Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Wednesday, 9 May 2012

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የልማት ሠራዊት የሀገሪቱን አንጡራ ሀብት ሲያባክን.... ታረቀኝ ሙጬ

May 8th, 2012 

በትግራይ ክልል የልማት ሠራዊት እንዲሆኑ ተብለው የተመደቡ አካላት የወረዳና የቀበሌ አስተዳዳሪዎች በሕወሓት ካድሬ መሪነት ነው እሚንቀሳቀሱት፡፡ የታዘዙትን የሚፈጽሙ ናቸው፡፡ እነዚህ አካላት የተሰማሩበት የሥራ ዓላማ በገጠር በተመረጡ ቦታዎች በመስኖ የሚለማ ግብርና ማፋጠን የሚል ነው፡፡ ለዚህ ተብሎ የታቀደው የልማት አቅጣጫ ደግሞ በተመረጡ የገጠር መንደሮች እያንዳንዱን ገበሬ በእርሻ ማሣው የውሃ ጉድጓድ መቆፈር እንዳለበት ነው፡፡ በተጨማሪ ከደደቢት የብድር ተቋም የውሃ ሞተር በብድር መልክ በመውሰድ ከጉድጓድ ውሃ እየመጠጠ ወደ እርሻ ማሳ እንዲጠያሰራጭ ታስቦ ነው፡፡ ለዚህ ጉዳይ የተመደበው ባጀት እንደሚከተለው ነው፡፡
1. አንድ ጉድጓድ ለመቆፈሪያ፣ ለድንጋይ ግንባታና ለስሚንቶ መግዢያ የተመደበ የገንዘብ ልክ ብር 50000 ሺህ ነው፡፡
2. የውሃ ሞተር ከደደቢት የብድር ተቋም ገበሬው በብድር መልክ ይሰጠዋል፤ዋጋው አልታወቀም፡፡ በተጨማሪም በቅድሚያ ለማዳበሪያ መግዣ ብር 1300 ገበሬው እንዲከፍል ይደረጋል፡፡
ከተመረጡ ቦታዎችና የውሃ ጉድጓዶች ከተወሰዱት(ከተወሰኑት?)መካከል
1. ዓዲጉዶ አካባቢ እጅግ በጣም ብዙ ጉድጓዶች ተቆፍረዋል፡፡
2. ይሓ ድብድቦ አካባቢ ብዙ ጉድጓዶች ተቆፍረዋል፡፡
3. ውäሮማራይና ዓቃብሠዓት አካባቢዎች ብዙ ጉድጓዶች አሉ፡፡
4. ደንሸም ከዓGብ ሰርዓ በታች ያለ ቦታ 25 ጉድጓዶች አሉ፡፡
5. ማይ ንዕቢና ዓዲ ናጉል አካባቢ 30 ጉድጓዶች ተቆፍረዋል፡፡
6. በለስና አካባቢው ጉድጓዶች በብዛት ተቆፍረዋል፡፡
7. ዓዲኢታይና አካባቢው 25 ጉድጓዶች ተቆፍረዋል፡፡
8. ዓዲ ገዳድና አካባቢ 20 ጉድጓዶች ተቆፍረዋል፡፡
9. ፈረስ ማይ አካባቢ ብዙ ጉድጓዶች ተቆፍረዋል፡፡
ከላይ የተጠቀሱ ቦታዎችና የውሃ ጉድጓዶች የተሠሩት በሰው ኃይልና ኢክስካቫተር በመጠቀም ነው፡፡ በጉድጓዶቹ መካከል ያለው ርቀት ከ50 እስከ 100 ሜትር ብቻ ነው፡፡ ሥራው ከተከናወነ በኋላ በሞተሮች ውሃ በመሳብ ማሣውን ማጠጣት ከተጀመረ አንድ ሳምንት ሳይሞላው ጉድጓዶቹ በሙሉ ደረቁ፡፡ ውሃ የሚባል የላቸውም፡፡ ስለዚህ የተዘራው የእርሻ ሰብል ሁሉ አረረ፡፡ ቦታው ደረቀ፡፡ ገበሬው ከድካም በስተቀር ምንም ፋይዳ አላገኘም፡፡ ለምሳሌ ያህል በፈረስ ማይ አካባቢ ከጥንት ጀምሮ በመስኖ ነው ሕዘብ የሚጠቀመው፡፡ በአካባቢው የውሃ ጉድጓድ ከተቆፈሩ በኋላ ሕዝቡ ይጠቀምባቸው የነበሩ የውሃ ምንጮችና ጉድጓዶች በሙሉ ደረቁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ሕዝቡ የውሃ ችግር አለበት፡፡
