የ“ብሩኅ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ” መግለጫ
ኢትዮጵያ እጅግ ረጅም የአገርነትና ተከታታይነት ያለው የመንግሥትነት ታሪክ ካላቸው ጥቂት አገሮች አንዷ ናት፡፡
የረጅም ዘመን አገርነቷና የተከታታይ በሀወርታዊ መንግሥት ባለቤት መሆኗ፣በጥንታዊ ሥልጣኔ ቅሬቶቿና በራሷ የጽሑፍ
ቋንቋ የተገለጸ ነው፡፡ የአክሱም ሀውልት፣የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት፣ በአገሪቱ ልዩ ልዩ ታሪካዊ ቦታዎች
በአርኪዮሎጂስቶች ጥናትና ምርምር ከምድር ውስጥ ተቆፍረው የተገኙት የድንጋይ ላይ ጽሑፎች፣ ገንዘቦችና ልዩ ልዩ
መገልገያ መሣሪያዎች የረጅም ዘመን ታሪኳ ቋሚ ነቃሾች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ረጅም አገራዊና የመንግሥትነት ታሪክ ልዩ የሚያደርገው ተጨብጦ በነበረው ጥንታዊ ሥልጣኔና
ተከታታይነቱን በጠበቀ መንግሥትነት መኖር ብቻ ሳይሆን፣ አገሪቱ የብዙ ማኅበረሰቦች አገር መሆኗና፣ ማኅበረሰቦቹ
በኢትዮጵያዊነት ማዕቀፍ ውስጥ፣ ደስታና መከራን፣ ሰላምና ጦርነትን፣ሰፈራና ስደትን ዕኩል የተጋሩ የጀግኖችና የኩሩ
ሕዝብ መታወቂያ በመሆኗ ጭምር ነው፡፡
የአገሪቱና የመንግሥቱ ተከታታይነት፣ የማኅበረሰቡ በሀወርታዊነት፣ እንዲሁ በልዩ ተዓምር ዕውን የሆነ አይደም፡፡ ተስፋፊነትንና ቅኝ ገዥነትን መነሻና መድረሻ
አድርገው በተደጋጋሚ ሊወሩን፣ ቅኝ ተገዥ ሊያደርጉን፣ ነፃነታችን ሊገፉ፣ ሃይማኖታችን ሊያስለውጡ፣ ሊነጣጥሉንና
ተዋራጅ ሊያደርጉን በተለያዩ ጊዚያት፣ ወራሪና ቅኝ ገዥ ሠራዊት አሰልጥነውና አደራጅተው፣ ባሕር አቋርጠው፣ ድንበር
አልፈው የመጡ፣ የፖርቱጋልን፣ የኦቶማን ቱርክን፣ የግብፅንና የጣሊያንን ወራሪዎችና ቅኝ ገዥዎች ፍላጎት፣ ሕዝቡ
በየዘመኑ ከነበሩ ንጎሦችና የየአካበቢው ገዥዎች ዙሪያ በመሰለፍ በከፈለው ውድና ምትክየለሽ የሕይወት፣ የአጥንትና
የደም ዋጋ ነው፡፡ ይህ ዋጋ የኢትዮጵያ አንድነትና በሀወርታዊነት ለረጅም ተከታታይ ዘመናት ፀንቶ እንዲኖር፣
የኢትዮጵያዊነት መሠረት፣ ቋሚ፣ ምሰሶ፣ ማገርና ጣራ በመሆን አገልግሏል፡፡
በሌላ በኩል ኢትዮጵያውያን መጨረሻ ግቡ ሥልጣንን መቆጣጠር የሆነ፣ መነሻ
ምክንያቶቹ ወይም ስበቦቹ ደግሞ፣ አካባቢያዊነት፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ኢኮኖሚ፣ ባህልና ርዕዮተ-ዓለም በሆኑ ጉዳዮች
ዙሪያ ልዩነቶችን በመምዘዝ በሚፈጠር ግብግብ አገሪቱ ባላቋረጠ የርስበርስ ጦርነቶች ውስጥ ያለፈችና ያለንም መሆኑ
