Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Sunday, 13 May 2012

የሰዉ ልጅ ከእንስሳት ሲያንስ

በሀብተጊዮርጊስ ለገሰ /ኦስሎ ኖርዌይ/
በልጅነት ትዝታ ልጀምረዉ፣፣ተመልሶ የማይገኘዉ ይህ ጊዜ የምንሰራዉ ነገር ሁሉ ትክክል የሚመስለን ወቅት ነበር፣ ፣ ግልጽ የሆነ ዓላማ ለሌለዉ በሰፈር ተከፋፍለን በሰንሰለት፣ በብረት ቦክስ፣ ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በታዋቂ የድብድብ መሪዎቻችን አማካይነት ስንቧቀስ ዉለን ስንገባ ጀብደኝነት ይሰማናል፣፣ ከትልልቆቹ ተደባዳቢዎች አይበገሬዉ የዉሀ ስንቁ ሰፈር ተፈራ ትዝ ይለኛል፣ ፣ ለብዙዎቻችን ያ በልጅነት በጭካኔ እርስ በርስ ስናደርገዉ የነበረዉ ድብድብ ለዛሬዉ ፍቅራችን መሰረት ሁኗል፣ ፣ ነገር ግን በዚህ የጭካኔ ድርጊታቸዉ የቀጠሉ እንዳሉም መዘንጋት የለብንም፣ ፣ ከነዚህም ዉስጥ የሀገር መሪነት ደረጃ ለይ የደረሱ ጨካኞችም በአለማችን ተከስተዋል፣ ፣ እነዚህ መሪዎች በልጅነታዉ የተጠናዎታቸዉ ጥላቻና የበታቸኝነት ስሜት የወለደዉ ጭካኔ የዛሬዉ ሰይጣናዊ ድርጊታቸዉ ነጸብራቅ ሁኗል፣ ፣ እነዚህ መሪዎች ለበቀልና ለተንኮል ስል የሆነ አእምሯቸዉን በመጠቀምና የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍልን በማሳመን በጠላትነት የሚፈርጇቸዉን ሌሎች የህብረተብ ክፍልና ግለሰቦችን ለሞትና ለጉዳት ዳርገዋል፣ ፣
ጋብርኤል ማርሴል (Gabriel Marcel) የተባሉት ምሁር ልባቸዉ በጥላቻና በጭካኔ የተሞላ መሪዎች ወይም ግለሰቦች የተወሰነ የህብረተሰብ ክፍልን ለማጥፋት ወይም ለመጉዳት ሲፈልጉ የዚህን የህብረተሰብ ክፍል የሰዉ ልጅነት በመሸፈን ከሰዉ ልጅነታቸዉ የሚያሳንሳቸዉ (Dehumanization) ሀሳባዊ የሆነ ስም በመስጠት(The spirit of Abstract idea) ይህንንም የሰዉ ልጅነታቸዉን የሚያስረሳ ሀሳባዊ ስም በተከታዮቻቸዉና በተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል አእምሮ ዉስጥ እንዲሰርጽ በማድረግ ዓላማቸዉን ያሳካሉ ይሉናል፣ ፣
ከቀደምት የዓለም ታሪክ እንደምንረዳዉ የባሪያ አሳዳሪዎች የሰዉን ልጅ እንደፈለጉት የሚያዙት የእራሳቸዉ ሀብት ለማድረግ ሲሉ የሰዉ ልጅ መሆናቸዉን በመካድ ባሪያ የሚባል ስም በመስጠት እንደ ዕቃ ሲጠቀሙባቸዉ መቆየታቸዉ ይታወሳል፣ ፣ የጀርመኑ ሂትለር በተጠናወተዉ የበታችነት ስሜት ለበቀል በመነሳሳት የእስራኤላዉያንን የሰዉ ልጅነት አይጥ (Rats) በሚል በመጥፎ መንፈስ በተሸፈነ ስም አብዛኛዉን የጀርመንን ህዝብ በማሳሳት 6 ሚሊዮን እስራኤላዉያን ለህልፈት ሕይወተ አብቅቷቸዋል፣ ፣አሜሪካኖች ጃፕስ (Japs) የሚባል ስም ለጃፓኖች በመስጠትና በጠላትነት በመፈረጅ ንጹህ የጃፓን ህዝብ ሁለት ጊዜ በአዉቶሚክ ቦንብ እንዲቃጠል ከማድረግ ባሻገር አካለ ጎደሎ የመፍጠር አባዜዉ እስከአሁኑ ትዉልድ ድረስ ቀጥሏል፣ ፣