ከላይ በተጠቀሱ አካባቢዎች ጉድጓዶቹ ይቅርና ቀደም ብለው ሕዝቡ ይጠቀምባቸው የነበሩ የውሃ ጉድጓዶችና የውሃ ምንጮች በሙሉ ደረቁ፡፡ አካባቢው ሁሉ ደረቅ ሆነ፡፡ ይህ የሚያሳየው የሕወሓት ካድሬዎች አስተሳሰብ ሁልጊዜ እኛ ነን ዐዋቂዎች ባይነታቸውን ነው፡፡ የልማት ሠራዊቱ ምንም ፋይዳ ሳይፈጽም ሥራው ከንቱና እርባና የሌለው ሆኖ ቀረ፡፡ ይህ ዓይነት አሠራር ደግሞ በሕወሓት የተለመደ ነው፡፡ ምክንያቱም ከጫካ ጀምሮ ይዞት የመጣው ፈሊጥ የተማረና ባለሙያን መናቅና ማንቋሸሽ ነው፡፡ የተማረ ሰው እንደጠላት ይቆጠራል፡፡ መካከለኛ ትምህርት ያለው ደግሞ ወላዋይ ይባላል፡፡ የሕወሓት ወዳጅ ድሃ ገበሬና ተራ ሠራተኛ ነው፡፡ ይህ ደግሞ የኮሚኒስትን አስተሳሰብ ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ በዚህ ምክንያት ነው እነዚህ ቦታዎችና የተቆፈሩ ጉድጓዶች ያለከምንም ጥናት በሕወሃት ካድሬ አመራር በዘፈቀደና በግምት የተሠሩት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንም ካደሬዎችን እያስተማሩ ናቸው እሚመስለው፡፡ የሃይድሮ ጂኦሎጂ ሙያ ሳይኖራቸው አይቀርም የሚል ግምት አለ(ኝ)፡፡ ነገር ግን በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕክምና ተማሪ ነበሩ ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ እግረ መንገዳቸውን የከርሰ ምድር ውሃ ጥናት ተምረው ሊሆን ይችላል፡፡ ያም ሆነ ይህ የጉድጓዶቹ በካድሬዎቹ መመረጥ ያስገርማል፡፡ ጉድጓዶቹ በቅርብ ጥልቀት ውስጥ የተገኙባቸው በቤድሮክ ላይ የተከማቸ ነው፡፡ በላዩ ላይ ያለው አፈር (overburden) ይባላል፡፡ ከዚያ በታች ከሆነ ደግሞ በአለት ውስጥ ይሆናልና በሰው ኃይል መቆፈር አይቻልም፡፡ ስለዚህ ግራውንድ ዎተር አኪዩፈር ለማግኘት ከተፈለገ ማሽን ያስፈልጋል፡፡ ይህን ሁሉ ለማድረግና የከርሰ ምድር ውሃ ጠባይ ለማወቅ ባለሙያ ያስፈልጋል፡፡ በወይን(‹ይ›ን አጥብቃችሁ አንብቡ!) መጽሔት እንዳነበብኩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት አንድ ሦስተኛ የትግራይን መሬት በመስኖ ለማልማት ማቀዳቸው ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን የመስኖ ውሃ ከየት ነው እሚገኘው? ከከርሰ ምድር ውሃ በሕወሓት ካድሬ ተፈልጎ የሚገኝ አድርገው አስበው ከሆነ ውጤቱ እንዳየነው ነው እሚሆነው፡፡ ባለሙያዎች አሰማርተው ሥራው የሚካሄድ ከሆነ የሚደገፍ አሳብ ነው፡፡ ነገር ግን በሕወሓት ካድሬዎች የሚሠራ ከሆነ ትርፉ ድካምና ገንዘብ ማባከን ነው፡፡ ኋላ አንድ ቀን የትግራይ ሕዝብ ይፋረደወታልና በሠፈሩት ቁና ይሠፈራሉ፡፡
ሕወሓት ምንጊዜም ከስህተቱ ተምሮ አያውቅም፡፡ ለምሳሌ ከዚህ በፊት የሕወሓት ካድሬዎች የሆነ ሀገር ይጎበኙና ሆረዬ የሚባል የእርሻ ዘዴ ይዘው መጡ፡፡ ከዚያ በኋላ የትግራይ ገበሬ የሆረዬ ጉድጓድ ቆፍር ተባለ፡፡ በክረምት ጊዜ ውሃ ለማቆር ታስቦ ጉድጓዶቹ በላስቲክ እንዲሸፈኑ ተደረጉ፡፡ ነገር ግን ሁላችንም እንደምናውቀው ነገሩ ሁሉ ከሸፈ፡፡ ያን ጊዜም ገበሬው ላስቲኩንም ከደደቢት የብድር ተቋም በብድር ተገድዶ ነው የወሰደው፡፡ ከዚያ በኋላ ብድርህን ክፈል ተብሎ ከብቶቹንና እህሉን እየሸጠ ከፈለ፡፡ መክፈል ያቃተው ስንቱ ገበሬ ነው ሀገር ለቅቆ እንዳይታሰር በመስጋት የሸሸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ የሆረዬ ላስቲክ በየከተማው የዲኤስ ቲቪ አዳራሽ መሥሪያ ሆኖ ይገኛል፡፡ በገጠርም የእንስሳ ቤትና የደሳሳ ቤቶች መጠገኛ ነው የሆነው፡፡
