Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Monday, 2 April 2012

(እግር ኳስን በብሎግ ይመልከቱ) by Abe Tokechaw

ኢህአዴግ አታሎ ለአባይ አሻማ! (እግር ኳስን በብሎግ ይመልከቱ)
ውድ ተመልካቾቻችን ጨዋታው ከተጀመረ ሃያ አመት ሞልቶታል። እስከ አሁን ድረስ ኢህአዴግ በህዝቡ ላይ ተደጋጋሚ የማጥቃት እርምጃ ወስዷል። በእውነቱ ህዝቡ ዘንድ ኳስ ሊደርስ አልቻለም።

እስከ አሁን አስደንገጭ የሚባል ሙከራ የተሞከረው በ1997ኛው ደቂቃ ነበር። በእውነቱ ይህ ሙከራ ሙከራ ብቻም አልነበረም። እኛ ራሳችን በአይናችን እንዳየነው ጎሉ ገብቶ ነበር። ነገር ግን ለኢህአዴግ ተከላካይ ሆኖ ሲጫወት የነበረው ፌደራል እና አጋዚ የተባለው እውቅ በረኛ ኳሷን ከገባችበት አውጥተዋታል። እውነቱን ለመናገር ህዝቡ በህብረት እና በቅንጅት ማራኪ የጨዋታ እንቅስቃሴ ካደረገ በኋላ፤ ወደ ጎል የመታት ኳስ ከመርብ ጋር ተነካክታ ነበር። ምን ዋጋ አለው ዳኛው አልገባም አሉ። የሚገርም ነው!

ህዝቡ በዳኛው ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ እያሰማ ነበር። በዚህ ግዜ የኢህአዴግ አምበል የሆኑት መለስ ዜናዊ ፊሽካውን ከዳኛው ተቀብለው “ጎሉ አልገባም ብያለሁ አልገባም” ብለው ህዝቡ ተቃውሞውን እንዲያቆም አስጠነቀቁ። ይሄ በእውነቱ በየትኛውም ጨዋታ ታይቶ የማይታወቅ ክስተት ነው። ዳኛ እያለ የተቃራኒ ቡድን አምበል ማስጠንቀቂያም ሆነ ፍርድ አይሰጥም። የ… ሚገርም ነው።

በነገራችን ላይ በዚች ጎል የተነሳ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ የኢህአዴግ ተጫዋቾች በመቶዎች የሚቆጠሩ የህዝቡ ደጋፊዎችን ገድለዋል። ኦ… በጣም ዘግናኝ ነበር። ይሄ በአለም የጨዋታ ህግ ክፉኛ የሚያስጠይቅ ነው።

ለማንኛውም አሁንም ጨዋታው ቀጥሏል። ህዝቡ እስከ አሁን ድረስ ይሄ ነው የሚባል ሙከራ አላደረገም። ኢህአዴግ ግን ተደጋጋሚ የማጥቃት እርምጃዎችን እየወሰደ ነው። የሚገርም ጨዋታ ነው።

በአሁኑ ሰዓት ኳስ በህዝቡ ሜዳ ላይ ብትሆንም ኳሷን የያዙት የኢህአዴግ አጥቂዎች ናቸው። ትንሽ ግራ የተጋቡ ይመስላል።

በነገራችን ላይ ተመልካቾቻችን ከኢህአዴግ ጋር ተመሳሳይ የጨዋታ ስልት ሲጠቀሙ የነበሩ በርካቶች በቅርብ ግዜያት በተጋጣሚዎቻቸው ተሸንፈው ከሜዳ ወጥተዋል። በቤን አሊ የሚመራው የቱኒዚያው ቡድን በህዝቡ ክፉኛ ከተሸነፈ በኋላ የግብፁ ኦስኒ ሙባረክ እንዲሁም የሊቢያው ጋዳፊ ቡድንም በተጋጣሚያቸው ህዝብ ሽንፈትን ቀምሰዋል።

እንግዲህ ተመልካቾቻችን ይህ በኢህአዴግ ላይ ትንሽ ግራ መጋባት ሳይፈጥርበት አይቀርም የሚል ግምት አለ።

ሆኖም ኳስ አሁንም በኢሀዴግ እጅ ነች። የኢሃዴግ ሰዎች በህዝቡ ሜዳ ኳሷን ይዘዋታል። እያታለሉ ነው። (…. ተመልካቾቻችን አጠገቤ ያለው ባልደረባዬ እያጭበረበሩ ነው በል ነው የሚለኝ…. ኦ….ያያያያ… እያጭበረበሩ ነው….የሚገርም ገለፃ ነው)

ተመልካችቻችን ጨዋታው ከተጀመረ ሃያ አመት አልፎታል። አንዳንድ የህዝቡ ደጋፊዎች “ኢህአዴግ ደክሞት ኳሱን ካላቆመ ጥቃቱ የሚቻል አይደለም ” የሚል አስተያየት እየሰጡ ነው። ሌሎች ደግሞ ከመቼውም ግዜ በተለየ ጥቃቱን ለመከላከል ብሎም ለማጥቃት ቁርጠኛ አቋም ይዘዋል።

