Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Wednesday, 9 May 2012

ዋና ኦዲተር የመንግሥት መሥርያ ቤቶችን የሒሳብ ግድፈቶች አጋለጠ.........ሪፖርተር

•    በደንቡ መሠረት ያልተወራረደ 1.2 ቢሊዮን ብር ተገኝቷል
•    ትክክለኛነቱን ማረጋገጥ ያልተቻለ 2.03 ቢሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል
የመንግሥት መሥርያ ቤቶች በ2004 በጀት ዓመት የፈጸሙትን በርካታ የሒሳብ አያያዝ ግድፈቶችንና የውስጥ ቁጥጥር ድክመቶችን ይፋ አደረገ፡፡ ከደንብና መመርያ ውጭ የሆኑ አፈጻጸሞችም ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አስገንዝቧል፡፡

የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ ባለፈው ሳምንት ለተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ሪፖርት እንደገለጹት፣ የሚኒስትሮች ምክር ቤት የፋይናንስ አስተዳደር ደንብ በሚደነግገው መሠረት የተሰብሳቢ ሒሳብ በወቅቱ መወራረዱ ሲጣራ፣ በ59 መሥርያ ቤቶች 1.27 ቢሊዮን ብር በደንቡ መሠረት በወቅቱ ሳይወራረድ ተገኝቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ የትምህርት ሚኒስቴር 723.77 ሚሊዮን ብር፣ የመከላከያ ሚኒስቴር 133.78 ሚሊዮን ብር፣ የግብርና ቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና 115.02 ሚሊዮን ብር ባለማወራረድ ከፍተኛ ድርሻውን ይዘዋል፡፡

የገቢ ሰብሳቢ መሥርያ ቤቶችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በገቢ ግብር፣ በቀረጥና በታክስ እንዲሁም በሌሎች ገቢ መሰብሰብን በሚፈቅዱ አዋጆች፣ ደንቦችና መመርያዎች መሠረት የመንግሥትን ገቢ የሰበሰቡ መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፣ በ16 መሥርያ ቤቶች በድምሩ 952.94 ሚሊዮን ብር በተለያዩ ምክንያቶች ሳይሰበሰብ ተገኝቷል፡፡ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ከፍተኛ ግብር ከፋዮች ቅ/ጽ/ቤት  638.14 ሚሊዮን ብር፣ ምሥራቅ አዲስ አበባ ቅ/ጽ/ቤት 132.56 ሚሊዮን ብር፣ ድሬዳዋ ቅ/ጽ/ቤት 10.58 ሚሊዮን ብርና የውኃና ኢነርጂ ሚኒስቴር 120.63 ሚሊዮን ብር ያልሰበሰቡ ዋና ዋና መሥርያ ቤቶች ናቸው፡፡

የመንግሥት ገቢ በወቅቱና በአግባቡ መሰብሰባቸውን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና መሥርያ ቤትና በሥሩ ባሉ ሰባት ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ከውዝፍ ግብር፣ ከወለድና ከቅጣት መሰብሰብ የሚገባው  272.15 ሚሊዮን ብር ሳይሰበሰብ መቅረቱን በሪፖርታቸው የገለጹት ዋና ኦዲተሩ፣ ገቢን በወቅቱ መሰብሰብ መንግሥት ለሚያከናውነው የልማትና ማኅበራዊ ሥራዎች ወሳኝ በመሆኑ ለጉዳዩ ትኩረት ተሰጥቶት የመንግሥት ገንዘብ በወቅቱ እንዲሰበሰብ አሳስበዋል፡፡

ይኼው የዋናው ኦዲተር ሪፖርት እንዳመለከተው፣ የዕቃና አገልግሎት ግዢ በደንብና መመርያ መሠረት የተፈጸመ መሆኑን ለማጣራት ኦዲት ሲደረግ፣ በ33 መሥርያ ቤቶች 313.26 ሚሊዮን ብር የመንግሥትን የግዢ አዋጅ፣ ደንብና መመርያ ያልተከተለ ግዢ ተፈጽሞ ተገኝቷል፡፡ ከደንብና መመርያዎች ውጪ ግዢ ከፈጸሙ መሥርያ ቤቶች መካከል መቀሌ ዩኒቨርሲቲ 224.22 ሚሊዮን ብር፣ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ 41.38 ሚሊዮን ብር፣ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ 7.56 ሚሊዮን ብርና የመቀሌ ጤና ሳይንስና አይደር ሪፈራል ሆስፒታል 3.06 ሚሊዮን ብር ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ከላይ የተጠቀሱት መሥርያ ቤቶች ካልተከተሏቸው የግዢ ደንብና መመርያዎች ውስጥ የጨረታ ማስታወቂያ በማውጣት ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ግዢዎች ያለጨረታ ማስታወቂያ በመግዛት፣ በዋጋ መወዳደሪያ (ፕሮፎርማ) አማካይነት መፈጸም ያለበትን ግዢ ውድድር ሳይደረግ በመፈጸምና ተገቢ የውል ስምምነት ሳይደረግና በአቅራቢነት ካልተመዘገቡ ድርጅቶች ግዢ ማከናወን የሚሉት ይገኙበታል፡፡ የግዢ መመርያን ሳይከተሉ ግዢ መፈጸም ለምዝበራና ለጥፋት የሚዳርግ መሆኑን በሪፖርታቸው የጠቆሙት አቶ ገመቹ፣ የመንግሥት ግዢ ደንብና መመርያን አክብረው በማይሠሩ መሥርያ ቤቶች ላይ የተጠናከረ ዕርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

