Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Wednesday 9 May 2012

እንደወጣ የቀረው ነጻ ሚዲያ......ፋሲል አያሌው (ኖርዌይ)


ፋሲል አያሌው (ኖርዌይ)

ነጻነት እና ዲሞክራሲ የምንላቸው ሁለት ጽንሰ ሃሳቦች ወደ ምድር ወርደው ተግባራዊነታቸው የሚረጋገጠው ህዝብ የሚፈልገውን መሪ፣ቡድን፣ፓርቲ፣ወይም አለቃ በነጻነት መሻር መምረጥ ሲችልና ለሀገሩ ይጠቅማል፣ ያዋጣል፣ ያስኬዳል ብሎ ያመነበትን ሀሳብ ያለምንም ተጽእኖና ፍርሃት መግለጽ መቻሉ ዋነኞቹ ናቸው፡፡ እነዚህን ትልልቅ ጽንሰ ሀሳቦች በመሪ ተዋናይነት ከሚተውኑት ተዋናዮች መካከል ማለትም ከህዝብና ከመንግስት ጎን ለጎን ነጻ ሚዲያዎች ያላቸው ሚና ከፍተኛ መሆኑ የነጻው አለም ልጆች (Free world boys)ብቻ ሳይሆኑ እኛም ምስክር ነን የነጻው አለም ልጆች እና እኛን ከሚለያዩን ብዙ ነገሮች መካከል ደግሞ አንዱ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለነጻነት እና ዲሞክራሲ መገለጫዎች ወይንም ነጻነትና ዲሞክራሲ በተግባር ከሚረጋገጥባቸው ቅርንጫፎች
አንድ አንጓ የሆነውን ነጻ ሚዲያ ለማግኘት ካልታደሉት ሀገሮች አንዷ መሆኗ ነው:: ለእኛ ኢትዮጵያውያን ከመንግስት ቁጥጥር ነጻ የሆነ የግል ቴሌቪዝንና ሬዲዮ ማግኘት ህልም ነው:: ባለፉት ሃያ አመታት የወያኔን
ስርአት እስርና እንግልት ተቋቁመው ሲሰሩ የነበሩ የግል ጋዜጦችና መጽሄቶች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ እንዳይመለሱ ተደርገው ጠፍተዋል ሁላችንም እንደምናስታውሰው የዛሬ አስራ አራት እና አስራ አምስት አመት ገደማ በስንት መከራና እስር ውስጥ የቻሉትን እየቆፈሩ እያወጡ የወያኔን ዘረኛ መንግስት ግፍና መከራ ሲያጋልጡ የቆዩት የተለያዩ ጋዜጦችና መጽሄቶች ስርአቱ በሚያደርስባቸው እንግልት፣እስርና አፈና አዘጋጆቹም ሆነ ባለቤቶቹ ከስራቸው ብቻ ሳይሆን አብዛኛዎቹ ከሃገራቸውም ጭምር ተፈናቅለዋል ጦብያ፣ ወንጭፍ፣ ሰይፈ ነበልባል፣ ምኒሊክ፣ ሳተናው፣ ኢትኦጵ፣ ነጻነት፣ አዲስ ዜና፣ መብረቅ፣ ሰንደቅ፣ ታሪክ፣ ቤዛ፣ አሌፍ፣አስኳል፣ ሙዳይ፣ መዝናኛ፣ አዲስ ነገር፣ አውራምባ ታይምስ፣ ዘ ፕሬስ፣ ጎህ፣ ጽጌሬዳ፣ ኢትዮጲስ፣አፍሪካ ቀንድ፣ ጦማር፣ሞገድ፣
ገናናው፣ክብሪት፣ፍተሻ፣አባይ፣ ኢትዮታይም፣ ማዕበል፣ ሉሲ፣ ርጂ፣ ጠቋሚ፣ ሀገሬ፣ ኤክስፕሬስ፣ ትኩረት፣ ገሞራው፣ዘጋቢ፣ፈለግ፣ቅይጥ፣ ንጋት፣ሩሃማ፣መዲና፣ እና ሌሎችም ጋዜጦችና መጽሄቶች የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ የቅርብ ጊዜ ትዝታዎቻችን ናቸው ዛሬ ግን እነዚህን ሁሉ በኢትዮጵያ ምድር ላይ አታዩያቸውም።
መቼም እነዚህ ሁሉ ጋዜጦችና መጽሄቶች ከስረው ወይም ስራቸውን ወደ ሌላ ሞያ ቀይረው እንዳልሆነ በሚገባ እናውቃለን ይልቁንስ አብዛኛዎቹ በወያኔው ስርአት በሚደርስባቸው አፈናና እንግልት ብዙሃኑ ሀገር ለቀው ሲሰደዱ የቀሩትም ስራቸውን አቁመውታል::

