Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Sunday, 1 April 2012

ድሀ እና ከተማ

ድሀ እና ከተማ(አዱ ገነት አዱሲዖል እንዳትሆንብን!)
ስለ ድሀ የተገጠሙ ሀገር በቀል ስንኞችንና አባባሎችን ስፈልግ በምናቤ የመጣልኝ አንድ ሀገራዊ የህዝብ አባባል ነው።
ድሀና ገበያ አይገናኙም!ይህን ቃል ወደዘመናችን አባባል ስንቃኘው
ድሀና ከተማ አይገናኙም!
ወደሚል ተቀራራቢ አባባል ብቀይረውስ?ተሳዳቢው ጠቅላይ ሚንስትር መለስ ዜናዊ በአንድ ወቅት ስለሀገራችን ድህነት ሲናገሩ `ድሮ ድሀ ሆኖ መኖር ይቻል ነበር በአሁኑ ዓለም ግን ድሀ ሆኖ መኖር አይቻልም´ዘይገርምሻሸመኔ! ይሉሀል እንዲህ ነው።በዓለም ላይ ከሚሉን ይልቅ በኢትዮጵያ ድሀ ይኖርዘንድ አይፈቀድለትም(አልፈቅድለትም)ቢሉን ኖሮአባባላቸውተቀባይነት ይኖረው ነበር።በዓለም ላይ ድህነት ድሮም ነበር፣አሁንም አለ፣ወደፊትም ይኖራል ይህ እውነታ የተፈጥሮም ግዴታ ነው አንፃራዊ ተቃራኒ መስተጋብሮ ጨለማ-ብርሀን፣ምድር-ሰማይ፣ድሀ-ሀብታም ወዘተ... ከዚህ እውነታ ውጪ መሆን ቅዠት ነው።ባይሆን ድህነት በራሱ ደረጃ አለው፣የሚለው ሁላችንንም ያስማማናል።
በአውሮፓ ከታክስ ከፋዩ የሚሰበሰበው ቀረጥ ስራአጥ ለሆኑና መስራት ለማይችሉት ዜጎቻቸው ድጎማ የሚያደርጉ ሀገራት አሉ።በአረብሀገራትምቀጥተኛና ተዘዋዋሪ በሆነ መንገድ ዜጎቻቸውን ይደጉማሉ።እነዚህ በዕርጥባን የሚኖሩ ዜጎች ከሌሎቹ የሀገራቸው ከፍተኛና መሀከለኛ ገቢካላቸው ጋር ህይወታቸው ሲመዘን ድሀ ይባላሉ፣መሰረታዊ የሆኑት የሰው ልጅ ማግኘት ያለባቸውን የመጠለያ፣ምግብ፣የአልባሳት ችግሮች ግን የሉባቸውም።የእኛዎቹን ስናይ ግን ሁላችንም የምናውቀው በመሆኑ ለቀባሪው አረዱት ይሆንብኛል።ከድህነት ወለል በታች (በሂሳብ ሲሰላ ነጌቲቭ ድህነት ማለት ነው)አቶ መለስ ግን ድሀ ሆነን መኖር አንችልም አሉ።ከየትኛው የፍልስፍና መፅሀፍ የተቀዳ እንደሆነ ወይም ትንቢት አልነገሩንም።ብቻ ወቃሽም ከሳሽም የለባቸውምና ከእውነታ ጋር እንደለመዱት ተላተሙ።ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም እንዳሉት `ሎጂክ የሚባለውን ቃል አቶ መለስ አያውቁትም ወይም ሊያውቁት አይፈልጉም´ትክክል ብለዋል ፕሮፌሰር።
ድህነት ድሮና ዘንድሮ ብናየው እየሱስ ክርስቶስን ከሚከተሉት ውስጥ የዕለት ጉርሳቸውን ለመብላት አብረውት የሚዞሩ ድሆች መኖራቸውን ድርሳናት ፅፍዋቸዋል፣በወቅቱ ትራፊ(ፍርፋሪ)ሳይሆን አብረው ዕኩል መዐድ ይቀመጡ ነበር።በእስልምና ዕምነትም ነብዩ መሀመድ ምፅዋት(ዘካ) መስጠትን የዕምነቱ ግዴታዎች ውስጥ እናገኘዋለን።በቡዲስቶችም በአይሁድም ዕምነቶች መስጠትን የዕምነቶቹ መሰረት ሆነው እናገኘዋለን።ለምን ይህ ሆነ? ብለን ራሳችንን ብንጠይቀው በወቅቱ ድሆች ስለነበሩ ሲሆን ለምን ግዴታ ሆነ?ብንል ደግሞ ድሆች ወደፊትም ስለሚኖሩ ነው።
