Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Sunday, 12 August 2012

በምግብ እጥረት ለተጎዱ ዜጎች ዕርዳታ ሊጠየቅ ነው


Horn of Africa famine: Somalia, Ethiopia and Kenya suffer worst drought in 60 yearsበዓመቱ አጋማሽ ላይ በተከሰተው የበልግ ዝናብ አለመኖር ምክንያት የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው በሚሊዮን ለሚቆጠሩ ዜጎች የሚያስፈልገው የዕርዳታ ምግብና ቁሳቁስ  መጠን፣ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ለለጋሾች ይፋ ይደረጋል፡፡ ከየካቲት እስከ ግንቦት ወር 2004 ዓ.ም. ባለው ጊዜ በልግ አብቃይ የሆኑ አካባቢዎች በኤልኒኖ ክስተት ምክንያት የዝናብ እጥረት ስላጋጠማቸው የምግብ ችግር ተፈጥሯል፡፡

የበልግ የዝናብ እጥረት ገጥሞቸው የበልግ ሰብሎችን ማብቀል ያልቻሉት  የኦሮሚያ፣ የደቡብና የሶማሊያ ክልሎች  አንዳንድ አካባቢዎች ናቸው፡፡ የተለያዩ የመረጃ ምንጮች እንደሚገልጹት፣ በደቡብ ክልል ብቻ በክስተቱ በ80 ወረዳዎች ከፍተኛ የምግብ እጥረት ተከስቷል፡፡ በአጠቃላይ ይፋ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው የምግብ መጠን ከካቻምናው ይጨምራል እንጂ አያንስም የሚሉት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ናቸው፡፡


የግብርና ሚኒስቴር የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ዘርፍ ከነሐሴ 2004 ዓ.ም እስከ ጥር 8 ቀን 2005 ዓ.ም. ድረስ  የምግብ ችግር ላጋጠማቸው ዜጎች የሚያስፈልገውን የዕርዳታ ምግብና ቁሳቁስ መጠን ነገ  ነሐሴ 7 ቀን 2004 ዓ.ም. ይፋ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይፋ የሚደረገውም ለምግብ ችግር ለተጋለጡ ወገኖች የሚያስፈልገው  የዕርዳታ እህልና ቁሳቁስ መግዛት የሚያስችለው የገንዘብ መጠን  ነው፡፡

የግብርና ሚኒስቴር የአደጋ መከላከል ዝግጁነት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ምትኩ ካሳ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናትና ነፍሰጡር እናቶች ተጨማሪ ተመጣጣኝ ምግብ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የምግብ እጥረት ላጋጠማቸው ወገኖች የሚጠየቀው ስንዴ፣ በቆሎና ጥራጥሬ ነው፡፡ ለነፍሰጡሮችና ለሕፃናት ተጨማሪ ተመጣጣኝ ምግቦች ስለሚያስፈልጉ የተለየ አሠራር ተዘርግቷል ብለዋል፡፡

በበልግ ዝናብ ያለመኖር ምክንያት የምግብ እጥረት የተከሰተባቸው ክልሎች በራሳቸው መንገድ ግምገማ ያካሂዳሉ፡፡ ከክልሎች ጋርም የለጋሽ አገር ድርጅቶች ለምሳሌ ዩኤስኤይድ፣ ዲኤፍአይዲ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት  የዓለም የምግብ ፕሮግራምና የዓለም  የእርሻ ድርጅት አብረው ይሠራሉ፡፡

ይህ ግምገማ ተጠቃሎ ለአቶ ምትኩ ቢሮ ቀርቦ ውይይት ይካሄድበታል፡፡ የሚደረስበት ውጤትም ለምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ  ለሚመራው ብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚቴ ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ ይፀድቃል፡፡

የሪፖርተር ምንጮች በአሁኑ ወቅት የሚያስፈልገው የዕርዳታ መጠን በኮሚቴው መፅደቁን ገልጸዋል፡፡ ይሁንና አሁን የሚያስፈልገው  የዕርዳታ ገንዘብ መጠን  ምን ያህል እንደሆነ አቶ ምትኩ  ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡

ምንጮች እንደሚሉት ግን በጥር ወር 2004 ዓ.ም ከለጋሾች ብቻ  እንደሚፈለግ ከተገለጸው መጠን የማይተነፍስ እንዲያውም ብልጫ ያለው ዕርዳታ እንደሚያስፈልግ ነው፡፡

በጥር ወር 2004 ዓ.ም. አስቸኳይ ዕርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች ያስፈልጋሉ ተብሎ በመንግሥት ለለጋሾች የቀረበው የዕርዳታ ጥሪ 168.7 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ 365,612 ሜትሪክ ቶን ምግብና ቁሳቁሶችን ያጠቃልላል፡፡  በወቅቱ ለምግብ እጥረት የተዳረጉ 3.2 ሚሊዮን ወገኖች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡

No comments:

Post a Comment