ታሪካችንና የምንገኝበት ነባራዊ ሁኔታ ያስረዳል፡፡ ይህም በመሆኑ የአገራችን ታሪክ በአመዛኙ የጦርነት ታሪክ
እንዲሆን አድርጎታል፡፡
ሁለቱ ጦርነቶች ማለትም የውጭ ወራሪዎችንና ቅኝ ገዥ ኃይሎችን የመከላከሉና የውስጥ የሥልጣን ግብግብ ጦርነቶች
በታሪካችን ውስጥ ሁለት ጉልህ ተቃራኒ ክስተቶች ጎን ለጎን እንዲጎለብቱ አድርጓል፡፡ የመጀመሪያው ክስተት የማፍረስ
ሲሆን፣ ሁለተኛው የመገንባት ባህርይ ነበረው፡፡
የአገራችን የረጅም ዘመን ታሪክና በተለይም፣ ከ1ኛው እስከ 5ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ ጨብጣው የነበረው
የሥልጣኔ ደረጃና የቴክኖሎጂ እንቅስቃሴዎች ዛሬ ከምንገኝበት የዕድገትና አጠቃላይ ሁኔታ ጋር ሲነፃፀር፣ ከላይ
ከተገለጹት ሁለት ተቃራኒ ክስተቶች የማፍረስ ጎኑ እጅግ የበረታ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ የአገርን ዳር ድንበር፣
የሕዝቡን ነፃነትና ሉዓላዊነት ለመከላከልና ለማስጠበቅ፣ እንዲሁም በሥልጣን ይገባናል ባዮች የተቀሰቀሱ የርስበርስ
ጦርነቶች ተገንብተው የነበሩ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የባህል፣ የማህበራዊ፣ የወታደራዊና የቴክኖሎጂ መፍለቂያ
ተቋሞች፣አሠራሮች፣ ግንኙነቶች ወዘተ … እንዳሉ በማውደሙ፣ የዕድገት ተከታታይነት እንዲቋረጥ በማድረግ፣ አገሪቱ
የተገነባን በማፍረስና አዲስ መሠረት በመጣል ሽክርክሪት ውስጥ አስገብቶ ዕድገቷ የኋሊት እንዲጓዝ አድርጓል፡፡
ዕድገት የተከታታይ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ባህላዊ ፖሊሲዎች ውጤት እንደሆነ ይታመናል፡፡ ይህ
ተከታታይነት ደግሞ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ባህል ውስጥ እንኳን ትናንት ዛሬም በፖለቲከኞች ኅሊና ውስጥ ተገቢ ቦታውን
ያገኘ ባለመሆኑ፣ ዕድገት ለኢትዮጵያ በርቀት የሚታይ አድማስ ከመሆን አላለፈም፡፡
በአገራችን ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ጎልተው ከሚታዩት የጦርነት ክስተቶች ሌላኛው ጎን፣ ጦርነቱ ልዩ ልዩ
ማኅበረሰቦችን እንዲዋሐዱና አንድ ሕዝብ፣ የወል ታሪክ፣ የጋራ አገር፣ የወል ኢትዮጵያዊ የማንነት ዕሴቶችና ተመሳሳይ
ሥነልቦና እንዲመሠርቱና የልዩነት ግድግዳዎችን ደረማምሰው ኢትዮጵያዊ ዜጋ እንዲሆኑ ያስቻለው የግንባታ ሂደት ነው፡፡
በልዩ ልዩዎቹ ማኅበረሰቦች መካከል የተፈጠረው አንድነት በአመዛኙ በሁሉም የጋራ ፍላጎት ሰጥቶ የመቀበል፣ ወስዶ
የመመለስ፣ በተናጠልና በወል እንቅስቃሴዎች፣ በተፈጥሮ ገፊና ሳቢ አስገዳጅ ኃይሎች
