/ ድርድሮች የሚፈርሱት ተደራዳሪዎች
ቅድመ ሁኔታዎችን ስለሚያስቀምጡ ነው፡፡
-   ለህዝብና ለሀገር ጥቅም ሲባል ሠፊና ሀገራዊ የትብብር መድረክ ለመፍጠር ፈቃደኝነትና ዝግጁነት ደካማነው፡፡
-   በፖለቲካ ፓርቲዎች ዘንድ የተለመደው በአሸናፊነት የማንበርከክ ፍላጎትና የበላይነት ማስፈን አካሄድ ነው፡፡  እምቢ ከተባለ ደግሞ ለመጥፋትም መንቀሳቅ አለ፡፡
2.6 የሠላማዊ ትግል ስልቶችን መጠቀም አልተጀረም
-   ሠላማዊ ትግል Passive መሆን አይደለም፡፡ ሠላማዊ ትግል በእንቅስቃሴ የተሞላ ትግል ነው፡፡
-   ሠላማዊ ትግል፣ ኃይል/ጉልበት አልባ፣ ህጋዊ፣ ህገ-መንግሥታዊና ዴሞክራሲያዊ ነው፡፡ ሌላን ለመጉዳት /የታለመ አይደለም፡፡
-   ሠላማዊ ትግል አንዳንድ ውሳኔዎች፣ አንዳንድ ሕጎችና አንዳንድ ተቋማት የራስን ወይም የሌላን ሰው መብቶች የማነኩ ከሆነ ለነዚህ ውሳኔዎች፣ ሕጎች፣ ወይም ተቋማት እምቢ ማለትንና ያለመታዘዝን ያካትታል /የሚጠይቅ ነው፡፡
-    ሠላማዊ ትግል ዜጎች ባለመታዘዝ፣ ለመከላከያነት የሚጠቀሙበት የተቃውሞ መሣሪያ ነው እንጂ የነውጥ ወይም የአመጽ መሣሪያ አይደለም፡፡
-     የሠላማዊ ትግል ዓይነቶች ብዙ ናቸው፡፡
ለምሳሌ ያህል፡- የአዳራሽ ወይም የአደባባይ ስብሳዎች፣ Sit-ins፣ አድማ/መታቀብ Boycott (ሥራ፣ ትምህርት፣ ግዥ፣ ምርጫ) እና ሰልፍ የተለመዱ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ውስጥም ባገራችን ተግባራዊ እየሆኑ ያሉት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
-   ሠላማዊ ትግል ሠፊ  የመደራጀት፣ የዝግጅት ሥራን ይጠይቃል፡፡
2.7 ውጫዊ ኃይልን የመጠበቅ ልምድና ባህል የተንሰራፋበት አገር ውስጥ ነን
-   ለችግሮች መፍትሔ መለካታዊ ኃይልን መጠበቅ አለ፡፡
-   ዜጎች ለራሳቸውና ለሌሎች ዜጎች መብቶች መከበር በራስ ከመታገል ይልቅ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ይጠብቃሉ፡፡
-   ከግለሰቦችም ፈውስ የመጠበቅ አዝማሚያም ይታያል፡፡
-   የውጭ ኃይሎች (መንግሥታት) ችግሮቻችን ይፈቱልናል ብሎ መጠበቅም አለ፡፡
-   ይህ ሁሉ መንም ውጤት እንዳላስገኘ መላልሰን አይተናል፡፡
3. የወደፊት ትግላችን አቅጣጫ ምን መሆን አለት፣
3.1 ህዝብን ለለውጥ እንዲንቀሳቀስ ለማድረግ፣
-   የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች በስፋት መሠራት አለባቸው፡፡
-   የመረጃ መስጫ ዘዴዎች መጠናከርና መስፋት ይኖርባቸዋል፡፡ (ለምሳሌ ዘመናዊ/ማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን)
-   በሕዝብ ውስጥ የማደራጀትና የማቀናጀት ሥራዎች መሠራት አለባቸው፡፡
