ይህ ጨዋታ ለዚህ ሳምንት ፍትህ ጋዜጣ የተላከ ነበር። ነገር ግን ፍትህ አሁንም በሀገሪቱ እንድትኖር ሰዎቻችን
አልፈቀዱም። በፍርድ ቤት የታዘዘው ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት “መጀመሪያ ሌላ ቦታ አሳትሙና በሚቀጥለው ሳምንት
እኔ አትምላችኋለው” ብሎ መልስ ሰጠ ሲባል ሰማሁኝ። ይሄ በጣም አስቂኝ ነው…! ሌላ ማተሚያ ቤት እኮ የለም። አንድ
ቦሌ ማተሚያ ቤት ነበረ እርሱም ደንበኛችን ስላልሆናችሁ አናትምላችሁም ብሏል። ወደየት እየተገፋን እንደሆነ እግዜር
ይወቀው!
እስቲ ለማንኛውም ወጋችን ይጀምር…ሰላም ወዳጄ እንዴት ሰነበቱልኝ? ፍትህ ጋዜጣ በፍትህ ችግር ታግታ ሰነበተችና ተጠፋፋን አይደል!? ጉልቤው
ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ቤት ያለ ምንም ህጋዊ አግባብ የእናንተን ጋዜጣ አላትምም ብሎ ደጅ ሲያስጠናን ቆይቶ ይኸው
ዛሬ “የተከበረው” ፍርድ ተቆጥቶልን ለመገናኘት በቅተናል።
ብዬ ነበር የጀመርኩት… እኔማ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ማክበር የሁላችንም ግዴታ መስሎኝ ነበር። ለካስ ፍርድ ቤቱን
ማክበር የአንዳንዶቻችን ብቻ ነው…! አንድ ቀን አንዳንድ ከመሆን ተላቀን አንድ እንሆን ይሆናል! ብቻ ግን አስቲ
ወጋችን ይቀጥል…
ፍርድ ቤት ካልኩኝ አይቀር፤ የአንድነት ፓርቲ አመራር አባላትን “ክቡር” ፍርድ ቤቱ “ኑ እንመካከር” ብሎ
ጠርቷቸው ሲያበቃ ምንም ባልተከሰሱበት እና ባልተከራከሩበት ችሎት ገትሮ እያደረጋችሁ ያላችሁትን እናውቃለን ነገረ
ስራችሁ በሙሉ ጥፋት ነውና እና “ወዮላችሁ” ሲል ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው አይደለም እንዴ!?
ነገሩ እንዲህ ነው፤ የፓርቲው አመራር አባላት በትግል አጋሮቻቸው “እነ አንዷለም አራጌ እንዲሁም ጋዜጠኛ
እስክንድር ነጋ ላይ የተፈረደው ፍርድ አግባብ አይደለም” ብለው በየ ሚዲያው ተቃውሞ ሲያሰሙ ነበር፤ ታድያ ፍርድ
ቤት ሆዬ “ይሄማ እልም ያለ ጥፋት፤ ጭልጥ ያለ ወንጀል ነው።” ብሎ ጠርቶ ማስጠንቀቂያ ሰጣቸው። በነገራችን ላይ
ለአንድነት ፓርቲ ፍርድ ቤቱ የላከው ደብዳቤ ላይ ተከሳሽ ማን እንደሚል ያውቃሉ…? “አቃቤ ህግ!” ነው የሚለው።
ወይ ጉድ! እናንተዬ አንዳንዴ ይሄ የኮምፒውተር ታይፕ መንፈስ ቅዱስ ያናግረዋል እንበል እንዴ!? የሆነ ሆኖ አቃቤ
ህግ “ተከሳሽ” ተብሎ በተፃፈበት የመጥሪያ ወረቀት አንድነቶች ትህትና ይዟቸው ሄዱ… ከዛም ጥፋተኛ ናችሁ ተባሉ።
እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ፍርድ ቤት ሰዎችን ጥፋተኛ ለማለት ችሎት አቁሞ ሰዎቹ ተከራክረው ዳኞች ግራ ቀኙን
አይተው ነበር ጥፋተኛ የሚሉት…! ወይስ ይሄ ነገር ዘወትር ማክሰኞ ማታ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ ብቻ ነው…!? ብዬ
ልሳለቅ አማረኝና ግዜው የልማት እንጂ የስላቅ ነውን…!? ስል ራሴ ላይ ክልከላ አድርጌያለሁ።
እኔ የምለው ወዳጄ ልማቱ እንዴት ይዞታል!? ማለቴ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ በኋላም እየተቀላጠፈ ነው ወይስ
እየተንቀራፈፈ ነው? አይ እርሳቸው እንደው ሜዳ ላይ በትነውን እልም አሉ እኮ! አንዳንድ የፌስ ቡክ አሽሟጣጮች
“አባይን የደፈሩ መሪ ሞትንም ደፈሩት!” እያሉ ሲናገሩ ሰምቻለሁ። እንዴት ነው ነገሩ በቃ ቁርጡ ታወቀ እንዴ!?