ግፊት፣በጦርነት፣በጋብቻ፣በስደት፣ በፍልሰት፣ በንግድ፣ በጉዲፈቻ፣ወዘተ..አማካኝነት ተለንቅጦ የተዋሐደ በመሆኑ፣
የተፈጠረውን አንድነት በቀላሉ ለማንተርተር፣ለማንጓለልና ለማበጠር እንዳይቻል አድርጎታል፡፡ ኢትዮጵያ የብዙ
ማኅበረሰቦች የአንድነት አገር ናት የሚያሰኛትም ይኸው አንዱን ማኅበረሰብ ከሌላው ነጥሎ በራሱ ለማቆም የሚያስችል፣
የመነጠያ ሁለንተናዊ የማንነት መከሰቻ ሁኔታ የሌለ፣ አገሪቱ የማኅበረሰቦቿ ፍጹም ውሕድ አንድነት የተፈጠረባት ሕዝብ
አገር በመሆኗ ነው፡፡
የአገራችን ጥንታዊ ሥልጣኔ፣ ጨብጣው የነበረው ዕድገትና በዓለም ላይ የነበራት ተደማጭነት፣የያዘችው
ጂኦ-ፖለቲካዊ ቦታ፣ ያላት የውኃ ሀብትና የተፈጥሮ ሀብት፣ በአውሮፓ ቅኝ ገዥዎች ላይ የተቀዳጀችው አንጸባሪቂ ድል፣
ለጥቁር አፍሪካ ሕዝቦች ነፃነት ያበረከተችው የአርኣያነት ተግባር፣በጥቅሉ፣ ኢትዮጵያ ያላት ቁሳዊና ኅሊናዊ ሀብት፣
የመከበሪያ፣ የመታፈሪያ፣ የመደመጫና የተከታታይነት ዕድገት መጨበጫ የሁለንተናዊ ብቃት ቋት በሆነን ነበር፡፡
የሆነው ግን ተቃራኒው ነው፡፡ ተከታታይነትና ወጥነት ያለው ፖለቲካዊ ባህል፣ የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማኅበራዊ ፖሊሲ
አለመኖር፣ በጥንታዊ ሥልጣኔአችን ላይ መሠረት ያደረገ ቴክኖሎጂ ማዳበር አለመቻላችን፣ ያለንን የተፈጥሮ ሀብት
አልምተን በጥቅም ላይ አለማዋላችን፣ ያለንን ካፒታል በአግባቡ መጠቀም አለመቻላችን፣ ይህ ሁኔታ ጠላት ገዥ በመሆን
የጥቃት ዒላማ እንድንሆንና ለዙሪያ ገብ ችግሮችና ተዋራጅነት ተዳርገናል፡፡
ከሁሉም በላይ ባለፉት አምሳና ስልሳ ዓመታት ትውልዱ ከነባራዊ የወል ኢትዮጵያዊነት ዕሴቶች መውጣት ብቻ
ሳይሆን፣ የአገራዊ አንድነት መሠረት የሆኑትን ተቋሞች፣ ዕምነቶች፣ አሠራሮችና ግንኙነቶች ከማጥፋት ባሻገር፣
በልዩነቶች ማለትም፣ በርዕዮተ-ዓለም፣ በቋንቋ፣ የነባሯን ኢትዮጵያ ታሪክ በመቀበልና ባለመቀበል ዙሪያ በመደራጀት
አገሪቱን የጦርነት አውድማ በማድረግ ከመኖር ወደ አለመኖር እንድትሸጋገር እይደረጋት ነው፡፡
በተለይ የወያኔ አገዛዝ የሚያራምደው የዘር ፖለቲካ፣ ያደራጀው በልዩነት ላይ የተመሠረተ የመንግሥት ቅርጽ፣
አገሪቱን ወደብ አልባ ማድረጉና የጥንታዊት ኢትዮጵያ ሥልጣኔና አገራዊ መሠረት የነበረችውን ባሕረ-ነጋሽ/ምድረ
ባሕሪ ማስገንጠሉ፣ ምዕራባዊ የግዛት አካሏን ለሱዳን መሥጠቱ ወዘተ…የአገራችን የጥፋት የቁልቁለት ጉዞ ማመላከቻ ቋሚ
ነቃሾች ናቸው፡፡
ኢትዮጵያውያን ከተጋረጡብን የመበተንና እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ያለመቀጠል ታላቅ አደጋ በተጨማሪ፣ በልዩ
