ግንቦት ፳፫ (ሃያ ሦስት) ቀን ፳፻፬ ዓ/ም
ኢሳት ዜና:-በዋሽንግተን ዲሲ፣ በደቡብ አፍሪካ እና በስዊዘርላንድ ሙስሊም ኢትዮጵያውያን የተቃውሞ ሰልፎችን አካሂደዋል፣ በካናዳም ተመሳሳይ ሰልፍ እየተካሄደ ነው።
የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ኣለም ኣቀፍ ጊዜያዊ ኣስተባባሪ ኮሚቴ (Ethiopia Muslims International Adhoc Committee) ለ ሜይ 31 ቀን 2012 ዓ.ም በመላው ኣለም « ድምፃችን ይሰማ » በሚል መሪ ቃል የጠራው አለም አቀፍ የተቃውሞ ሰልፍ አካል የሆነው እና በስዊዘርላንድ ውስጥ ካለፉት 4 ኣመታት ጀምሮ የሚንቀሳቀሰው ቢላል ኢትዮ- ስዊዝ ማህበር ያስተባበረው የጄኔቫው የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ የደመቀ ነበር
የተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፉ የኢትዮጵያ መንግስት በሃይማኖት ተቋማት በተለይም በስልምና ሃይማኖት ተከታዮች መካከል መከፋፈል እንዲፈጠር ሆን ብሎ የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት እንዲያቆም በኣንክሮት የጠየቀ ሲሆን በሰልፉም ላይ በስዊዘርላንድ የሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮችም ተካፍለውበታል ::
አቶ ኤልያስ ረሺድ የቢላል ኢትዮ ስዊዝ ማህበር መስራችና ዋና ፀሃፊ እንዲሁም የሰላማዊ ሰልፉ ዋና አስተባባሪ በተለይ ለኢሳት መንግስት በእስልምና ሃይማኖት ጣልቃ መግባቱን የሚያሳዩ 11 ማስረጃዎችን በመዘርዘር አስረድተዋል ::
እንደ አቶ ኤልያስ ገለፃ « መንግስት ዛሬ እያደረገ ያለውን የሃይማኖት ጣልቃ ገብነትን በመካድ እና ህጋዊና መሰረት ያለው የህገ-መንግስት ስልጠና እየሰጠሁ ነው የሚለውን የሃሰት ፕሮፓጋንዳና ዘመቻ ሃሰተኛ ሲሆን ሌላው ዛሬ የተጀመረው ሌላኛው አጀንዳ ደግሞ ክርስትያን ወገኖችንና እና ሙስሊሙን የጉሪጥ እንዲተያዩና በጉርብትናም ይሁን በአንድ ቤት ውስጥ የሚኖሩ የሃገር ልጆችን በመሃል መተማመንን ለማጥፋት ከፍተኛ ስራ እየተሰራ እንዳለ ጠቁመው ይኸውም « ሙስሊሞች ሽርዕያዊ መንግስት ለመመስረት የሚጥሩትን አሸባሪዎች ነው እየታገልን ያለነው « የሚል የሃሰት ፕሮፓጋንዳ እየነዛ ይገኛል ብለዋል ።
መንግሥት በእስልምና ሃይማኖት ጣልቃ ስለመግባቱ በርካታ ማስረጃዎችን ማቅረብ የሚቻል ቢሆንም በተለይም ካለፈው ዓመት ጀምሮ እጅግ አስገራሚና አሳዛኝ በሆነ መልኩ ጣልቃ ገብነቱ ግልጽ ሆኖ እየተስተዋለ እንደሆነና ይህ ማለቅያ የሌለው የሃሰት ሰንሰለት ከለት ወደ እለት መቀያየሩና አንዱ ሲያልቅ ሌላኛው መተካቱ አይቀሬ ስለሆነ ዋናውና መሰረታዊ የሙስሊሙ ህብረተሰብ ጥያቄ ምን እንደሆነ በግልጽ ቋንቋ ለማስቀመጥ ይረዳ ዘንድ በሚል በጥቂቱ አስራ አንዱን ብቻ ለማስታወስ
- መጅሊስ በደህንነቶች ተጽእኖ የሚመራ መሆኑ
- ከአመታት በፊት ከንቲባው አሊ አብዶ የመጅሊስ ባለስልጣን መሾማቸው
- የመንግስት ባለስልጣናት አህባሾችን ጋብዘው ማምጣታቸው
- የዶክተር ሽፈራው ንግግር
- የአዲስ አበባ ፍትሕ ቢሮ ሃላፊ አቶ ጸጋዬ ሀ/ማርያም ንግግር
- የአንዋር መስጊድ ኢማም ጣሃ መሀመድ ንግግር
- መንግስት ለመጅሊስ እያደረገ ያለው ህገወጥ ድጋፍ
- ስልጠናውን ያዘጋጀው ራሱ መንግስት መሆኑ
- የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር አቶ ወርቅነህ ገበየሁ በሻሸመኔ የተናገሩት ንግግር
- የሲቪል ሰርቪስ ሚኒስትሩ አቶ ጁነዲን ሳዶ ንግግር
- ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ አንዱን መጤ ሌላውን ነባር ሲሉ መፈረጃቸው ……
በመዘርዘር መንግስት በእስልምና ሀይማኖት ጣልቃ መግባቱን የሚያሳዩ በቂ ማስረጃዎች ናቸው በማለት አስረድተዋል ::
ሰልፈኞቹ በዕለቱ ካሰሟቸው መፈክሮች መካከል
- ሙስሊሙን እና ክርስቲያኑን በማጋጨት የስልጣን ዕድሜ ማራዘም አይቻልም
- አክራሪነትና አሸባሪነት የኢትዮጵያ መንግስት የሃሰት ድራማ ነው
- የኢትዮጵያ መንግስት በአርሲ ኣሰሳ በሰላሚ ሙስሊሞች ላይ የፈፀመውን ኢሰብዐዊ ጭፍጨፋ እናወግዛለን
- ለመብት መታገል አሸበሪነት አይደለም
- ኢትዮጵያ የሁሉም ሃይማኖት ሃገር ናት
- ሙስሊም እና ክርስቲያን ወገኖች በአንድነት እንቁም…………………… የሚሉና ሌሎችም ይገኙበታል
No comments:
Post a Comment