በእርግጥ እዚህ ውጪው ሀገር የሚገኙ መገናኛ ብዙሃኖች መርዶውን ካረዱን ቆይተዋል። የሀገር ውስጥ ዘጋቢዎቻችን ግን
አንዴ ገቡ፣ አንዴ ወጡ፣ አንዴ አረፉ፣ አንዴ አገገሙ እያሉ እያምታቱን ነው።
በዛ ሰሞን ፋና ኤፍ ኤም ራዲዮን “ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ነገር ቢሆኑ ማን ይተካቸዋል!?” የሚል የህግ
ውይይት ማድረጉን ስሰማ ይሄ ነገር በቃ ለይቶለታል ማለት ነው…? መቼም እዚህ አገር “ደግ አይበረክትም” ብዬ
ተንሰቅስቄ ነው ያለቀስኩት። አሁን በቅርቡም ለጠቅላይ ሚኒስትራችን የስጋ ዝምድና እንዳላቸው የሚነገርላቸው እሜቴ
ሚሚ ስባቱ ራዲዮ ላይ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢያርፉ እንኳ ሀገሪቷ በአንድ ሰው መሞትና አለመሞት ላይ የሚመጣ ለውጥ
የለም” የሚል እጅግ ጨካኝ የሆነ አስተያየት ሰማሁኝ! በእውኑ ጠቅላይ ሚኒስትራችን አንድ ሰው የሚባሉ ናቸውን…?
ለነገሩ ባለፈው ጊዜም እኚያ አቦይ ስብሀት “ፋጢመት ሞተች አልሞተች ዘሪሁን ሞተ አልሞተ መለስ ሞተ አልሞተ እኛ
ምን አገባን” አይነት ነገር ሲናገሩ በሰማሁ ጊዜ በእውነቱ ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከእኛ በቀር አንድ እንኳ አሳቢ ሰው
እንደሌላቸው ተረድቻለሁ።
ኧረ ስለ እትዬ ሚሚ ካነሳን አይቀር የምንቀደው አለን…
እማማ ሚሚ በኤፍ ኤም ራዲዮናቸው ላይ “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሞቱም ግዴየለም” ከሚለው ጨካኝ ንግግር ጋር አብረው
የዘመድ አንጀት ሆኖባቸው ነው መሰል “ደግሞም ሀገር ውስጥ ያለው ህዝብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጤና እየፀለየላቸው
ነው!” ብለው ሆድ አስብሰውኛል። እሜቴ ሚሚ ልብ አላሉም እንጂ በውጪ ያለውም ኢትዮጵያዊ እንዴት በአንድ በአንድ
እግሩ ቆሞ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚፀልይ ቢመለከቱ ይደነቁ ነበር። የምሬን ነው የምልዎት በርካታ በውጪ ሀገር
የሚገኝ ኢትዮጵያዊ ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ትልቅ ፀሎት እያደረገ ነው። እርግጥ ነው የአብዛኛው ሰው ፀሎት
እርሳቸው ድነው የበደሉትን ይቅርታ እንዲጠይቁ እና ለንስሀ ሞት እንዲበቁ መሆኑን ሰምቻለሁ። (እኔ እንደሆንኩ
የሰማሁትን መደበቅ አይሆንልኝም።)
ወደ እትዬ ሚሚ ስንመለስ “ክብ ጠረቤዛ” የሚል አንድ ፕሮግራም አላቸው። እርሱን ፕሮግራም አልፎ አልፎ
ለማዳመጥ እድሉ ገጥሞኛል። አንድ ግዜ ቁጭ ብዬ ስሰማ አንዱ ወዳጄ ሰማኝና ምን አለኝ መሰልዎ… ይሄ ፕሮግራም