ልዩ የችግር አረንቋ ውስጥ ነን፡፡ ርሀብና ቸነፈር ከሚገመተውና ከሚነገረው በላይ በሕዝቡ ሕይዎት ውስጥ ሥር
ሰዷል፡፡ የርሃቡ ክፋትና ስፋት በ1880ዎቹ ተከስቶ ከነበረውና በታሪካችን ከሚታወቀው አሰቃቂ ርሃብ የሚለየው
“እናት ልጇን በላች” የሚለው አሳፋሪ፣ አሳዛኝና አስደንጋጭ ዜና አለመሰማቱ ብቻ ነው፡፡
የአገሪቱ ድንግልና ለም መሬቶች ለሳውዲ ዓረቢያ፣ ለሕንድና ለቱርክ ባለሀብቶች ገበሬው እየተፈናቀለ፣ በስጦታ
በሚያሰኝ ደረጃ በርካሽ ዋጋ ለ99 ዓመታት እየተሸጠ ነው፡፡ ሆን ተብሎ በሚራገበው የዘር ፖለቲካ የጎሳ ብጥብጥና
የሃይማኖት ግጭቶች አገራችን በታሪኳ አይታው ወደማታውቀው የጥፋት ነውጥ ውስጥ ገብታለች፡፡ ሕዝቡ ሰብአዊና
ዲሞክራሲያዊ መብት ሳይሆን፣ሠርቶ የመኖር የዜግነት መብቱን ካጣ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡
እነዚህና መሰል ችግሮች የተወሰኑት ካለፉት ዘመናት የወረስናቸው ሲሆኑ፣ አብዛኛዎቹ ወያኔ በታሪካዊና ወቅታዊ፣
በነባራዊና ጊዜአዊ፣ በሩቅና በቅርብ ጠላቶቻችን ለዘመናት ሲደግሱልን የነበረውን የጥፋት ተልዕኮ አስፈጻሚ በመሆን
የሚያራምደው የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ ፖሊሲዎች ውጤቶች ናቸው፡፡ በግልጽ እንደሚታወቀው የአገራችን ችግሮች
ብዙና ውስብስብ ናቸው፡፡ የችግሮቹ ቋት ወይም ቋጠሮ ግን የመልካም አስተዳደር ዕጦት እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡
በሂደት የተንከባለሉትንም ሆነ፣ ወያኔ ሆን ብሎ፣ በፖሊሲ ቀርጾ እያራገባቸው ያሉትን ሁለንተናዊ የአገርና
የሕዝብ ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለማስወገድ፣ ብሎም ያለንን ካፒታል በሥርዓትና በአግባቡ ተጠቅመን ድህንትን፣ በሽታን፣
ርሃብንና አጠቃላይ ኋላ ቀርነትን ለማስወገድ ያለው ብቸኛ አማራጭ የሀሳብ፣ የአመለካከት፣ የዓላማና የተግባር
አንድነት የሚያስገኝ ድርጅታዊ ኃይል መፍጠር ነው፡፡ ይህም ኃይል ሌላ ምንም ሳሆን፣ ሕዝቡ ዕውነተኛ ፍላጎቱን፣
መሆን የሚሻውን ሊገልጽበት የሚችል፣የችግሮቹ ማስወገጃ፣ የሰላሙ ማስፈኛ፣ የዕድገቱና ብልጽግናው ማስገኛው፣
የነፃነቱና የዕኩልነቱ ማረጋገጫው፣ የሰብአዊ መብቱና የዲሞክራሲያዊ መብቶቹ ማስከበሪያ የሚሆን ሕዝባዊ ኃይል ማለት
ነው፡፡
ከአገራችን የፖለቲካ ድርጅቶች ታሪክና ከሕዝቡ ፖለቲካዊ ባህል አንፃር ያለውን አስቸጋሪነት በመመዘን፣ ይህን
