Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Wednesday, 15 August 2012

ኢራፓ፦”አገሪቷን ማን እንደሚመራት ባለመታወቁ በስጋት እየታመሰች ትገኛለች”አለ

ኢሳት ዜና:-ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥራ ላይ አለመሆናቸው ከተነገረና ከተረጋገጠ ጊዜ አንስቶ፣ ኢትዮጵያን ማን እየመራት እንደሆነ ለሕዝብ ይፋ ባለመገለጹ አገሪቱ በወሬ፣ በሐሜት፣ በፍርኀትና በሥጋት እየታመሰች ትገኛለች ሲል የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ ገለጸ።
ኢራፓ ባወጣው ወቅታዊ መግለጫ   አገሪቱ በማን እየተመራች እንደሆነ  ለኢትዮጵያ ህዝብ በግልጽ እንዲነገረው አሣስቧል።
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 12(1) የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ መከናወን እንዳለበት መደንገጉን ያወሳው ኢራፓ፤  በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 75 በተደነገገው መሠረት፣ ኢትዮጵያ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይም በሌላ አካል እየተመራች ከሆነ፣ የሕገ መንግሥቱ ቃል ሳይሸራረፍ በግልጽና በትክክል ለሕዝብ ሊገለጽ እንደሚገባ አስታውቋል፡፡
የፓርቲው ፕሬዚዳንት አቶ ተሻለ ሰብሮ እንዳሉት፤ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29(3ለ) የሕዝብ ጥቅምን በሚመለከት ሕዝቡ መረጃ የማግኘት መብት እንዳለው የሚያረጋግጠው መብት ሊከበር ይገባል፡፡
ኢራፓ ሰላማዊና ሕገ መንግሥታዊ ዘላቂ መፍትሔ ከመፈለግ አንፃር፣ አገራዊ አጀንዳዎች በተወሰኑ ቡድኖች ከመጋረጃ በስተጀርባ መታየትና መወሰን እንደሌለባቸው ጽኑ እምነት አለው የሚለው የፓርቲው መግለጫ፤ ተቃዋሚና ተፎካካሪ ፓርቲዎችንና ኅብረተሰቡን አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ የውይይት መድረክ በመፍጠር፣ ለብሔራዊ መግባባት ጥርጊያ መንገድ መመቻቸት እንዳለበት አስረድቷል፡፡
ኢራፓ እንዳለው፤ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥራ ላይ አለመሆናቸው ከተነገረና ከተረጋገጠ ጊዜ አንስቶ፣ ላለፉት ስድስት ሳምንታት ኢትዮጵያን ማን እየመራት እንደሆነ ለሕዝብ ይፋ አልተደረገም። ይህም አገሪቱን በወሬ፣ በሐሜት፣ በፍርኀትና በሥጋት እንድትታመስ አድርጓታል። ሁኔታው በዚህ ከቀጠለ፤ለውጭና ለውስጥ ጠላቶች ምቹ ሁኔታዎች ይፈጠራል የሚል ስጋት አለ፡፡
ይህ እንዳይፈጠር፤ መንግስት  ለህዝብ ግልጽ መሆን አለበት ብሏል-ኢራፓ።
ሰው እስከሆኑ ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ  ለምን ታመሙ? እንደማይል ይልቁንም መልካም ጤንነታቸውን እንደሚመኝ የገለጸው ኢራፓ፣ ድነው የአመራር ዘይቤአቸውንና የአስተዳደር ሥርዓታቸውን  የሚፈትሹበት የንስሀና የመሠረታዊ ለውጥ አብሳሪ የሚሆኑበት ዕድል እንዲገጥማቸው ተመኝቷል፡፡

No comments:

Post a Comment