ግንቦት ፩ (አንድ) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት
ዜና:-የኢሳት የጋምቤላ ዘጋቢ ኡጁሉ ኦሞድ በላከው መረጃ እንዳመለከተው፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት የሆኑት አቶ ኦሞድ
ኦቦንግ ለአቶ መለስ ዜናዊ፣ ለኢህአዴግ ጽህፈት ቤት፣ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ ለፌደራል ፖሊስና ለመከላከያ ሰራዊት
በላኩት ደብዳቤ፣ የጋምቤላ የጸጥታ ችግር ከክልሉ መንግስት አቅም በላይ በመሆኑ ተጨማሪ የፌደራል ፖሊስ እና
የመከላከያ ሰራዊት አባላት እንዲላክላቸው ጠይቀዋል።
ፕሬዚዳንቱ በደብዳቤያቸው በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ የሆነ
የፖለቲካ ዝቅጠት እና የአመራር ብልሹነት ያለ በመሆኑ የፌደራል መንግስቱ የአመራር ለውጥ በማድረግ አስቸኳይ
እርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል። ደብዳቤውን በእነ አቶ መለስ ግፊት ይጻፉት በራሳቸው ፈቃድ አልታወቀም። ብዛት
ያላቸው የመከላከያ እና የፌደራል ፖሊስ ባለስልጣናት በያዝነው ሳምንት ጋምቤላ መግባታቸው ታውቋል።
በሌላ በኩል ደግሞ በጋምቤላ ህዝብ ላይ መጠነ-ሰፊ ጥቃት እየተፈፀመ ነው፣ ሰዎችም እየተገደሉ እና እየታሰሩ ነው ሲል አኢጋን አስታወቀ።
ሰሞኑን
ሚያዚያ 24 ቀን 2004 ዓ ም በጋምቤላ – አቦቦ ወረዳ ፖኪዶ ቀበሌ በጠራራ ፀሃይ ንፁሃን በጥይት ተደብድበው
መገደላቸውን ተከትሎ የአካባቢው ህዝብ ብሶትና ቁጣ ከመቼውም በላይ ገንፍሎ እየወጣ መሆኑን የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ
ንቅናቄ ገለጿል።
የአካባቢው ህዝብ ፦ “. . . እየጨረሱን ነው፤ ብቀላው ተጀምሯል፤ ድረሱልን. . .” ሲል ለኢትዮጵያን እና ለዓለም አቀፍ መንግስታት ተማጽኖ እያሰማ ነው።
“ ተማጽኖው ለትግራይ ወንድም፣ እህት፣ እናት፣ አባት. . . ህዝብና ወገኖችም ጭምር ነው” ያለው ንቅናቄው ፤-“ምክንያቱም ድርጊቱ በትግራይ ህዝብ ስም እየተፈፀመ በመሆኑ ነው”ብሏል።
የ
ዓይን እማኞችን ጠቅሰሶ ንቅናቄው እንደዘገበው፤ ሚያዚያ 24 ቀን ከቀኑ በስድስት ሰዓት ገደማ የመከላከያ
ሰራዊት አባላት ወደ ፖኪዶ መንደር በመሄድ አንድ መሳሪያ የያዘ ሰው ከፊት ለፊታቸው ሲያገኙ ያለ አንዳች ጥያቄ
ተኩሰው ይገድሉታል። ሟች በክልሉ አስተዳደር አካባቢውን እንዲቆጣጠር የተመደበ የፖሊስ አባል ሲሆን፣ ወንድሙ ደግሞ
በምስራቅ ኢትዮጵያ በግዳጅ ላይ የሚገኝ የመከላከያ ሠራዊት አባል ነው።
ወንድሙ በባልደረቦቹ የመከላከያ ሰራዊት አባላት የተገደለበት ወጣት ለቀብር ለመድረስ ከጅጅጋ ወደ ጋምቤላ መምጣቱን የጠቀሱት የዜናው ምንጮች፤” እሱ የለበሰውን መለያ የለበሱ፣ አገርንና ህዝብን ከጠላት ለመጠበቅ የማሉ ባልደረባዎቹ ያለምንም ጥፋቱ ወንድሙን እንደገደሉበት ሢሰማ ምን ብሎ ይሆን?” ሲል ጠይቋል።