“በማሽካካት እና በጫጫታ የተሞላ በመሆኑ አንዳንድ ጊዜ ክብ ጠረቤዛ ነው ክብ ባንኮኒ ብዬ እጠራጠራለሁ።” ብሎኛል
የምር ግን እኔ ራሴ ፕሮግራሙን ሳዳምጥ በተለይ አንዳንድ ጊዜ በገደል ማሚቶ የታጀበ ሳቅ እና ሁካታውን ሳዳምጥ
ይሄንን ሰፈር የት ነበር የማውቀው…? ብዬ አይኔን ጨፈን አድርጌ አስባለሁ… ትዝ ሲለኝ ለካስ ቺቺኒያ እና ካዛንቺስ
ነው….! የብርጭቆው ኳኳታ የለም እንጂ በእውነት “መሸታ” ቤቶቻችንን ትውስ ያደርጋል!
በነገራችን ላይ እነ እማማ ሚሚ ሲበሳጩ የሚናገሩትን አያውቁትም እየተባሉ ይታማሉ። ባለፈው ጊዜ ሙስሊም
ወንድምና እህቶቻችን ላይ ሲያደርጉ የነበረው ዘለፋ እና ስድብ የቀለጠው መንድር ድራማ ላይ እንኳ የለም።
ብዙ ግዜ ሚዲያ ላይ ያለ ሰው ለብዙሃኑ ህብረተሰብ ስሜት እና እምነት ይጠነቀቃል። ማህበረሰቡ ውስጥ
የአመለካከት ችግር አለ ብሎ እንኳ ቢያምን የሚሰራውን “ስህተት” ቀስ ብሎ በተለያዩ የኪነጥበብ ዘዴዎች እና ለዛ
ባላቸው አቀራረቦች ለማረቅ ይሞከራል እንጂ እንደነ እትዬ ሚሚ “የጉራንጉር ሰፈር ስድብ” እየተሳደቡ መውረግረግ
እንኳንስ ሚዲያ ላይ እና ሜዳ ላይም ቢሆን ከጨዋ ልጅ የማይጠበቅ ነውር ነው።
ከሁሉ የገረመኝ እማማ ሚሚ ሙስሊም ወንድሞቻችንን እና መንግስትን ለማሸማገል የሞከሩ ግለሰቦችንም በዜሮ
ማባዛታቸው ነው። “የምን ሽምግልና ነው!? ሽምግልና የሚባል ነገርማ የለም!” ብለው ከእርሳቸው የሚጠበቅ (ታይፕ
ግድፈት የለውም “የሚጠበቅ” ነው ያልኩት) ከእርሳቸው የሚጠበቅ አሳዛኝ ንግግር ሲናገሩ ሰምቼ፤ ሽምግልናን
የሚያጥላላ እንደምን ያለ እርኩስ መንፈስ ተጠናወታቸው!? ብዬ ክፉኛ አዘንኩላቸው! ቢችሉ ራሳቸው ሽማግሌ ሆነው
ማስማማት ሲገባቸው ሽምግልናማ “የለም” ማለታቸው እጅግ አስደናቂ ነው! ስማቸው ሚሚ ቢሆንም ዕድሜያቸው ለሽምግልና
በቂ ነበር። ለነገሩ ለሽምግልና ዕድሜ ሳይሆን መሰጠት ያስፈልገዋል።
በዚሁ ፕሮግራም ላይ የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስቴሩ አቶ ጁነዲን ሳዶ ላይ እነ ሚሚ ክፉኛ ተሳልቀውባቸው ሲያበቁ
“ዛሬ ነገ ሳይሉ ከስልጣናቸው በራሳቸው ፈቃድ እንዲለቁ” እንደሚመክሩ እንዲሁም ፖሊስም በአስቸኳይ
“እንዲቀፈድዳቸው” ከጣራ በላይ እየተሳሰቁ ሲጠይቁ ነበር።
እኔ የምለው ድሮ በደርጉ ጊዜ መንግስቱ ኃይለማሪያም ጓደኞቻቸው ላይ ሞት እየፈረዱ አብዮት ልጆቻን ትበላለች
እየተባለ ይነገር ነበር። አሁንም ኢህአዴግ ነብሴ ቁልፍ ቁልፍ የሆኑ እና በአብዮታዊ ዴሞክራሲ አምነው የተጠመቁ
ግለሰቦች እና ድርጅቶች በራሱ በአብዮታዊ ዲሞልራሲ ክፉኛ ጥቃት እየተሰነዘረባቸው ነው። ታድያ ይሄ ነገር “አብዮታዊ
ዴሞክራሲም ልጆቿን ትበላለች” ያስብለን ይሆን!?