(Hydrogeology and groundwater) ጥናት በሕወሓት ፖለቲከ ትምህርት ቤት ይሰጣል መሰለኝ፡፡ እነዚህ ካድሬዎች ስለከርሰ ምድር ውሃ ጠለቅ ያለ ዕውቀት ያላቸው በመመስል በዘፈቀደ ሥራ የሚከናወን ይመስላቸዋል፡፡ የከርሰ ምድር ውሃ እንቅስቃሴ በጣም አዝጋሚ መሆኑ አልገባቸውም፡፡ እያንዳንዱ ጉድጓድ (pump-test) መደረግ ነበረበት፤ የሞተር አቅም ለማወቅና ከጉድጓዱ ውሃ ብዛት (ጋር) ተመጣጣኝ ለማድረግ እንዲቻል፡፡ ይህ ሁሉ ሳይደረግና ምንም ጥናት ሳይደረግ ወደግምታዊ ተግባር ይገባሉ፡፡ የከርሰ ምድር ውሃ ባሕርይና ጠባይ ከቦታ ቦታ ይለያያል፡፡ ዝም ብሎ በመላ ምት የሚሠራ አይደለም፡፡ ስለዚህ ነው የከርሰ ምድር ጥናት በዩኒቨርስቲ ደረጃ ትምህርት የሚሰጠው፡፡ እንደዚህ መሆኑን ካድሬዎች አያውቁም፡፡
በዚህ አጉል አስተሳሰብ ስንትና ስንት የሀገር ሀብት ያለ አግባብ ይባክናል፡፡ ምክንያቱም እነዚህን ካድሬዎች የሚቆጣጠራቸው ሰው የለም፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለሚመሩ ማን ደፍሮ ይነካቸዋል? ከዚህ በፊት የሆረዬ የሥራ ውጤት አልባ በሆነበት ጊዜ ማንም የጠየቃቸው የለም(አልነበረም)፡፡ አሁንም ማንም የሚጠይቃቸው አይኖርም ብዬ እገምታለሁ፡፡ ያለን ዕድልም ሩቅ ሆኖ መመልከት ብቻ ነው፡፡
ባለፈው የትግራይ ገበሬ የሆረዮ ላስቲክ ዋጋ ዕዳውን መክፈል አቅቶት (ነበር) ከሀገር የሸሸው አሁን ደግሞ መከረኛው የትግራይ ገበሬ ያለበትን የውሃ ሞተር ዋጋ ዕዳ እንዴት አድርጎ ይከፍለዋል? ስለዚህ ስንት የትግራይ ገበሬ ነው ሀገር ለቅቆ የሚሸሸው? ወዴት እንደሚሸሽም አይታወቅም፡፡ የሕወሃት መንግሥት ግን በየመገናኛ ብዙኃኑ ለሕዝብ ቆሜያለሁ እያለ ፕሮፖጋንዳውን ሲነዛና ዲስኩር ሲያሰማ ውሎ ያድራል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር የልማት ሠራዊት ስሙን ቢለውጥ ይሻለዋል፡፡ የልማት ሠራዊት መባል ቀርቶ የጥፋት ሠራዊት ነው የሆነው፡፡ የሀገር ሀብት ያለአግባብ ሲባክን ሁልጊዜ ይታያልና የሕወሓት ካድሬዎች የሰው ምክር አይሰሙም እንጂ የሚመክራቸው አልጠፋም ነበር፡፡
የሚገርመው ነገር በትግራይ ያሉ ጂኦሎጂስቶችና ሃይድሮጂኦሎጂስቶች ምን እያደረጉ ናቸው? በሙያቸው እንዳይሠሩ ተደርገዋል፡፡ የተማራችሁትን ሙያ ሌሎች ሰዎች እየተጫወቱበት እያያችሁ ዝም ትላላችሁ? ይህማ ነውር ነው፡፡ ምንስ ስትሆኑ(እስክትሆኑ) ነው እንደዚህ የሆናችሁት? ለሙያችሁ ጠበቃ መሆን አቃታችሁ ማለት ነወይ? ሳይንሳዊን ሃቅ መካድ የለባችሁም፡፡ ምንም ሳይንስ እማያውቁ የሕወሃት ካድሬዎች በድፍረት ያን ሁሉ ብልሹ ሥራ ያለሀፍረት እየሠሩ እናንተ ምነው ዝም አላችሁ?