የመንግሥት ገንዘብ ወጪ ሆኖ የተገዛው ንብረት ለመሥርያ ቤቱ ገቢ ለመሆኑ የንብረት ገቢ ደረሰኝ የተቆረጠለት መሆኑን ለማረጋገጥ ኦዲት ሲደረግ፣ በዘጠኝ መሥርያ ቤቶች በ83.99 ሚሊዮን ብር የተገዙ ዕቃዎች የንብረት ገቢ ደረሰኝ ሳይቆረጥላቸው ሒሳቡ በወጪ ተመዝግቦ ተገኝቷል፡፡ ከዚህ ውስጥ ትምህርት ሚኒስቴር 75.26 ሚሊዮን ብር፣ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ 4.02 ሚሊዮን ብርና የኢትዮጵያ ሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ 3.9 ሚሊዮን ብር የተገዛው ዕቃና ንብረት ገቢ ለመደረጉ ማስረጃ ሳይቀርብ ሒሳቡን በወጪ ከመዘገቡት መሥርያ ቤቶች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

በበጀት ዓመቱ መሥርያ ቤቶች የፈጸሙትን ክፍያ ትክክለኛነት ለማጣራት ኦዲት ሲደረግ፣ በስምንት መሥርያ ቤቶች 2.03 ቢሊዮን ብር በተለያዩ ምክንያቶች የወጪውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ያልተቻለ መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

የወጪውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ ካልተቻለው ሒሳብ ውስጥ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ለሠራዊት ደመወዝ ወጪ ያደረገው 1.87 ቢሊዮን ብር፣ ብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት 54.25 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም የውስጥ ደኅንነት ጥበቃ ዋና መምርያ 33.34 ሚሊዮን ብርና የኢሚግሬሽንና የዜግነት ጉዳይ ዋና መምርያ 49.99 ሚሊዮን ብር ወጪ ያደረጉ ዋና ዋና መሥርያ ቤቶች ናቸው፡፡

በሪፖርቱ ላይ እንደተጠቀሰው ሦስቱ የደኅንነት መሥርያ ቤቶች ለደመወዝ፣ ለነዳጅ፣ ለስልክ፣ ወዘተ ወጪ ያደረጉትን ሒሳብ ለማረጋገጥ ዝርዝር መረጃዎች እንዲያቀርቡ ተጠይቀው ባለመቅረቡ የወጪውን ትክክለኛነት ማረጋገጥ አልተቻለም፡፡ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ለፌዴራል ዋና ኦዲተር በላከው መልስ ከመረጃው ሚስጥራዊነትና ከደኅንነት አንፃር ችግር ያለበት በመሆኑ፣ ለወደፊቱም ቢሆን እንደዚህ ዓይነት ዝርዝር ከሚስጥርና ከደኅንነት ጋር የተያያዙ ሰነዶችን አሳልፎ መስጠት አስቸጋሪ መሆኑን ገልጿል፡፡

በንብረት አያያዝና አስተዳደር ረገድ የታዩ የውስጥ ቁጥጥር ሥርዓት ድክመቶችም በሪፖርቱ የተጠቀሱ ሲሆን፣ በበርካታ መሥርያ ቤቶች መጋዘን ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ዕቃዎች ከሚወገዱ ዕቃዎች ጋር ተቀላቅለው ተቀምጠው እንደሚገኙ፣ የተለያዩ ኬሚካሎች፣ ጎማዎችና ሌሎች ዕቃዎች በወለል ላይ ለብልሽት  በተጋለጠ ሁኔታ መቀመጣቸው ተገልጿል፡፡ በዚህ ረገድ ድክመት የታየበት ዋነኛው መሥርያ ቤት ግብርና ሚኒስቴር ነው፡፡

ለረጅም ዓመታት ግምጃ ቤት ገቢ የተደረጉ፣ በተለይም በ1996 ዓ.ም. የተለያዩ መሥርያ ቤቶች ሲዋሀዱ ተመላሽ የተደረጉ ንብረቶች በዓይነትና አገልግሎት የሚሰጡና የማይሰጡ ሳይለዩ ለቁጥጥር በሚያስቸግር ሁኔታ ምንም ዓይነት ምዝገባ ሳይከናወን በተለያዩ ዘጠኝ የግብርና ሚኒስቴር መጋዘኖች ለረጅም ጊዜ ተከማችተው መገኘታቸው፣ መሥርያ ቤቱ ለረጅም ጊዜ የንብረት ማስወገድ ሥራ ባለመሥራቱ ምክንያት ብዛት ያለው ንብረት፣ የአገልግሎት ዘመን ያለፈባቸው ኬሚካሎች፣ የእንስሳት መድኃኒቶችና ሰብሎች ተከማችው የሚገኙ መሆናቸው ተመልክቷል፡፡ ቃሊቲ በሚገኘው የመሥርያ ቤቱ መጋዘን በክልሎች ስም የመጡ የተለያዩ ብዛት ያላቸው የግብርና መሣርያዎች፣ እንዲሁም በዕርዳታ የተገኙ ለግብርና ሥራ የሚያገለግሉ ልዩ ልዩ ዕቃዎች ያለአገልግሎት ተቀምጠው መገኘታቸው፣ በግብርና ሚኒስቴር ውስጥ የቁጥጥር ሥርዓት ድክመቶች መኖራቸውን የሚያሳዩ ዓይነተኛ ምሳሌዎች ተደርገው ተጠቅሰዋል፡፡

No comments:

Post a Comment