Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Tuesday, 1 May 2012

ከ70 በላይ የፓኪስታን ዜጎች ጋምቤላን ለቀው ወጡ

ሚያዚያ ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ባለፈው ቅዳሜ በጋምቤላ በፓኪስታንና በኢትዮጵያውያን ላይ በተፈጸመው ጥቃት አራት ኢትዮጵያውያን እና አንድ ፓኪስታናዊ መገደላቸውን እንዲሁም አራት ፓኪስታናውያንና 5 ኢትዮጵያውያን መቁሰላቸውን ተከትሎ፣ በሼክ ሙሀመድ ሁሴን አል አሙዲን ሳውዲ ስታር ኩባንያ ውስጥ በከፍተኛ አመራርነት ይሰሩ የነበሩ ከ70 በላይ የፓኪስታን ዜጎች አካባቢውን ለቀው ዛሬ ወደ አዲስ አበባ ተጉዘዋል።
 ፓኪስታናውያኑ አካባቢውን የለቀቁት የፓኪስታን ኢምባሲ ባለስልጣናት ጋምቤላ መግባታቸው ከተነገረ በሁዋላ ነው። ኢንጂነሮች፣ የተለያዩ ማሽኖች ላይ ሲሰሩ የነበሩ ፓኪስታናዊያን አካባቢውን ለቀው የሚወጡት በዚህ ሁኔታ ለመስራት እንደማይችሉ ካስታወቁ በሁዋላ ነው። አንድ ፓኪስታናዊ እንደተናገረው ” መቼ እንደምንመለስ አናውቅም፣ ነገር ግን አሁን ባለው ሁኔታ ወደ ዚህ አካባቢ ተመልሰን እንመጣለን የሚል እምነት የለንም፣ ሁኔታው አስፈሪ ነው” ብሎአል።
የፓኪስታናዊያኑ ስራ አቋርጦ መሄድ የሳውዲ ስታር መዘጋትን ሊያስከትል ይችላል የሚል ስጋት ማሳደሩም ታውቋል። በአሁኑ ጊዜ የኩባንያው ሰራተኞች ስራቸውን ሙሉ በሙሉ ያቆሙ ሲሆን፣ ትናንት ጋምቤላ የተገኙት የሳውዲ ስታርና የሚድሮክ  ባለስልጣኖች ለፓኪስታናዊያኑ በቂ የደህንነት ዋስትና ሊሰጡዋቸው ባለመቻላቸው ፣ ፓኪስታናዊያኑ ለመልቀቅ ሳይገደዱ እንዳልቀረ መረጃዎች ይጠቁማሉ።
 ከትናንት ጀምሮ ደግሞ የመከላከያና የክልሉ ባለስልጣናት ህዝቡን ሲያነጋግሩ መዋላቸው ታውቋል። የመካለከያ ባለስልጣናቱ ለነዋሪዎች ” የእኛ እዚህ መኖር የእናንተ ድጋፍ ካልታከለበት ዋጋ የለውም፣ አጥፊዎችን አጋልጣችሁ ካልሰጣችሁን እኛ በራሳችን የደህንነታችሁን ዋስትናችሁን ለማረጋገጥ አንችልም።” በማለት ሲቀስቀሱ እንደነበር ታውቋል።
 በዛሬው እለትም የክልሉ ፕሬዚዳንት ሳይቀር በቅስቀሳው ስራ ላይ በመሰማራት ” ታጣቂዎቹ ከእኛ አልፈው በውጭ አገር ዜጎች ላይ ጥቃት መፈጸም በመጀመራቸው ህዝቡ ማንነታቸውን አጋልጦ ለመንግስት አሳልፎ ሊሰጥ ይገባዋል።” በማለት ሲናገር ተደምጧል።
የህዝቡ ዝምታ ያስፈራው የክልሉ መንግስት ትናንት ባደረገው ዝግ ስብሰባ ” ነዋሪው የፊታችን ሀሙስ ወደ አደባባይ በሰልፍ በመውጣት ድርጊቱን እንዲያወግዝ እንዲሁም የልማት እንቅስቃሴው በፈቃዳችን የሚካሄድ እንጅ ያለፍላጎታችን የሚካሄድ አይደለም በማለት የአገሪቱ ዋና ዋና የመገናኛ ብዙሀን ባሉበት እንዲገልጥ ይህም በመገናኛ ብዙሀን በስፋት እንዲሰራጭ” ውሳኔ አሳልፎአል።
 በሌላ በኩል ደግሞ  10 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ፕሬዚዳንት ተናግረዋል። በክልሉ የሚፈጸሙት ጥቃቶች በክልሉ የሚካሄደውን የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ ለማደናቀፍ ያለመ መሆኑን ርእሰ መስተዳድሩ አቶ ኦቦንግ ኦሞድ አረጋግጠዋል።  ጥቃት አድራሾቹ የክልሉ ልማት የማይዋጥላቸው ልማቱን ለማደናቀፍ የሚንቀሳቀሱ የጸረ ሰላም ሃይሎች ናቸው ያሉት ኦሞድ  በርካታ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውንም ተናግረዋል።
 ሌሎችን የድርጊቱን ፈጻሚዎች ተከታትሎ ለመያዝም የፌዴራልና የክልሉ ፖሊስ ከመከላከያ ሰራዊት ጋር በመሆን እየተንቀሳቀ እንደሚገኝ ነው አቶ ኦሞድ የገለጡት።
ከፍተኛ ወታደራዊ ጥበቃ በሚካሄድባት ጋምቤላ የሚፈጸመው ጥቃት ፣ የመለስ መንግስት በአገሪቱ ውስጥ እየደፈረ የመጣውን ሰላም ለማስቆም አለመቻሉን እንደሚያሳይ ምሁራን ይናገራሉ።
የመከላከያ ሰራዊት አባላት እስካሁን ድረስ ችግሩን ለመቆጣጠር ያልቻሉት ጸቡ ከህዝቡ ጋር በመሆኑ ነው በማለት የሚገልጡ ወገኖችም አሉ። እነዚህ ወገኖች እንደሚሉት በጋምቤላ የሚካሄደውን የመሬት መቀራመት መላው ህዝብ እያወገዘው እና እየተወጋው የሚገኝ በመሆኑ፣ ሰላም ማስከበር የሚቻለው መላውን ህዝብ መጨፍለቅ ሲቻል ብቻ ነው በማለት መንግስት የጀመረው የሀይል እርምጃ እንደማያዋጣው ይገልጣሉ።
የሼክ ሙሀመድ አላሙዲ ድርጅት ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ሰራተኞች ላይ ለደረሰው ጉዳት እንዲሁም ባለፈው ቅዳሜ በፓኪስታናዊያኑ እና በኢትዮጵያውያኑ ላይ በደረሰው ሞት ከፍተኛ ካሳ ሊከፍል እንደሚችል የውስጥ ምንጮች ይናገራሉ።

No comments:

Post a Comment