የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ በገጠማቸው የጤና ችግር ምክንያት ከ45 ቀናት በላይ በመደበኛ ስራቸው ላይ ባለመሆናቸው በኢህአዴግ አመራሮች መካከል በስልጣን ሽኩቻ እንደተፈጠረና አቶ ስዩም መስፍን የአቶ መለስን ቦታ ተክተው በመስራት ላይ እንደሚገኙ የፍኖተ ነፃነት ታማኝ ምንጮች ጠቆሙ፡፡
የፍኖተ ነፃነት ታማኝ ምንጮች እንደገለፁት የቻይና ዲፕሎማቶች ከህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ጋር ባደረጉት ድርድር የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ስዩም መስፍን ከቻይና ኮሚኒስት ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ጋር በመምጣት ቤተመንግስት ሆነው የመሪነቱን ሚና እየተጫወቱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የዝግጅት ክፍላችን ይህንን ለማጣራት የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ በረከት ስምዖን ጋር ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ቢያደርግም ስልካቸው ባለመነሳቱ ሐሳባቸውን ማካተት አልቻልንም፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲን ጠይቀናቸው “አምባሳደር ስዩም መስፍን በአሁን ወቅት በቻይና የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ናቸው፡፡ መደበኛ ሥራቸውም ይሄ ነው፤ ከዛ ውጭ እንደማንኛውም አምባሳደር ለስራ ጉዳይ ሀገር ቤት ይመጣሉ” በማለት ተጨማሪ ሀሳብ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጤና አስመልክቶ የተለያዩ አስተያየቶች በተለያዩ ብዙኃን መገናኛዎች እየተገለፀ ቢሆንም በቅርቡ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ ቤት የጠ/ሚኒስትሩን መታመምና በህክምና ላይ መሆናቸውን እንዲሁም እረፍት እንደሚያስፈልጋቸው በሐኪሞቻቸው እንደተነገራቸው ከማሳወቅ ውጭ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱን በግልፅ ማን እየመራ እንዳለ ከመግለፅ በመቆጠቡ ይታወሳል፡፡
አቶ መለስ ምነው ጣራቸው እንደዚህ ከ 45 ቀን በላይ ፈጀ፥፣ ለምን ያጉዋጉናል፥፥
ReplyDelete