Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Thursday 16 August 2012

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳዉሎስ በ76 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ


Image




 ሸገር ኤፍ ኤም ዛሬ ጠዋት እንደዘገበዉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክና የአለም አቢያተ-ክርስቲያናት ፕሬዝዳንት የሆኑት አብነ ጳዉሎስ በገጠማቸዉ ከባድ የጤና እክል ምክንያት በባልቻ ሆስፒታል ተኝተዉ  የህክምና እርዳታ ሲደረገላቸዉ ቆይቶ ዛሬ ሌሊት በ76 ዓመታቸዉ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳዉሎስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ በመሆን ላለፉት 20 ዓመታት ያገለገሉ ሲሆን ከኢትዮጵያ ኦርዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ስርዓት ዉጭ በሆነ መንገድ ተሹመዋል በሚል ሲወነጀሉ ቆይተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር ከመንግስት ጋር ባላቸዉ የጠበቀ ግንኙነትና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ያሳዩት በነበረ ፍፁም ወገንተኝነት በብዙዎች ዘንድ ይተቹ ነበር፡፡

በተለይም 20ኛ ዓመት በዓለ ሢመታቸዉን ሐምሌ 5 ቀን 2004 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ካከበሩ በኃላ ሐምሌ 16 ቀን 2004 ዓ.ም ምሽት በሼራተን አዲስ ለሁለተኛ ጊዜ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትን፣ አምባሳደሮችንና ታዋቂ ሰዎችን ጨምሮ ከ500 ያላነሱ ሰዎች የታደሙበት ድል ያለ የራት ግብዣ አካሂደዋል በሚል በሰፊዉ ሲተቹ ነበር፡፡

በቅርቡም መንግስት በዋልድባ ገዳም አቅራቢያ ገዳሙን ፍፁም በሚነካ መልኩ የስኳር ፋብሪካ ለማቋቋም መነሳቱን ደግፈው በመነኮሳቱ ላይ እየተወሰደ ያለውን ኢ-ፍትሀዊ እርምጃ ባለመቃወማቸውና በተቃራኒው የመነኮሳቱን ተቃዉሞ በመንቀፋቸዉ ብዙዎች  ሲያዝኑባቸዉ ነበር፡፡ ህመማቸው እንደተሰማም “የዋልድባ ቁጣ” ዉጤት ነዉ ሲሉ በርካታ ክርስቲያን ወገኖች ሲናገሩ ነበር።

እንደሚታወቀዉ ኢሳት ደጀ-ሰላም የተሰኘ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚዘግብ ድህረ-ገፅ ጠቅሶ ትናንት ማለትም ሐምሌ 8/2004 አብነ ጳዉሎስ በገጠማቸዉ ከባድ የጤና እክል ምክንያት በባልቻ ሆስፒታል ተኝተዉ ከባድ የህክምና እርዳታ እየተደረገላቸዉ ነዉ ሲል ዘግቦ የነበረ ሲሆን ፤ መረጃዉ በሳቸዉ ዙሪያ ባሉ ሰዎች ተቃዉሞ ገጥሞት ነበር፡፡

ከገባ ሳምንት ያለፈዉን የፍልሰታ ማሪያም ፆም ተከትሎ በቅዱሰ ቅዱሳን ማርያም ገዳም በፀሎተ ቅዳሴ ላይ እንደነበሩ ድህረ ገፁን ጠቅሶ ያተተዉ የኢሳት ዘገባ ትናንት በጠና በመታመማቸዉ ባልቻ ሆስፒታል መግባታቸዉን ገልፆ ነበር፡፡
ኢሳት አያይዞም ድህረ-ገፁን በመጥቀስ ፓትርያርኩ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የጤንነት ሁኔታቸዉ እየተባባሰ በመምጣቱ ምክንያት ወደ መኪናቸዉ ሲገቡም ሆነ ሲወጡ ከግራና ከቀኝ ሰዎች እየደገፋቸዉ እንደ ነበር ጠቁሞ ነበር፡፡

No comments:

Post a Comment