እውነት ለመናገር በትግራይ ብዙ ባለሙያዎች ያቀፉ ድርጅቶች የጂኦሎጂና የውሃ ሀብት ጥናትና ፍለጋ እንዳሉ የሚታወቅ ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ ድርጅቶች ምን እየሰሩ ናቸው? ተብለው ቢጠየቁ ምን መልስ አላቸው? ምንስ ምክንያት ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ትምህርትና ሙያ ሀገርንና ሕዝብን ካላገለገሉ ምን ፋይዳ አላቸው ሊባል ይችላል፡፡ ማንም ሰው ዕድል አግኝቶ ከተማረ ያን ትምህርት ደመወዝ ለማግኘት ብሎ ካሰበ ይህ ሰው ተምሯል ለማለት ያስቸግራል፡፡ ትምህርት ለደመወዝ ብቻ ነው ከተባለ ምን ዓይነት አስተሳሰብ ያለው ዜጋ እየተፈጠረ ነው? ከላይ እንዳየነው ምንም ሙያና የከርሰ ምድር የጥናት ዕውቀት የሌላቸው ያን ሁሉ ጥፋት እየሠሩ ባለሙያዎች ዝም ብለው ሲመለከቱ ማየት አስነዋሪ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች አድርባዮች ናቸው ከማለት ሌላ ስም ሊሰጣቸው አይችልም፡፡ የፈለገውን ምክንያት ቢደረድሩ ተቀባይነት ሊኖረው አይገባም፡፡
ጎልጎል ራያ ብዙ የሃይድሮሎጂ ጥናት ተሰርቷል፡፡ ብዙ የከርሰ ምድር ውሃ እንዳለው በሳይንስ ተረጋግጧል፡፡ ለምን ያንን ቦታ አይቆፍሩምና ለመስኖ እርሻ አያውሉትም? ያልታወቁ ቦታዎች በዘፈቀደ ከመቆፈርና ገንዘብ ከማባከን የተሻለ አማራጭ ነበር፡፡ ይህ ሁሉ የሚያሳየው የክልሉ አስተዳዳሪዎች ባለሙያዎችን ለማማከር ስለማይፈልጉ ነው፡፡ እኛ እናውቃለን ባይ የሕወሓት ካድሬዎች በትዕቢት የተወጠሩ መሆናቸው ከእኛ በላይ ላሣር ባዮች መሆናቸውን የትግራይ ሕዝብ ያውቃል፡፡ አብሮ መመካከርና አብሮ መሥራት የማይፈልግ የትግራይ ሰው የለም በማለት በርግጠኝት መናገር ይቻላል፡፡
ለምን እነዚያ ጉድጓዶች ሊደርቁ ቻሉ? ለሚለው ጥያቄ የሚኖሩት ምላሾች የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ጉድጓዶቹ እርስ በራሳቸው የተቀራረቡ በመሆናቸው (interference between water wells) ተጽዕኖ ይኖራቸዋል፡፡ በሌላ አባባል አንድ ጉድጓድ ለሌላው ጉድጓድ የሚኖረው ተጽዕኖ በሁለቱ ጉድጓዶች ያለው ርቀት የሃይድሮጂኦሎጂ ሳይንስ ሥርዓት ከሚፈቅደው ውጪ ሲሆን ነው፡፡ ምንያቱም ከሁለት ኪሎ ሜትር ያነሰ መሆን የለበትም፡፡
2. የውሃው ሞተር የመምጠጥ አቅምና የከርሰ ምድር ውሃ ወደጉድጓድ የሚፈስበት መጠን ወሳኝ ሚና አላቸው፡፡ ምክንያቱም ወደጉድጓድ የሚገባ የውሃ መጠንና ከጉድጓድ የሚመጠጥ የውሃ መጠን እኩል ካልሆኑ የጉድጓዱ ውሃ ቶሎ ያልቅና ሞተሩ በውሃ ፋንታ አየር መምጠጥ ይጀምራል፡፡ ስለዚህ ጉድጓዱ ይደርቃል ማለት ነው፡፡
እነዚህ ሁለት ነገሮች ግምት ውስጥ መግባት አለባቸው፡፡ ስለዚህ ጥንቃቄ የጎደለው አሠራር እዚህ ውስጥ መግባት የለበትም፡፡ ማለትም እንደማናቸውም ሥራ በዘፈቀደ መሠራት የለበትም ለማለት ፈልጌ ነው፡፡ ስለዚህ ሥራው ውጤታማ ሊሆን ከተፈለገ ባግባቡ መሠራት አለበት፡፡
