Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Friday 25 May 2012

አጭር መልዕክት፤ የምር ኢህአዴግ ነን የምትሉ እጃችሁን አውጡ! (አቤ ቶኪቻው)

ሰሞኑን ጋዜጠኛ አበበ ገላው የጠቅላይ ሚኒስትራቸንን ቆሌ  ገፎ “ትልቁን” ሰውዬ ትንንሽ ያደረገበት ክስተት እስከ አሁንም ድረስ ያልበረደ አንግጋቢ ጉዳይ ሆኗል።
እኔ እና እኔን መሰል የርሳቸው “አዛኝ ቅቤ አንጓቾች” አበበ ያስቆጠረባቸው ነጥብ ከሜዳቸው ውጪ በመሆኑ፤ “ተሳትፎ አድርገው መምጣታቸው ራሱ ቀላል ነገር አይደለም” እያልን ላገኘናቸው ሁሉ መስክረናል። ደግሞም፤ “እስቲ አበበ ገላው በራሳቸው ሜዳ ወንድ ከሆነ ይሞክራቸው!” ስንልም ፎክረናል። በዚህም አላበቃንም፤ ክቡርነታቸው በቅርቡ በሜዳቸው ላይ (ያው ሜዳቸው ፓርላማችን መሆኑን ይገባችኋል ብዬ ነው) እናም በሜዳቸው ሁሉንም የፓርላማ አባላት አሰልፈው ልክ ልክ በመንገር የቀድሞ ክብራቸውን እና ሞገሳቸውን እንደሚያስመልሱም ተስፋ ሰንቀናል! (በሌላ ቅንፍም አንገታችን ተሰብሮ አይቀርም! ብለን እናቅራራ እና ከቅንፍ እንወጣለን!)
እኔ የምለው “ኢንሳ” እና የመሳሰሉት ቦታዎች አንዳንድ ጉዳዮችን በማገድ የተሰማራችሁ አባላት ግን ስራችሁን በአግባቡ የማትሰሩት ለምንድነው? ለምሳሌ የአበበ ገላው ንግግር በኢትዮጵያ ስልክ ያለው በስልኩ፤ ኮምፒውተር ያለው በኮምፒውተሩ፣ ሁለቱም የሌለው ሰው ደግሞ በልቡ ላይ “ዳውሎድ” አድርጎ ደጋግሞ እየሰማው እና እያለው እንደሆነ ሰምተናል። ልብ አድርጉልኝ ይህ ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትሩን እንደ ሀዘን ባንዲራ ዝቅ ያደረገ ንግግር ነው። “መለስ ዜናዊ አምባ ገነን ነው… ከምግብ በፊት ነፃነት እንፈልጋለን… እስክንድር ነጋ እና ሌሎች የፖለቲካ እስረኞች ይለቀቁ… ነፃነት ነፃነት ነፃነት…!” ታድያ ይሄ ንግግር ሰዉ በተለያየ መልኩ ሲቀባበለው ዝም ብሎ የተመለከተ ካድሬ በእውኑ የኢህአዴግ አባል ነው ለማለት ያስደፍራል…? (“…ምን አባል ለማለት ያስደፈራል…? ራሱ ሰው ያስደፍራል እንጂ…” ብሎ ያጉረመረመ እርሱ  በአብዮታዊ ዴሞክራሲ የተባረከ ነው!)
እውነት እውነት እላችኋለሁ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በነገሱባት ከተማ እና ሀገር እርሳቸውን የሚሸረድድ እና የሚያዋርድ ቃል የስልክ መቀበያ ጥሪ ሆኖ ከሚገኝ፤ ሞባይሎች በሙሉ አሁኑኑ መሰብሰብ የለባቸውምን…? ኮምፒውተሮችስ ለዚህ ህዝብ ምን ያደርጉለታል? በእውኑ የጠቅላይ ሚኒስትራችንን አንገት ስብራት የሚያሳዩ ምስሎች በውስጣቸው ይዘው ከሚቀመጡ በከተማውና ባጠቃላይ ሀገሪቱ ያሉ ኮምፒውተሮችን ሰብስቦ በአንድ መጋዘን መቆለፍ አይገባምን…?
አንዳንድ እጅግ የከፉ ግለሰቦች “ይህንን ሁሉ ብትሰበስቡም ቅሉ የአበበን ንግግርም ሆነ የጠቅላይ ሚኒስትሩን አንገት ስብራት በልባችን አኑረነዋልና ምን ታመጣላችሁ…?” ሲሉ ሊመፃደቁ እንደሚችሉ እንጠረጥራለን ጠርጥረንስ እንደምን ዝም እንላለን…? የእያንዳንዱ ሰው ልብ ተሰብስቦ ስለምን በመንግስት ቁጥጥር ስር አይውልም!? ለመሆኑ ለዚህ ህዝብ ልማት እንጂ ልብ ምን ያደርግለታል? “በርካታ ሀገሮች ልብ ሳይኖራቸው ልማትን እንዴት እንዳፋጠኑ” ጠቅላይ ሚኒስትራችን እስኪናገሩ መጠበቅ  ተገቢ ነውን…? በልብ እና በልማት መካከል ምንም አይነት ታሪካዊ ግንኙነት እንደሌለ አታውቁምን…? ስለዚህ የእያንዳንዱን ሰው ልብ ከተቻለ ስለጠቅላይ ሚኒስትራችን እና ስለ ድርጅታችን ክፉውን እንዳይመዘግብ “ብሎክ” ማደረግ አልያም ደግሞ ሰብስቦ በመጋዘን ውስጥ ማከማቸት ካቃተን፤ በእውኑ እኛ ኢህአዴግ ነን ለማለት ያስደፍራልን…? እውነት እላችኋለሁ፤ ህዝቡ በልቡ የጋዜጠኛውን “መለስ ዜናዊ ኢዝ ኤ ዲክታተር” ንግግር መዝግቦ እየዞረ እንደምን ያለ ግንቦት ሃያ ልናከብር ነው…!?
የምር ኢህአዴግ የሆናችሁ እጃችሁን አውጡ! ይህንና ማደረግ ካቃታችሁ ከድርጅታችን ውጡ! ያኔ እርሳቸውም ብቻቸውን መሆናቸውን ቁርጡን ይወቁት! አዎ ክቡርነታቸው ሁሉም በልቡ መዝግቦ በያዘው ክፉ ቃል እየተደበደቡ ከክቡርነት ወደ ከበሮነት ከመለወጣቸው በፊት መላ አምጡ! ቻይና ልከን ያስተማርናችሁ ለብልሀት እንጂ ለማብላት አይደለም!

No comments:

Post a Comment