ከሚያዚያ 9 ቀን 2004
ዓ.ም የጠ/ሚ/ሩ ከፓርላማ ውሎ በኋላ ት/ት ቤቶች መምህራንን በሰበብ አስባቡ እያባረሩ መሆኑን ምንጮቻችን ገልፀዋል፡፡ በደረሰን መረጃ መሠረት የእርከን እና የደሞዝ ጭማሪውን የጠየቁ መምህራንን ሲያስተባብሩ ነበር የተባሉት መምህራን ጠንሳሽ
(master mind) በሚል ስም ተለይተው ከማስተማር ስራቸው እየተሰናበቱ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ከየካ ክ/ከተማ የት/ት ጽ/ቤት ቢሮ የወጣ አንድ የስንብት ደብዳቤ “የተጣለበትን ኃላፊነት ወደ ጎን በመተው ከ17/7/2004
ዓ.ም ጀምሮ በት/ቤት ያሉ መምህራንን በማስተባበር የሥራ ማቆም እንዲመታ” አድርገዋል ካለ በኋላ “ይህ ተግባር በህግ የሚያስጠይቅዎ
መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ከስራዎ የተሰናበቱ መሆንዎን እንገልፃለን” ይላል፡፡ በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ተሰናባች መምህራን “ህገ መንግሥታዊ መብት የሚሆነው ለገዥዎች ሲሆን ብቻ ነው” ያሉ ሲሆን “ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ስርዓቱ የሚፈቅድ አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አማራ ክልል ውስጥ ከሚገኝ አንድ ት/ት ቤት የተባረሩት መምህራን በበኩላቸው “ሚያዝያ 9 ቀን 2004
ዓ.ም ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ መብታቸውን የጠየቁ መ/ራንን አውግዘው ነበር፤ ብቃት የሌላቸውና የማስተማር ፍላጐቱ የሌላቸው እንዲሁም በተማሪዎችና በወላጆቻቸው የማስተማር ብቃት የሌላቸው ናቸው ተብለው በሌሎች መ/ራን እንዲተኩ
ጥያቄ ሲቀርብ መልስ አለመስጠታችን ነበር ክፍተቱ የተፈጠረው›› ሲሉ ሀላፊነት የሌለዉ ቃልመናገራቸዉን ይገልጻሉ፡፡ አስተያየት ሰጪዎቹ የመምህራንን አከርካሪ ለመስበር ስውር ስትራቴጂ እንደነበር አስታዉሰዉ ልክ ለጋዜጠኞችና ለፖለቲከኞች ‹አሸባሪ› የሚል ሴራ እንደተሴረላቸው ሁሉ ለመምህራንም ይህ መዘጋጀቱን ይናገራሉ፡፡
በያዝነው ሣምንት መገባደጃ በአዲስ አበባ አንድ ት/ቤት የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው ለአንዳንድ መ/ራን ከስራ እንዲታገዱ የሚገልጽ ደብዳቤ ደርሷቸዋል፡፡ የዚህ ደብዳቤ ይዘት እንደሚገልፀው የመማር ማስተማሩ ሥራ ጉዳት እንዳይደርስበትና የግቢውን ፀጥታ ከማስጠበቅ አኳያ እንዲሁም የመማር ማስተማሩ ሂደት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በመፍጠር የተከሰሱበት ክስ ውሳኔ እስከሚያገኝ ድረስ የመማር ማስተማሩን ሥራ እንዲያቆሙና በውጭ ሆነው የዲሲፕሊኑን ውሳኔ እንዲጠብቁ ት/ቤቱ ያሳውቃል የሚል ነው፡፡ ይህንን ዘገባ እየሰራን እስካለንበት ድረስ እነዚህ መ/ራን ት/ቤት ግቢ ውስጥ ሳይገቡ በውጭ ሆነው ውሳኔ በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን ምንጮቻችን ገልፀዋል፡፡
No comments:
Post a Comment