-በጥይትና በከባድ ድብደባ የተጎዱ ተማሪዎች ህክምና ላይ ናቸው
-የከተማው ነዋሪም ተቃውሞውን ተቀላቅሏል
ትላንት ለተቃውሞ በወጡ የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ ታጣቂዎች በጥይትና በዱላ ጉዳት ማድረሳቸውን ምንጮቻችን ገለፁ፡፡ ከትላንት በስቲያ እሁድ ሚያዝያ 28 እና ትላንት ሰኞ ሚያዝያ 29 በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ግጭት ሊከሰት የቻለው ተማሪዎች ተጓደለ ያሉትን የምግብ ጥራት በመቃወማቸው እንደሆነ ምንጮቻችን ዘግበዋል፡፡ እሁድ
ሚያዝያ 28 ከቀኑ 10፡30 ጀምሮ በተቀጣጠለው በዚህ ተቃውሞ አብዛኛው ተማሪ ቁጣውን የዩኒቨርስቲውን መስታወቶች በመሰባበር እንደገለፀ የሚናገሩት ምንጮቻችን ምሽት ላይ በድንገት ወደ ግቢው የገቡት ታጣቂዎች ተማሪዎቹ ላይ ከመጠን ያለፈ ኃይል በመጠቀም ጉዳት እንዳደረሱ ገልፀዋል፡፡ በወቅቱ በታጣቂዎች በተወሰደው እርምጃ ከ60 ያላነሱ ተማሪዎች መታሰራቸውና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎች ላይ ድብደባ እንደተካሄደ ታውቋል፡፡ በወቅቱ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ከፍተኛ የተኩስ እሩምታ የተሰማ ሲሆን ኢብራሂም መሀመድ የተባለ የ2ኛ አመት የማኔጅመንት ተማሪ በጥይት መመታቱ ታውቋል፡፡ ተማሪው በደረሰበት ከፍተኛ ጉዳት በደብረ ማርቆስ ሆስፒታል የህክምና እርዳታ በመከታተል ላይ እንደሚገኝ ፍኖተ ነፃነት ስፍራው ድረስ በመደወል አረጋግጣለች፡፡
ተማሪ ኢብራሂም መሃመድ በስልክ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፀው ከትላንት በስቲያ ምሽት ታጣቂዎቹ በቀጥታ በጥይት እግሩ ላይ መተው አቁስለውታል፡፡ ሌላው በታጣቂዎች ከፍተኛ ድብደባ የተፈፀመበት የ2ኛ አመት የማኔጅመንት ተማሪ የሆነውና ከትግራይ ክልል የመጣው ገብረ ኪዳን ብርሃኔ ትላንት ጠዋት በጀርባውና በተለያዩ የሰውነት ክፍሎቹ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰበት ለዝግጅት ክፍሉ ተናግሯል፡፡
በትላንትናው እለት ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ ‹‹የታሰሩ ተማሪዎች ይፈቱ››
የሚል ጥያቄን ይዞ የቀጠለው ተቃውሞ ቀስ በቀስ ከዩኒቨርሲቲው ውጪ መስፋፋቱን ከከተማው ያገኘናቸው መረጃዎች አመላክተዋል፡፡ ተቃውሞው በደብረ ማርቆስ ከተማ ጎዳናዎች ላይ በቀጠለበት ወቅት በርካታ የከተማው ነዋሪዎችም ትዕይንቱን ተቀላቅለው ጥያቄው ፖለቲካዊ ይዘት ተላብሶ ገዢውን ፓርቲ በማውገዝ እና ለኑሮ ውድነቱ ገዢውን ፓርቲ መኮነናቸውን ምንጮቻችን ተናግረዋል፡፡ ይህን ተከትሎም ታጣቂቆች ቶክስ በመክፈታቸው ተቃውሞው ተበትኗል ሲሉ ምንጮቻችን ዘግበዋል፡፡ በሁኔታው የተደናገጡት ተማሪዎች ወደ ተለያየ አቅጣጫ ሲበታተኑ ታጣቂዎችና ፖሊሶች አብዛኞቹን እያፈሱ ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንዳጓጓዟቸው የከተማው ነዋሪዎች ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡ አንዳንድ ተማሪዎች ወደ ህትመት እስከገባንበት ጊዜ ድረስ አፈሳው እንደቀጠለ ተናግረዋል፡፡ ጨምረውም በድብደባዉ ከተጎዱ ተማሪዎች መካከል አይናቸዉ ተመትቶ ኡፕራሲዮን የተደረጉ እንደሚገኙበት አስረድተዋል፡፡ ከስፍራው የደረስን መረጃ እንደሚያመለክተው በተማሪዎቹ ላይ እርምጃ የተወሰደው ስልጠናቸውን ባልጨረሱ ፖሊሶች ጭምር መሆኑን ያመለክታል፡፡ ማምሻውን የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው አሁንም በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ትገኛለች፡፡ ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች ትምህርታቸውን እንዲቀጥሉ ጥሪ አስተላልፏል፡፡
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ለማግኘት ወደ ዩኒቨርሲቲውና ወደ ደብረማርቆስ ሆስፒታል ደውለን ምላሽወደ ህትመት እስከገባንበት ሰአት ድረስ ምላሽ ማግኘት አልቻልንም፡፡
oh GOD am so happy dat u post z truth n we need our students out of prison immediately.
ReplyDeleteso true!!!!!!!!!!!!!!!!!!