Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Sunday, 27 May 2012

መልእክተ ፍትህ-ለኢህአዴግ

ከሁለት ቀን በኋላ ኢህአዴግ ስልጣን የያዘበት 21ኛ አመት የግንቦት ሃያ በዓል ይከበራል። እናም በአለፉት 21 አመታት በሀገሪቱ የታዩ ለውጦች እንዳሉ ሆነው ዋና ዋና የሚባሉ ጉዳዮች ላይ ግን የነበሩ ተስፋዎች ከመምከንም አልፈው ፍፁም እየጠፉ በመሆናቸው በዚህ ርዕስ አንቀፅ ለኢህአዴግ መልእክት ማስተላለፍ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተነዋል።
1ኛ የፕሬስ ነፃነት
በየትኛውም ሀገር አስፈላጊ እና ወሳኝ ከሚባሉት የሚመደበው አንዱ የፕሬስ ህልውና ነው። የፕሬስ አስፈላጊነት ከሕግ አውጭው፣ ከሕግ ተርጓሚው እና ከሕግ አስፈፃሚው ቀጥሎ እንደ አራተኛ የመንግስት አካል ተደርጎ እስከመወሰድ ይደርሳል። ይሁንና ኢህአዴግ የፕሬሱን ህልውና በተሻለ ደረጃ እንዲኖር የፈቀደው ላለፉት አስራ አምስት አመታት ብቻ ነው። ምክንያቱም ከምርጫ 97 በኋላ በርካታ የግል ጋዜጦች እና መጽሔቶች ከመዘጋታቸውም ባሻገር በመቶዎች የሚቆጠሩ
ጋዜጠኞች ለስደት ተዳርገዋል። ከዚህም በኋላ ቢሆን ወደ ህትመት የመጡት አዳዲስ ጋዜጦች ለህልውናቸው አደገኛ በሆኑት የፕሬስ እና የፀረ ሽብር አዋጆች መዳፍ ስር እንዲወድቁ ተደርገዋል። ይህንንም ተከትሎ አዲስ ነገር እና አውራምባ ታይምስ የተባሉ ጋዜጦች የመዘጋት ዕጣ ሲገጥማቸው ጋዜጠኞቹም የነፍስ አውጭኝ ሽሽት እንዲያደርጉ ተገድደዋል። የተቀሩት ጥቂት ጋዜጦች ደግሞ በሚታይ እና በማይታይ መንግስታዊ ጫና ውስጥ ሆነው እንዲሰሩ ለመደረጋቸው ፍትህ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታ ዋነኛ ምስክር ነው።
2ኛ በሀገሪቱ የነበረው ደካማ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ከ19 አመት በኋላ ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋ ተደርጓል። እናም ሀገሪቱ ራሱን አውራ ፓርቲ ብሎ በሚጠራ በአንድ ጉልበተኛ ፓርቲ እና በአንድ ሃሳብ ስር ወድቃለች። እናም ከገዢው ፓርቲ አካሄድ አንፃር የፖለቲካው ምህዳር መጥበቡ ሰላማዊ ትግሉን ይበልጥ አቀጭጮታል።
3ኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ሀገር በቀል ድርጅቶችን ጨምሮ በርካታ አለም አቀፍ ድርጅቶች ሲወተውቱ እና ሲመክሩ ቢቆዩም አንዳች ለውጥ ሳይታይ የዘንድሮ ግንቦት 20 ላይ ደርሰናል።
4ኛ ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት መጎልበትም ሆነ ለሁለንተናዊ የሀገር እድገት የማይተካ ሚና እንዳላቸው የሚታወቀው የሲቪል ማህበረሰብ /መያድ/ ተቋማት በፓርቲው የአፈና አዋጅ የተነሳ የሚረባ እንቅስቃሴ ማድረግ ተስኗቸዋል። ቁጥራቸውም ሆነ ተቋማዊ አቋማቸውም በእጅጉ አሽቆልቁሏል።
5ኛ ኢህአዴግ ዘላቂ ሰላም አስፍኛለሁ ቢልም በሀገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ቁጥራቸው የበዛ ብሄር ተኮር ግጭቶች እየተባባሱ መጥተዋል።
6ኛ ኢትዮጵያን እንደሚመራ ፓርቲ የኢህአዴግ ውስጣዊ የኃይል መስተጋብር ወሳኝ ከመሆኑ አንጻር፣ የአመራሩን የመተካካት ሂደት ተከትሎ አደገኛ ሁኔታዎች ሊከሰቱ እንደሚችሉ እየተነገረ ነው። ለሃያ አመታት ሀገሪቱን በብቸኝነት የመራ ፓርቲ ለመፈራረስ እየቀረበ መምጣቱ መንግስታዊ ስርዓቱ ላይ የሚያደርሰውን አደጋ ከፍተኛ ያደርገዋል።
