ግንቦት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በአዲስ አበባ እሁድ ለአባይ ግድብ ድጋፍ ማሰባሰቢያ ታስቦ በተዘጋጀው የሩጫ ፕሮግራም ላይ ገዥው ፓርቲ ከፍተኛ ተቃውሞ ሊገጥመው ይችላል የሚል ሥጋት መፈጠሩን የኢሳት ምንጮች ጠቆሙ፡፡
የገንዘብ
ድጋፍ ማሰባሰቢያ የሩጫ ፕሮግራሙ ቀደም ሲል ከመስቀል አደባባይ፣ በታላቁ ቤተመንግስት በኩል በፍልውሃ አድርጎ ወደ
መስቀል አደባባይ ለመመለስ መርሃግብር ወጥቶለት የነበረ ቢሆንም ከጸጥታ ሥጋት ጋር በተያያዘ መነሻው መስቀል
አደባባይ ሆኖ በቄራዎች ድርጅት በማድረግ ተመልሶ መስቀል አደባባይ እንዲያበቃ ተወስኗል፡፡የተሳታፊዎች ቁጥሩንም
በተመለከተ ከ30 ሺ በላይ የአ/አ ነዋሪ ይሳተፋል ተብሎ መርሃግብር ከወጣ በኃላ አሁንም በተለይ ሙስሊሞች ሊረብሹ
ይችላሉ ተብሎ በመሰጋቱ ነዋሪውን ለማሳተፍ የነበረው እቅድ እንዲሰረዝና በየአካባቢው የተመረጡ አባላትና ደጋፊዎች
ብቻ በሩጫው እንዲሳተፉ በመወሰኑ የተሳታፊዎች ቁጥር ወደ 12 ሺ ዝቅ ይላል ተብሏል፡፡
ምንጮቹ አያይዘውም የሩጫው ዓላማ ለግድቡ ቀጣይ ድጋፍ ማሰባሰበብ ሆኖ ሳለ በተፈጠረው የጸጥታ ሥጋት ምክንያት ሕዝቡ ባለመሳተፉ ዝግጅቱ ዓላማውን መሳቱን ተናግረዋል፡፡
በተያያዘ
ዜና ሙስሊሙ ህብረተሰብ በነገው ሩጫ ላይ በመሳተፍ ሠላማዊ በሆነ መንገድ ተቃውሞውን ለመግለጫ እንዲጠቀምበት
የሚጠይቅ ወረቀት እየተበተነ መሆኑን ምንጮቻችን ቢጠቁሙም ወረቀቱን ለማግኝት ግን ያደረግነው ሙከራ ለግዜው
አልተሳካም፡፡
በሌላ በኩል ዓርብ ዕለት ሙስሊሙ ህ/ስብ እንደተለመደው በተቃውሞ የታጀበ ጁምአ ያካሄደ
ሲሆን ከወትሮው ለየት ያለ ግልጽና ሰውር ጥበቃ ተጠናክሮ ታይቷል፡፡መንግሥት ከሙስሊሙ ጥያቄዎች መካከል አንዱ
የሆነውን “መጅሊስ ይውረድ” የሚለውን ተግባራዊ ለማድረግ ቀን ቆርጦ የተንቀሳቀሰ ቢሆንም ምርጫው ጥያቄ ያቀረቡ
ወገኖችን ባሳተፈና በራሱ በሙስሊሙ ሕዝብ መካሄድ ይገባዋል በሚል ጥያቄ ባቀረቡ ወገኖች ዘንድ ተቃውሞ
ገጥሞታል፡፡ጥያቄያአቸውን ሲያቀርቡና ከመንግስት ጋር ሲደራደሩ የቆዩት ወገኖች ባወጡት መግለጫ ሕዝበ ሙስሊሙ ላነሳው
ጥያቄ ምላሸ የሚያሰገኝ ሒደት መጀመሩን በአዎንታ እንደሚያዩት ጠቁመው የሥልጣን ሸግግሩ ግን ሕዝባዊነት በሌለውና
አሁን በሥልጣን ላይ ባለው የመጅሊስ መዋቅር አጋር የሆነው የኡላማዎች ም/ቤት መሰጠቱን ተቃውመው፣ ሙሉ ሒደቱን
ሕዝበ ሙስሊሙ በንቃት እንዲከታተለው ጥሪ ማስተላለፋቸው ይታወሳል፡፡
መግለጫው አያይዞም ከሠላማዊ የሙስሊሙ ትግል ጋር በተያያዘ በመላ አገሪቱ የታሰሩ ወገኖች እንዲፈቱ ለመንግስት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
No comments:
Post a Comment