ዓይነት ባሕሪና ተልዕኮ ያለው ድርጅት እንዴት ዕውን ማድረግ ይቻላል? በዚህ ዓላማ ዙሪያ የተደራጁ በርካታ ድርጅቶች
እያሉ፣ ይህ አዲስ የሚመሠረት ድርጅት ካሉትና ከነበሩት በምን ይለያል? አዲሱን ድርጅታችንን ለውጤት የሚበቃ
ለማድረግ ምን ዓይነት የአሠራርና የአደረጃጀት ስልት እንከተላለን? የሚሉት ጥያቄዎች መነሳትና ተገቢ የሆነ መልስ
ማግኘት ያለባቸው ናቸው፡፡
በዚህ ረገድ “ብሩኅ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄን” መሥራቾች ላለፉት ሦስት ዓመታት በተከታታይ በቡድንና
በተናጠል ከላይ በተነሱትና መሰል ኢትዮጵያን በሚመለከቱ ጥያቄዎችና ርዕሶች ዙሪያ ሰፊ ውይይትና ክርክር፣ ጥናትና
ምርምር በማድረግ ሕዝባችንን የዘላቂ ድል ባለቤትነና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ፣
ግቡ፡-
- በመሣሪያ ኃይል ሥልጣን ላይ ያለውን የወያኔ መንግሥት ተብዬ፣ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም፣ የሕዝቡን ሉዓላዊነት፣ ብሔራዊ ዳርድንበሯንና የሕዝቡን አንድነት ሆን ብሎ የጎዳ በመሆኑ፣
- የሃገራችን፡ የተፈጥሮ፡ ሃብት፡ ዘርፎ፡ ለዘራፊ፡ በመስጠት፡ ህብረተሰቡን፡ ለድህነት፤ ርሃብ፤ የኑሮ፡ ዋጋ፡ ግፍሸት፤ ጥገኝነት፤ ታዛዥነት፤ ስደት፤ የዳረገው፡ በመሆኑ፤
- የአገሪቱን ጥንታዊ፣ ታሪካዊ፣ ባህላዊና ሕጋዊ የተፈጥሮ በሯን ወዶና ፈቅዶ የሰጠ በመሆኑ፣
- የተከተለው የመንግሥት አደረጃጀት ቅርጽና የሚያራምደው፤ የዘር፡ የፖለቲካ፤ ማህበራዊና፤ የኢኮኖሚ፡ አመራር፡ ከጥቅሙ፡ ጉዳቱ፡ ያመዘነ፤ ለጥቂቶች፡ የሃብት፡ ማካበቻ፡ ለአብዛኛው፡ ህብረተሰብ፤ አሰቃቂና፡ ተስፋ፡ የሚአስቆርጥ፡ ሁንየታወች፡ ስለፈጠረ፤ ስራቱ፡ የአገራዊ ክህደት መጸብራቅነቱ፡ ግልጽ፡ እየሆነ፡ በመታየቱና፡ ለመበታተን፡ ያለውን፡ አደጋ፡ ለማቆም፡ ስለማይችል፤ በምትኩ ሕዝቡ በነፃ ኅሊናውና ፍላጎቱ እንዳሻው የሚወስንበት ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መመሥረት እንዳለበት ሙሉ ስምምነት ደርሰናል፡፡
ወደዚህ ግብ ለመቃረብም በስልት ደረጃ መከተል ያለብን፣ በነባሯ ኢትዮጵያ ብሔራዊ አንድነት፣የግዛት ክልልና
ታሪክ፣በህግ የበላይነትና በነጻ የሕዝብ ተሳትፎ ምርጫ ከሚያምኑ ብሔራዊና ህብረ -ብሔራዊ ንቅናቄዎች፣ ፓርቲዎች፣
ድርጅቶች፣ ቡድኖችና ግለሰቦች ጋር በሚያግበቡንና አንድ በሚያደርጉን ጉዳዮች ዙሪያ ተባብሮና ተመካክሮ መሥራት፣
በተቻለ መጠን ልዩነቶችን በውይይትና በምክክር መፍታት እንጂ፣ በጠላትነት ላለመፈራረጅ ብርቱ ጥንቃቄ ማድረግ