አረረረ… አህአዴግ አልተቻለም ኳሷን ለኑሮ ወድነት አቀበላት። በእውነቱ ይሄ ከባድ ጥቃት ነው። ኦያያያ… ይሄ አደገኛ ኳስ ነው።

በኢህአዴግ ዘመነ መንግስት እያደገ የመጣው፤ ቁመተ ዘላጋው እና አረበ ሰፊው የኑሮ ውድነት በተደጋጋሚ ኳስ ያየዘ ቢሆንም የአሁኑ ግን የከፋ አያያዝ ነው። ኳሱን ለማንም አልሰጠም እንቅ አድሮጎ ነው የያዘው። ኦያያያ… ኢህዴግ ሌላ ኳስ ወደ ሜዳው አስገባ የሚገርም ጨዋታ ነው።

በእውነቱ ህዝቡ በተጫዋቾቹ ተስፋ እየቆረጠ ነው። እስከ አሁን ይሄ ነው የሚባል ጥቃት ማድረስም ሆነ መከላከል አልቻሉም። ስለሆነም ህዝቡ እንደ አረቡ አገራት ህዝቦች ወደ ሜዳ ለመግባት ያቆበቆበ ይመስላል። ኢህአደግ ኳሷን አሁንም ይዟል። እያታለለ ነው።

ኳስ በህዝቡ ሜዳ ላይ ነች ኢህአዴግ የህዝቡ አሳብ ሳይገባው አይቀርም። ህዝቡ ወደ ሜዳው ከገባ ከባድ ችግር ላይ ይወድቃል። ከሷን እያንከባለለ ነው። የሚያሻማ ይመስላል። አሻማ! ኦያያያያ… ኳስ በቀጥታ የህዝቡ ተጫዋች ወደ ሆነው አባይ ደረሰው።

የሚገርም ነው የኢህአዴግ ተጫዋቾች የህዝቡ አዝማሚያ የገባቸው ይመስላሉ። በተለይ ኳስ ለኑሮ ውድነት በተደጋጋሚ ከደረሰች በኋላ ህዝቡ የደረሰበትን ጥቃት መቋቋም አልቻለም። በመሆኑም ህዝቡ የአረቡን ሀገር የጨዋታ ስልት ይጠቀማል የሚል ስጋት በኢህአዴግ ተጫዋቾች ዘንድ ተፈጥሯል። ለዚህም ይመስላል ምንም ባልታሰበ መልኩ በድንገት ኳሷን የህዝቡ ተስፋ በመባል ለሚታወቀው እና ለግብፅ ብሄራዊ ቡድን በመጫወት ከፍተኛ ቁጭት ሲፈጥር ለነበረው የህዝቡ ወሳኝ ልጅ አባይ ሰጥተዋል። ምን ነካቸው። በእውነቱ ግራ የሚያጋባ ጨዋታ ነው። አባይ ከዚህ በፊት ለኢህዴግ እንደሚጫወት ውልም፣ ፊርማም፣ ሃሳቡም አልነበረውም። የኢህአዴግ ተጫዋቾችም አስበውት አያውቁም ነበር።

ኦያያያ… አባይ ምንም ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ኳስ ደርሶታል። የሚገርም የጨዋታ ስልት ነው። አሁን ህዝቡ በተደበላለቀ ስሜት ውስጥ ይገኛል።

ኢሀዴግ በዚህ በኩል ህዝቡን በኑሮ ውድነት እያጠቃ ነው። በተጨማሪም የህዝቡ ተከላካይ የሆኑ ሀይማኖት የተባሉ እውቅ “ዲፌንሶች” ላይ ጉዳት እያደረሰ ነው።

አዎ… ሌላም አለ። ኢህአዴግ ለሽብርተኝነት ባቀበለው ኳስ በርካቶችን ከጨዋታ ውጭ ኦፍ ሳይት ለማድረግ ሞክሯል። ኢህአዴግ “ይህንን ተጫዋች የገዛሁት ምርጥ ተሞክሮ ካላቸው አገራት ነው” ቢልም ይህ ሽብርተኝነት የተባለው ተጫዋች ግን እጅግ በጣም ያልተገባ ጨዋታ እየተጫወተ ይገኛል። በርካቶች “እርሱ እያለ መጫወት አልቻልንም” ብለው ከጨዋታ ሜዳው እርቀዋል። በነገራችን ላይ ይህ ተጫዋች አንዳንዴ ኳስ ወደ “ኮሚታተርስ” ወይም የጨዋታው ዘጋቢዎች ሳይቀር እየለጋ የዘገባ ስርዓቱን አስተጓጉሏል። አንዳንድ የኳሱ ዘጋቢዎችም መዘገብ አልቻልንም ብለው ትተውታል። ሆኖም ኢሃዴግ “ምርጡ ተጫዋቼ ነው” እያለ ይገኛል። እርሱም ማጥቃቱን ቀጥሏል።