በሩዋነዳም ቱትሲዎችን በረሮ (Cockroach) በማለት የተፈጸመዉ እልቂትና ባይሳካለትም ጋደፊ ተቃዋሚዎችን ለማጥፋት እነዚህን አይጦች ጨርሷቸዉ ብሎ ያቀረበዉ የህዝብ ጥሪ የመሪዎች የጭካኔና የጥላቻ ድርጊት ምሳሌዎች ናቸዉ፣፣
በአገራችንም ጠ/ሚኒስትር መለስና ተከታዮቻቸዉ የአማራን የሰዉ ልጅነት በመካድና ነፍጠኛ የሚል በመጥፎ ድርጊት የተሸፈነ መንፈሳዊ ስም በመስጠት ድርጅታቸዉ ከተጠነሰሰበት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ይህንን ዘር የማጥፋትና የመጉዳት (ስነ ልቦናዊና አካላዊ) ሴራ በስልት ቀጥለዉበታል፣፣የጉራፈርዳ አማሮች መፈናቀል የዚህ ሴራ አንዱ አካል ነዉ፣፣የወደፊቱን ተስፋ ሰንቆ፣የሚጓዘዉና በፍቅር የተሳሰረዉ ቤተሰብ፣ ስለዚች ዓለም ክፋት ምኑንም የማያዉቁት ህጻናትና ንጹሀን ዜጎች የዚህ ኢሰብአዊ ድርጊት ሰለባ ሲሆኑ አብዛኞቻችን በዝምታ እያየነዉ ነዉ፣ ፣ይህ ድርጊታችን ደግሞ ከእንስሳ የሚያሳንሰን ይሆናል፣፣
ሆፍማን(Frank L.Hoffman) የአእምሮ ህክምና መጽሄት(Journal of Psychiatry 1964.3) በዝንጀሮ ላይ ያቀረበዉን የቤተሙከራ ሪፖርት መስረት በማድረግ የሚከተለዉን ትንታኔ ሰጥተዋል፣፣
በዚህ ብዙ ዝንጀሮዎች በተሳተፉበት ቤተሙከራ በባለቀለም መብራቶች ጠቋሚነት መሰረት በቀኝ ወይም በግራ በኩል ያሉትን ገመዶች ሲስቡ ዝንጀሮዎቹ ምግብ እንደሚያገኙ በቅደም ተከተል እንዲለማመዱ ተደረገ፣ ፣ይህንን ልምምድ ካደረጉ በሗላ ዋናዉ የቤተ ሙከራ ስራ ተጀመረ፣ ፣ከዋናዉ ቤተሙከራ መጀመር ጋር ምግብ ለማግኘት ትክክለኛዉን ገመድ በሚስቡት ዝንጀሮዎች ትይዩ በመስታዎት ዉስጥ ሌላ ዝነጀሮ እንዲቆም ተደረገ፣፣ የተራበዉና ምግብ ፈላጊዉ ዝንጀሮ ምግብ ለማግኘት ባለቀለም መብራት በሚበራበት በኩል ያለዉን ገመድ ሲስብ ሌላኛዉ ገመድ ፊትለፊት መስታዎት ዉስጥ ያለዉን ዝንጀሮ የኤለክትሪክ ንዝረት ስለሚያስከትልበት ያሰቃየዋል፣፣ ይህንን ስቃይ ምግብ ፈላጊዉ ዝንጀሮ በግልጽ እንዲያየዉ ተደረገ፣፣የዚህ የቤተሙከራ ዉጤት ያሳየዉ አብዛኛዎቹ ዝንጀሮዎች ረሀባቸዉን የሚያስታግስ ምግብ ላለመብላት እምቢተኛነታቸዉን አሳይተዋል፣፣ የተራቡና የምግብ ፍላጎታቸዉ ከፍተኛ ቢሆንም አበዛኛዎቹ ገመዱን ለመሳብ አልተባበሩም፣፣በዚህ የምርምር ሙከራ 13% ጓደኛቸዉ በኤለክትሪከ ንዝረት እየተሰቃየ ገመዱን እየጎተቱ ምግብ የበሉ ቢሆንም 87% ግን የጓደኛቸዉን ስቃይ ከማየት በረሀብ መቆየትን መርጠዋል፣፣በተለይ አንዱ ዝንጀሮ ካለምግብ 12 ቀናት ቆይቷል፣፣በዚህ ሙከራ እንሰሳት ሌሎችን ከስቃይ ለማዳን ራሳቸዉን መስዋዕት ለማድረግ ፍቃደኛ እንደሆኑ አሳይተዋል፣፣ይህ ሙከራ ቅርበት ያላቸዉ የሚተዋወቁ ዝንጀሮዎችንና የማይደተዋወቁትንም ጭምር ያካተተ ቢሆንም ዉጤቱ ግን ተመሳሳይ ነበር፣፣
