Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Tuesday, 22 May 2012

ሚኒሰትሩ የጋምቤላ ችግር የእርስ በርስ ሽኩቻ ውጤት ነው አሉ

ግንቦት ፲፬ (አስራ አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-ከግንቦት 10 እስከ 12 የፌደራል ከፍተኛ ባለስልጣናት በተገኙበት በጋምቤላ በተደረገው  ስብሰባ ላይ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒሰትር የሆኑት አቶ ሺፈራው ተክለማርያም  ” የክልሉ ችግር የእርስ በርስ የስልጣን ችኩቻ የወለደው ነው ” ብለዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በጋምቤላ ሰላም በመጥፋቱ በርካታ ነዋሪዎች ቤት ንብረታቸውን እየጣሉ ወደ ደቡብ ሱዳን ተሰደዋል፤ የክልሉን ጸጥታ የማስጠበቅ ስራ ለፌደራል ፖሊስና ለመከላከያ ሰራዊት  ተሰጥቷል። ይሁን እንጅ በቅርቡ የሼክ ሙሀመድ አልአሙዲን ንብረት በሆነው ሳውዲ ስታር ኩባንያ ተቀጥረው ይሰሩ በነበሩ በፓኪስታንና በኢትዮጵያው ተወላጆች ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ ችግሩ ከአቅም በላይ መሆኑን በመግለጥ ፕሬዚዳንቱ አቶ ኦሞድ ኦባንግ ለፌደራል መንግስቱ ” ክልሉን ማስተዳደር ” እንዳልቻሉ የሚገልጥ ደብዳቤ ለመጻፍ ተገደዋል።
ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቀናት በክልሉ የተካሄደውን ስብሰባ የመሩት የቀድሞው ምክትል ጠቅላይ ሚኒሰትር የነበሩት አቶ አዲሱ ለገሰ፣ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒሰትር አቶ ሺፈራው ተክለማርያም፣ የአቶ መለስ የጸጥታ አማካሪው አለቃ ጸጋየ በርሄ፣ የትምህርት ሚኒስቴር ዲኤታ አቶ ፉአድ ኢብራሂም ፣ በክልሉ የተፈጠረው ችግር፣ የመልካም አስተዳዳር አለመኖርና የስልጣን ሽኩቻ መሆኑን አብራርተዋል። ዶ/ር ሽፈራው ” የጋምቤላ ችግር እርስ በርሳችሁ ለስልጣን የምታደርጉት ሽኩቻ የወለደው ነው፣ በዚህም የተነሳ መሪያችንን በአለማቀፍ ደረጃ እንዲወቀሱና እንዲወገዙ እያደረጋችሁዋቸው ነው” በማለት ሲናገሩ አቶ አዲሱ ደግሞ በክልሉ አንድ ሻማ አለ ያ ሻማ እንዲጠፋ አንፈልግም ብለዋል። አቶ አዲሱ በሻማ የወከሉት የክልሉን ፕሬዘዳንት አቶ ኦሞድን ነው ተብሎአል። አቶ አዲሱ በክልሉ ምንም አይነት የልማት ስራዎች አለመሰራታቸውን ለምክር ቤቱ አባላት ገልጠዋል። ለሌሎች የክልሉ ባለስልጣናትም ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። አቶ ፉአድ ኢብራሂም በበኩላቸው በክልሉ ለትምህርት ቢሮ የተለገሰው ገንዘብ በሙስና በመበላቱ ለስምንተኛ እና ለ 10ኛ ክፍል ተማሪዎች የሚዘጋጀው ፈተና፣ ለማተማያ ቤት የሚከፈል ገንዘብ በመጥፋቱ፣ ተማሪዎች ፈተናውን መውሰድ እንደማይችሉ ገልጠዋል።
አንድ የምክር ቤት አባል ” የክልሉ ባለስልጣናት ስልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኞች አይደሉም፣” በማለት ንግግር ሲጀምሩ እንዲያቆሙ ተደርጓል። በዚሁ ጥብቅ መመሪያዎች በተላለፉበት ስብሰባ፣ የፌደራል መንግስቱ ከፍተኛ የሆነ የስልጣን ሽግሽግ ሊያደርግ መሆኑ ተሰምቷል። የስልጣን ሽግሽጉ ፕሪዘዳንቱን የሚቃወሙትን ለማባረር ይሁን፣ አይሁን አልታወቀም። ይሁን እንጅ የምክር ቤት አባላት የፕሪዚዳንቱ የጊዜ ገደብ ሁለት ወራት ብቻ የቀሩት በመሆኑ ስልጣን ማስረከብ መጀመር አለበት የሚል አቋም እያንጸባረቁ ነው።

No comments:

Post a Comment