Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Wednesday 23 May 2012

ኢትዮጵያ በሐኪሞች ቁጥር የታዳጊ አገሮችን መስፈርት አታሟላም


Wednesday, 23 May 2012 09:44
By Haile Mulu

የጠቅላላ ሐኪሞችና ስፔሻሊስቶች ከፍተኛ እጥረት ያለባት ኢትዮጵያ፣ የዓለም ጤና ድርጅት ለታዳጊ አገሮች ያስቀመጠውን ደረጃ እንኳን ማሟላት አለመቻሏ ተገለጸ፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት ለታዳጊ አገሮች ባስቀመጠው መስፈርት መሠረት አንድ ሐኪም ለ10,000 ሰዎች ሲመደብ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን በአሁኑ ጊዜ አንድ ሐኪም የሚደርሰው ለ36,158 ሕዝብ ነው፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖም የሚኒስቴሩን የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ትናንት ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለጹት፣ የሐኪሞችን እጥረት ለመቅረፍ አዲስ ሥርዓተ ትምህርት በመቅረፅ ዓመታዊ የሕክምና ተማሪዎች የቅበላ አቅምን አሁን ካለበት 1,400 ወደ 3,000 ከፍ ለማድረግ የታቀደ ሲሆን፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራትም በዘጠኝ ነባርና 13 አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች 2,628 የሕክምና ተማሪዎችን ተቀብለው ማሠልጠን ጀምረዋል፡፡

‹‹በየደረጃው በጤናው ሴክተር ከፍተኛ እጥረት በሚታይባቸው ሐኪሞች፣ አዋላጅ ነርሶች፣ ሰመመን ሰጪ ነርሶች፣ የተቀናጀ የድንገተኛ የማህጸንና ፅንስ ቀዶ ሕክምና ባለሙያዎችን በማሠልጠን፣ ክፍተቱን ለመሙላት ትኩረት ሰጥተን እየሠራን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኤችአይቪ/ኤድስን በተመለከተ ባቀረቡት ሪፖርት ደግሞ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የኤችአይቪ ምርመራ ካደረጉ 7,411,425 ሰዎች መካከል 108,301 ሰዎች ቫይረሱ በደማቸው የተገኘባቸው መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ 61,353 ሴቶች ናቸው፡፡

ኤችአይቪ/ኤድስ በኢትዮጵያ መኖሩ ከተረጋገጠበት እ.ኤ.አ. ከ1984 ጀምሮ ለመጀመርያዎቹ በርካታ ዓመታት ሥርጭቱ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ የመጣ ቢሆንም፣ ባለፉት ዓመታት ሥርጭቱ በመቀነስ በመረጋጋት ላይ እንደሚገኝ የጠቆሙት ዶ/ር ቴዎድሮስ፣ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ውስጥ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር 790 ሺሕ መድረሱን አስታውቀዋል፡፡ የቫይረሱ ሥርጭት መጠንም 1.5 በመቶ (በሴቶች 1.9 በመቶ በወንዶች አንድ በመቶ) መድረሱን አክለው ገልጸዋል፡፡

የሚኒስትሩ ሪፖርት እንደሚያመለክተው፣ የፀረ ኤችአይቪ/ኤድስ መድኃኒት ተጠቃሚዎች ቁጥር በ2003 ዓ.ም. መጨረሻ ከነበረበት 248,805 ወደ 326,136 ለማድረስ ታቅዶ፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተጠቃሚዎቹን ቁጥር ወደ 270,543 ማሳደግ ተችሏል፡፡

No comments:

Post a Comment