ከሰዎች ነባራዊ ሁኔታና ሞራላዊ ግዴታ አንጻር ስናየዉ አንድም ቀን ቤተክርስትያን ሂደዉ የማያዉቁት፣ ስለ አስርቱ ትዕዛዛት ሰምተዉ የማያዉቁ፣የግብረገብነት ትምህርት አንድም ቀን ት/ቤት ገብተዉ ያልተማሩ ዝንጀሮዎች ለመጥፎ ድርጊት ከመተባበር ይልቅ የሚደርስባቸዉን ስቃይ በድፍረት በመቋቋም የጥሩ ስራ ተምሳሌት ሁነዋል፣፣
የአብረሃም ጌታ ርሁሩሁ አምላካችን አብርሃምን ፈርሀ እግዚአብሔር ያደረብህ ነህ፣፣ከልጅህ በላይ እግዚአብሔርን እንደምትወድ ስለአወቅሁኝ ከልጅህ ላይ እጅህን አንሳ እንዳትነካዉ አለዉ፣፣የአቶ ሽፈራዉ ሸጉጤ ጌታ ግን የርሁሩሁ አምላካችን ተቃራኒ በመሆናቸዉ ታማኝ
አገልጋዬ መሆንህን ስለተረዳሁ ከጉራፈርዳ አማሮች ላይ እጅህን አንሳ እንዲሉ አንጠብቅም፡፡
እግዚአብሔር አብርሃምን ለፈተና የሚያቀርብበት ጊዜ ደረሰ ይላል መጽሐፍ ቅዱስ፣፣አብርሃንም ጠራዉና በጣም የምታፈቅረዉን አንድ ልጅህ የሆነዉን ይስሐቅን ይዘህ ሞርያህ( Moriah )ወደሚባለዉ ምድር ሂድ፣፣እዚያም ስትደርስ የማሳይህ አንዱ ተራራ ላይ መሰዋዕት ታደርገዋል፣፣አብርሃምም በጥዋት ተነሳ፣፣ለእሳት የሚሆነዉን እንጨትና አህያዉንም ለጉዞ አዘጋጅቶ ልጁንና ሌሎች ሁለት ሰዎችን በማስከተል እግዚአብሔር ወደ ነገረዉ ቦታ አመራ፡፡
ከሶስት ቀን ጉዞ በሗላ በሩቅ ቦታዉን ሲመለከት አብረዉ ይጓዙ የነበሩትን አምልኮ አድርሰን እስክንመለስ እናንተ እዚህ ቆዩ በማለት ልጁን እንጨቱን በማሸከም እሱ ቢላዋና እሳቱን በመያዝ ወደ ቦታዉ አመራ፣ይስሐቅም አባቴ እንጨትና እሳት ይዘናል ነገር ግን መስዋዕት የሚሆነዉ እንስሳ ዬት አለ? አለዉ፣፣አብረሃምም መስዋዕት የሚሆነዉን እንስሳ እግዚአብሔር ራሱ ይሰጠናል ብሎ መልስ ሰጠ፣፣ አበረሃምም እቦታዉ እንደደረሰ ለመስዋዕት የሚሆነዉን ቦታ በማዘጋጀት ልጁንም እግሩንና እጁን በማሰር የመሰዊያ ቦታ ላይ አጋደመዉ፣፣ልጁንም መስዋዐት ለማድረግ ቢላዋዉን አወጣ፣፣
አቶ ሽፈራዉ ሽጉጤ የአማራዉ የጉራፈርዳ ነዋሪዎች መዉደቂያ አጥተዉ ከነልጆቻቸዉ ጎዳና ላይ እንዲጣሉ በመወሰን ለጌታቸዉ ታማኝነታቸዉን እያረጋገጡ ነዉ፣፣ አዛዡም ጨካኝ ታዛዡም ጨካኝ በመሆናቸዉ የተፈናቃዮቹ በአጠቃላይ የኢትዮጵያዉያን ፍዳና መከራ አላቆመም፣፣
ስለዚህ እንደ ይሰሐቅ በየዋህነት ወደ መሰዊያዉ ቦታ እየተጓዝን ያለነዉም እንንቃ፣ጌታችን አይምሬ ነዉና፣ ፣ ትርፍራፊ ለመልቀም ስንል የወንድሞቻችን ስቃይ አልታይ ያለንም ዝንጀሮዎቹን ባንበልጥም የእነሱን ያህል እንኳን ለመሆን ወደ ህሊናችን እንመለስ፣፣
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኖራለች!!!
habtegiorgis1@gmail.com
ሚያዚያ 20/2012

No comments:

Post a Comment