ኢትዮጵያ ሲሆን ሲሆን የብዙ የግል ቴሌቪዝንና ሬድዮ ጣቢያውች ባለቤት መሆን ሲገባት ለጥቂት የግል ጋዜጦችና መጽሄቶች እንኳን አለመታደላችን በእጅጉ ያበሳጫል ይህ በአጭሩ አቶ መለስና ጋሻ ጃግሬዎቹ በሀገራችሁ ጉዳይ አያገባችሁም መናገር፣መጻፍ፣ መተቸት፣ሃሳብ መለዋወጥ፣መማማር አትችሉም እኔና እኔ ያልኳችሁን ብቻ ስሙ፣አድምጡ፣እዪ እያለን ነው (አያድርስ ነው ያንን የውሸት ቋት የሆነ የመንግስት ሚዲያ ለጆሮአችን በግድ ሲታዘዝልን እንደውም ልጆቻችሁን ከETV አርቁ በኋላ ውሸት እንዳይለምዱባችሁ የምትል የፌስ ቡክ ቀልድ ትዝ አለቺኝ ልበል ) እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸውም ይሁኑ ሌሎች ነጻ ጋዜጦችና መጽሄቶች ለህብረተሰባችን ከዜና ምንጭነታቸው በተጨማሪ ሁሉን አቀፍ የሆነ እውቀት ሲያስጨብጡን የነበሩና (በአንድ ወቅት አንድ ወጣት አዲስ አድማስ ጋዜጣን ማንበብ ከጀመረ በሁዋላ በቀለም ትምህርቱ እየጎበዘና እየተሻሻለ መምጣቱን ለራሳቸው ለአዲስ አድማሶች ገልጾላቸው እንደነበር አስታውሳለሁ) ስለ ሀገራችን ታሪክ፣
ባህልና ልማድ እንዲሁም አለማቀፋዊም ሆነ ሀገራዊ ትንታኔዎችን (issues) በስፋት ሲያካፍሉን የነበሩ ለመሆናቸው እኔም ሆንኩ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ አንባቢዎቻቸው ህያው ምስክሮቻቸው ነን ለዚህም ድንቅ ስራዎቻችሁ ባለውለታዎቻችን ናችሁና እናመስግናችሁሃለን::