ወደተነሳሁበት ርዕሴ ስመለስ ድሀና ከተማ በእኛ ሀገርና በሌሎች የአፍሪካና የምዕራባዊያን ሀገራት ያላቸውን ተዛምዶና ተቃርኖ በሚጢጢ እይታዬ ልቃኘው እሞክራለሁኝ።ከሀጉራችን ታላላቅ ከተሞች ከሆኑት ካይሮና ሌጎስ ብንነሳ በእነዚህ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ የናጠጡ ሀብታሞች
መኖሪያዎችና ያጡ የነጡ የድሀ መንደሮችን በተቃራኒው እናገኛለን።ፓሪስና ሪዮዴጄኔሮ፣ቶኪዮና ሞስኮም የሀብታሞች መኖሪያዎች ብቻ አይደሉም።እኛ ሀገር ስንመጣ ከየትኛው ሀገር የከተማ አሰራር የተወሰደ ተሞክሮ እንደሆነ አልተነገረንም(ያው መቼም የእራሳችን የሆነ ፈጠራ የሌለን ዜጎች
ህጉም፣መመሪያውም፣አፈፃፀሙም ከሌሎች ሀገራት የተወሰዱ እንባላለን ዘወትር በመኮረጁ የሚኮራ መንግስት አለን)መዲናችን አዲስ አበባን ከድሆች ለማፅዳት የተጀመረው ዘመቻ ሃይ ባይ አላገኘም።የከተሞች ዕድገትን ስናስብ የሀገሪቱ ዜጎችን ወደጎን የገፋ አካሄድ የማያዋጣ ለቀጣይም ዋስትና ሊሆን አይችልም።
እኛ ስለ`ራሳችን ያለን አመለካከት የተዛባ ብቻ ሳይሆንየተነሳንበትን መንደርና ያደግንበትን ማህበረሰብ በመካድ ተወዳዳሪ የለንም።በዓለማችን ካሉት ትልቅና ውብ ከተሞች አንዷ የሆነችው
ኒውዮርክ ለቱጃሩም ለመናጢ ድሀውም እናት ናት ያንን የእናትነት ድርሻ መዲናችን አዲስ አበባ(በአራዳ አጠራር አዱገነት)ለምን ትከለክለናለች?ለአንዱ እናት ለሌላው የእንጀራ እናት ትሆንብናለች?
አዲስ አበባ የትውልድ ሀገሬ፣
ያደኩብሽ መንደር መርካቶ ሰፈሬ፣
ከልጅነት እስከ ዕውቀት ያየሁት ኑሮዬ...
እያለ ድምፃዊ ጌታቸው ካሳ ያዜመላት አዲስ አበባ መዲናችን ከየክፍላተሀገሩ በስልጣን መከታ ዘርፈው ቢልየነር የሚለውን ታፔላ በለጠፉ መጤዎች ተወራ ለዘመናት የኖሩትን ልጆቿን ጎዳና ላይ መጣልዋ አዱ ገነትን አዱሲዖል ለማድረግ እየተሰራ ያለውን አካሄድልማት ነው ወይስ ጥፋት?በሌሎች ሀገራት እንዳለው አሰራር ቢሆንማ ኖሮ ከበርቴዎች ከከተሞች ራቅ ብለው የራሳቸውን ቪላዎችይሰራሉ፣ንፁህ አየርምያገኛሉ፣የመጓጓዣ፣የነዳጅ የሚባሉ የኪስ ድርቅ ችግሮች ስለማይመለከቷቸው ማለት ነው።የእኛዎቹ ግን ድሀውን ከመኖሪያው አፈናቅለው ከእራሱ ከድሀው ዜጋ ላይ በዘረፉት ገንዘብና ስልጣን መከታ አድርገው ከቀዬው ያፈናቅሉታል።ድሀና ከተማ አይገናኙም! አባባልዋ አልተመቻችሁም?አዱ ገነት ለልጆችዋ አዱ ሲዖል እዳያረጉብን ስጋትና ፍርሃቱ አለኝ።መቼም ከዚህ መንግስት ያተረፍነው ቢኖር ፍርሃትና ስጋት ብቻ ነው።ዛሬ ላይ ሆነን ነገን መፍራት።
ምቅናይ ፅቡቅዩ
ኩሉኑ ምርዐይ
ምቅናይ ምቅናይ...
ሁሉንም ለማየት መቆየት
ጥሩ ነው.. ማለት ነው ትርጉሙ ድምፃዊ ኪሮስ አለማየሁ ነበር ያዜመው እኛንም ይሰንብተን።ሰው ከቆየ ከሚስቱ ይወልዳል! ይባል የለም ልሰናበታችሁ ቸር ያቆየን።

No comments:

Post a Comment