ተመልካቾቻችን አሁን ኳስ ለአባይ ደርሳለች። አባይ ኳሷ ድንገት ስለደረሰችው የተደናገጠ ይመስላል። ኳስ ከያዘ በኋላ ሜዳው ላይ ባልተለመደ መልኩ ሚሊኒየም የሚል መለያውን ቀይሮ ህዳሴ የሚል ሌላ መለያ ለብሷል። በእውነቱ ይሄ የሚያስቅ ነው። ኳስ አመታቱም ግራ የሚያጋባ ነው አንድ ግዜ አምስት ሺህ ሌላ ግዜ ደግሞ ስድስት ሺህ ይለጋል። ኦያያያ… አባይ ምንም አልተዘጋጀም። ኢህአዴግ አሁን አባይን እንደ ራሱ ተጫዋች እየቆጠረው ነው። አታለል… ኢህአዴግ አታለል!!! ህዝቡም በአባይ አጨዋወት ግራ ቢጋባም ተወዳጅ ተጫዋች በመሆኑ እየዘመረለት ይገኛል። ኦ ያያያ… የኢህአዴግ አጨዋወት ግራ ነው የሚያጋባው።

ተመልካቾቻችን ጨዋታው እንደቀጠለ ነው። የኑሮ ውድነቱ ኳሷን እንደያዘ ነው። በመከላከል ረገድ የህዝቡ አለኝታ የሆኑ ሃይማኖቶች አሁንም ከኢሃዴግ አጥቂዎች ተደጋጋሚ ጥቃት እየደረሰባቸው ይገኛል። ከህዝቡ ወገን የነበሩ አንዳንድ “ሀብቴ የህዝብ ፍቅር ነው” ሲሉ የነበሩ አርቲስቶች ከኢህአዴግ ጎን ተሰልፈዋል።

አሁን ኳስ በአባይ እጅ ትገኛለች። ህዝቡ በጣም የሚያደንቀው ተጫዋች አባይ ኳስ የደረሰው ምንም ባልተዘጋጀበት ሁኔታ ስለነበር፤ የተለያዩ አስገራሚ ትዕይንቶችን እያከናወነ ነው። ለህዝቡ በአጥቂነት የሚጫወቱ ተጫዋቾች አባይ ላይ እያጉረመረሙበት ይገኛሉ። አጥቂዎቹ እንደሚሉት ከሆነ “አባይ በደንብ ተዘጋጅቶ መጫወት አለበት!” ሳይዘጋጅ የሚያደርገው ጨዋታ መልሶ ህዝቡ ላይ ጉዳት ሊያመጣ ይችላል በሚል ስጋታቸውን እየገለፁ ነው። በእውነቱ አባይ ኳስ ይዞ እያሟሟቀ ነው። ወደ ሜዳ ሳይገባ በፊት ነበር ማሟሟቅ የነበረበት። ይሄ ጡንቻ መሸማቀቅም ሊያመጣ ይችላል እያሉ የህዝቡ ወጌሻዎች እየተናገሩ ነው።

ተመልካቾቻችን ጨዋታው ከጀመረ ሃያ አንድ አመት ሊሞላው ነው። ኢህአዴግ አሁንም በጥቃቱም በማታለሉም አልተቻለም።

የህዝቡ እውቅ አጥቂ የነበሩት ቅጅት እና ህብረት የተባሉ ታዋቂ ተጫዋቾች በወቅቱ በደረሰባችው ጉዳት በአሁኑ ግዜ በሜዳው ላይ አይታዩም። አሁን ለህዝቡ ትንሽ እንቅስቃሴ የሚያደርጉት ከመሀል መድረክ እና መኢአድ የተባሉ ተጫዋቾች ናቸው። ህዝቡ ተናበቡ እያለ እያጉረመረመ ይገኛል።

ራቅ ብሎ የኢህአዴግን ማጥቃት ለመከላከል አዲሲቷ ኢትዮጵያ ንቅናቄ እና ዲያስፖራው ማህበረሰብ በመባል የሚታወቁት ተከላካዮች በሰላማዊ ሰልፍ እና በማመልከቻ ጥቃቶችን ለመከላከል እየሞከሩ ይገኛሉ።

እንዲሁም በክንፍ በኩል ራቅ ብለው ለማጥቃት የተዘጋጁ ግንቦት ሰባት፣ አርበኛ እና ኦነግ የተባሉ አጥቂዎች አሉ። በነገራችን ላይ እስከ ቅርብ ግዜ ድረስ ኦነግ ለራሴ ብድን ነው የምጫወተው ብሎ የቆየ ቢሆንም በቅርቡ ግን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የሆነውን የህዝቡን መለያ ለብሶ ከህዝቡ ጎን ለመጫወት ፈርሟል። ይህ ተጫዋች በተለይ በማጥቃቱ የረጅም ግዜ ልምድ ያለው መሆኑ ይታወቃል።

የሆነ ሆኖ ኢህአዴግ እያታለለ ነው።

ጨዋታው መቼ እንደሚያልቅ እኔንጃ እኔም ደከመኝ!

መልካም ውጤት ለብዙሃኑ እመኛለሁ አረፍ አረፍ እያልኩ ዘገባውን አቀርባለሁ መልካም ዕድል!

No comments:

Post a Comment