ኢትዮ ቻናል የተባለው ወሳኝ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ደቀ መዝሙር ራሱ ይኸው በቅርቡ ክፉኛ ጥቃት ደርሶበት ላልተወሰነ ጊዜ ጋዜጣውን ብቻ ሳይሆን ሳምሶን ማስታወቂያ ድርጅትም ሊዘጋ መሆኑን ሰምተን አዘነናል።
ሳምሶን ማስታወቂያ ድርጅት እና ኢትዮ ቻናል ጋዜጣን የሚያሳትመው ዜድ አሳታሚ ድርጅት ሁለት አመት ሙሉ
የመንግሰት ግብር ሳይከፍሉ ቁጭ ብለው በመገኘታቸው ባለቤቶቹ ከታሰሩ በኋላ ለዋስትና ሁለት መቶ ሺህ ብር “ሆጭ”
አድርገው ከፍለው ነው የተለቀቁት።
አቶ ሳምሶን ሲናገሩ “ግብር አለመክፈል በኔ አልተጀመረም የታሰርኩት ከበስተጀርባው ሌላ ነገር ኖሮ ነው” ሲሉ
ቅሬታ አሰምተዋል። ወይ ጉድ! “ጉድ ሳይሰማ መቼም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፍፃሜ አይታወቅም” አቶ ሳምሶን ምን ነካቸው?
ምንስ ከጳጳሱ የሚበልጡ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ሰባኪ ቢሆኑ ግብርን ያህል ነገር ለሁለት አመታት ሳይከፍሉ መቆየት
ነውር አይደለም እንዴ!? እዝች ጋ አንድ የተባረከ ወዳጄ የነገረኝን ልንገርዎትማ… “ኢትዮ ቻናል ነፃ ጋዜጠኝነት
ሲባል ከግብር ነፃ መስሏት ነው እንዴ ይሄንን ያህል ጊዜ ግብር ያልከፈለችው?” ሲል ጠይቆኛል። ጋሽ ሳምሶን ምን
ልመልስለት? ደሞስ ከጀርባው ሌላ ነገር አለ ማለት ምን ማለት ይሆን? የእኛ ሰዎች ቅኔ መቼም ብዙ ነው! የታሰርኩት
በግንቦት ሰባት ሴራ ነው… ይበሉና እስኪ ያስቁኝ!
ለማንኛውም ፍርድ ቤት ቀርበው ዋናውን ቅጣት እስኪያገኙ ድረስ ሁለት መቶ ሺህ ብር ዋስትና አስይዘዋል። ላልተወሰነ ግዜም “ተወዳጇን” ኢትዮ ቻናል ጋዜጣ ገበያ ላይ አናያትም ማለት ነው።
የሆነ ሆኖ ግን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ልጆቿን እየበላች ያለበት ሁኔታ ነው ያለው። (“ያለበት ሁኔታ ነው ያለውን” ለኢቲቪ ብቻ ማን ሰጠው!?)
