Welcome

"The thing that lies at the foundation of positive change, the way I see it, is service to a fellow human being." - Lech Walesa

Thursday, 31 May 2012

ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከሦስት ዓመታት በኋላ ጡረታ እንደሚወጡ በድጋሚ አረጋገጡ

- የተዋጣለት ዴሞክራሲ አልገነባንም
- በሀገሪቱ መከላከያ ሠራዊት የብሔር ተዋፅኦ ቢሻሻልም አመራሩ ግን ቀድሞ ከሕወሓት ታጋዮች አልተላቀቀም
- እየተገነቡ ባሉ የውሃ ኃይል ማመንጫ ግድቦች ላይ የምዕራብ አካባቢ ተቆርቋሪዎችን ተፅዕኖ ፈርተውታል
ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ከእንግሊዛዊው ጋዜጠኛ ሪቻርድ ዳውደን ጋር ከሰሞኑ ቃለ-ምልልስ አድርገው ነበር። ሪቻርድ ዳውደን የሮያል አፍሪካ ሶሳይቲ ዳይሬክተር ሲሆን፤ በጋዜጠኝነት በታላላቅ የእንግሊዝ ጋዜጦችና በዘኢኮኖሚስት መፅሔት የአፍሪካ ኤዲተር ሆኖ ሰርቷል። በአፍሪካ ዙሪያ መፅሐፍቶች ፅፏል።
ሪቻርድ ዳውደን ለዓለም የኢኮኖሚክ ፎረም ስብሰባ እዚህ አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደበት ወቅት ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ጋር ቃለ-ምልልስ አድርጎ ነበር በቃለ-ምልልሳቸውም ከሦስት ዓመት በኋላ ጡረታ እንደሚወጡ አስታውቀዋል። ዳውደን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቃለ-ምልልስ ዋና ዋና ነጥቦች በመለየት ከሰሞኑ በራሱ ብሎግ ላይ አስፍሮታል። በጎንዮሽም፤ “መለስ ኢትዮጵያን እንዴት እየመሯት ነው” የሚል ጠንከር ያለ ሐተታ አቅርቧል።
ሪቻርድ ዳውደን እ.ኤ.አ በ1901 ዓ.ም የተመሰረተውን ሮያል አፍሪካን ሶሳይቲ እ.ኤ.አ ከ2002 ጀምሮ በዳይሬክተርነት በመምራት ላይ ይገኛል። ሮያል አፍሪካን ሶሳይቲ የአፍሪካንና የታላቋን ብሪታንያን ግንኙነት ወደተሻለ ደረጃ ለማድረስ ተብሎ የተቋቋመ ተቋም መሆኑ ይታወቃል። በዚህ መነሻ ሪቻርድ ዳውደን በተቋሙ ድረገፅ ላይ በራሱ ብሎግ የአፍሪካን ሐተታዎችን በማቅረብ ይታወቃል። በአፍሪካ አንዳንድ ጉዳዮችም ላይ መጣጥፎችና ዘጋቢ ፊልሞች ሰርቷል።
ዳውደን አዲስ አበባ በመጣበት ወቅት አቶ መለስን ለማነጋገር ችሏል። በቃለ-ምልልሱም ላይ አቶ መለስ በኢትዮጵያ በሕዝቦች በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ሕገ-መንግስት ቢፀድቅም፣ በሀገሪቱ ያሉ ብሔረሰቦች በቋንቋቸው እንዲናገሩ በርካታ ስራዎች ቢሰራም የተዋጣለት ዴሞክራሲ አለመገንባቱን ግን አምነዋል።
ሌላው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት በዴሞክራሲና በኢኮኖሚ እድገት መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት አለመኖሩን ነው። ምንም እንኳ ዴሞክራሲ በኢኮኖሚ እድገት ጥሩ እና አስፈላጊ ቢሆንም፤ የዴሞክራሲ ጉዳይ ግን በራሱ የሚቆም ነው ብለውታል።
የሀገሪቱን መከላከያ ሠራዊት የብሔር ተዋፅኦ እና የቀድሞው የትግራይ ነፃ አውጪ ግንባር (ሕወሓት) በሠራዊቱ ላይ ስላለው ተፅዕኖ ተጠይቀው ተራ ሠራዊቱ ከብሔር ተዋፅኦ የተሻለ ደረጃ ላይ ቢገኝም አመራሩ ግን ከህወሓት የቀድሞ ታጋዮች ተፅዕኖ አለመላቀቁን ማመናቸውን ዳውደን በቃለ-ምልልሱ ላይ ይፋ አድርጎታል።