በወይን መጽሔት እንዳነበብኩት በብዙ ቦታዎች የስኳር አገዳ እርሻና የስኳር ፋብሪካዎች ለማቋቋም በሀገር ደረጃ እንደታቀደ ያመለክታል፡፡ በጣም ጥሩ ሃሳብ ነው፡፡ ነገር ግን እንደሚታወቀው የስኳር አገዳ ሰብል ብዙ ውሃ የሚያስልገው የእርሻ ሰብል በመሆኑ የሚያስልገው የውሃ መጠን አስቀድሞ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ ከዚያ በፊት የውሃ አጠቃቀማችን ምንጩ ከየት እንደሆነ በቅድሚያ ተጠንቶ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ መቅደም አለበት፡፡ በዚህ ጉዳይስ ለባሙያዎች አስተያየት ቅድሚያ መሰጠት የለበትም ወይ? የማንም ዕቅድ ወይም ሊሠራ የተፈለገ ነገር በቅድሚያ መጠናት አለበት፡፡ምክንያቱም ያለጥናት የሚደረግ ሥራ ውጤት አልባ ነው የሚሆነው፡፡ ከዚህ በፊት ያየናቸው በዘፈቀደ የተሠሩ ሥራዎች ውጤታቸው ያማረ አልነበረም፡፡ በዚህ ምክንያት የሀገራችን ሀብት በከንቱ ይባክናል፡፡
ከስህተታችን መማር መቻል አለብን፡፡ የመመካከር ባህል ሊዳብር ይገባዋል፡፡ ሁሉን ነገር በፖለቲካ ዐይን መመዘኑ ይቅር፡፡ ያስተዳዳሪዎች አስተሳሰብ በፖለቲካ ብቻ የተገነባ ነው የሚመስለው፡፡ ሁሉ ነገር በፖለቲካ ዓይን መታየት አለበት ባዮች ናቸው ነገር የሚያበላሹት፡፡
አንድ የዓለም ባንክ ሠራተኛ ወደነበርኩበት መሥሪያ ቤት በየጊዜው ሲመጣ ላስተናግደው እመደብ ነበር፡፡ ለልመና እንዲመች በጥሩ ሁኔታ እንዳስተናግደው እታዘዝ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ አሉ የተባሉ ሆቴሎች እጋብዘው ነበር፡፡ አንድ ቀን ምሣ ከበላን በኋላ ቡና እየጠጣን እያለን ኢትዮጵያን በመጥፎ ቃላት መስደብ ጀመረና በጣም ተሰማኝ፡፡ እንዳልሰድበውም የልመናው ነገር ሊበላሽ ነው፡፡ ዝም እንዳልለው ሀገሬ እየተሰደበች አልቻልኩምና ቁጭቴን በውስጤ አምቄ እንዴት አድርገህ እንደኢትዮጵያ ያለችውን ድሃና ኋላቀር አገር ከሀገርህ አሜሪካ ጋር ታነጻጽራለህ አልኩት፡፡ ሰውዬው በጣም ተናደደና ኢትዮጵያ ድሃ አይደለችም፤ኋላቀርም አይደለችም፡፡ እኛ እንኳ የ200 ዓመት ታሪክ ያለን ሕዝብ ነን፡፡ ኢትዮጵያ ግን በሺህ የሚቆጠር ዓመታት ታሪክ ያላት (Ethiopia is under managed country) ሀገር ናት ሲለኝ አፈርኩ፡፡ ምክንያቱም የሚናገረው እውነት ስለሆነ ነው፡፡ይህን የሰውዬውን አባባል ምን ጊዜም አልረሳውም፡፡ እኔ ሦስት መንግሥታትን ያየሁ ሰው ነኝ፡፡ ሰውዬው እንዳለው ምን ጊዜም አስተዳደራችን ሲመዘን ባዶ ነው፡፡ የአስተዳደር ድሆች ነን፡፡ የጥሩ መንግሥት ድህነት እንጂ ሌላ ችግር የለብንም፡፡ እንዴት ሀገራችንን እናስተዳድር ብለን በጥሞና ማየት አለብን ብዬ ለብዙ ጊዜ አሰብኩ፡፡ እንቅልፍ እስከማጣ ድረስ አሳሰበኝ፡፡ ምን ያልታደልን ሕዝብ ነን?
