Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Sunday 22 April 2012

የቴዲ አፍሮ አልበም ሽያጭ ሬከርድ አስመዘገበ

Sunday, 22 April 2012 00:00
By Tibebesilassie Tigabu

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የተለቀቀው የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ‹‹ጥቁር ሰው›› አልበም በ300 ሺሕ ሲዲና በ120 ሺሕ ካሴት ሽያጭ፣ በአጠቃላይ ከሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ አሥር ሚሊዮን ብር ገደማ በማስገባት፣ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ኢንዱስትሪ ታሪክ አዲስ ሬከርድ ማስመዝገቡ ታወቀ፡፡ ሽያጩ የተመዘገበው አልበሙን ከአዲካ ኮሙዩኒኬሽንና ኢቨንትስ ተቀብለው በማከፋፈል እየሸጡ ካሉት ከኤሌክትራና ከአምባሰል ሙዚቃ ቤቶች፣ እንዲሁም ከጣና ኢንተርቴይንመንት ነው፡፡ ኤሌክትራና አምባሰል ሙዚቃ ቤቶች በአዲስ አበባና በተለያዩ ክልሎች ለሽያጭ ሲያቀርቡ፣ ጣና ኢንተርቴይንመንት በሰሜን ኢትዮጵያ ያከፋፍላል፡፡

አዲካ ለሙዚቃ ቤቶቹ እያንዳንዱን ሲዲ በብር 17.50 እያንዳንዱን ካሴት ደግሞ በዘጠኝ ብር ሲያስረክብ፣ ገበያው ውስጥ አንዱ ሲዲ 25 ብር አንዱ ካሴት ደግሞ 13 ብር እየተሸጠ ይገኛል፡፡ ምንም እንኳ አንዱ ሲዲ በተወሰነለት ዋጋ እንዲሸጥ ቢታሰብም በየመንገዱ እስከ ሃምሳ ብር እንደተሸጠ ታውቋል፡፡

አዲካ ከሳምንት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ከሽያጮቹ 6.3 ሚሊዮን ብር ያገኘ ሲሆን፣ ቀሪው ገንዘብ ደግሞ ለሙዚቃ ቤቶቹና መንገድ ላይ ለሚሸጡ ገቢ ይሆናል፡፡ አልበሙ ከወጣበት ሚያዝያ 6 ቀን 2004 ዓ.ም. ጀምሮ በብዛት እየተሸጠ መሆኑም ታውቋል፡፡
በተለይም አልበሙ በወጣበት ሚያዝያ 6 ቀን በርካታ ሰዎች በሙዚቃ ቤቶች ደጃፍ ወረፋ ሲጠብቁና ሌሎችም መንገድ ላይ ካሉ ሻጮች በጭማሪ ዋጋ ሲገዙ ታይተዋል፡፡

‹‹በተለያዩ ሚዲያዎች የሙዚቃ አፍቃሪያን ከተወሰነው ዋጋ በላይ አውጥተው አልበሙን እንዳይገዙ ብናስታውቅም፣ አንዳንድ ነጋዴዎች እጥረት ያለ አስመስለው ከተተመነው ዋጋ በላይ ሲሸጡ ነበር፤›› በማለት የአዲካ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ ዘለቀ ገልጸዋል፡፡

አቶ አሸናፊ ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ 500 ሺሕ ሲዲዎችና 200 ሺሕ ካሴቶች ሙዚቃ ቤቶቹ እንደሚያስፈልጋቸው በመጀመርያ ስላስታወቁ አልበሙ አሁንም እየታተመ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ አልበሙ በአዲካ ወኪሎች በኩል በውጭ አገር በመሸጥ ላይ ቢሆንም፣ አቶ አሸናፊ ግን ምን ያህል ኮፒዎች አንደተሸጡ ገና አልታወቀም ብለዋል፡፡

ከአሁን ቀደም ለገበያ ከቀረቡ የሙዚቃ ሥራዎች ከፍተኛ ሽያጭ በማስመዝገብ የአገሪቱን ሬከርድ ይዟል የተባለለት የቴዲ አፍሮ አልበም መሆኑን በሙዚቃው ዘርፍ ውስጥ ያሉ ይስማማሉ፡፡ ሳምንት ባልሞላ ጊዜ እንኳን 300 ሺሕ ሲዲ መሸጥ ይቅርና ኦሪጂናል አልበም ለመሸጥ ከፍተኛ ችግር እንደነበር በሙዚቃ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ይስማሙበታል፡፡

በተለይም ከቅጂ መብት ጥሰት ጋር በተያያዘ በርካታ የሙዚቃ ሰዎች ተስፋ እስከ መቁረጥ መድረሳቸውም ይታወሳል፡፡ ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ አንድ የሙዚቃ ባለሙያ፣ ‹‹የቴዲ አፍሮ አልበም ሽያጭ የአገሪቱ ሬከርድ ሲሆን፣ ምናልባት ለኢትዮጵያ ሙዚቃ ኢንዱስትሪም ዓይን ከፋች ሊሆን ይችላል፤›› ብለዋል፡፡ አልበሙ በሕዝብ ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት ቢያገኝም እሳቸው ግን በግላቸው የተለየ አመለካከት እንዳላቸው ገልጸው፣ ዝርዝር ውስጥ ገብተው ከመናገር እንደሚቆጠቡ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ሕዝብ ሆ ብሎ የተቀበለውን ነገር ለመተቸት መነሳት ለጊዜው አስፈላጊ አይደለም፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

No comments:

Post a Comment