ፖሊሱ
ሲገደል ተኩስ የሰሙ የመንደሩ ታጣቂ ሚሊሻዎች መሳሪያ በመያዝ ወደ ስፍራው ሲያመሩ አሁንም ያለ አንዳች ንግግር
የመከላከያ ሰራዊት አባላት ተኩስ ከፍተው ከመካከላቸው ሁለቱን መግደላቸውን እና ሁለት ማቁሰላቸውን ነዋሪዎቹ
ገልጸዋል።
በዚህ ጊዜ ነበር የፖኪዶ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችና መምህራን በመደናገጥ ከክፍላቸው የወጡት።
ይህን ጊዜ የህወሃት ታጣቂዎች መሳሪያቸውን ወደ ትምህርት ቤቱ አቅጣጫ በማዞር ከየአቅጣጫው ተኩስ በመክፈት አንድ መምህርና አንድ ተማሪ መግደላቸውን ንቅናቄው አመልክቷል።
ወደ ህወሃት ሰራዊት ዋና ካምፕ የተወሰደ ሌላ የ 19 ዓመት ወጣትም በደረሰበት ከባድ ድብደባ ህይወቱ ሳያልፍ እንዳልቀረ እየተነገረ መሆኑን ገልጿል።
በተፈጠረው
ያልተጠበቀ ጥቃት የተደናገጡ ተማሪዎች ወደ ጫካ ለመሸሽ መገደዳቸውን የገለጹት የአካባቢው ነዋሪዎች ፤ በሚሸሹት
ተማሪዎችና ያካባቢው ተወላጆች ላይ የተኩስ እሩምታ ይወርድ ስለነበር በትክክል የሟችና የቆሰሉትን ቁጥር መለየት
እንደማይቻል ተናግረዋል።
ከጥቂት ቀናት በፊት በአካባቢው አስር ሺህ ሄክታር መሬት በወሰደው የሳዑዲ ስታር
ሜካናይዝድ የሩዝ እርሻ ሰራተኞች ላይ የደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የአካባቢው ተወላጆች ላይ እየደረሰ ያለው የጅምላ
እስር መባባሱን ከተለያ አቅጣጫዎች መረጃዎች ያመለክታሉ።
እስር ቤት ያሉት ንፁሃን በየቀኑ እየተደበደቡ
እና እየተንገላቱ እንደሚገኙ ታማኝ ምንጮቹን ጠቅሶ ያመለከተው ንቅናቄው፤ ምን ያህሉ ህይወታቸው እንዳለፈ ለጊዜው
ዝርዝር ማቅረብ ባይቻልም፤ በድብደባ ብዛት የሞቱ እንዳሉ ማረጋገጡን አመልክቷል።
“ድፍን
የአኙዋክ ብሄረሰብ አባላት በሽፍትነት ተፈርጀናል፣ ችግሩ አሳሳቢ ነው። በቀሉ ተጀምሯል። አሁን እየተካሄደ ያለው
ግድያ በ1996 ከተካሄደው ጭፍጨፋ የሚተናነስ አይደለም። አገርና ህዝብ ከጠላት ለመጠበቅ የማለ ሠራዊት፤ የራሱን
ህዝብ እንዲጨርስ ታዟል። እንዲህ ያለ ተግባር የጠላት ሠራዊት እንኳን አያከናውንም” ሲሉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ለንቅናቄው ሀዘናቸውን ገልጸዋል።
አስተያዬት
ሰጪው እንዳሉት፤ አንድ የአካባቢው የአገር ሽማግሌ ፤ በአገራቸው ባህል መሰረት ከባለቤታቸውና ከልጆቻቸው ጋር
ዛፍ ጥላ ስር ተቀምጠው ሳለ፣ የህወሃት/ኢህአዴግ የመከላከያ አባላት ድንገት ወደተቀመጡበት በመምጣት፦ “ለሽፍቶች ቀለብ የምትሰጠው አንተ ነህ” በማለት ሙሉ ቤተሰባቸውንና አዛውንቱን ረሽነዋቸዋል። የቤተሰቡ ታሪክም በዛው ተደምድሟል።
