Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Sunday 12 August 2012

ባንኮች የውጭ ምንዛሪ መስጠት አዳግቷቸዋል

ethiopia36: Addis Ababa, Ethiopia:  Commercial Bank of Ethiopia - Gambia street - photo by M.Torres - (c) Travel-Images.com - Stock Photography agency - Image Bank

ከውጭ ምንዛሪ ክምችት እጥረት ጋር በተያያዘ በአገሪቱ ውሰጥ የሚንቀሳቀሱ የንግድ ባንኮች የውጭ ምንዛሪ ለሚፈልጉ ኩባንያዎች ሌተር ኦፍ ክሬዲት (L/C) መክፈት እንዳልቻሉ ታወቀ፡፡ በተለይ የአገሪቱ ትልቁ የንግድ ባንክ የሆነው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ለደንበኞቹ ሌተር ኦፍ ክሬዲት መክፈት ሲያቆም፣ ባንኩ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የአገሪቱ የሦስት ወራት የውጪ ንግድ ከመቀነሱ ጋር በተያያዘ ነው የሚል መልስ እየሰጠ መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ ሁሉም የንግድ ባንኮች ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ የፈለጉትን ያህል የውጭ ምንዛሪ ከብሔራዊ ባንክ ባለማግኘታቸው፣ ለደንበኞቻቸው ሊከፍቱ የሚገባቸውን ሌተር ኦፍ ክሬዲት መክፈት አልቻሉም፡፡ በሁሉም ባንኮች በርካታ ደንበኞች አገልግሎቱን ለማግኘት ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡

በተለይ ካለፉት አራት ሳምንታት ወዲህ ደግሞ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይገዙት የነበረው የውጭ ምንዛሪ ሙሉ ለሙሉ በመቋረጡ፣ በግል ከዓለም አቀፍ ባንኪንግ ዲፓርትመንቶቻቸው በኩል ከሐዋላ የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ ገቢ፣ አንገብጋቢ ለተባሉ ግዥዎች ብቻ ሌተር ኦፍ ክሬዲት ለመክፈት መገደዳቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡

መንግሥታዊው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም በአሁኑ ጊዜ ሌተር ኦፍ ክሬዲት የሚከፍተው ለነዳጅ፣ ለመድኃኒትና ለመሳሰሉት ቅድሚያ ይሰጣቸው ለተባሉ ምርቶች ግዥ ብቻ እንደሆነም ተጠቁሟል፡፡

ላለፉት ጥቂት ወራት በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ የንግድ ባንኮች በውጭ ምንዛሪ እጥረት በጣም የተጎዱበት ወቅት እንደነበር የሚያስታውሱት የንግድ ባንክ ባለሙያዎች፣ በተለይ እጥረቱ በግል ባንኮች ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ሽያጩን ቢያቋርጥም ለባንኮች ምክንያቱን ያልገለጸ መሆኑን ምንጮች አስታውቀው፣ ባንኮችም ለውጥ ካለ በማለት በየቀኑ ለብሔራዊ ባንክ ጥያቄ እያቀረቡ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ እጥረት መኖሩ ሊገለጽልን ይገባ የነበረው ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ከመድረሱ በፊት መሆን አልነበረበትም የሚሉ በንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ አስተያየት ሰጪዎች፣ እጥረቱ በምን ምክንያት እንደተከሰተ እንኳን አለማወቃቸውንም ይጠቁማሉ፡፡

ዋናው ጉዳይ ግን የብሔራዊ ባንክ ዕርምጃ የአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት እጅግ አነስተኛና አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የሚያሳይ ነው የሚሉ የባንክ ባለሙያዎች አሉ፡፡

አሁን ለተከሰተው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ዋነኛ መንስኤ ሊሆን የሚችለው ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በሕገወጥ መንገድ ከአገሪቱ በመውጣቱ እንደሆነ የሚገልጹ የፋይናንስ ባለሙያዎች፣ በዚህ ወቅት ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ ሽያጩን ማቆሙም ትክክል ነው ይላሉ፡፡ እንደ ምክንያት የሚያቀርቡትም የውጭ ምንዛሪ ክምችት ካነሰ የባሰ ደረጃ ላይ ሳይደርስ መቆጣጠር ስላለበት ነው የሚለውን ነው፡፡

ሌላው አሁን ለተፈጠረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት መንስኤ የሆነው ኤክስፖርተሮች ከትክክለኛው የገበያ ዋጋ በተለየ የወጪ ንግድን ዋጋ ማሳነስ (Under Invoicing) አንዱ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ አስመጪዎች የገቢ ንግድ ዋጋን ከፍ በማድረግ (Over Invoicing) ከማድረግ ጋር የተያዘ ሊሆን ይችላልም ይላሉ፡፡

ተሻሽሎ በወጣው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አዋጅ ውስጥ እንደተጠቆመው፣ ዓለም አቀፍ የመጠባበቂያ ገንዘብ ከሚያስፈልገው መጠን ያነሰ እንደሆነ ወይም ሊያንስ እንደሚችል የብሔራዊ ባንክ ገዥው ካመነበት አስፈላጊ ናቸው የሚላቸውን ዕርምጃዎች ሊወስድ ይችላል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የመጠባበቂያ ገንዘቡ በቂነት የመቀነስ አዝማሚያ እያሳየ መሆኑን ሲገነዘብ የመጠባበቂያ ገንዘቡን ይዞታ፣ ለችግሩ መንስኤ የሆኑትን ወይም ሊሆኑ የሚችሉትን ምክንያቶችና ሁኔታዎችን ለማሻሻል አስፈላጊ የመሰለውን የመፍትሔ ዕርምጃ የያዘ የውሳኔ ሐሳብ ለባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሪፖርት ማቅረብ እንደሚኖርበትም ይደነግጋል፡፡

ችግሩ እየተባባሰ መሄዱን ከተገነዘበ የብሔራዊ ባንክ ገዥው የውጭ ምንዛሪ ፈቃድ እንዳይሰጥ ሊያግድ የሚችል ሥልጣን ጭምር ስላለው፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የውጭ ምንዛሪ ላይ ጠበቅ ያለ ዕርምጃ እየወሰደ ያለው ችግሩን ለማቃለል ታስቦ ነው ሲሉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡

ሆኖም አሁን የታየው የውጭ ምንዛሪ እጥረት በዚሁ ከቀጠለ ምናልባት አዳዲስ ዕርምጃዎች ሊወሰዱ ይችላሉ የሚል ግምት አለ፡፡ ከእነዚህ ውስጥም የብር ምንዛሪ ለውጥ አንዱ ሊሆን ይችላል፡፡ ከወራት በፊት ብሔራዊ ባንክ ባቀረበው የዘጠኝ ወራት የሥራ ሪፖርቱ በቂ ዓለም አቀፍ መጠባበቂያ ገንዘብ መኖሩን ገልጾ እንደነበር ይታወሳል፡

No comments:

Post a Comment