Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Friday 11 May 2012

መንግስትን ሆይ ሲደግፉህ እሺ በል … ሞቅ ብሎሃልና! (አቤ ቶኪቻው)

ጋሽ ግዛው በድፍን ሽሮሜዳ ታዋቂ የነበሩ ሞቅታን እንደገንዘብ እየቆጠቡ የሚጠቀሙ ሰው ነበሩ። እርሳቸውን ሳይሰክሩ ያያቸው ሰው ካለ እርሱ አብሯቸው ያደረ መሆን አለበት፤ በቀረ ግን ሁሌም ሞቅታ ውስጥ ናቸው።
ጋሽ ግዝሽ ሁልግዜም ወደቤታቸው የሚገቡት እምቢኝ እያሉም ቢሆን፤ በሰዎች ተደጋግፈው ነው። አንዳንዴም በወሳንሳ! አለበለዛ ሲወድቁ ሲነሱ የሚያዩት አበሳ አይወሳ…! ጋሽ ግዛው በሞቅታቸው ተዓምር ካመጡት ልዩ ልዩ ጠባይ ውስጥ የሚከተሉት ይጠቀሳሉ። ከመንግስታችን ተዓምራዊ በሀሪያት ጋር እየተነፃፀረ ይቀርባል።
አንድ፡
ያለ አጠጋቢ ምክንያት መሳደብ እና መዝለፍ። ለነገሩ ምክንያቱ ለርሳቸው አጥጋቢ ነው በሞቅታ ውስጥ ለመግባት ላልታደለ ሰው ግን፤ “እንዲህ አይነት ክፉ ቃል ከእርሳቸው አንደበት ይጠበቃል?” በሚያስብል መልኩ አላፊ አግዳሚውን እና በአግዳሚ ወንበር ላይ የተቀመጠውን ጠጅ ጠጪ ሁላ ሙልጭ አድርገው ነው የሚሳደቡት። መንግስታችን በተለይም ዋናው ጠቅላይ ሚኒስትራችን በፓርላማ ዘመናቸው የሰነዘሩብንን ሃይለ ቃል… (ስድብ ማለት አላስችል አለኝ እኮ!) ያ ታማኝ በየነ ለታሪክ ይሆናል ብሎ ሰብስቦ አስቀምጦልዎታል  ከጥቂቶቹ መካከል “ቆሻሻ… በክት… የበሰበሰ…እብድ ውሻ…” የሚሉት ይበልጥ እውቅና ያገ  ስድቦቻቸው ናቸው። በእውነቱ እንዲህ አይነቱን ስድብ ጋሽ ግዛውም አይሞክሩትም።
በተለይ አሁን አሁን የሀይማኖት ሰዎች ላይ የሚያወርዱትን የስድብ ናዳዎች ስናይ በእውኑ መንግስታችን ሞቅ ብሎታል ያሰኛል። መቼም አንድ መነኩሴን “የተለየ የፖለቲካ አጀንዳ ያለው!” ብሎ መጠርጠር ከስድብ በላይ ነው። ስሙ ራሱ “ሰላም” የሆነውን ሙስሊም አሸባሪ ብሎ መኮነንም ደረጃውን የጠበቀ ስድብ ነው።
ሁለት
ጋሽ ግዛው ሰክረው ሲወጡ ህፃናትን ማባረር እና ሲይዟቸውም መምታት። መለያ የስካር ባህሪያቸው ነው። በርግጥ ህፃናቱም እርሳቸውን ከመተቸት ወደ ኋላ ብለው አያውቁም። “ሰካራም ቤት አይሰራም ቢሰራም ቶሎ አይገባም ቢገባም ቶሎ አይተኛም … ቢተኛም….” እያሉ መስከር ያለውን ጦስ በቀልድም በዋዛም ይነግሯቸዋል። እራሳቸው ግን ማንም ምንም እንዲናገራቸው አይወዱም። ስለዚህ ህፃናትን ያሳድዳሉ ሲያገኙም ይደበድባሉ። መንግስታችን እና ጋሽ ግዛው አንድ ናቸው። ቀላል ማስረጃ ይህው እነ እስክንድር የታሰሩት እነ ዳዊት ከበደ እና መስፍን ነጋሽ የተሰደዱት “ሰካራም ቤት አይሰራም ቢሰራም ቶሎ አይገባም” ብለው ትችት ስላቀረቡ አይደለምን!?
