Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Sunday 12 August 2012

በገርጂ የኃይል ማስተላለፊያ የሚገኝ ትራንስፎርመር በድንገት ፈነዳ

•    የፍንዳታው ምክንያት በመመርመር ላይ ነው

ባለፈው ዓርብ ከምሽቱ አራት ሰዓት ገደማ ገርጂ መብራት ኃይል አካባቢ የሚገኘው ወረገኑ የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ ጣቢያ ውስጥ ከሚገኙት ትራንስፎርመሮች አንዱ፣ ባልታወቀ ምክንያት ፈንድቶ መቃጠሉንና የፍንዳታው መንስዔ በመጣራት ላይ መሆኑ ተገለጸ፡፡ ፍንዳታው በደረሰበት ሰዓት የኦሊምፒክ የሴቶች 5,000 ሜትር የሩጫ ውድድርን ለማየት በጉጉት በመጠበቅ ላይ በነበሩት የአካባቢ ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ድንጋጤ የፈጠረ ሲሆን፣ ፍንዳታውን ተከትሎም በጣቢያው የነበሩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ሠራተኞች በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ከቤታቸው ወጥተው እንዲቆዩ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸው ታውቋል፡፡

የፍንዳታው መንስዔ በመጣራት ላይ መሆኑን የኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ምስክር ነጋሽ ገልጸዋል፡፡ ትራንስፎርመሩ ያረጀ በመሆኑ ከኃይል ጭነት ብዛት፣ ከማርጀት ጋር ወይም ከተፈጥሮ ጋር የተያያዘ መሆኑን ለማጣራት የኮርፖሬሽኑ ባለሙያዎች በምርመራ ላይ እንደሚገኙና ውጤቱም በዛሬው ዕለት እንደሚታወቅ አብራርተዋል፡፡


በጣቢያው ውስጥ ያሉት የተቀሩት ትራንስፎርመሮች ያረጁ በመሆናቸው የኃይል ማስተላለፊያ ጣቢያውንና በአካባቢው የሚገኙትን ነዋሪዎች ከተመሳሳይ አደጋ ለመጠበቅ ምን ዋስትና አለ? በሚል ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ ኮርፖሬሽኑ በአገር አቀፍ ደረጃ የተለያየ ቮልቴጅ መጠን ያላቸው ትራንስፎርመሮችን የቅድመ ጥገና ክትትል እያደረገላቸው መሆኑን ምላሽ የሰጡት ኃላፊው፣ አቅማቸውንም የማሳደግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

አደጋው ከተከሰተ በኋላ ቅድሚያ የሚሰጠው በተቃጠለው ትራንስፎርመር ምክንያት ኃይል የተቋረጠባቸው አካባቢዎች ኃይል የሚያገኙበትን አማራጭ ማፈላለግ እንደሆነ የገለጹት አቶ ምስክር፣ ከዚህ ትራንስፎርመር ኃይል የሚተላለፍላቸው አካባቢዎች ግማሾቹ ከሌላ ትራንስፎርመር ኃይል ማግኘት መቻላቸውንና ቀሪዎቹም እስከ ትናንት ምሽት ድረስ እንደሚያገኙ አስታውቀዋል፡፡

በትራንስፎርመሩ መቃጠል ምክንያት የኤሌክትሪክ ኃይል ያጡት አካባቢዎች ሲኤምሲ፣ ገርጂ፣ የረር፣ መሪ፣ መገናኛ በከፊል፣ ቦሌና ባምቢስ መሆናቸው ተገልጿል፡፡ ይሁንና ከፍንዳታው በፊትም ቢሆን በተለይ በየረር፣ በመብራት ኃይል፣ በገርጂና በሌሎች አካባቢዎች ካለፉት ሳምንታት ጀምሮ ኃይል በተከታታይ በመጥፋት ላይ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የደረሰውን አደጋ ለማየት የውኃና የኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑና የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ምሕረት ደበበ በሥፍራው በትናንትናው ዕለት መገኘታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ከተሞች ባለፉት ሳምንታት በተለያዩ ቀናት የኃይል መቋረጥ እየተከሰተ ሲሆን፣ የኮርፖሬሽኑ ሠራተኞች በያዝነው ሳምንት ለተከታታይ ቀናት የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎትን በዘመናዊ፣ በቀልጣፋና በአስተማማኝ መንገድ ለማቅረብ የሚቻልበትን መንገድ በመምከር ላይ መቆየታቸውን አቶ ምስክር አያይዘው ገልጸዋል፡፡

ሆኖም የሪፖርተር ምንጮች እንደገለጹት፣ በአሁኑ ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙትን አሮጌ ትራንስፎርመሮች ለመተካት የሚገዙ አዲስ ትራንስፎርማሮች በብዛት ጥራታቸውን ያልጠበቁ ናቸው፡፡ በመሆኑም ከዕቃ ግዥ ጋር በተያያዘ ብልሹ አሠራሮች በግልጽ እየታዩ እንደሆነና ሠራተኞችም ይህን እንዲያጋልጡ ስብሰባው በተካሄደባቸው ቀናት የጦፈ ክርክር መነሳቱን አስረድተዋል፡፡

No comments:

Post a Comment