“እንዲህ ያለው አሰቃቂ ተግባር የሚፈፀመው አቶ መለስ በሚመሩት ህወሃትና በትግራይ ህዝብ ስም ነው”ሲሉ አስተያዬት ሰጪው እያለቀሱ ተናግረዋል።
እኚሁ ግለሰብ እንዳሉት፤ እዚያው መንደር ውስጥ ከሁለት ሳምንት በፊት ማር ለመቁረጥ ጫካ የሄደ አንድ ግለሰብ ሲመለስ የህወሃት/ኢህአዴግ ሠራዊት አባላት ያገኙታል። ከዚያ በቀጥታ፦ “ለሽፍቶች ምግብ አድርሰህ ነው የምትመለሰው” በማለት ከገደሉት በሁዋላ አስከሬኑን ጫካ ውስጥ ጥለውታል።
በአካባቢው የሚያልፉ ሰዎች በጠረኑ አማካይነት የሟቹን አስከሬን እንዳገኙት ተናግረዋል።
የፐርቦንጎ
መንደር ነዋሪ የሆነ በመካከለኛ እድሜ የሚገኝ አንድ ወጣት ደግሞ ጥቃቱ በተፈፀመበት ሚያዚያ 24 ቀን ከመንደሩ
ወጥቶ በዝግታ ርምጃ ሲያዘግም በጥይት ተገድሏል። በጋምቤላ አሁን ያለው ነገር፤ ሰዎችን ያለ አንዳች ጥያቄ በጥይት
መገደል፣ ማሰር፣ መግረፍ፣ “ሽፍቶችን አጋልጡ” በሚል ማሰቃየት ብቻ ነው ይላሉ-የ አካባቢው ነዋሪዎች።
እንደ
ንቅናቄው መግለጫ፤ይህ ሁሉ ግፍና በደል እየተፈጸመ ነው የአኙዋክ ብሄረሰብ አባል የሆኑት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ
ኦሞት ኦባንግ ወገኖቻቸው የሆኑትንና በጅምላ “ሽፍታ” ተብለው የሚጨፈጨፉትን የአኙዋክ ብሄር አባላትን በመሰብሰብ
“ሽፍቶችን አውግዙ” በሚል ሽፍቶች እንዲያወግዙ የክልሉ አስተዳደር ባዘጋጀው የተቃውሞ ሰልፍ ነዋሪው እንዲገኝ
ማሳሰቢያ የሰጡት።
ተሰብሳቢዎቹን እጅግ እንዳበሳጨ የተነገረለት ስብሰባ፣ በሰላማዊ ሰልፉ ሽፍታ የሚባሉትን
“ፀረ መንግስት፣ ፀረ ልማት፣ ፀረ ኢንቨስትመንት” በማለት እንዲያወግዙና በሳዑዲ ስታር የውጭ አገር ዜግነት
ያላቸው ሰራተኞች ላይ የተፈፀመውን ግድያ እንዲቃወሙ፣ ይህንን ካላደረጉ የሽፍቶች ደጋፊ ለመሆናቸው እንደማረጋገጫ
ተደርጎ እንደሚወሰድ፣ አቶ ኦሞት ያስጠነቀቁበት ነበር።
ንቅናቄው ያሰባሰበውን መረጃ በመጥቀስ እንዳለው፤
አቶ ኦሞት ይህንን ቢሉም ሚያዚያ 25/ 2004 ዓም በማስፈራሪያና በአኙዋክነታቸው ብቻ በጅምላ “ሽፍታ” ተብለው
የተፈረጁት የብሄሩ አባላት ሰልፍ መሄዳቸው ቀርቶ ባብዛኛው ቀብር ላይ ነበሩ።
በተቃውሞ ሰልፉ ላይ ሴቶች፣ ህፃናት፣ ቁጥራቸው እጅግ አነስተኛ የሆኑ ካድሬዎችና በግዳጅ ሰልፍ እንዲወጡ የታዘዙ የመንግሥት ሰራተኞች ታይተዋል።
በአካባቢው
ልጆቻቸው የተገደሉባቸው አንድ ወላጅ፦“ውሰዱኝ፣ ገዳዮቹ ያሉበት ቦታ አድርሱኝ፣ እኔንም እንደ ልጆቼ ይግደሉኝ፣
ብቻዬን ቀርቼ እንዴት እኖራለሁ? አልችልም። ልጆቼ፣ ልጆቼ . . . ውሰዱኝና ይግደሉኝ” ሲሉ ተሰምተዋል።
“ብሶት የትግራይን ሰዎች ብቻ ሳይሆን ሌሎችንም ይወልዳል። እንኳን ሰው ከብትም ሲብስበት ያመራል። ብሶት እንስሳንም ይወልዳል” ሲሉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ ተናግረዋል።
No comments:
Post a Comment