የአቶ ጁነዲን ሳዶ ባለቤትን ፖሊስ በሽብር ወንጀል እንደጠረጠራቸው ተናግሯል። እነ እሜቴ ሚሚ እንዳሉት ከሆነ
ደግሞ አቶ ጁነዲንም የሚቀርላቸው አይመስልም። እኒህ ሰውዬ ዋና ከሚባሉት የአብዮታዊ ዴሞክራሲ ልጆች አንዱ ናቸው።
በጥቅሉ እንደሚወራው ከሆነ… ከአቶ መለስ እና ከህውሃት ጋር የስጋ ዝምድና የሌለው ማነኛውም የአብዮታዊ
ዴሞክራሲ ልጅ የመበላት ዕጣ ፈንታ አለው…! እንዴት አይነት ርሃብ ቢገባ ነው…? ብሎ ማሽሟጠጥ አይገባም።
በመጨረሻም 1
ርዮት አለሙ
የርዮት አለሙ መፅሀፍ አሁን ገና ደረሰኝ። “የኢህአዴግ ቀይ እስክርቢቶን” ሽፋኑ ላይ ተመለከትኩት። ልጅቷ
መምህርትም አይደለች…!? እናም በመምህርኛ ኢህአዴግዬ ዴሞክራሲ የሚለውን ኤክስ አድርጎ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ሲል
ታሳየናለች። መድብለ ፓርቲ የሚለውንም በቀይ እስክርቢቶ ሰርዞ አውራ ፓርቲ ብሎ ይተካል። ነፃ ፕሬስ የሚለውን ደግሞ
“በልማታዊ ሚዲያ” ያስተካክለዋል። ኢትዮጵያዊነት የሚለውንስ…? የኢህአዴግ እስክርቢቶ ምን ጣጣ አለው “ጎሰኝነት”
ብሎ “ያስተካክለዋል” ታድያ ከዚህ ሁሉ የደነቀኝ ምን መሰልዎ…!? የእጅ ፅሁፉ! ኢህአዴግ ማስተካከያውን ሲፅፍ
ቃላቱን ብቻ ሳይሆን ፊደል አጣጣሉንም ውልግድግድ አድርጎ መሆኑ በጣም አስቆኛል። የራሱ የሆኑትን እነ “አብዮታዊ
ዴሞክራሲ” እንኳን በጥሩ የእጅ ፅህፈት አያሰፍራቸውም። ትለናለች ርዕዮት!
በእውነቱ ሽፋኑ ብቻ ብዙ ነገር የሚናገር መፅሐፍ ስል አድንቄያለሁ። እስቲ ደግሞ ገብቼ አነበዋለሁ! እጅሽን ቁርጥማት አይንካው ብለን እንመርቃታለን!
በመጨረሻም 2
ኦሎምፒክ
የለንደን ኦሎምፒክ እንዴት አዩት!? ሴቶች ማራቶን ከአስራ ስድስት አመት በኋላ ወደ ውጤት መጣን! በእውነት
ቲኬ ገላና ትሰራለች ገና የምትባል አይነት ወጣት መሆኗ ደግሞ ለቀጣዮቹ ጊዜያትም ተስፋ እንድንሰንቅ አድርጎናል።
ጥሩዬ እና መሲም ወርቅ አለብሰውናል። አቦ ወርቅ ልበሱ እንበላቸው እንጂ!
ያ “ፋራ” የተባለ እንግሊዛዊ ስሙን ፋራ አድርጎ የአራዳ ስራ አይደል እንዴ የሰራብን…? ከየት መጣ ሳይባል
የምንታወቅበት እና የምንመካበትን አስር ሺህ እና አምስት ሺህ ሜትር ሩጫ ውጤት አሳጣን እኮ! ለነገሩ ነሀስ እና
ብራችንንን ማን አየብን!? ትላንት ወዳጃችን ዮሐንስ ሞላ ማምሻውን ባደረሰን ግጥም እንዲህ ብሏል። ትንሽ
እንቆንጥር፤
“…ዋጋው መሰቀሉን ገበያውን ለሰማ
መድመቅ ለራበው ወንድ ማጌጥ ለተጠማ
አመሻሽ ላይ ሲገኝ ወርቅ ነው ብርማ” (አዲሱ ባለቅኔ ዮሐንስ ሞላ፤ ምስጋና ይገባዋል)
ወዳጄ እስከ አሁን ያወራነውን ለፍሬ ያድርግልን። እና በቃህ ብለው ያሰናብቱኝ…
አማን ያሰንብተን!
No comments:
Post a Comment