7ኛ ባለፉት ሃያ አንድ ዓመታት ዴሞክራሲያዊ ስርዓት በሚገባ ባለመተግበሩ የማዕከላዊ መንግስቱን ህልውና ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ እንቅስቃሴዎች በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች እየተሞከሩ ነው። ከዚህ በተጨማሪ የድህነቱ መባባስ እና ስርዓቱ መንግስታዊ ሀላፊነቱን ያለመወጣቱ ሀገሪቱን ወደ ክስመት እያመራት ነው።
8ኛ.ከውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አንፃር ያለፉትን አመታት በተለያየ መልኩ የተሳኩ ናቸው ለማለት አያስደፍርም። መንግስት በውጭ ግንኙነት ፖሊሲና ስትራቴጂ ላይ እስከዛሬ የተጓዘባቸው መንገዶች በብዙ መልኩ ወጥነት የጐደላቸው ከመሆናቸውም በተጨማሪ የወደፊቷን ኢትዮጵያ መልክ በተሻለ መልኩ የማየት እድል አለው ብለን ደፍረን ለመናገር አንችልም። ለዚህ ማሳያ የሚሆነን በተለያዩ ጊዜያት በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ለተነሱ ግጭቶች መንግስት እየሰጠ ያለው ትኩረት አንዱ ነው። በድንበር የሚዋሰኑን የቀንዱ አባል አገራትን በተመለከተ ይህ ነው የሚባል ጥረት ያለ አቋም ሲንፀባረቅ አይስተዋልም። ከአብዛኞቹ ግጭቶችና አለመግባባቶች ጀርባ የውጭ ኃይል ተፅዕኖ በእጅጉ ይንፀባረቃል። በሶማሊያ እና ኤርትራ ላይ የተወሰደው የመንግስት አቋም የግጭቱን ምክንያቶች ከስሩ እልባት የሚሰጥ ሳይሆን በተደጋጋሚ ለሚነሱ አለመግባባቶች ጊዜያዊ መፍትሄ ብቻ እየሰጠ የሚያልፍ ሆኗል። ይህ ደግሞ በሀገር ሀብትና ንብረት ከመቀለድ እና የዜጐቻችንን ህይወት ከመገበር ውጭ በዘላቂነት ያመጣቸው ለውጦች አለመኖራቸውን መታዘብ እንችላለን።
የኢህአዴግ መንግስት ቀድሞ ከምዕራባውያን ጋር ከነበረው ጥብቅ ግንኙነት ተላቆ ሙሉ ለሙሉ ፊቱን ወደምስራቁ የአለማችን ክፍል ማድረጉ ብዙ ፖለቲካዊ እንድምታዎች እንዳሉት እውን ነው። የቻይና መንግስት የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ መሰረት የሚያደርግ በአገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት የሚለውን ነው። ይህ ደግሞ የአምባገነን መሪዎችን ማን አህሎኝነት በእጅጉ የሚደግፍ በመሆኑ ቻይናን ተመራጭ ያደርጋታል። ከዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብት አያያዝ አንፃር ቻይና ለማንም አገር ተምሳሌት የሚያደርጋት ተሞክሮ የላትም። ስለዚህ ነው የኢህአዴግ ሃያ አመታት የቻይና ውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ዴሞክራሲ ከመገንባት አንፃር ያለው ፋይዳ ከዛም አይደለም ብለን የምናምነው።
ስለዚህም በፍትህ እምነት ኢህአዴግ ሰሞኑን የሚያከብረውን ሃያ አንደኛ የድል በዓል መሰረት በማድረግ ብሄራዊ እርቅ እንዲፈጠር አመቻችቶ፣ በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ላሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጥሪ በማድረግ እና በማሳተፍ ጊዜያዊ የሽግግር መንግስት መስርቶ አዲስ ምርጫ እንዲካሄድ በማድረግ ሀገሪቷን ከመበታተን አደጋ የማደን ታሪካዊ ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ ይህንን ታላቅ ሀገራዊ አደራም ግንባሩ ይወጣ ዘንድ ፍትህ ትጠይቃለች፡፡

No comments:

Post a Comment