-   እውቀት የሌለው፣ መረጃ የማያገኝ ህዝብ፣ የተደራጀና የተቀናጀ አደረጃጀቶች የለለው ሕዝብ ለውጥ ሊያመጣ አይችልም፡፡ ከፖለቲካ ድርጅቶች የሚጠየቀውና የሚጠበቀው የተናደደ ሕብረተሰብን መፍጠር ሳይሆን መረጃ የሚያገኝ፣ እውቀት ያለው፣ የተደራጀና ድርጅቶቹ የተቀናጁ ሕብረተሰብ መፍጠር ነው፡፡
-   ስለሆነም የወደፊት የትግል አቅጣጫችን የማሳወቅ፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ የማደራጀትና፣ ድርጅቶችን የማቀናጀት ሥራን ማዕከል ያደረገ መሆን አለበት፡፡
3.2 ገዢውን ፓርቲ በተመለከተ፡-
  – የትኛውም ገዢ መደብ ተገድዶ እንጂ በልመና፣ በመለማመጥ በፈቃደኝነት ህዝብ የሚፈልገውን ለውጥ አያመጣም፡፡ ገዢው ፓርቲ ለለውጥ የሚገደደው በሕዝባዊ ኃይል ብቻ ነው፡፡ ገዢውን ፓርቲ ለለውጥ የሚያስገድድው ህዝባዊ ሠፊ እንቅስቃሴ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ገዢውን ፓርቲ ለማስገደድ ህዝባዊ እንቅስቃሴ የሚፈጠርበትን መንገዶች መቀየስና በነሱ ላይ መሥራት የወደፊት የትግል አቅጣጫችን መሆን አለበት፡፡
3.3  የፓርቲ ሥርዓታችንን የመለወጥ ሥራ አንዱ የትግል አቅጣጫችን መሆን አለበት
-   ይህም የሚሆነው ገዢው ፓርቲ የሚጠቀመውን  Patronage (አባታዊነት) እና የሙስና (Corruption)ስልት የፓርቲዎች አባላት፣ ደጋፊዎችና አጠቃላይ ህዝቡ እንዲታገሉት  ካደረግን ነው፡፡ ይህም አንድ የወደፊት የትግላችን አቅጣጫ ነው፡፡
-   ከዚህ አኳያ አንዳድ ተቃዎሚ ፓርቲዎች ከኢህአዴግ የሚሰጣቸው ድጎማ የጥገኝነትና የጠባቂነት ባህልን የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ ሙሰኝነት መሆኑን እንዲረዱ በቀጣይነት ማስረዳት ያስፈልጋል፡፡
3.4  ብልሹ የምርጫ ሥርዓትን መለወጥ የወደፊት የትግል አቅጣጫችን ማድረግ አለብን፡፡
-   ዴሞክራሲ በምርጫዎች ዘመን መሀከልም ሆነ በምርጫ ወቅትም መስፈን ያለበት ነው፡፡ ስለሆነም የፖለቲካ ምህዳር እንዲስተካከል በቁርጠኝነትና በቀጣይነት መታገል ይኖርብናል፡፡
-   ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ ተፈጥሮ ምርጫን በተመለከተ የተመጣጠነ (Proportional) የምርጫ ሥርዓት እንዲገነባ ለማድግ ሕገ-መንግሥቱ የሚሻሻልበትን ሁኔታ ለመፍጠር መታገል  አስፈላጊ ነው፡፡
-   ከአጭር ጊዜ አኳያ የትግል አቅጣጫችን ለ2ዐዐ5 ምርጫ የተስተካከለ ምህዳር እንዲፈጠር መታገል ነው፡፡
3.5  ችግሮችን ለመፍታት በጋራ መንቀሳቀስ
-       ላገራችን ችግሮች መፍትሔ ለማፈላለግ ሁሉን አቀፍ ብሔራዊ እርቅ መጥራት አስፈላጊ ነው፡፡   የፖለቲካ ችግሮችን/ልዩነቶችን ለመፍታት አንድነት በፕሮግራሙ ያስቀመጠው አቅጣጫ ትክክል ነው፡፡ ስለሆነም ችግሮችን በሠላማዊና ዴሞክራሲያዊ መንገድ በውይይትና በድርድር የመፍታትን ባህል የበለጠ መዳበር የትግላችን አቅጣጫ መሆን አለበት፡፡
