ሚያዚያ ፲፮ (አስራ ስድስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት
ዜና:-አንድ ጎልማሳ ኢትዮጵያዊ ዛሬ ከቀኑ 11፡00 ሰዓት ላይ በመሐል አዲስ አበባ ጊዮርጊስ ዳግማዊ ምኒልክ
ሃውልት ፊት- ለፊት በሚገኘው የአውቶብስ መቆሚያ ጎዳና ፤ አዲስ ምሩቅ ተማሪዎች የሥራ ማስታወቂያ የሚመለከቱበት
ቦታ ላይ ራሱን በላስቲክ የውሃ መያዣ በያዘው ቤንዚን አቃጠለ፡፡
በሥፍራው የነበሩ ሰዎች በውሃ እና
ለፍራፍሬ ንግድ ከለላ የተደረገ ህንፃ ሲሰራ እንደ ከለላ የሚጠቀሙበት ሸራ መሰል ነገር፤ በማንሳትና በማራገፍ
እሳቱን ሊያጠፉለት ቢሞክሩም ግለሰቡ ተውኝ መሞት መፈለጌን ህዝብና መንግሥት እንዲያውቅልኝ እፈልጋለሁ ብሏል ሲሉ
የዐይን እማኞች ተናግረዋል፡፡
እንደ እማኞች ገለፃ ግለሰቡ ከወገቡ በላይ ሙሉ በሙሉ ተቃጥሎ ቆዳው የተኮማተረ ሲሆን ጀርባው በእሳቱ በእጅጉ የተጎዳ ሲሆን፣ ጸጉሩም መርገፍ ጀምሮ አይኑ ብቻ ከጉዳት ተርፏል፡፡
ዘጋቢያችን
11፡ 30 ሰዓት ላይ ከሥፍራው ሲደርስ ራሱን ያቃጠለው ግለሰብ የለበሰው ጃኬት እንደ ወረቀት አሮ ወዳድቆ፣ ወይን
ጠጅ ነጠብጣብ ያለው የተቃጠለ ሸሚዝ ቁርጥራጭ ወዳድቆ የተመለከተ ሲሆን ግለሰቡን ፌዴራል ፖሊስ በፓትሮል መኪና
መወሰዱን እማኞች ነግረውት የቀይ መስቀል አምፑላን መጥቶ ፖሊስ ወስዶታል ተብሎ ባዶውን ሲመለስ ከሥፍራው ታዝቧል፡፡
ዘጋቢያችን
ከሥፍራው በእቡእ እማኞችን ለማናገር የሞከረ ሲሆን ሁኔታውን እየሰቀጠጣቸው የተመለከቱ በአካባቢው የጋዜጣ፣
የመጽሔት ንግድ ላይ የነበሩ እማኞች ሰውየው ከታክሲ መውረዱንና በወቅቱ በአኳ ላስቲክ የያዘው ቤንዚን ሳይሆን ውሃ
እንደመሰላቸውና ንግግርም ሲያደርግ ትኩረት እንዳልሰጡት ገልጸዋል፡፡
ቤንዚኑን ራሱ ላይ በመላ አካላቱ
እያፈሰሰ ሁለት ጊዜ ክብሪት ሲጭር እምቢ ብሎት በሦስተኛው ቦግ ብሎ መንደድ እንደጀመረና እየሮጠ ወደ አውቶብስ
ተጠጋ በማለት የገለጹት እማኞች፣ የአውቶብስ ሹፌር በሮቹን ዘግቶበት ተመልሶ የማስታወቂያ መመልከቻው ቦታ ላይ
ተዝለፍልፎ በመውደቁ ሰዎች እየተሯሯጡ ውሃ በማፍሰስ እና በሸራ በመጠቅለል ሊያጠፉለት ቢሞክሩም እስትንፋሱ ሙሉ
ለሙሉ ባይጠፋም ጉዳቱ ከፍተኛ ሆኗልብለዋል፡፡
የፌዴራል ፖሊስም ወደ ሥፍራው በፍጥነት በመምጣት ሰዎችን
በትኖ የሚያጣጥረውን ግለሰብ በፓትሮል መኪና በመውሰድ በአካባቢው በቅርብ የተመለከቱ ሰዎችን ሰብስቦ እዚያው አካባቢ
የሚገኝ አንድ ቅጥር ጊቢ ሰብስቦ የሞባይል ስልካቸውን በመንጠቅና በማስፈራራት ጊቢውን ዘግቶ አግቷቸዋል ብለዋል፡፡
በአካባቢው
የሥራ ማስታወቂያ ስትመለከት የነበረች አንዲት ግለሰብ ጎልማሳው በሰውነቱ ደህና የሚባል ሰው ሲሆን ጸአዳ ስኒከር
ጫማ ግሬይ ጅንስ ሱሪና ወይን ጠጅ ሸሚዝ ከጃኬት ጋር መልበሱን በእድሜውም ከ25 እስከ 35 ሊደርስ እንደሚችል
ለዘጋቢያችን ገልፃ ከታክሲ ወይም ከባስ መውረዱን ያዩት ሰዎች ነግረውኛል እኔ ግን ሲቃጠል ብቻ ነው የተመለከትኩት
ስትል እንባ እየተተናነቃት ለዘጋቢያችን ገልጻለች፡፡
ዘጋቢያችን በቦታው ባደረገው ቅኝት ግለሰቡ ወደቀ
የተባለበት ሥፍራው ላይ የልብሶቹ ቁርጥራጮችን፣ እሳቱን ሊያጠፉበት የሞከሩትን ሸራ መሳይ ላይለን፣ በውሃ የረጠበ
ሥፍራ ተመልክቷል፤ የፌዴራል ፖሊስም ሰዎችን አግቶ እና አንድ ግለሰብን ደግሞ (እማኞች በሞባይል ለመቅረጽ ሞክሮ
ነበር ብለዋል) አንበርክከው ሲመቱት ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ቴሌቭዥን ሪፖርተርና የካሜራ ጋዜጠኛ
በሥፍራው ተገኝተው ቦታውን ቀርጸው ሁኔታውን የተመለከቱ ሴት እማኞችን ቃለ መጠይቅ ያደረጉ ሲሆን የደህንነት ሰዎች
መጥተው እንዳይቀርጹ ሲከለክሏቸው እኛ ኢቲቪዎች ነን ሥራችንን እንስራበት በማለት ቀረፃቸውንና ቃለ- መጠይቃቸውን
የቀጠሉ ሲሆን የደህንነት ሠራተኞቹም ለዘብ ብለው ሰዎችን ወደ መበተኑና ወደ መጠጋጋቱ ሲያመሩ ዘጋቢያችን
አስተውሏል፡፡
hello!
ReplyDelete