Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Wednesday 8 August 2012

ጋዜጠኛዋ በምሽት በደህንነቶች ተጠለፈች

ነሀሴ ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-የፍትሕ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ተመስገን ደሳለኝን በሽብርተኝነት ለመክሰስ የወሰነው የኢህአዴግ መንግስት፤ አንዲት ጋዜጠኛን በምሽት  በደህንነቶች በማስጠለፍ  በተመስገን ላይ በሀሰት እንድትመሰክር  ትዕዛዝ እና ማስፈራሪያ መስጠቱን የማዕከላዊ ምንጮቻችን አጋለጡ።
ምንጮቻችን እንዳሉት፤  በአንድ ሳምንታዊ የአማርኛ ጋዜጣ የምትሠራ ጋዜጠኛ  ባለፈው ሐሙስ ምሽት ከቢሮዋ ወጥታ በኮንትራት ታክሲ ወደ ቤቷ በምታመራበት ወቅት  የደህንነት ሀይሎች ታክሲዋን አግተው በመጥለፍ ወደ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ይወስዷታል።
ደህንነቶቹ ጋዜጠኛዋን ወደ ወንጀል ምርመራ ክፍል በማስገባት፦”ከተመስገን ደሳለኝ ጋር ያለሽን ግንኙነት ደርሰንበታል። ሀጎስ ኪዳኔ የተባለና  ከአልሸባብ ጋር አብሮ የሚሠራ የሻዕቢያ ሰው ከ አልሸባብ በአንቺ በኩል ለተመስገን በርካታ ብር እንደተላከለት ስለመሰከረ እና ይህንንም ተመስገን ስላመነ፤ አንቺም ፍርድ ቤት ቀርበሽ ይህንኑ እንድትመሰክሪ እንጠይቅሻለን” ብለዋታል።
ደህንነቶቹ በማያያዝም፦ ጋዜጠኛዋ ፍርድ ቤት ቀርባ የተባለችውን የማትመሰክር ከሆነ፤እርሷም አብራ ከተመስገን ጋር  እንደምትከሰስ አስፈራርተዋታል።
ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከወር በፊት የላኪ ስም፦”አል ሸባብ “የሚል በሀሰት የተቀነባበረ ደብዳቤ በአድራሻው እንደደረሰው በይፋ ማጋለጡ ይታወሳል።
ከዚያም የላኪ ስም፦”ሐጎስ ኪዳኔ “የሚል ሆኖም  በይዘቱ ቀደም ሲል በአልሸባብ ስም ከተፃፈው ደብዳቤ ጋር ተመሣሳይ የሆነ  የሀሰት ደብዳቤ በድጋሚ እንደደረሰው ይፋ በማድረግ ፤መንግስት እሱንና ፍትህ ጋዜጣን በሀሰት  ለመወንጀል እያቀናበረ ባለው ሴራ በመፍራት  ፍትሕ ጋዜጣ  የአቋም ለውጥ እንደማታደርግ አስታወቀ።
ብዙም ሳይቆይ  ፍትህ ጋዜጣ ታገደች።ጋዜጣዋ በታገደች ከሁለት ሳምንት ብዙም ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ነው የደህንነት ሀይሎች እንስት ጋዜጠኛን በመጥለፍ፦” ተመስገን፤  ሆጎስ ኪዳኔ ከተባለ የሻዕቢያ ሰው ጋር ግንኙነት አለው ብለሽ መስክሪ፤ ባትመሰክሪ አንችም ትታሰሪያለሽ” በማለት እያስፈራሩ ያሉት።
በምሽት ተጠልፋ ማዕከላዊ የተወሰደችው ጋዜጠኛም በቀረበላት ጥያቄ በመደንገጥ “አስብበታለሁ” የሚል ምላሽ መስጠቷን የጠቀሱት ምንጮቻችን፤ ምላሿን እሰከ ዛሬ ጠዋት 3፡00 ድረስ ማዕከላዊ ቀርባ እንድትሰጥ ገደብ እንደተቀመጠላት ጠቁመዋል።
ጋዜጠኛዋ በተመስገን ላይ ከመሰከረች ምንም ችግር እንደማያጋጥማት ቃል የተገባላት ሲሆን፤ ለመመስከር ፈቃደኛ ካልሆነች ግን ክስ ተመስርቶባት ወደ ወህኒ እንደምትወርድ ተነግሯት በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እንደምትገኝ ለማወቅ ተችሏል።
ቀደም ሲልም በተመሳሳይ  የፍትህ አምደኛ  መምህርት ርዕዮት ዓለሙን ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ሳይቀሩ፦ በነፃ መለቀቅ ከፈለገች  በሀሰት እንድትመሰክር እንዳባበሏት፤”ሆኖም ለመመስከር ፈቃደኛ ካልሆንሽ ግን  እስር ቤት  ትበሰብሻታለሽ”ብለው  እንዳስፈራሯት መዘገባችን አይዘነጋም።

No comments:

Post a Comment