ኤርትራን በተመለከተም ከኢሳያስ አፈወርቂ ጋር ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የድንበር አካላይ ኮሚሸን ውሳኔውን በመቀበል ለመነጋገር በወቅቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን ደብዳቤ ፅፈው የነበረ ቢሆንም፤ ጥያቄአቸው ግን በኢሳያስ እምቢታ አለመሳካቱን፣ ነገር ግን ወደፊትም አምስቱ የሰላም ኀሳቦች እንዳሉም ሆነው ከኢሳያስ ጋር ለመነጋገር ፍላጎት እንዳላቸው መግለፃቸውን ጠቅሷል።
በተጨማሪ የጋዳፊ መውደቅ በተመለከተም ጋዳፊ በቀጠናው መጥፎ ተፅዕኖ ቢኖረውም ውድቀቱ ግን የተፈራውን ያህል አለመሆኑን፣ እንዲሁም የዓረብ አገራት ሕዝባዊ መነሳሳት በተመለከተም ተጠይቀው የቱኒዝያ ኢኮኖሚ ሁሉ አቀፍና ፍትሐዊ ባለመሆኑ የመጣ ስለመሆኑ እና ሙስናንም በተመለከተ የአፍሪካ መሪዎች በታላላቅ ኩባንያዎች አባላጊነት የሚፈፀም ስለመሆኑም ተናግረዋል። ሀገር በቀል የሙስና አስተሳሰብ በሕዝቡ እንዳይሰርፅ መደረግ እንዳለበትም መግለፃቸውን አትቷል።
በሀገሪቱ እየተገነቡ ያሉ የኃይል ማመንጫዎች እንደተፈራው ብዙ ሕዝብ የማያፈናቅሉ ቢሆንም፤ የምዕራብ የአካባቢ ተቆርቋሪ ነን የሚሉ ግን ከአካባቢ መቆርቆር ባለፈ የስለላ ስራ ሊያካሂዱ እንደሚችሉና ይሄም እንደሚያስፈራቸው ተናግረዋል።
የሀገሪቱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን በተመለከተም በሁለት ከፍለው እንደሚያዩዋቸው አንደኛዎቹ አሁን ያለውን ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት መዘርጋቱን ሀገር ከመበተን አንፃር ወንጀል እንደተሰራ አድርገው የሚያዩ፣ ሌሎቹ ደግሞ በጣም መጥፎና ጨካኝ ሴራ በማራመድ የብሔር ብሔረሰቦችን ፍላጎት በማኮላሸት የራሳቸውን ሀገር ለመመስረት የሚሰሩ መሆናቸውን ነገር ግን ሁለቱም የማይጠቅሙ ቢሆኑም፤ ዋናው ነገር ወሳኙ ሕዝቡ መሆኑን መግለፃቸውን በቃለ-ምልልሱ ላይ አመልክተዋል።
ያም ሆኖ አቶ መለስ የገነቡት ስርዓት ካለፉት ስርዓቶች በተለየ ከአርብቶ አደሮች አካባቢዎች በስተቀር በሁሉም የሀገሪቱ መንደሮች ድርጅታቸው የተመረጠ መሆኑንና መንግስታቸው በሀገሪቱ ግልፅና ጠንካራ መሠረት መጣሉን፣ ተቃዋሚዎች ግን በገጠር ሙሉ በሙሉ የማይፈለጉ መሆኑን ተናግረዋል።
ለጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ሪቻርድ ዳውደን ካቀረበላቸው ጥያቄዎች መካከል ቀጣይ የስልጣን ዘመናቸውን በተመለከተ ሲሆን እሳቸውም እ.ኤ.አ በ2015 (ከሦስት ዓመት በኋላ) ጡረታ እንደሚወጡ፣ ጡረታ ከወጡም በኋላ ምናልባት በአመራር አካዳሚ ውስጥ እንደሚያስተምሩ፣ አልፎ አልፎ መፅሐፍ እንደሚፅፉ እና በአዳንዳንድ ዓለም አቀፍ ወይም የፓን-አፍሪካን ጉዳዮች ላይ በቋሚነት ባይሆንም በጊዜአዊነት መሳተፍ እንደሚፈልጉ ገልፀውለታል።
በኢህአዴግ የመተካካት ዕቅድ መሠረት አቶ መለስ ዜናዊ የአሁኑ የምርጫ ዘመን ሲጠናቀቅ ኃላፊነታቸውን ለተተኪያቸው በማስረከብ እንደሚለቁ በተደጋጋሚ መግለፃቸው የሚታወስ ነው።
ምንጭ: ሰንደቅ ጋዜጣ

No comments:

Post a Comment