እንዳለብን፣ የእንቅስቃሴአችን ሙሉ ትኩረት በወያኔ አገዛዝ ላይ እንጂ፣ ለኢትዮጵያ አንድነት በሚማስኑ ኃይሎች ዙሪያ
እንዳይሆን ሙሉ ስምምነት ላይ ደርሰናል፡፡
በዚህም መሠረት በንቅናቄው መመሥረት አስፈላጊነት፣ በግቡና በስልቱ ዙሪያ ላይ የወል መግባባት ከተደረሰ በኋላ፣
በዚህ ታሪካዊ ወቅት ንቅናቄው እውን እንዲሆን ያስፈለገበት ምክንያቶች ከዚህ በታች ተዘርዝረዋል፡
እነዚህም፡-
- የሚመራበት የዓለም አመለካከት ከኢትዮጵያዊነት መልካም ዕሴቶች የሚመነጭ፣ አስተዳደራዊ፣ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፖሊሲዎቹ በኢትዮጵያ መልካም ውርሶችና ቅርሶች ላይ እንዲመሠረት ማድረጉ ወይም ለኢትዮጵያዊነት ዕሴቶች ልዩ ትኩረትና ክብር መስጠት መቻሉ፤
- የንቅናቄው የአደረጃጀት መርህ፣ ዲሞክራሲያዊ፤ ፍትሃዊ፤ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነትን መሠረት ያደረገና የምንደራጀውም ልዩ በሚያደርጉን ጉዳዮች ዙሪያ ሳይሆን፣ አንድ በሚያደርገን ኢትዮጵያዊነት ዙሪያ መሆኑ፤
- ልዩነቶቻችን ፈርጦቻችንና ጌጦቻችን እንጂ፣ መራኮቻና መለያያ መስመሮቻችን አለመሆናቸውን መረዳታችን፤
- ኢትዮጵያ የበሀወርታዊ ሕዝብና መንግሥት አገር መሆንና ለረጅም ዘመን የዘለቀ ታሪክ ያላት መሆኑን አምነን፣ ይህ ታሪክ ዘመንና ወቅቱ ከሚጠይቁት ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር እየተጣጣመ ወደላቀ የዕድገት ደረጃ እንዲሸጋገር አስፈላጊ ሁኔታዎችን ማሟላት ያለብን መሆኑን በማመናችን፤
- የነባሯ ኢትዮጵያ ታሪክና የማዕከላዊ መንግሥት አመሰራረት ሂደት፣ በዓለም ከታዩት አገሮች አፈጣጠር የሚለየው በቦታ፣ በጊዜና በአድራጊ ግለሰቦች እንጂ፣ በሌሎች መሠረታዊ ሂደቶች የማይለይ፣ በግድ መታለፍ የነበረበት የነባራዊ ሁኔታዎች ውጤት መሆኑን ተገንዝበን፣ ተሠሩ ለሚባሉ ስሕተቶች በታሪክ ዓይን እየተመረመሩ፣ ስሕተቶች ከነበሩ ወደፊት የማይደገሙበትን ሁኔታ በማመቻቸት በመልካም የወል ውርሶቻችን ላይ በመመሥረት የአገሪቱን ልማትና ዕድገት ለማፋጠን የቆምን መሆኑ፤
- የኢትዮጵያ መፃዒ ዕድል በልጆቿ አንድነት ላይ የሚወሰን በመሆኑ፣ ይህ አንድነት ደግሞ ያላንዳች ሳንካ ዕውን የሚሆነው ባለፉት ዘመናት በርዕዮተ-ዓለም፣ በዘር፣ በክልል፣በስልጣን ግብ-ግብ፤ በሃይማኖት ወዘተ..ዙሪያና በዓላማ ማስፈጸሚያ ስልቶች ተለያይተው የተዳሙ፣ ፊት የተዟዟሩና አለመግባባት የፈጠሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ብሔራዊ እርቅ ሲያወርዱ ስለሆነ፣ ለዚህ ተግባራዊነት ተገትን የምንሠራ መሆኑ፤