ሶስት
ዋና የጋሽ ግዝሽ መገለጫ መጣችላችሁ፤ “እኔ ግዛው ቀብራራ እኮ ነኝ አሁን ይሄንን ገብቼ ዘለዝልና  ከዚህ እዛ ድረስ ክሪስመርስ ነው ያማስመስለው” ብለው በጋዜጣ የተጠቀለለች ቅንጥብጣቢ ስጋ ለመንገደኛው በሙሉ ያሳያሉ። እውነቴን ነው የምልዎ ቅንጥብጣቢዋ እቤት ሳትገባ መንገድ ላይ ተበትና የምትቀርበት ግዜ ይበዛል። አንዳንዴ በሰላም እቤት ከገባች ደግሞ ለነገም መፎከሪያ ስለምትሆን ተጠቅልላ ትቀመጣለች እንጂ አትበላም። ብለው የሚያሟቸው ብዙ ናቸው። ታድያ እዝችጋ መንግስታችን ትዝ አላላችሁም…? ይሄ እኮ “መልካም ገፅታ ግንባታ” ነው። (ነውንዴ በዚህማ መንግስታችን ከጋሽ ግዛውም ይበልጣል! ሳይሉ አይቀሩም ብዬ ልጠርጥር?)
አራት
ጎረቤት ወይም ሌላ አሳቢ ሰው “ለምን ይሰክራሉ?” ብሎ የጠየቃቸው እንደሆነ፤ አሁን ትልቅ ፀብ ተነሳ! ከመንግስት ቋንቋ እንዋስላቸው “ይሄ የውስጥ ጉዳያችን ነው ከጣማችሁ ተቀበሉ ካልጣማችሁ በሊማሊሞ በኩል አቋርጡ!” ይላሉ። ታድያስ መንግስታችንስ ማንን ሲሰማ አይተው ያወቃሉ? (ቻይናን… ብለው እንዳያላግጡ ብቻ!)
በጥቅሉ
መንግስታችንም ሆነ ጋሽ ግዛው ሞቅታ ውስጥ መሆናቸው ጥርጥር የለውም። እናም ደገፍ ደግገፍ ካላደረግናቸው በቀር ክፉኛ አወዳደቅ እንዳይወድቁ ያሰጋል። ትልቁ ችግር ግን ጋሽ ግዛውም ሆኑ መንግስታችን እንደግፋችሁ ብለው የቀረቧቸውን ሁሉ እንደሌባ ነው የሚቆጥሩት…? እናም ማንንም አያስጠጉም ታድያ ብዙ ግዜ ክፉኛ አወዳደቅ ይወድቃሉ።
ቀጥሎ መንግስቴን እመክራለሁ። (ይህ ምክር እንደ አቋም መግለጫም ይታይልኝ!)
ማንም የተቃወመ ቢመስል ቅሉ ለሀገር እና ለመንግስቱ ልስራ ላገልግል ያለ ነው። መንግስቴ ሆይ እሺ በል “ተቃዋሚ” “አሸባሪ” “ነውጠኛ” ያልካቸው በሙሉ እንደግፍህ እያሉ እንደሆነ ምን ታውቃለህ…? በእውኑ ብቻህን እየተንገዳገድክ አይወድቁ አወዳደቅ ከምትወድቅ ደግፉኝ አግዙኝ ማለት የአባት ነውና ዛሬውኑ እንደግፍ ስላሉ የታሰሩት ይፈቱ! “ሞቅታ ይብቃ” ብለው የሚመክሩትም ይሰሙ!

No comments:

Post a Comment