(ከ)አሁን በኋላ ወደኋላ ዘወር ብለን ማየት ያስፈልገናል፡፡ ያደረግነው ሁሉ ትክክል ነበር ወይ ? ስህተት አለው ብለን ራሳችንን መጠየቅና ረጋ ብለን ማየት አለብን፡፡ ስህተት ካለ ከስህተታችን ምን ተማርን ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን፡፡ ወደሌላ ርምጃ ከመሄዳችን በፊት፡፡ ይህ ሊሆን የሚችለው አስተሳሰባችንን ካስተካከልንና የሰዎችን ሃሳብ ከተቀበልን ብቻ ነው፡፡ በስሜት ሳይሆን ረጋ ብለን በማሰብ ወሳኝ የሆነ እርማት ማካሄድ ያስፈልጋል፡፡ ለወደፊት ያቀድነው ሥራ ካለጥንቃቄ በማድረግ የሃሳቡን ዙሪያ ማየትና ማስተዋል ይኖርብናል፡፡ ሃሳቡንም በትክክለኛ ጥናት የተመሠረተ መሆን አለበት ብለን ማመን አለብን፡፡
በቅድሚያ ያለ ፈቃድ የሰው ጽሑፍ ወደኮምፒተር ገልብጬ በመላኬ የፍትህ ጋዜጣና የጽሑፉን ባለቤት ኢንጂነር አብደልወሃብ ቡሽራን ከልብ ይቅርታ እጠይቃለሁ፤ ከኢንጂነር የካበተ ልምድና ዕውቀት ለመማርና ለሌሎችም ዕድሉን ላላገኙት ለማካፈል ከመፈለግ በመነጨ በቅንነት እንዳደረግሁት ይቆጥሩልኛል ብዬም ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ያለፈው ዓርብ የገዛኋትንና ያለችንን ብቸኛ ጋዜጣ አሁን ከመሸ ሳነብ ይህ ጽሑፍ በጣም መሰጠኝ፡፡ እናም ገልብጠህ ወደድረ ገፆች ላከው እሚል ነገር በጆሮየ ሹክ አለኝ፡፡ አምሮኝ ለምን ይቅር አልኩና እንቅልፍ እያወላገደው የነበረ ኮሌጅ የበጠሰ ልጄን እንዲያነብልኝ አድርጌ በአሳደህ በላው የሌባ ጣት ትየባ አስነካው ጀመር፡፡ ብዙ ጊዜ ቢፈጅብኝምና ልጄም ግማሹን እንኳን ሳያጽፈኝ እንቅልፍ ቢያሸንፈውም ‹አባተ ቢሞት ተተካ ባልቻ፤ መድፍ አገላባጭ ብቻ ለብቻ› እንደተባለው ታናሽ እህቱ አግዛኝ ይሄውና ከነአርትዖቱ ጨርሼ ልልክላችሁ በቃሁ፡፡ ፎቶውን ከጋዜጣው ያስገባሁት በካሜራ ነው፤ በቅንፍ የሚታዩት አብዛኞቹ ጭማሪዎች ጽሑፉን ይበልጥ ለማስዋብ እንዲጠቅሙ ብዬ ራሴው ያደረግሁት ነው፡፡
አንድ ነጥብ ስለመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ብጨምር ደስ ይለኛል – ከፍ ሲል ከተገለጸው የመለስ ባሕርይ ጋር ቁርጥ ቁምጥ የሆነ ፡፡ ላሊበላ እሚያገባው በሰው ተዝካር ነው ይባላል መቼም፡፡