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ በጣት የሚቆጠሩ የግል ጋዜጦችና መጽሄቶች ከወያኔው ስርአት የሚደርስባቸውን ጫናና ፈተና ተቋቁመው እየታገሉ ናቸው እነሱንም ወያኔ በክስና በተለያዩ ነገሮች እያዳከማቸው ይገኛል በአለም ላይ በብዛቱ ተወዳዳሪ የሌለው ኢትዮጵያዊ ጋዜጠኛ ሀገሩን ለቆ የተሰደደ ሲሆን እነ እስክንድር ነጋ፣ ውብሸት ታዬ፣ርዮት አለሙ እና ሌሎችም ጋዜጠኞች በአሸባሪነት ተከሰው እሰር ቤት እየማቀቁ ነው የወያኔው ስርአት የጸረ ሽብር ህጉን ካጸደቀበት ጊዜ አንስቶ ህጉን በደንብ ተግባራዊ እያደረገ ያለው ጋዜጠኞች ላይ ሲሆን በአለም ላይ አሸባሪ ጋዜጠኞች የተፈጠሩት ኢትዮጵያ ውስጥ ነው (እድሜ ለወያኔ ገና አሸባሪ መምህራን፣
አሸባሪ ጤና ረዳት፣አሸባሪ የታላቁ ሩጫ ተሳታፊ፣አሸባሪ የጥቃቅንና አንስተኛ ነጋዴ፣አሸባሪ ጥገኛ ባለሃብት፣ አሸባሪ ስግብግብ ነጋዴ፣አሸባሪ……. እያለ ገና ክሱ ይቀጥላል ይህን እንዴት ጠረጠርክ ካላችሁኝ በቅርቡ አቶ መለስ ዜናዊ በፓርላማ የደሞዝ ማሻሻያ እርከን የመብት ጥያቄ ያቀረቡትን መምህራን ከአሸባሪ ድርጅቶች አይዞህ ባይ ያገኙ አንዳንድ መምህራን ሲሉ መምህራኖችን መዝለፋቸውን እናስታውሳለን ታዲያ ይሄ ምን ያሳያል) ጽሁፍ አዕምሮን ከአዕምሮ የሚያገናኘ ድልድይ ነው እንዲሉ እነዚህን ስራ ያቆሙና የተዘጉ ጋዜጦችና መጽሄቶች በማጣታችን ምን ያህል እንደተጎዳንና እየተጎዳን እንዳለን መገመት ይቻላል:: 

በ1997 ዓ.ም. በምርጫው ሰሞን ከህጻን እስከ አዋቂ አንድ ሰው በቀን እስከ አምስት የተለያዩ ጋዜጦችን እየገዛ የሃገሩን ጉዳይ ሲከታተልና በንቃት ሲሳተፍ የነበረው ህዝብ ዛሬ ከገዥው መንግስት የተለያዩ ጫናና ማስፈራራያዎች ጋር እየተፋጠጡ የአቅማቸውን የሚታገሉ ጥቂት ጋዜጣና መጽሄቶችን ብቻ እንዲያነብ ተደርጓል ገዥው መንግስት ካለው ከፍተኛ የህዝብ ተቀባይነት ማጣትና የአሰራር ብልሹነት የተነሳ አንድና ሁለት ጋዜጦች እንኳን በሚያወጡት ጽሁፍ ምን ያህል እንደሚደነብር በተደጋጋሚ የታዘብነው ጉዳይ ነው። አሁን በቅርቡ ደግሞ ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት የህትመት ስራ ስታንዳርድ ውል በሚል ባወጣው የስራ ውል መመሪያ ህግን የሚተላለፍ መስሎ የታየኝን ጽሁፍ አላትምም ይህንንም አውቃችሁ ፈርሙ ሲል ለነዚሁ ጥቂት ጋዜጣና
መጽሄት በላከው ጽሁፍ አሳውቁዋል ላለፉት ሃያ አመታት ሲሰራበት የቆየውን መመሪያ የሚያስለውጥ ምን አዲስ ነገር እንደመጣ ወያኔና ብርሃንና ሰላም ናቸው የሚያውቁት። እንግዲህ የዲሞክራሲ ግንባታ ላይ ነን ተብሎ በአዋጅ በሚለፈፍበት ሀገር የሀገሪቷ ጋዜጦችና ጋዜጠኞች ሀገር ለቀው እንዲወጡና ያሉትም ጋዜጠኞች በአሸባሪነት ተከሰው እስር ቤት በሚማቅቁበት ሁኔታ ሀገሪቷ ላይ የሚገነባው ዲሞክራሲ ነው ወይስ የሙሰኞች
ህንጻ?

መልስ የሚያሻው ጥያቄ አይመስሎትም 

ቸር ያሰንብተን

1 comment: