Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Friday, 11 May 2012

የኢትዮጵያ መንግስት በዜጎቹ ላይ እያደረሰ ያለውን የመብት ረገጣ እና እስራት በአስቸኳይ ያቁም!


በሀይማኖቶች ላይ ጣልቃ መግባቱን እና ዜጎችን ማፈናቀሉን ያቁም!!
በብራሰልስ ከኢትዮጵያዊያን የተቃውሞ ሰልፍ አዘጋጅ ድርጅቶች የተሰጠ መግለጫ
ሜይ 03፣ 2012
ብራሰልስ፣ ቤልጀም
አገራችን ኢትዮጵያ የዲሞክራሲያዊ ስርዓት ጎዳና መከተሏ፣ የህግ የበላይነት ስለመረጋገጡ እና የዜጎች ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች መከበራቸው እየተደሰኮረልን ሁለት አስርት አመታትን አስቆጥረናል። ይሁንና በእነዚህ ሁለት አሥርት ዓመታት ዉስጥ ያየነው እና እያየንም ያለነው እውነታ ከዚህ የመንግስት ፕሮፓጋንዳ ተገላቢጦሽ ነው። አገሪቱ የምትገኝበት ሁኔታ የዲሞክራሲ እምርታ ይቅርና ጭላንጭሉንም አይታለች ለማለት የሚያስደፍር አይደለም። ከፓርቲ አንባገነንነት አልፎ የግለሰቦች ወይም የጥቂት ቡድኖች አንባገነናዊነት እውን የሆነባት አገር ከሆነች ዉሎ አድሯል። መንግስት ራሱ ያጸደቀውን ህገ-መንግስት ሳይቀር በመጣስ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊያን ላይ እያደረገ ያለውን ግፍ አጠናክሮ ቀጥሎበታል። በዚያው መጠን የህዝብ እሮሮ፣ ስቃይና መከራ ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ መጥቷል። በኢትዮጵያ ሰፊ ህዝብ ዘንድ ያለው ተቀባይነት እየመነመነ መጥቶ እርቃኑን የቀረው ስርዓት አሁንም ለህዝቦች ፍላጎት ጆሮ በመስጠትና የአገሪቱን አጠቃላይ ደህንነት ከግምት በማስገባት ድርጊቱን ከማሻሻል ይልቅ አፈናዉን አጠናክሮ ቀጥሏል። ከዚህም የተነሳ፦
  • የ 1997 አገር አቀፍ ምርጫ ዋዜማ ላይ በተወሰነ ደረጃ ታይቶ የነበረው የዴሞክራሲ ጭላንጭል ሙሉ በሙሉ ከተዳፈነ በኋላ ገዢው ፓርቲ የስልጣኔ ተቀናቃኝ ናቸው በማለት የፈረጃቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎች በእስር ቤቶቹ አጉሮ ይገኛል፤ አሁንም እያጎረ ነው። እነዚህ በየማጎሪያ ቤቶቹ የሚገኙት የፓለቲካ እስረኞች ቁጥር በእጅጉ ከመጨመሩም በላይ ታስረው በሚገኙበት ቦታ የሚፈጸመው እንግልት እና ስቃይ ተባብሷል፤
  • ስርዓቱ በህዝብና በአገር ላይ እያደረሰ ያለው ጥፋትና ውድመት ለሰሚ ጆሮ እንዳይደርስ እና አለማቀፋዊ ትኩረት እንዳያገኝ፤ እንዲሁም የአፈና ስራው ይሰምር ዘንድ የህዝብ የመረጃ ምንጭ የሆኑትን የግል ሚዲያዎች ህልውና እያዳከመ ይገኛል፤ ጋዜጠኞች ለእስር እና ለስደት ተዳርገዋል፤ ጋዜጦች ከሕትመት ውጭ ሆነዋል፤
  • የህዝብ ንብረት የሆኑ የመገናኛ አውታሮች (ቲቪ፣ ሬድዮ፣ ስልክ፣ …) ህብረተሰቡን ማገልገል ሲገባቸው የስርዓቱ የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ከመሆን አልፈው ህዝብን የማፈኛ፣ የማሸበሪያ እና የመሰለያ አካል ሆነዋል፤
  • ኢትዮጵያዊያን ተወልደው ካደጉበትና ከሚኖሩበት ቀየ እየተነሱ መሬታቸው ለውጭ ዜጎች እና ለስርዓቱ ታማኝ ናቸው ለሚባሉ ግለሰቦች በሀራጅ እየተቸበቸበ ይገኛል፤ በዚህም በአፋር፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል፣ በሶማሌ፣ በደቡብ፣ በኦሮሚያ እና በሌሎች በርካታ የአገሪቱ ክፍሎች ኢትዮጵያዊያን ይህ ነው ለማይባል ስቃይና እንግልት ተዳርገዋል፤
  • ለዘመናት ተቻችሎና ተከባብሮ የኖረውን ህዝባችንን በእምነቶቹ ጣልቃ በመግባት እርስ በርሱ እንዲተላለቅ የሚያደርጉ ስራዎች ከመንግዜውም በላይ ተጠናክረው ቀጥለዋል፤
  • በሙስሊሙ ህብረተሰብ እምነት ጣልቃ በመግባትና “አህባሽ” የተባለ የአምልኮ አስተሳስብ በህዝቡ ላይ በሀይል ለመጫን እየተንቀሳቀሰ ነው፤ ይህን የተቃወሙ ሙስሊሞች ለእስራት ብቻ ሳይሆን በአገዛዝ ስርዓቱ ታጣቂዎች በግፍ ደማቸው እየፈሰሰ ይገኛል፤
  •  የአገርና የእምነት ቅርሶች ህልውናቸው እንዲያከስም እየተደረገ ነው። በታሪካዊነቱና በጥንታዊነቱ ታዋቂ የሆነው የዋልድባ ገዳም የዚህ አገርን እና ህዝብን በማጥፋት ስራ ላይ የተሰማራ መንግስት ሰለባ ሆኗል፤
  • በአለም አቀፍ ደረጃ የተወገዘ የሽብርተኝነት ህግ (Anti-Terrorism Law) በማውጣት ዜጎች ዘወትር መግስትን ፈርተውና ተሸማቀው እንዲኖሩ ተደርገዋል፤ ብሶቶቻቸውን ከመግለጽ መቆጠብ ብቸኛ አማራጫቸው ሆኗል። የሕዝብን ብሶት ሲያሰሙና የመንግስትን ፖሊሲዎችና አተገባበራቸውን ሲተቹ የነበሩ ጋዜጠኞች እና የፖለቲካ ፓርቲ አባላትም በዚሁ ሕግ እንደ ሽብርተኛ ተቆጥረው ለወንጀል ክስ እና እስራት ተዳርገዋል። ገሚሶቹም ከአስር አመት በላይ እስራት ተፈርዶባቸው በማረሚያ ቤት ይገኛሉ፤
  • የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ህግን (Civil Society and Charity Proclamation) በማውጣት ኢትዮጵያዊያን በአገራቸው ውስጥ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ፣ በሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ፣ እንዲሁም መብትን መሰረት ባደረጉ የልማት ሥራዎች ላይ ለመሰማራት እንዳይችሉ እና በነጻ የመደራጀትና ተደራጅተውም የመንቀሳቀስ መብታቸውን ነፍጓቸዋል፤
  • ዜጎች በየትኛውም የአገሪቱ ክፍሎች ተዘዋውረው ሕጋዊና ሰላማዊ በሆነ መንገድ የመኖርና ህይወታቸውንም የመምራት መብታቸውን ተነፍገዋል። በቅርቡ ከደቡብ ክልል በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵዊያን በተደረገባቸው የማፈናቀል ዘመቻ በገዛ አገራቸው ውስጥ ስደተኛ ሆነዋል፤
  • መንግስት በሚከተለው የተሳሳተ የኢኮኖሚ ፓሊሲ ሳቢያ ህዝባችን ለኑሮ ዋስትና ማጣት ተዳርጎ ጥቂቶች በንዋይ ውቅያኖስ ውስጥ ሲዋኙ ሰፊው ህዝብ ግን ወደተመጽዋችነት ደረጃ እየወረደ ይገኛል፤
  • ሕጋዊ በሆነ መንገድ የመብት ጥያቄዎችን በማንሳታቸው ብቻ መምህራን ከሥራ ገበታቸው ተባረዋል። መንግስት የመምህራኑን አስተዳደራዊ ጥያቄዎች ተቀብሎ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ሲገባው በመምህራኑ ላይ ዛቻና ማስፈራሪያ በመሰንዘር ጥያቄያቸውን አፍኗል፤
  • የሰራተኞች እና የሙያ ማህበራትን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠር ድርጅቶቹን የኢሕአዴግ ካድሬዎች መፈንጫ እንድሆኑ ወይም ተለጣፊ በማበጀት ሕዝቡን እንዲያደናግሩ ተደርጓል፤
  • በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በነጻነት የመደራጀት፣ የመሰብሰብ፣ ሃሳብን የመግለጽ፣ መንግስትን በሰላማዊ ሰልፍ የመቃወም እና ሌሎች መሰረታዊ መብቶች ታፍነዋል።
እነዚህን እና መሰል ግፎችን ኢትዮጵያዊያን አቅማቸዉ በፈቀደ ሁሉ እየታገሉ ይገኛሉ። ለቀሪው ወገንም የድረሱልን ጥሪያቸውን እያሰሙ ነው። ይህን እያየና እየሰማ አርፎ የሚቀመጥ ህሊና ሊኖረን አይችልም። በኢሕአዴግ መሪነት በአገራችን እና በህዝባችን ላይ እየተደረገ ያለውን የመብት ጥሰት፣ አገርን እና ህዝብን የማጥፋት ዘመቻዉ ሊያበቃ ይገባዋል። ግፉንም ሰላም ወዳድ ለሆነው የአለም ህዝብና መንግስታት ማሳወቅ ይገባናል። በዚህም መሰረት የአገዛዝ ስርአቱ መልካም እየሰራ እየመሰላቸው በገንዘብም ሆነ በዲፕሎማሲ ድጋፍ ለሚያደርጉለት መንግስታት አገሪቱ የምትገኝበትን አሳሳቢ ሁኔታ ለማስረዳት ሜይ 16፣ 2012 በብራሰልስ ቤልጀም የተቃውሞ ሰልፍ ተዘጋጅቷል።
በዚህ ከቤልጀም ብቻ ሳይሆን ከአውሮፓ የተለያዩ አገሮችና ከተሞች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ይሳተፉበታል ተብሎ በሚጠበቀው ሰልፍ ላይ መንግስት ከላይ በዘረዘርናቸውና በሌላም መልኩ በህዝባችን ላይ የሚያደርሰውን የመብት ረገጣ በአፋጣኝ እንዲያቆም ይጠየቃል። የአውሮፓ መንግስታትም በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየደረሰ ያለውን የመብት ጥሰት ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጡና ራሳቸውን አምባገነናዊ ከሆነው የኢሕአዴግ መንግስት በመነጠል አጋርነታቸውን የጭቆና ቀንበር ከተጫነበት ሰፊዉ ህዝብ ጋር እንዲያደርጉ ጥሪ ይደረግላቸዋል።
ከዚህ በተጨማሪም ሰልፉ የኢትዮጵያ ህዝብ ስርዓቱ ካዘጋጀለት የሀይማኖት፣ የጉሳና የዘር መከፋፈያ ወጥመድ ዉስጥ ሳይገባ በአንድነት በመነሳት አገሩንና ራሱን እንዲታደግ ጥሪ የሚቀርብበት፤ ለዲሞክራሲ፣ ለፍትህና ለህግ የበላይነት የሚደረገውን ትግል በመደገፍም አጋርነታችንን የምንገልጽበት ይሆናል። በሁሉም ቦታና በሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች፣ በሁሉም የእምነት ተቋማትና ምዕመናን ላይ እየተፈጸመ ያለውን ህገወጥ ድርጊትና ጣልቃገብነት እንዲያቆም ድምጻችንን የምናሰማበትም ነው።
ስለሆነም በዚህ ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ መገኘት የሚችሉ ሁሉ ሜይ 16፣ 2012 ከቀኑ 13፡00 ሰዓት ጀምሮ በብራስልስ የአውሮፓ ኮሚሺን ህንጻ ፊት ለፊት በመገኘት ድምጻቸውን እንዲያሰሙ ጥሪያችንን እናቀርባለን። በአሁኑ ወቅትም በተለይ በኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች የተጀመረውን የመብታችን ይከበር ጥያቄ በመደገፍና የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መብት ይከበር ዘንድ በያለንበት እንንቀሳቀስ የሚል መልክታችንን እናስተላልፋለን። ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ።
የሰልፉ አስተባባሪ ድርጅቶች፦

No comments:

Post a Comment