መንጌ ገሞራው በደቡቡ የሀገራችን ክፍል ይሄድና በሙጃና የፊላ ሣር የተሸፈነውን መሬት ‹በሉ፣ በዚህ ለምለምና አረንጓዴ መሬት ላይ ቡና ተተክሎ ለቀጣዩ ጉብኝቴ እንዲጠብቀኝ› ብሎ ያዛል፡፡ አንዱ ኢንጂኔር ‹ክቡር ሊቀ መንበር ሥፍራው እኮ…› ከማለቱ ‹ነግሬያለሁ፤ ምንም ማቄን ጨርቄን ማለት አያስፈልግም፤ ይተከል ብያለሁ – ይተከል› ይላል፡፡ ዘወር ይልናም ሌላውን የአፈር ተመራማሪ ‹ሣይነቲስት› አብሮ ተጓዥ በመጥራት ‹አሁን ይሄ ለምለም ሥፍራ ለቡና አይሆንም?› ብሎ ድንገት ሲያፋጥጠው ይየዘውንና ይጨብጠውን ያጣው ምሁር ሳያስበው ወደመሬት ጎንበስ ይልና አፈሩን ዘግኖ በምላሱ በመቅመስ ‹ኧረ ይሆናል ጌታዬ! በሚገባ እንጂ ክቡር ሊቀ መንበር!› ይለዋል፡፡ ሥራው በዘመቻ መልክ ተጀመረ፡፡ ስንትና ስንት ኹዳድ መሬት በቡና ችግኝ ተጥለቀለቀ፡፡ ነገር ግን ያ ሊቀ መንበሩን የሸወደው የልምላሜ ወራት ሲያልፍ ሀሩሩ ከሰማይ ተለቀቀና ያንን ሁላ ችግኝ እንዳይሆን አድርጎ ለአቅመ አበባነትም እንኳን ሳይደርስ በለጋነት ዕድሜው አሣርሮ ቀጨው፡፡ ሊቀ መንበሩም ዳግመኛ መጣ፡፡ ነገሩ ተነገረው፡፡ እንዲህ አለላችሁ፡- ‹ በሉ አሁን ይጠና!› አይ ዕድላችን? ማንም አምባገነን ባልጩት ራስ በብልጣብልጥ ጮሌነትና በማይማን ሠራዊት ታግዞ የአራት ኪሎን የምንሊክ ቤተ መንግሥት እየተቆጣጠረ እንዲህ ይጫወትብን? ከተኮሱ በኋላ ‹ቁም፣ ማን ነህ!› የሚሉ ቦዘኔዎችን ተሸክመን እምንጓዘው እስከመቼ ይሆን? አሁን ኢትዮጵያ እውን ከመንግሥቱና ከመለስ የተሻለ ሰው አጥታ ነው ወይንስ ኃጢያታችን መልካም ሰዎቻችንን እየደበቀብን ተቸግረን ይሆን? ኧረ እግዚኦ እንበል! የአምባገነኖች መመሳሰል ግን ከምን ይሆን? የሚሠሩበት ሥጋና ደም፣ አጥንትና ጅማት አንድ ይሆን? ሁላቸውም ዋሾዎች፣ ሁላቸውም ጨካኞች፣ ሁላቸውም ተጠራጣሪና ቦቀቦቅ ፈሪዎች፣ ሁላቸውም ገዳዮች፣ ሁላቸውም ዐዋቂና ጠቢብ ለመምሰል እሚጥሩ ጉረኞችና ሰው ጤፉዎች፣ ሁላቸውም ቁሣውያን አጋሰሶች፣ ሁላቸውም ሃይማኖትና ሞራል ባል ይሉኝታ … የለሾች፣ሁላቸውም መጨረሻቸው የማምር የተረገሙ ከይሲዎች…
ታረቀኝ ሙጬ ነኝ፤ ‹ለፍትህ ጋዜጣ ዘጋቢ› ከአዲስ አበባ፡፡ ወጉሳ ማዕረጉሳ – ለምን ይቅርብኝ?

No comments:

Post a Comment