ከአጭር ጊዜ አኳያ የመድረክ መፈጠር፣ የ11 ፓርቲዎች በቅርብ ጊዜ የፈጠሩት መቀራረብ፣ የ2ዐዐ5 ምርጫን በተመለከተ የ33 ፓርቲዎች አብሮ መሥራት መጀመር  
የዚህ አቅጣጫ ጅማሮ ነው፡፡ ስለሆነም የዚህን ዓይነት እንቅስቃሴ ማበረታትና መደገፍ ይጠበቅብናል፡፡ በቅርብ ጊዜ አንድ ሀገራዊ የምክክር ኮንፍራንስ እንዲጠራ የሚጠይቅ ሃሳብ እየተጠናከረ መጥቶአል፡፡ ይህን ጥሪ መደገፍና ማዳበር ይጠበቅብናል፡፡
-   ልዩነቶችን በጉልበትና በመሣሪያ ኃይል ለመፍታት መሥራት ይቅር፡፡
-   ለሥልጣን፣ ለዝናና ለሀብት ብለን መከፋፈልን እናቁም፡፡
-   ለውይይቶችና ለድርድሮች ቅድመ ሁኔታ አናስቀምጥ፡፡
-   የማንበርከክ/የማስጎብደድ ፍላጎት ባህል ይቅር፡፡
-   ፍፁማዊነትን አስወግደን ‹‹የልዩነት መኖር መብት ለዘላለም ይኑር››እንበል፡፡
-   ለህዝብ ወሳኝነትና የሥልጣን ባለቤትነት ጠንክረን በቀጣይነት እንታገል፡፡
-   የማጎብደድና የተንበርካቢነት ባህልን በጽናት እንታገል፡፡
-   ደፋር እንሁን፡፡ መጥፎ የሆነውን ነገር ከማስወገድ አንቆጠብ፡፡ መጥፎውን እናስወግድ እንጂ አንለማመድ፡፡
3.6 የሠላማዊ ትግል ስልት ባንድ በኩል የፈሪዎች የትግል ስልት ነው ብለው የሚያጣጥሉ አሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ሠላማዊ ትግል (Passivism) ነው ተብሎም ይወሰዳል፡፡  ነገር ግን የሠላማዊ ትግል ስልት ባግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ ትልቅ ውጤት የሚያስገኝ ነው፡፡  የሠላማዊ ትግል ስልት  ባገራችን ገና ባግባቡ ጥቅም ላይ አልዋለም፡፡ ስለሆነም የወደፊት የትግል አቅጣጫችን ለውጥን ለማምጣት የሠላማዊ ትግል ስልትን ባግባቡ መጀመርና ማዳበር መሆን አለበት፡፡ ሠላማዊ ትግል ባግባቡ መካሄድ አለበት ሲባል ግን ሠፊ ዝግጅት እና ጥንቃቄ እንደሚያስፈልግ መረሳት የለበትም፡፡
3.7  ውጫዊ ኃይልን ከመጠበቅ ይልቅ በራስ መተማመንና የራስን ችግር ለመፍታት በራስ መንቀሳቀስ እንዲለመድ ለማድረግ መሥራት ሌላው የወደፊት በትግላችን ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም በሁሉም የሀገራችን  የኃይማኖት ተቋማት ይህን በተመለከተ የአመለካከት ለውጥ መምጣት ያስፈልጋል፡፡ ቤተሰብ፣ ትምህርት ቤትና የመገናኛ ብዙሃንም ከዚህ አኳያ የማይናቅ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡
የኔን ችግር ፍታልኝ ብሎ ከመፀለይ ችግሮቼን ራሴ ለመፍታት እንድችል ጉልበት ስጠኝ ብለን አምላክን መለመን  ይኖርብናል፡፡
በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ  የአንድነት ፓርቲ ሊቀመንበር
ለአንድነት ፓርቲ የህዝብ ግንኙነት ክፍል
ለአባላት ትምህርታዊ ፕሮግራም የቀረበ ወቅታዊ የመነሻ ጽሁፍ
ህዳር 16 ቀን 2ዐዐ5 ዓም
አዲስ አበባ

No comments:

Post a Comment