ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መሞታቸውን “ታማኙ” ኢቲቪ ነገሮናል። በርካቶችን “መርዶ ነጋሪ አትሁኑ” እያለ
የሚሰብከው መንግስታችን የጠቅላዩን መሞት የስራ ባህሪው ስላልሆነ አይነግረንም ብለን ብናስብም ከባህሉ ባፈነገጠ
መልኩ መርዶ ነገሮናል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መታመማቸውን እና ሳይሞቱ እንደማይቀር ጭምጭምታ መስማቱን የዘገበው ተመስገን ደሳለኝ ግን፤
“ምን ሲደረግ ታመሙ ትላለህ እንዴት ሆኖ ታሟርትባቸዋለህ…?” ተብሎ ሰላሳ ሺህ የታተሙ ጋዜጣዎቹ በብላሽ
እንዲቃጠሉ እንዲሁም ከዛች ጊዜ በኋላም ተወዳጇ ፍትህ ጋዜጣ ከነጭርሹ እንዳትታተም በመቀጠልም እርሱም ወደ እስር
ቤት እንዲሄድ ተደረገ።
እስከ ትላንት ድረስ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሞት እና የሀዘን እንጉርጉሮ ስመለከት ጠቅላዩ
ያደረጉትን ሁሉ እረስቼው በሀዘን ውስጥ ሰጥሜ አንዳንዴም ማለቀስ ሲያሰኘኝ ነበር። ድንገት ትላንት ወዳጄ ተሜ
መታሰሩን ስሰማ ሀገሪቷን ወደ እስር ቤት እንዴት እንደለወጧት ድጋሚ ትዝ አለኝ። ድጋሚ እንደርሳቸው ያላሰበ በሙሉን
“አሸባሪ” ሲሉ የነበረው ፈሊጣቸው ታወሰኝ። ድጋሚ “ጣቱን የቀሰረ ጣቱ ይቆረጣል” ብለው ሲያሰፈራሩን ታዩኝ።
ሙት አይወቀስም በሚለው ሀገራዊ ብሂል መሰረት በተሜ እስር ሳቢያ ትዝ ያሉኝን በደሎች ለጊዜው ከመዘርዘር
እቆጠባለሁ። ቢያንስ ቀብር እስኪያልፍ በአደባባይ እንዲህ በደለው እንዲህ አድርገው ብለን ብንወቅሳቸው መልካም
አይደለም።
አይገርማችሁም፤ ልክ ይሄንን ስፅፍ የሀረሪ ክልል መገናኛ ብዙሃን አመራሮች እና ሰራተኞች “ጠቅላይ ሚኒስትሩ
በፕሬስ ነፃነት ላይ ያመጡትን ነፃነት የሚያስመሰግናቸው ነው።” ሲል በኢቲቪ መግለጫ ሲሰጥ ሰማሁ። ወድያውም
እውነትም በተሰጠው ገደብ አልባ የፕሬስ ነፃነት ሳቢያ እስር ቤት የሚገኙት እነ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣
ርዮት አለሙ እና አሁን ደግሞ እጅግ ወዳጄ የሆነው ተመስገን ደሳለኝ በር ተቆልፎባቸው ታዩኝ! ከተቆለፈው በር ጀርባ
የሚደረግውን እስር ቤቱ ይቁጠረው።
አሁንም ቢሆን፤ ቢያንስ ግብዓተ መሬታቸው እስኪፈፀም ድረስ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከመውቀስ እንቆጠብ እና
እንቀጥል። አዲሱ መንግስታችን አሁንም የምንታሰርባት፣ መናገር እና መፃፍ የማንችልባት፣ በነፃነት ማሰብ
የሚከለከልባት ኢትዮጵያ እጁ ላይ ናት። የተለያዩ የመንግስት ባለስልጣናት “ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጀመሩትን
እናስቀጥላለን” ሲሉ ደጋግመው ይናገራሉ። ስለዚህ እስሩም አፈናውም ይቀጥላል ማለት ነው!?
ወዳጄ ተመስገን ደሳለኝ ደፋር ጋዜጠኛ ነበር። እኛ ተፈጥሯዊ በሆነ ፍርሀት ተሸብበን ሽሙጥ፣ ስላቅ እና
ምፀትን እንደመለያ በያዝንበት ጊዜ ሁሉ፤ ተመስገን ደግሞ ተፈጥሯዊ በሆነ ድፍረት ዶማን ዶማ አካፋን አካፋ ሲል
ቆይቷል።
ዶማ እና አካፋዎቹም ከእነርሱ የሚጠበቀውን ስራ ሰርተውበታል።
እውነቱን ለመናገር ድብርት ላይ ነኝ። ተሜም እንደዋዛ…! መታሰሩ ታላቅ ድብርት ይፈጥራል። ምናለ ለጠቅላይ
ሚኒስትሩ የጀመርነውን ሀዘን እንኳ አንድ ላይ አዝነን ብንጨርስ!? ምናለ ቀብር እንኳ እስኪያልፍ እንኳ ቢጠበቅ።
ተሜ እንደ እኛ “አውሮፕላን አውጪኝ” ብሎ ሀገር እንደማይለቅ እንደሆነ ደጋግሞ አሳይቷል። የሚጠፋ ቢሆን ኖሮ
እስከዛሬ የደረሱበት ወከባዎች ይቅሩ፤ አሁን በቅርቡ እንኳ ያለ አንዳች መጥሪያ ክሱን በራዲዮ ሰምቶ “ከሶስት ቀን
በኋላ ችሎት እንገናኝ” መባሉን ሲሰማ “ሊነካው” ይችል ነበር። (“መንካት” ማለት በአራዶቹ ቋንቋ መሄድ ማለት
ነው።) እሺ እርሱም ይቅር ነሀሴ 9 “ይኸው መጣሁላችሁ” ብሎ ሲቀርብ “ዳኛ አልተሟላም” ተብሎ ለነሐሴ 17 ሲቀጠር
በርካታ ወዳጆቹ “በቃ እንድትሄድላቸው ነው የፈለጉት እባክህ ቀን እስኪያልፍ ደስ ይበላቸው ሽሽ” ብለው ሲመክሩት፤
ተሜ ግን “ስላሰባችሁልኝ አመሰግናለሁ ነገር ግን ሌላ ሀገር የለኝም! የትም አልሄድም!” ብሎ የቀጠሮ ቀኑን
ሲጠባበቅ ነበር።
በዚህ መሀል ነው መለስ የሞቱት… ተመስገንን ጨምሮ ሁላችንም አዘንን። በደላቸውንም ረሳን! ነገር ግን ቀብር እንኳ ሳያልፍ በደላቸውን የሚያስታውስ ሌላ በደል ተሰራብን! ተሜም እንደዋዛ ታሰረ!
ይደብራል!
No comments:
Post a Comment