- የንቅናቄው አባላት የሚመዘኑት በዘራቸው፣ በፆታቸው፣ በሃይማኖታቸው ወይም ባለፈ ታሪካቸው ሳይሆን፣ በኢትዮጵያዊነታቸውና ለኢትዮጵያ አንድነትና ፍትሃዊ እድገት ዳብሮ መቀጠል ከሚያበረክቱት አስተዋጽዖ አንፃር ብቻ መሆኑ፤
- የንቅናቄው አባላት የሚቀበሉትና የሚያምኑት፤ የትግሉ መስክ ኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመራ መሆኑ፤
- የዲሞክራሲ ዋነኛ መገለጫ ከሆኑት መሠረታዊ ጉዳዮች አንዱ ሕዝብ የሥልጣን ባለቤት ሆኖ፣አማራጮች ቀርበውለት የፈለገውን የመምረጥ መብት ማረጋገጡ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የአማራጭ ሀሳቦችንና አሠራሮችን መኖር ይጠይቃል፡፡ ከዚህ አንፃር፣ የኢትዮጵያን ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ ለማዳበርና ዲሞክራሲያዊ መብቱን ተግባራዊ እንዲያደርግ ደጋፊና አማራጭ ሆነን መቅረባችን ናቸው፡፡
“ቆሎን መቆርጠም እንጂ፣ ማሸት አይጨርሰውም” እንደሚባለው፣ የኢትዮጵያን ችግሮች ማስወገድ የሚቻለው ስለችግሯ
በማውራት ሳይሆን፣ በመሥራት ነው፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ዙሪያ ከሦስት ዓመታት በላይ
ሲወያይ፣ ሲመክርና ሲከራከር የኖረው ስብስብ የሀሳብና የተግባር መገለጫው የሆነ “ብሩኅ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲዊ
ንቅናቄ” የተሰኘ ድርጅት በመመሥረት ከመጋቢት 30 ቀን 2004 ዓ.ም ጀምሮ ይፋ እንቅስቃሴ መጀመራችንን
ለኢትዮጵያ አንድነት ዳብሮ መቀጠል ቁርጠኛ ፍላጎት ላላቸው ኢትዮጵያውያን ስናበስር፣ ከተደራጀን የማንፈታው ችግር
እንደሌለ በመተማመን ነው፡፡
“ከፖለቲካ በራቅን ቁጥር በምንበልጣቸው ሰዎች በመገዛት እንቀጣለን” ሲል ታላቁ የማኅበራዊ ሣይንስ ፈላስፋ
ፕሌቶ የተናገረው ዕውነታ፣ ዛሬ በአገራችን በገሀድ እየተፈጸመ ያለ በመሆኑ፣እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ከፖለቲካው
መድረክ በመራቁ ምክንያት በሚበልጣቸው ሰዎች በመመራት ከሚፈጸምበት ቅጣት ለመዳን የብሩኅ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲዊ
ንቅናቄ ንቁ አባል በመሆን ኢትዮጵያን ከጨርሶ ጥፋት እንድንታደጋት ብሩኅ ኢትዮጵያ አገራዊ ጥሪ ያቀርባል፡፡
ኢትዮጵያን ከጨርሶ ጥፋት እንታደግ!
ኢትዮጵያዊነት ኅብረ ብሔራዊ ማንነታችን ነው!
የብሩኅ ኢትዮጵያ ዲሞክራሲዊ ንቅናቄ (ብሩኅ ኢትዮጵያ)